Thursday, 15 February 2018

ቤተ ክርስቲያን መቅደም አለባት!

ከትላንት ወድያ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዙርያ ያልጠበቅናቸው መልካም አሳቢዎች እንደ ለማ መገርሳና አቢይ አህመድ ብቅ ማለት ጀመሩ። ትላንትና መንግስት ለረዥም ዓመታት የሚለመነውን ነገር አደረገ፤ ያለጥፋት የታሰሩትንና የተሰቃዩትን በርካታ እስረኞችን ፈታ። ዛሬ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስቴራችን ኃይለማርያም ደሳለኝ በፈቃደኝነታቸው ስልጣናቸውን ከቀቁ። መልካ ለውጦች ይታያሉ፤ እግዚአብሔር መጨረሻውን ያሳምርልን።

ግን ከፖለቲካው ቤተ ክርስቲያናችን መቅደም አልነበረበትም? (ይህን ስል እኔም እንደ አንድ ምእመናን እራሴን እየወቀስኩኝ ነው።) የኛ ለማ መገርሳዎች፤ በትህትና አለመፍረድ፤ በፍቅርና በምሳሌ፤ የሚናገሩት የት አሉ? እርግጥ አሉ፤ ግን በሌሎቻችን ተከበው ድምጻቸው በአግባቡ አይሰማም። እስረኞችንን መቼ ነው የምንፈታው? በርካታ እስረኞች አሉን፤ ፍቅር፤ ሃላፊነት፤ እርቅ፤ ትህትና፤ ሰላም። እነዚህንንሁሉ አስረን ቁጭ ብለናል። መቼ ነው የምንፈታቸው? ደግሞ መቼ ነው ሃላፊነት ወስደን እራሳችንን ህዝብ ፊት ዝቅ የምናደርገው። እንዲህ የሚያደርጉ አሉ ግን በኔ አይነቱ ተከበው አይታዩም። እንቅፋትም ሆነናቸዋል።

ቤተ ክርስቲያናችን እንደ አቡነ ጴጥሮስ መምራት መጀመር አለባት። በፖለቲካው መመራት ወይም መቀደም እፍረት ነው። አሁን ከቤተ ክርስቲያን እርቅ በፊት በሃገራችን ፖለቲካ እርቅ ቢመጣ ታላቅ እፍረት አይደለም? ከዛ በሗላ መጀመሪያውኑ ፖለቲካ ነው ያስቸገረን ብለን ልናሳብብ ነው? እነ ቅዱስ ጴጥሮስ በሮሜ ፖለቲካ እየተሰውዉ ደፍሮ ያላሉትን ልንል ነው?! ይህ ቢሆን እጅግ አሳሳዛኝ ነው።

ስለዚህ እንምራ! በሃገር ውስጥና በውጭ ያሉት ስይኖዶስ መካከል ፈጥነን እርቅ እናምጣ። ለኢትዮጵያ ህዝብ ምሳሌ እንሁን። ፈተናው ብዙ ነው። ገና እየበዛ ይሄዳል። ግን እግዚአብሔር ሁልጊዜ በሁሉም ቦታ ከኛ ጋር ነው። ይህን ካመንን ለፍቅር እንድፈር፤ አንፍራ!

3 comments :

  1. ሀሳብዎ ሸጋ ነው:: ግን እኮ ቤተክርስቲያኗን ሀገርቤት እየመሩ ያሉት ካባ ይልበሱ እንጂ ከሆዳቸው እልፍ ብለው የማያስቡ እናታቸውን ይርገጥም በፍልጥ ያገላብጥ "እናቴን ያገባ ሁሉ አባቴ" ነው ባይ በሀይማኖት አባትነት ተኮፍሰው ምእመኑን ከክፉ እንጀራአባት በጨከነ መንገድ የሚያሰቃዩ ሸቃጮች ናቸው:: ቤተክርስቲያን ስትዘረፍ አብረውመዝረፍ ቤትክርስትያን ስትዋረድ አብረው ማዋረድ...ይህም አይደል ስራቸው?

