Showing posts with label ምእራባዊያን. Show all posts
Showing posts with label ምእራባዊያን. Show all posts

Thursday, 8 March 2018

ዴሞክራሲ

ስለ ዴሞክራሲ ብዙ ተጽፏል። በንደፈ ሐሳቡ ደረጃ ምንም መጨመር አልፈልግም። በዚህ ጽሁፍ አሁን ባለን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዳይ ዙርያ ስለ«ዴሞክራሲ» ያለን አመለካከት ምን ቢሆን ይበጀናል የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ነው የምወደው።

እንደ እስክንድር ነጋ አይነቶቹ በርካታ (ጀግና) የነፃነት ታጋዮቻችን የችግራችን መፍትሄ ዴሞክራሲ ነው ይላሉ። በአንድ ወቅት እኔም እንደዚሁ ይመስለኝ ነበር። ግን ጉዳይ ከዛ እጅግ ውስብስብ እንደሆነ ተረድችያለሁ።

ዛሬ ባለን ህገ መንግስትና ጠቅላላ የመንግስታዊ አወቃቀር የነፃ ምርጫ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ቢካሄድ ችግሮቻችን ይፈታሉ ብለን እንገመታለን? አሸናፊዎቹ፤ ተሸናፊዎቹ፤ ጦር ሰራዊቱ፤ የክልል መንግስታት ወዘተ ውጤቱን ተቅብለው ተስማምተው ይሰራሉ ብለን መገመት ኢንችላለን? አዲሱም መንግስት ሰላምና ፍትህ ያመጣል ወይም የፓርላማ ስልጣንና ኃይሉን ተጠቅሞ ግፍና ጭቆና ያሰፍን ይሆን? ህገ መንግስቱን ይቀየር የምንለውሳ? በቂ ድምጽ ካለን አናሳ ድምጽ ያላቸውን የራሳችሁ ጉዳይ ብለን በዚህ ድምጽ ኃይል እንቀይረውና አዲስ ህገ መንግስት እንጭንባቸው ይሆን? ዛሬ እነዚህ አይነቶቹ ከባድ ጥያቄዎች ጥሩና የተሟላ መልስ አላቸው ብዬ እርግጠኛ መሆን አልችልም። ለእነዚህ ጥያቄዎች በሚገባው መልስ ሳይኖረን ወደ ዴሞክራሲ የምንለው ምርጫ ከገባን ደግሞ አደጋ ነው የሚሆነው።

ስለዚህ እንደኔ እንደኔ በመጀመርያ ሰፊ ውይይት በተለያዩ ደረጃዎች ያስፈልጋሉ። የዚህ ውይይት ግብ በርካታ ባለጉዳዮቹ ከብዙሃን እስከ ልሂቃን የአገራችን ማንነትና ፖለቲካ ምን መምሰል አለበት በሚለው ጥያቄና መልስ አንድ ገጽ ላይ እንዲሆኑ ነው። ሰፊ ስምምነት እንድውል ነው። አሁን ያለንበት ደረጃ አገር መገንባት ላይ ነው። በህዝቡም በልሂቃኑም የፖለቲካ መተማመንና መሰረታዊ ስምምነት የለምና። ከላይ የጠቀስኳቸው አይነቶች መሰረታዊ የሆኑ ጥያቄዎች እንኳን ሊመለሱ አልተጠየቁም አልተወያየንባቸውም። ይህን የውይይት ሂደት ሳንጨርስና መሰረታዊ ስምምነት ላይ ሳንደርስ ወደ ምርጫ መሄድ አደገኛ ይመስለኛል። እንደ ግብጽ፤ ኢራቅ፤ እና ሌሎች ምርጫ ያላቸው ወይም የነበራቸው ግን ሰላምና ፍትህ የሌላቸው አገሮች እንድንሆን አይፈለግምና።

