ሆኖም ይህ ዜና በሃገራችን መሰረታዊ የሆነ አሳዛኝ አስተሳሰብ አሁንም እንዳለ ይገልጻል? «ጨቋኝ» እና «ተጨቋኝ» እራሱ የተሳሳተ ቋንቋ ነው። ጽንሰ ሃሳብ የመጣው ከውሸትና ኢባህላዊ የሆነ የምእራባዊ የኮምዩኒስት አስተሳሰብ የመነጨ ነው። እስቲ አንድ እርምጃ ወደ ኋላ ተመልሰን ለምንድነው የሰው ታሪክ በ«ጨቋኝና ተጨቋኝ» የሚለው አስተሳሰብ መወሰን ያለበት? እንደዚህ አይነቱ አስተሳሰብ በሃሳብም ደረጃ በተግባርም ግጭት፤ ቅሬታ፤ ቂም፤ ጦርነት፤ ግድያ፤ አብዮት ወዘተ የሚያስገድድ ነው። አንድነት፤ ፍቅር፤ ይቅርታ፤ ትህትና፤ መስማማት ወዘተ የሚቃረን አስተሳሰብ ነው።
አልፎ ተርፎ ማን ግለሰብም ህብረተሰብም ፍፁም ንፁሃን ፍፁም ጥፋተኛ የሆነ የለም። እያንዳዳችን ጨቁነናል ተጭቁነናል፤ በድለናል ተበድለናል፤ ወደናል ተወደናል፤ ተስማምተናል ተጣልተናል፤ ተሳስተናል ስታታችንን አምነን ይቅርታ ጠይቀናል፤ ቂም ይዘናል ይቅርታን ተቀብለናል። በዚህ ዓለም እኔ ነኝ ንጹ ተጨቋኝ የሚል የራሱን ጥፋት ስለማይመለከት ወደ ከባድ ጥፋጡስት ይገባል ሰፊ በደልም ይፈጽማል።
በዚህ ጉዳይ ታላቅ የሩሲያ ደራሲ አለክሳንደር ሶልዠኒትሲን ያሉትን በደምብ ሊገባን ይገባል፤
ከእስርቤታችን አልጋ የሆነው የበሰበሰው ገለባ ላይ ጋደም ብዬ ነው ለመጀመርያ ከውስጤ የበጎ መንፈስ የተሰማኝ። ቀስ በቀስ መረዳት የጀመርኩት ይህ ነው፤ ጥሩና ክፉን የሚለየው መስመር በሀገሮች፤ መደቦች፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችም መካከል አይደለም የሚያልፈው፤ ይህ መስመር የሚያልፈው በያንዳንዱ የሰው ልብ መኻል ነው። መስመሩ እድሜአችን በሙሉ ከውስጣችን ወደፊት ወደኋላ ይላል። በክፉ የተሞሉ ልቦችም ቢያንስ ቅንጣት ያህል ጥሩነት ይኖራል፤ ከሁሉም ጥሩ ከሚባለውም ልብ ከአንድ ጥጓ ትንሽ ክፉነት ይኖራል።ሶልዘኒትሲን ኮምዩኒስት የነበሩ ወታደር የነበሩ ስታሊን ለዓመታት በሞት እስር ቤት (ጉላግ) ያሰራቸው ከሩሲያ ወደ ኦርቶዶክስ ሃይማኖታቸው የተመለሱ የሩሲያ ጀግና ነበሩ። ተጨቋኝ ነኝ ማለት የሚገባቸው ነበሩ። ለሃገረቸው ጦርነት ተዋግተው በማግስቱ የታሰሩ ናቸው። አለምንም ጥርጥር ተጨቋኝ ነኝ ማለት የሚገባቸው ነበር። ግን እስር ቤት የሌሎችን ሳይሆን የራሳቸውን ኃጢያት እንዲገለጽላቸው አደረገ! የሰው ልጅ እውነተኛ ባሕርይ እንዲረዱ አደረገ። የሰው ልጅ ችግርም እንዴት መቅረፍ እንደሚቻል ገባቸው። በጦርነት፤ በማስወገድ፤ በማባረር፤ በመወገን ሳይሆን በንስሃ፤ በመስማማት፤ በመከባበር፤ በመቻቻል ነው።
በየቦታው እየዞሩ ያሉ ክፉ ስራ የሚሰሩ ክፉ ሰዎች ቢኖሩና እነሱን ከኛ መለየትና ማጥፋት ብቻ ቢሆን ኖሮ እንዴት ቀላል ነበር? ግን ጥሩና ክፉን የሚለየው መስመር ከያንዳንዱ የሰው ልጅ ልብ መካከል ነው የሚያልፈውና ማን አለ ከራሱ ልብ ቁራጭ ቆርጦ ለማጥፋት ፈቃደኛ ይሆነ?
