Friday 2 March 2018

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ

ይህንን የምጽፈው ሊህቃኖቻችንም እኛ ብዙሃንም አሁን ባለው የፖለቲካ ሁኔታ ትክክለኛ የሚመስለኝን ግንዛቤ እንዲኖረን ነው። በዛ ግንዛቤ ተመስርቶ ትክክለኛውን ሃሳብና ስራ በተግባር እንዲያውል ነው።

ዛሬ የፀደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በርካቶች ከሚያስቡት ተቃራኒ አስተዋሶ ነው የሚኖረው። የነጻነትን እንቅስቃሴውን ይጠቅማል እንጂ አይጎዶም።

ለማስታወስ ያህል ባለፉት ዓመታት ያየነው የህዝብ ተቃውሞና የኢህአዴግ የስልጣን መገለባበጥ በአንድ ጊዜ የምነጣ አይደለም። ለረዥም ዓመታት እየተንከባለለ የመጣ አዝማሚያ ነው። የህዝብ ብሶትና የአስተዳደሩ መሰረታዊ ችግር ያመታው ተቃውሞ ነው። የጎሳ አስተዳደርና የአውራ ፓርቲ የልማታዊ መንግስት አስተዳደር እንደ እሳትና ጭድ የሆኑ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለሞች በመሆናቸው ኤኮኖሚው ምንም ቢያድግም የህዝብ ቁታ እንዲንር አድርጓል። ይህ አገዛዝ ያመጣው በህዝቡ መካከል ያለው የአድሎ ግንዛቤ ህዝቡን እጅግ አምሮት ለዓመታት የማያቋረት ሰላማዊም አመጻዊም ሰልፍ እንዲካሄድ አድርጓል።

ይህን አዝማሚያ እንኳን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምንም ሊያቆመው አይችልም። ያለፈው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጀ እንዳላቆመው እናስታውስ! ትልቅ የፖለቲካ ለውጥ ብቻ ነው የህዝቡን ቅሬታ መመለስ የሚችለውና መሰረታዊ የፖለቲካ ብልሽቶችን ማስተካከል የሚችለው።

ምናልባት አንዳንድ ተቃዋሚዎች ስለኢህአዴግ ያላቸው ግንዛቤ የተጋነነ ስለሆነ በቀላሉ የተስፋ ምቁረጥ ባህሪ አላቸው። ይህ አዋጅ የህዝቡን ተቃውሞ ያቆመዋል ያከሽፈዋልና ከምርጫ 97 በኋላ እንደሆነው ለበርካታ ዓመታት የኢህአዴግ አገዛዝ ይቀጥላል ብለው ያምናሉ። ይህ ምን ያህል የተሳሰት እንደሆነ የሚያሳየው የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችንም ስለማያስቡት ነው! ስልጣናቸው እንደተነጋ ለሁሉም ግልጽ ነው። የሚሉትም ነገሮች፤ የሚወጣው ሚስጥሮች፤ የሚያደርጉት ድርጊቶች ሁሉ ይህንን ይመሰክራል። እስረኞችን የፈቱት ብርሀን ስላዩ አይደለም። ተሃድሶ እያሉ እርስ በርስ የሚፋጁት ከንቱ አይደለም። እነ ለማ መገርሳ እራሳቸውን ከፍ ያደረጉት አለ ምክንያት አይደለም። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያስፈለገውም ክንያት አለው! የህዝቡ ተቃውሞ ጋብ ይል ይሆናል ማለትም አለበት ግን ቀስ በቀስ ይቀጥላል ለውጥ እስኪመጣ።

ሌላው ማስተካከል የምወደው የተሳሳተ የሚመስለኝ አመለካከት ስለ ጦር ስራዊቱ ነው። የጦር መሪዎቹ ባብዛኛው የህወሓት አባሎች ቢሆኑም ጦሩ እራሱ ባብዛኛው አይደለም። ጠመንጃ የያዘው ኦሮሞ፤ አማራ፤ ሲዳማ ወዘተ ነው። ጦር ሰራዊት ውስጥ የታወቀ የፖለቲካ ክፍፍል አለ። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወታደሩ ብዙ ቅራኔዎች ካላጋጠሙትና ባብዛኛው ሰላማዊ የፍተሻና የሚመሳሰል የማያስጨንቅ ስራ የሚሰራ ከሆነ ይህ ክፍፍል ብዙ ላይታይ ይችላል። ግን ኃይለኛ አመጽ ከተነሳና በርካታ ቅራኔና ግድያ ከተከሰተ የወታደሩ የውስጥ የፖለቲካ ክፍፍል - በዘር ምክንያት - መውጣት ይጀምራል። ጦር ሰራዊቱን ወደ መከፋፈል ይገፋዋል። የጦር ሰራዊት መሪዎች ደግሞ ይህንን "risk" እጅግ ይፈራሉና ይሸሻሉ። ግን የአቸኳ አዋጁ በቆየ ቁጥር ይህ የመከሰቱ እድል እየጨመረ ስለሚሄድ የጦር ሰራዊቱ መሪዎችም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቶሎ እንዲቋረጥ ነው የሚፈልጉት።

ስለዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ብዙ ሌከርም አይችልም። ጊዜ መግዣ ነው። የአገሪቷ መንገዶችና ንግዶች እንዲንቀሳቀሱና ሰውዉ ለተወሰነ ጊዜ ቢሆንም ወደ ዘውትር ኑሮ እንዲመለስ ነው። ፖለቲከኞቹ ማቀዳቸውንና ውይይታቸውን እንዲቀጥሉ ነው። አይከፋም። የአገሪቷ የፖለቲካ ጠቅላላ አዝማሚያውን አይቀይርም ሊቀይርም አይችልም። ኢህአዴግ ባለበት አወቃቀር ከስጣን መውረዱ አቀርም። ወይ ለጉድ ይቀየራል ወይም ከስልጣን ይወርዳል። ጉዳዩ አልቋል። አሁን የጭዋታው መጨረሻ ("end-game") ላይ ነን። ስለዚህ ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከመጨነቅ ይልቁኑ እኛ ተቃዋሚዎች በርካታ የተጠራቀመ የቤት ስራችንን እንስራ። ጊዜውን እንጠቀምበት።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!