እሺ፤ በርካታና አስፈላጊዎቹ ባለጉዳዮች አንድ ገጽ ላይ መሆናቸውና ስምምነት ላይ መድረሳቸው እንዴት ልናውቅ እንችላለን? አንዱ ዋና ምልክት የሚመስለኝ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በስል ማለት ነው። ጠንከር ያለ ተቃዋሚ ፓርቲ ከሌለ ወይም ፓርቲዎቹ በጎሳ ብቻ የተመሰረቱ ከሆነ ይህ ጥሩ ምልክት አይመስለኝም። ተመሳሳይ የሆኑ አቋም ያላቸው ተቃዋሚዎች የመዋኸድን ሂደት ለማሟለት ብቃት ከሌላቸው ጥሩ ምልክት አይሆንም። ይህን ያልቻሉ እንዴት አብረው መንግስት ይሆናሉ ወይም እንዴት የአስተዳደሩን ህግ ያከብራሉ? የጎሳ ፓሪቲ ብቻ ካለ ደግሞ እንዴት ነው ፖለቲካ ስረአቱ የማይቀረውን የጎሳ ውድድሩን በሰላም ማስተናገድ የሚችለው? አሁንም ከባድ ጥያቄዎች። እንደምናየው ወደ ምርጫ ከመግባታችን በፊት ብዙ ስራ አለ ቀድመሁኔታዎችም መሟላት አለባቸው።

ይህን ካልኩኝ በኋላ እስቲ ይህን ጥያቄ ልጠይቃችሁ፤ ዴሞክራሲ ቢኖር ሰላምና ፍትህ ይኖራል ማለት ነው? እስቲ አንድ አንድ እውነታዎች እንመልከት። በዓለም ታላቅ የሚባለው ዴሞክራሲ አሜሪካ ነው። በጦሩ ኃይል በርካታ የዴሞክራሲ አገርዎች በሰላም እጠብቃለሁ እሸከማለሁ ባይ ነው። ግን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ አሜሪካ ወደ 20 ሚሊዮን ሰዎች በተለያዩ ጦርነቶች ገድሏል ይባላል። አጭር ትዝታ ያለን መቼም ስለ ኢራቅ፤ ሊብያ፤ ሶርያ እናውቃለን። ኢህአዴግ  ከዚህ ጋር ሲወዳደር መለአክ ነው ማለት ይቻላል! ግን አሜሪካ ለኑሮ ጥሩ አገር ነው። ገንዘብ አለ፤ ከሞላ ጎደል ፍትህ አለ፤ የተወሰነ ነፃነት አለ። ሁላችንም ወደዛ ለመሄድ እንሻለን። ግን ገንዘቡ ባይኖር በአሜሪካ ምን ይሆን ነበር?

ምናልባት አውሮፓ ያላችሁ ኢትዮጵያዊያን ለምን አሜሪካን እንደ ምሳሌ ትጠቀማለህ ትሉ ይሆናል። ሰላማዊዋ ስዊድንሳ? እውንቱን ለመናገር የስዊድን የጦር መሳርያዎች በዓለም ዙርያ ምን ያህል ሰው እንደተገደለ የተቆጠረ አይመስለኝም። ግን ትንሽ አይመስለኝም። ደግሞ ከሳውዲ አራቢያ ያላቸው ጓደኝነታቸው እንዴት ፍቅር የተሞላ ነው?!

ዴሞክራሲ ለሰላምና ፍትህ ሊበጅ ይችላል፤ ይህ ጥያቄ የለውም። ግን ሰላምንና ፍትህን ለማስፈን ሥርዓቱ በራሱ አይበቃም።  ብዙሃኑም ልሂቃኑም ቀድሞ በትወሰኑ መሰረታዊ ጉዳዮችና አስተሳሰብ መስማማት አለባቸው። ከህግና የሂደት ደምብ አስተሳሰብ ይቀድማል። አሰተሳሰቡ ካለ ህጉ ይመጣል በሚገባውም ይተገበራል። ህጉ ካለን አስተሳሰቡ ከሌለ ዋጋ የለውም። ብዙ ነገር በጽሁፍ ላይ የዋለ ህገ ደምቦች ሊካታቱ ይችላሉ ግን አስተሳሰብ በጽሁፍ ሳይሆን በልብ ውስጥ የሚሰክን ባህል ነው መሆን ያለበት። ከዛ በኋላ እንቅፋት ሲያጋጥም ይህ አስተሳሰብ፤ ስምምነትና አንድነት ናቸው ከወረቀት ላይ ከሰፈረው ህግ ይልቅ ወደ መፍትሄ የሚመሩን።