ይህ ሩሲያዊ ሶልዠኒትሲን የዘመኑን «ጭቋኝና ተጨቋኝ» አስተሳሰብን ትተው የእውነትን ባህላዊ የኢትዮጵያዊ አስተሳሰብ ነው የገለጹት። ሩሲያዊው ኦርቶዶክስ ባህላችንን ያስታውሱን። ለምንናውም የኢትዮጵያ ባህል፤ ማንኛውም ሃይማኖት፤ ይህ የ«ጨቋኝና ተጨቋኝ» ርእዮተ ዓለም በአድ ነው። በአድ ነው። ሚስኪኖቹ የጃንሆይ ተመሪዎች ወደ ሃገራችን ከምእራብ ሃገራት ያመጡት መርዝ ነው። መርዙን እናውጣው። ወደ እራሳችን እንመለስ።
እነ አቶ ለማ መገርሳ የሰሩትን ሥራ ማድነቅዎት አግባብ ነው:: የወያኔን ፍጹም ጨካኝነትና የመግደል የማሰቃየት ልምድ ብቻ ሳይሆን ሃራራ/ጥማት ጠንቅቀው እያወቁ ይህን ወያኔን (ይቅርታ ለቁዋንቁዋው) የሚያኮላሽ ወሳኝ እርምጃ መውሰዳቸው የሚያስደንቅ ነው:: ድንገት ካልሰሙት እኒህም ጀግና የወያኔ ካድሬዎች የሞሉትና የሚቆጣጠሩት የግሬያዊው አማራ ድርጅት አባልም ከአመት በፊት እንዲህ ብለው ነበር https://www.youtube.com/watch?v=VUHygV8ZhE4&feature=share
ReplyDeleteወደሌላው መሰረታዊ ሀሳቦ ስንሻገር "እቶ አለኒ - ጥያቄ አለኝ" እንዳለው ገጣሚ እኔም ጥያቄ አለኝ::
ቆይ ቆይ አሁን እርስዎ የሚሉት "ከጥላቻ ፍቅርን ማስቀደም ይሻላል" ነው ወይንስ "ጥላቻ ብሎ ነገር የለም?" አርስዎ ሕብረተሰብ ጨቁዋኝና ተጨቁዋኝ ተብሎ መከፈል አይችልም ምክንያቱም ሁላችንም በተፈጥሮ ሁለቱንም የመሆን ዝንባሌው በውስጣችን አለን ከሆነ የሚሉት ሸጋ ይሁን:: ግን እውነታው በተፈጥሮ መሆን መቻልና በተግባር መሆነ ለየቅል ነው ወይ ለሚል ውይይት መነሻ ማለፊያ ሀሳብ ነው:: አንዳንዴ ክፉ ማድረግ እየቻልንም አለማድረጉን እንመርጣለን:: ብዙን ጊዜ ደግሞ ማድረጉን ብንፈልግም የማድረጉ አቅማችን ውሱን ይሆንና አናደርገውም:: ታዲያ የመጨቆን ዝንባሌውም ፍላጎቱም አቅሙም በሙሉ ኖሮዋቸው ሕዝብ የሚጨቁኑትን ማለትም በሌላው ጉዳት የሚበለጽጉትን የሌላውን ቤተሰብ ደሳሳ ጎጆም ይሁን የተንጣለለ ቪላ ደርምሰው ለራሳቸው ህንጣ ቁጥር 11,...ህንጣ ቁጥር 20...ጥልቅ ህዳሴ የገበያ አዳራሽ የሚገነቡትን በሀገራቸው በባለግዜ ጉልቤዎች ሀገርአልባ ተደርገው ሜዳ ከተጣሉት በምን ሊለዩ ነው?