    በውጭው ዓለም ደግሞ በርካታ የሀገር ፍቅር የሚያንገበግባቸው አባቶች እንዳሉት ሁሉ ከወያኔ ተልእኮ ተቀብለው የመጡ ቀሳውስት ለምድራዊው እንጀራ ሽክን ባለ በወጥ ሲሉ የሰማዩን ችላ ያሉ "ለማላውቀው ነገ ከመጨነቅ የዛሬን አጣጥሜ ልብላ" ባዮች ብዙ ናቸው::

    እርስዎ አንዳሉትም ቀሳውስቱ ዙሪያ "ከኔ በላይ ክርስቲያን ለአሳር" ባይ ከክርስትና እምነት አስተምሮት ጋር በቅርብ የማይተዋወቁ ብዙ በጣም ብዙ አሉ:: አቤት ከብሮ ሲመጡ ሲያምርባቸው! አቤት ለቤትክርስቲያን ቀለም ማስቀቢያ ብር ለማውጣት ሲሽቀዳደሙ! በማህበር ደግሶ ለማብላትማ ማን እንደነሱ? እርግጥ ነው እርግጥ ነው ከእነኝህ መሀል ከልብ አማኞች ሀገር ወዳዶችም ብዙ አሉ:: ችግሩ ግን ለኢትዮጵያውቷ ቤተክርስቲያን ተበድረው የስድስት ወር ደሞዛቸውን የሚሰጡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትና ሀይማኖታቸው ጽናት ታስረው ለሚሰቃዩት መነኮሳትና ቀሳውስት ድምጽ አሰሙ ትንሽ ብር አዋጡ ሲባሉ "ቤተክርስቲያን በፖለቲካ ጉዳይ አትገባም እያሉ የሚቆጡ አሉ:: ትናንት በሀይለስላሴም ይሁን በደርግ ወይ በወያኔ ፖለቲካ ግንባር ቀደም ሁነው ሲሳተፉ የነበሩ ዛሬ ቤተክርስቲያን ሃይማኖት ውስጥ አትገባም ብለው እንደነጎድጉዋድ በሚያስተጋባ ድምጽ ሲሟገቱም እናያለን::

    ስለዚህ ጥሪዎ ሰም አግኝቶ ቤተክርስቲያኗ ከሀይለማርያም ደሳለኝ አድርባየንትና መዋረድ በቃኝ በሁዋልም እንኩዋን ቢሆን ከራሷ ታርቃ ቀና ቀናውን መንገድ መሄድ ብትጀምር ይበጃል:: ቤተክርስቲያኗ ለኢትዮጵያውነታችን ህልውና ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበራት እንድትቀጥል ኢትዮጵያዊነትንና እውነትን ትወግን:: እንእንትና ማህበር ይደግሳሉ ብር ያዋጣሉ አንድም እሁድ ነጠላቸውን አጣፍተው ቤተክርስቲያን ከመምጣት አይቀሩም አይነት መመዘኛ ይልቅ ክርስትና ለሚያስተምረው ትምህርት ታማኝ እንሁን ማለቱ ይበጅ ይሆን?

    የጴንጤውንማ ተዉት::ፖለቲካ እየሰራ ፖለቲካ ተኛ መንደር ዝርም አይል:: በኢትዮጵያዊነት ስም ተሰባስቦ እኛ ስለእግዚአብሔር እንጂ ስለኢትዮጵያ አናወራም...ጉድ እኮ ነው::

    ብቻ ይሄ ችግር ክርስቲያኑም እስላሙም ሌላ ሀይማኖት ተከታይም ዘንድ ያለ የጋራ ማህበራዊ ችግራችን ነውና አንዱ ባንዱ ጣት መጠቆም ሳይሆን በጋራ ለጋራ ህልውና መቆም ነው የሚበጅ::

    ReplyDelete
  2. ስለ አስተያየትዎ አማሰግናለሁ። እርግጥ ነው ጉዳዩ ያማርራል! ግን በዚህ ምድር አዲስ ነገር የለም። እግዚአብሔር የራሳችንን ድርሻ ለማድረግ ያብቃን!

    ReplyDelete

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!