ስለዚህ ዴሞክራሲን እንደ ዋና ግብ ወይንም እንደ ጣዖት አንመልከተው። ዋናው ግብ ፍቅር፤ ሰላምና ፍትህ ነው። እነዚህ እንዲሰፍኑ ዴሞክራሲ አንዱ መሳርያ ሊሆን ይችላል። በዴሞክርሲ ዘንድ ፍቅር፤ ሰላምና ፍትህ ሊሰፍኑ ይችላሉ። ግን ቀድሞ ዝግጅቶች ካልተደረጉ፤ ግባችን እነዚህ እንደሆኑና ዴሞክራሲ መንገድ ወይም ሂደት ባቻ እንደሆነ ካልተረዳን ፍቅር፤ ሰላምና ፍትህ የሌለው ዴሞክራሲ ሊሰፍን ይችላል። እንደዚህ አይነቱ ዴሞክራሲ ደግሞ በበርካታ አገራት ልምድ እንደምናየው አይበጅም።

Wednesday, 7 December 2016

የተማረ ገደለን

የኢትዮጵያ ወዳጅ ዶናልድ ሌቪን (ነፍሳቸውን ይማረው) ከ50 ዓመታት በፊት ጅምሮ ባህልንና ማንነትን የማያከብርና የሚክድ ህብረተሰባዊ ለውጥ አገር አፍራሽ ነው እያሉ ኢትዮጵያዊያንን ያስጠነቅቁ ነበር። ኃይለ ሥላሴ ወደ ምዕራብ አገር የላኳቸው ተማሪዎች በኢባህላዊ የሆነ  ከራስ ጋር የሚያጣላ ርዕዮት ዓለም ተነክረው ወደ አገራቸው ሲመለሱ በአስተሳሰባቸው ሰውዉን አስተንግጠዋል። አቶ ዶናልድ ሌቪን አንድ ያጋጠማቸውን እንደዚህ አስታወሱ ነበር፤ አንዱን «የተማረ» ምሁራንን እንደዚህ ብለው ጠየቁት «እንደምትመኘው የሶሽያሊስት አብዮት ቢካሄድ በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ እንደሚሞቱ ታውቃለህን?» ይህ የተማረ ምህር «በ10 ሚሊዮንም ቢሞቱ ይህን ርዕዮት ዓለምን ለማድረስ ስለሆነ ያዋጣል» ብሎ መለሰላቸው። ከራስ ባህል፤ ወግ፤ ትውፊት፤ ምንጭና ማንነት መራቅ እንደዚህ አይነቱን ቅዠታዊ አስተሳሰብ ነው የሚያመጣው።

ዛሬም ይህ አይነት የቀለም ትምህርት አምልኮ ለኢትዮጵያ ዋናው አጥቂና ጠላት ነው። የምዕራብ ዘመናዊ የቀለም ትምህርት በአገራችን እንደ ጣዎት እንደሚመለክ የሚገልጸው በኃይለ ሥላሴ ዘመን የተሰየመው አባባል «የተማረ ይግደለኝ» ነው። ይህ ዛሬም በኢትዮጵያዊያን ጭንቅላት ይንጸባረቃል። ፖለቲካችንን ካየን አብዛኛው የሚንጸባረቁት ሃሳቦችና አስተያየቶች ከኢትዮጵያ ውጭ የመነጩ ናቸው። የኛ ምሁራኖች እነዚህ ሃሳቦችን እየሰገዱላቸው ኢትዮጵያን ወደ እኒዝህ ርዕዮት አለምን ማስተካከል ይፈልጋሉ። ቢያንስ መደረግ የነበረበት እነዚህን ርዕዮት ዓለሞችን ለኢትዮጵያ እንዲሆኑ ማስተካከል።

