Monday, 19 February 2018

የህወሓት ትግል

ለህወሓት እራሱን መቀየር እጅግ ከባድ ስራ ነው የሚሆንበት። እንደምናውቀው ህወሓት የተመሰረተው የጽንፈኝነት በሽታ የኢትዮጵያ ምሁራንንና ፖለቲከኞችን በከባድ በሚያጠቃበት ዘመን ነበረ። ከጽንፈኝነት አልፎ ተርፎ ባህልን እና ተውፊትን የሚንቅ የምሁራን ትውልድ ነበር። ይህ  ትውልድ ነው እነ ህወሓት፤ ሻዕቢያ፤ ኢህአፓ፤ መኢሶን፤ ደርግ ወዘተ የፈጠረው። በዚህ ዘመን የተፈጠረ እና ኮሙኒዝም/አብዮታዊ ዴሞክራሲ/ጎሰኝነት አይነቶችን ርዕዮተ ዓለም እንደ ጣዖት የሚያመልክ ድርጅት መሰረታዊ ተሃድሶ ለማድረግ ከባድ ነው። ይህን በማውቅ እስካሁን ላደረጉት ትንሽም ቢሆኑ የአስተሳሰብ ለውጦች ህወሓት ሊደነቅ ይገበዋል።

ሌሎቻችን ይህ አመሰራረት ለህወሓት ምን ያህል ማነቆ እንደሆነ በቂ የሚገባን አይመስለኝም። በተማሪ ንቅናቄ ዘመን በነ ዋለልኝ መኮነን አይነቱ ተማሪና ምሁራን አመለካከት የኢትዮጵያ መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ኢትዮጵያ ሀገሪቷ እራሷ ጥላቻና ስር ነቅል ለውጥ ይገባት ነበር። የኢትዮጵያ ታሪክና ትውፊት በሙሉ ክፉና የተጣመመ ነውና መደምሰስ አለበት ተብሎ ነበር የሚታሰበው። ሃይማኖትም አብሮ እንደ ጠላት ይታይ ነበር። ኢትዮጵያ እንዳለ ተጥሎ ሙዚቃ፤ ጭፈራና ሙዚየሞች ብቻ ቀርተው ሌላው ባህልና ትውፊት በሁሉም ዘርፍ መጣል አለበት ነበር የነበረው አስተሳሰቡ።

ሻዕቢያና ህወሓት መካከል ደግሞ ከዚህ ሁሉ «የማንነት ጥላቻ» አልፎ የ«አማራ» ትላቻን አቀፉ። ለምን ቢባል ርዕዮተ ዓለማቸው ሁልጊዜ በጠላትነት የሚሰየም ቡድን ስለሚያስፈልገው የአማራ የግዥ መደብ ጨቋኝ ነው ተብሎ የዚህ የ«ጠላትን» ሚና ለመጫወት ምቹ ስለነበር።

እዚህ ጋር ቆም ብለን አንድ ጥያቄ መመለስ አለብን። በዛን ዘመን ከኢትዮጲያ ምሁራንና ፖለቲከኞች መካከል እንደዚህ አይነት አስተሳሰብ የሰፈነው በዓለም ዙርያ የነበረው የግራ ጸንፍ አመለካከት ብቻ ተመስርቶ ነው? በፍፁም። ሃገር ውስጥ ያለው ሁኔታ ነው ታላቁን ሚና የተጫወተው። በዛን ወቅት የነበረው የፖለቲካ አመራር ብዙሃኑ የሚያስፈልገውን የፍትሕና የሰላም መግባሮች ስላላሟላ ነው። መልካም አስተዳደር ባለመኖሩ ብሶት ተከማችቶ ነው ምሁራኑም ፖለቲከኞችም ወደዛ ወደ ሀገር አጥፊ ርዕዮተ ዓለም የገቡት።

ይህ ዋና ነጥብ ነው። ጣቶቻችንን እነህወሓት ላይ ብቻ እንዳንጠቁም ያስታውሰናል። እራሳችንን በሃሰት ከችግሩ መንጭ ነጻ አድርገን እንዳናይ ይረዳናል። ለሀገራችን ህልውና እና ትክክሉን መፍትሄ ለማግኘት «የተማሪው ንቅናቄ እና ተከታዮቹ የተፈጠሩት በራሳችን ጥፋት ነው» ብለን ማመን አለብን። እነዚህ ነገሮች ከመሬት አልተነሱም። ሁላችንም ጥፋታችንን መቀበል አለብን። ፈራጅ መሆን የለብንም። እርግት መፀፀት ነው ያለብን። በዚህ አህነት አስተሳሰብ ብቻ ነው እውነተኛው ፍትሕ እና ሰላም የሚገኘው። ሌሎችን ዝምብሎ በመኮነን ሳይሆን ሌሎችን በመረዳት እና እንደወንድማማቾች አንዱ የሌላውን ችግርና አመጣጥ በማወቅ ነው መፍትሄ ማምጣት የሚቻለው።