በመደምደምያውም አዎ ከጥላቻ ፍቅርን እናስቀድም:: አዎን እራስችንን ፍጹም ቅዱስ ሌላውን ፍጹም እርኩስ አድረገን ማየት መዋሸት ይሆንብናል:: ነገርግን በዳይም ተበዳይም አሉና በደል እንዲጠፋ በዳይን ከበደሉ እንዲታቀብ ማድረግ ተበዳዩን መደገፍና ነጻ እንዲሆን ማገዝ አስፈላጊ ነው:: በደል እያለ እንደሌለ ብናየው ሻጋታው እያፈነን የለም ማለትን በመምረጥ ይብለጥ እንዲስፋፋ ማገዝስ አይሆንም ወይ ነው ሥጋቴ::
ላስተያየትዎ እጅግ አመሰግናለሁ። ብዙ ውይይት ያስፈልገዋል።
ReplyDeleteባጭሩ፤ አመለካከቴ ከኦርቶዶክስ ሃይማኖቴ የምራዳው ነው። ከተሳሳትኩኝ ልታረም። ትእቢትና መፍረድ ታላቅ ሐጢያቶች ናቸው፤ ከእግዚአብሔር በታም የሚያርቁ። ሌሎች ላይ መጠቆም በነዚህ ሁለቱም ሐጢያት እንድንፈተን ያጋልጠናል። ስለዚህ ነው ከመጠቆም እራሳችሁን ቆጥቡ የሚባለው።
ይህ አስተሳሰብ በፖለቲካችን ሁኔታ ጋር ይሄዳል ብዬ እገምታለሁ። 1) «ጨቋኝና ተጨቋኝ» እያልን ጨቋኙ የሚጭቁንበት ሁኔቶች ተደጋግመው ተፈጥረዋል። 2) ህወሃት የአናሳ ቡድን ድጋፍ ነው ያለው እንላለን። ሆኖም ለሃገራችን ችግሮች ኢ-መጠናዊ ሃላፊነት በህወሃት እንጥላለን። እንዴት ነው 8% (ለምሳሌ) ድጋፍ ያለው ቡድን ሃገርን መቆጣጠር የሚችለው? ጥፋቱ ከ92% መሆን አለበት። እንደገነ ጣት ወደ ሌላ መጠቆማችን ይጎዳናል። ምናልባት እራሳችንን በማስተካከል ላይ ባቶኮርን ኖሮ ጉዳይ ድሮ አልቆ ነበር።
በታሪክም ዙሪያ «ጨቋኝ ተጨቋኝ» ታሪክን የዛሬ ብድር መመለስ ሰበ ያደርገዋል። ሁሉንም ይቅርታ ፈላጊ እንዲሆን ያደርገዋል፤ ማንም ይቅርታ ጠያቂ እንዳይሆን ያደርገዋል። ይህም ለፖለቲካ አይበጅም።
እንዲህ ነው የሚመስለኝ። ሁለት ጽሁፎች ልጠቁሞት፡
http://asfawdarguemeshal.blogspot.ca/2016/09/blog-post_15.html
http://asfawdarguemeshal.blogspot.ca/2016/09/blog-post_14.html