ይህ አቋሜን የሚደግፉ አንዳንድ ማስረጃዎች እንመልከት። በመጀምርያ ወደ ኋላ ሄደን የኃይለ ሥላሴ መንግስትን ተመልስን እንመልከት። የዛን ጊዜ ውጤቶች ዛሬ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ስለሆነ። በሳቸው መንግስት ዘመነ የምዕራብ «ዘመናዊ» ትምህርት በኢትዮጵያ ውስጥ ተስፋፋ። ተማሪዎች በሞላ ጎደል አለምንም መበረዝ ቀጥታ የምዕራብ ትምህርት ነበር የሚማሩት። ስለአገራቸው ጥቂት ውይም ምንም ነገር ሳይማሩ ይመረቁ ነበር። ለምሳሌ ስለ ዓለም ዙርያ መልክአምድር ተምረው ስለኢትዮጵያ መልክአምድር ምንም አያቁም ነበር! ስለራሳቸው ታሪክ፤ ትውፊት፤ ባህልና ሃይማንቶ አይማሩም ነበር። ሳይታወቅ ግራ የገባው ከፊል ኢትዮጵያዊ ከፊል ፈረንጅ የሆነ ትውልድ ተወለደ። የዝቅተኛ መንፈስ ያደረበት ትውለድ ተፈጠሪ። ሳያውቀው እራሱን የሚንቅና የሚጠላም ትውልድ ተፈጠረ። ግን ከዚህ ትውልድ ልጆች መካከል ግማሾቹ ኢትዮጵያዊነታቸው ቢሸረሸርም ለኃይለ ሥላሴ ታማኝ ነበሩ በሳቸውም «የዘመናዊ ስልጣኔ እቅድ» ይስማሙ ነበር። ሌሎቻቸው ግን እንኳን ታማኝ ለመሆን ጠላት ሆነው ተገኙ። አገሪቷን ያስከወሰ አብዮትን አስነሱ። ሁላችንም እንደምናውቀው ይህ አብዮት በአገራችን አስፈላጊ የሆኑ ለውጦችና መስተካከሎች ከማምጣት ፋንታ በጸረ ኢትዮጵያ የሆነውን በምዕራባዊያኑ ርዕዮት ዓለም በኮምዩኒዝም ስር አገራችንን እንድትወድቅ አደረጋት።

በደርግ ዘመነ መንግስት ደግሞ አብዛኛው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ንቅናቀዎች የጸረ ኢትዮጵያ አቋምና ርዕዮት ዓለም ይዘው ነበር የሚራመዱት። ጸረ ሃይማኖት ነበሩ። ጸረ ባህልና ጸረ ትውፊት ነበሩ። እርግጥ በዛን ዘመን ሙዚቃ ጭፈራ ወዘተ «ትስፋፍቷል»። ግን የተስፋፋው በምዕራባዊያን አመለካከት ዘንድ ነው - ስር የሰደደ የማንነት የሆነ ሳይሆን እንደ ልብስ ከላይ የሚለበስ ወይም እንደ ቴአትር የሚታይ ነበር። በመጀመርያ ኮምዩኒስት ነን፤ ግን እስክስታ የምንጨፍር ኮምዩኒስት ነን! በጠቅላላ አብዛኛው ፖለቲከኞችና ምሁራንም የኢትዮጵያ ማንነት መቀየር አለበት ብለው የሚያምኑ ነበሩ።

በኢህአዴግ ዘመን ይህ ወደ ውጫዊ አመለካከት ማድላት ወደ ጸንፍ ደረሰ። በሶሺአሊዝም የተሞላ በጎሳ የተመሰረተ ጸንፈኛ ህገ መንግስት በኢትዮጵያ ተጫነባት። ይህ ክስተት ከኢትዮጵያዊ «የተማረ» ኃይል በተደጋጋሚ የሚታይ አንድ ጸባይን በደምብ ያብራራል። ይህ ጸባይ ጸንፈኝነት ነው። የኢትዮጵያ መሰረታዊ ችግር የብሄር እኩልነት ነው ብሎ ቢታመንም ቋንቋ፤ ባህል፤ መልክአ ምድር፤ ጎሳም የሚያካተት ግን ለዘብተኛ የሆነ ህገ መንግስት ሊመሰረት ይቻል ነበር። ግን ያኔ የነበሩት ኃይሎች ጸንፍ ካልያዝን አሉ! በምድረ ዓለም ታይቶ የማይታውቅ አይነት ህገ መንግስት - ከሶሺያሊስት በላይ ሶሺያሊስት የሚያሰኝ ህገ መንግስት ካልደነገግን አሉ። ጭራሽ ከደቡብ አፍሪካ በቀር የሌለውን ጎሳ በመታወቅያ ጀመሩ! ሁላችንም እንደምናውቀው እስካሁን ይህ መርዝ ነው እያሳመመን ያለው።