በዚህ ረገድ የህወሓትን እና የሻዕቢያን ታሪክን ስንመለከት እነዚህ ድርጅቶች ከተመሰረቱ ጀምሮ በተለይ የደርግ የኢትዮጵያ መንግስት ጽንፈኝነታቸውን እና በኢትዮጵያ ያላቸውን ጥላቻ እንዲጨምርና እንዲንር ነው ያደረገው። የደርግ መንግስት የነህወሓትን ጥላቻና ብሶት ደመደመላቸው። በታሪክ በጎሳና በኢትዮጵያዊነት ያላቸውን ርዕዮተ ዓለማቸውን አረጋገጠላቸው። ከዛም ይባስ ሀገሪቷን አሳልፎ ሰጣቸው!

በ1950 አብዛኛው ኤርትራዊ ኢትዮጵያን ይወዱ ነበር ኢትዮጵያዊ ነን ይሉ ነበር። 40 ዓመት በኋላ ኢትዮጵያን ይጠሉ ነበር ኢትዮጵያዊም አይደለንም አሉ። እጅግ ያሳዝናል። የሀገራችን የፖለቲካ ችግር መጠኑን ምን ያህል እንደነበረ አሁንም እንደሆነ በደምብ ያሳየናል።

ህወሓት ስልጣን ከያዘ ጀምሮ የሚያምንበት እና እንደ የስልጣን ስልት የሚጠቀምበትን ጎሰኝነትን አራግቧል። በህግ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በማሕበረሰቡ ፕሮፓጋንዳ በመንዛት። ህወሓት ለነባር ኢትዮጵያ ያለውን ጥላቻ በተግባር አሳይቷል። ለምሳሌ «ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ይድከም»፤ «ኢትዮጵያዊነት ይድከም» የህወሓት እና ደጋፊዎቹ መፈከር ነበሩ። ትንሽ ቢያሰቡበት ኖሮ ግን ይህ አቋማቸው ለሚወክሉት የትግራይ ህዝብ እጅግ ጎጂ እንደሆነ ይገነዘቡት ነበር! አብዛኛው ትግሬ ኦርቶዶክስ ነው። ትክክል ቢሆንም ባይሆንም የጽንፈኛ ሙስሊም አካሄድ ያሳስባቸዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ጎሰኝነት ከሰፈነ በኢትዮጵያ ተጠቃሚ የሆኑት ትንናሽ ብሄሮች እንደ ትግሬና ጉራጌ ነው በመጀመርያ የሚጎዱት። እንደ ኦሮሚያ አይነቱ ትልቅ ብሄር ጎሰኝነትን ቢያራምድም የሚከተሉትን ጉዳቶችን በመጠኑም ቢሆን በግዙፍነቱ ምክንያት ሊቋቋማቸው ይችል ይሆናል። ትግራይ ግን የጎሰኝነትን እልቂት ልትቋቋም አትችልም። በነዚህ ምንክንያቶች የትግራይ ጥቅም የነበረው አሁንም የሆነው በጎሳ ያልተከፋፈለች አንድ ፈደራላዊ ኢትዮጵያ ነው። ግን ህወሓት ይህን እውነታ ትቶ የሚወክለውን ህዝብ የሚጎዳው አቋምን አራመደ።

ይህ የህወሓት ቅዠት (ወይም schizophrenia)በኃይለ ሥላሴ ዘመን የነበረው የኢትዮጵያ ፖለቲካ አለመስተካከል ምን ያህል ጉዳት እንዳመጣ ያሳየናል። የተለያዩ ጎራዎች ለመብትና ለጥቅማቸው ከመታገል ፋንታ በሚጎዳቸው እና ጥማቸውን በሚሽር መንገድ እንዲ ሄዱ አረገ! ህወሓት ለዚህ ሁሉ ዓመት ህዝቧን ለሚጠቅም አንድነት ከመቆም ፋንታ ህዝቧን ለሚጎዳ ጎሰኝነት ቆመች! ከጎሰኞች ጋር አብሮ አጨበጨበች። ምክር አልሰማ (https://www.youtube.com/watch?v=WaDzzD8uCYU&t=9s) አለች። አሁን ጉዳቱን እያየች እያለ እንዴት የ40 ዓመት እምነቷን ትቀየር?!

ከባድ ነው። ቅድም እንዳልኩት እስካሁን መግዛታቸውም አሁን ለውጥ ለማድረግ ማሰባቸውን ይደነቃል። ከተነከሩበት ርዕዮተ ዓለም መውጣት ከባድ ነው። ይህ ነው የህወሃት ትግል። የኛ ትግል ደግሞ አይዟችሁ እያልን ሳንፈርድባቸው እራሳችንን ደግሞ እያጠነከርን መሄድ ነው።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!