ይህ ሁሉ ሆኖ የአገራችን ገዥም ተቃዋሚም ፖለቲከኞችና ምሁራን አሁንም ውጫዊ በተለይ ምእራባዊ አመለካከት ነው ያላቸው። ገዝ ፓርቲ «ዘመናዊነት» የሚባለው አመለካከት ነው ያለው። ሃይማኖት ኋላ ቀር ነው። እግዚአብሔር ሳይሆን ሰው ነው የዓለም ቁንጮ። ባህል፤ ትውፊትና ወግ ውሸት ናቸው። ህዝብ ባህልን ትቶ ወደዚህ አይህነት አመለካከት እስኪ ገባ ድረስ እንደ ያላደገ ህጻን ነውና እኛ ስልጣን ተቆጣጥረን ልናሳድገው ይገባል። ካደገ በኋላ፤ ማለት እንደኛ የ«ዘመናዊ» አስተሳሰብ ካደረበት በኋላ - ስልጣናችንን እንለቃለን። በሌላ አባባል ኢትዮጵያዊነቱን አርግፎ ከኛ ይበልጥ «ያደጉትንና የሰለጠኑትን» ምእራባዊያን ከመሰለ በኋላ ነው ሰው የሚሆነው። ይህ ራስን ማንነትን መጥላት ካልሆነ ምንድነው?

ተቃዋሚው ደግሞ እንደ አሜሪካ ወይም እንደ አውሮፓ እንሁን ነው! (በጅምላ እየተናገርኩኝ ስለሆነ ይቅርታ።) የኢትዮጵያዊነት ራዕይ የለውም። እርግጥ አንዳንድ ጥሩ የሆነ ሃሳቦች እንደ ገዳ አሰራር አጥንቶ በተወሰነ መጠቅም ተነስተዋል። አንዳንዱም ደፋር የንጉሳዊ አስተዳደር (በወግ ደረጃ ብቻ ቢሆንም) ይመለስ የሚሉ አሉ። እነዚህ ሃሳቦች በርካታ ውይይትና ክትትል ያስፈልጋቸዋል ከነዚህ አይነቱ ባህላዊ መንገድ ነውና የአገራችን ውበት የሚመለሰው።

በብዙሃኑ ደረጃ ደግሞ ቤተሰብ ልጁን የምእራባዊ ባህልና ቋንቋ ለማስተማር ይሯሯጣል! ለልጁ ከቀለም ትህምሕርት በላይ በዚህ ዓለም ምንም የለም የሚል መልክት ነው ደጋግሞ የሚያስተላልፍለው። ልጁም የቀለም ትምሕርትን ጣኦት አድርጎታል። ከዛ በኋላ የልጁ አኗኗር ግራ የገባው ሲሆን፤ ትምሕርትና ስራ አለው ግን በሌላው ንሩው ያልተረገጋ መሰረተ ቢስ የሆነ ሲሆን - ወላጅ ግራ ይገባዋል። የዛሬው ትውልድ እንደዚህ ነው እንደዛ ነው ብሎ ያማርራል። ታድያ ባህሉን ያልወረሰ ሰው ሁልጊዜ ኑሮው እንደሚናወጥ አናውቅምን?

በትህትና ባይመስልም ግን የትህትና ምክሬ እንደዚህ ነው። በመጀመርያ የዘመናዊ ትምህርት ምን ያህል ጸረ ባህል፤ ጸረ ትውፊት፤ ጸረ ማንነት፤ ጸረ ኢትዮጵያ እንደሆነ እንረዳ። ሞያ፤ ሳየንስና ቴክኖሎጊ ችግር የለውም ከጥንትም የነበሩ ዘርፎች ናችሀው ከምንምም ጋር አይጋጭም። አደገኛው ግን «ዘመናዊነት» የሚባለው ርዕዮት ዓለም ነው። ቅድም የጠቀስኩት ጸረ ሃይማኖትና ጸረ ባህል የሆነ አስተሳሰብን እንደ መርፌ ይወጋል። ይህን አውቀን ስንዴውን ከንክርዳዱን መለየት አለብን። ጠቃሚውን ትምህርት እየተማርን ጎጂውን እራሳችንን እንድንጠላ የሚያደርገውን ለይተን አውቀን እንተው። የምንማረውን በባህልና ሃይማኖታችን መነጽር ወይም አመለካከት እንማረው። ለልጆቻችንም እንደዚሁ።

ይህ ነው ምክሬ። ዶናልድ ሌቪን እንዳሉት - ክሁሉ ጥቅሳቸው ይህን ነው እጅግ የምወደው - "The vitality of a people springs from feeling at home in its culture and from a sense of kinship with its past. The negation of all those sentiments acquired in childhood leaves man adrift, a prey to random images and destructive impulses…" ከኔ የምትሻሉት ተርጉሙት!