Wednesday, 26 October 2016

ያልተጠበቀው ህዝባዊ ዐመፅ የት ይደርስ ይሆን?

2009/2/16 .. (2016/10/26)

(pdf)

ላለፉት የተወሰኑ ወራት የተካሄደው የህዝባዊ ዐመፅ እንደሚከሰት አውቅ ነበር የሚል ካለ ቀልደኛ ነው። መንግስት አልጠበቀውም፤ ተቃዋሚዎች አልጠበቁትም፤ ሚዲያውም የፖለቲካ ተንታኞችም አልጠበቁትም። እኔም ጭራሽ አልጠበኩትም።

እርግጥ የኢህአዴግን መርህዎች ለሀገሪቷ አደገኛ ናቸው ብለን የምናምነው ሁልጊዜ ችግር ይመጣል ብለን እንዘፍናለን። እንደዚህ ሊቀጥል አይችልም፤ የሰውዉ ብሶት አንድ ቀን ይፈነዳል እንል ነበር... 25 ዓመት። ግን አሁን ይህ ዐመፅ ይነሳል ብለን አልጠበቅንም።

ዐመፁ አንዴ ከተነሳ በኋላ ትልቅ ችግር መኖሩን የሚያሳዩ ምልክቶች እንደነበሩ ማየት እንችላለን። ባለፉት ሁለት ዓመታት ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ሙስናን ለመቆጣጠር የነበራቸው ጠንካራ ፍላጎት፤ ይህ ባለመሆኑ ብስጭታቸውን በአደባባይ እስከ መግለጽ ያደረጋቸው ሙስናና አድሎ ምን ያህል ያሳሰባቸው እንደነበረ ያሳያል። ህብረተሰብ ውስጥም ስለ ሙስናና በተለይ አድሎ የነበረው ማግሮምሮም በየዓመቱ እጅግ እያየለ እንደሆነ ይታወሳል። ስለ አዲስ አበባ «ማስተር ፕላን» የነበረው አቤቱታ ትልቅ ምልከትም ነበር። ግን ማንም ይህ አይነት ዐመፅ ይከተላል ብሎ የገመተ የለም።

እኔ ያልገመትኩበት ምክንያት እኛ ኢትዮጵያኖች የኢህአዴግን የመንግስት ስረዓት ተቀብለነዋል ብዬ ገምቼ ስለነበር ነው። ይህ እጅግ ያሳዝነኝ ነበር። ልክ እንደ የቻይና ህዝብ ለ «ልማት» (ገንዘብ) ብሎ ለገዥ ፓርቲው ክብሩንና መብቱን እንደሸጠ የኛም ህዝብ ለገንዘብ፤ ለኮንዶሚኒየም፤ ለስራ እድል፤ ልድጎማ፤ ለሞቢለ ስልክ፤ ወዘተ የ«ልማት» ውጤቶች ብሎ ማንነቱን ክብሩንና መብቱን ለኢህአዴግ ሽቷል ብዬ ገምቼ ነበር።

ጎረቤቱ ቤቱንንና መረቱን መንግስት ነጥቆት ከከተመ ውጭ ባዶ መሬት ላይ ሲወረወር መልካም እድል ብሎ ምንም ሳይረዳውም የሚሸኘው አይነት ህዝብ ነው የተገነዘብኩት። በሙስና ምክንያት ፍርድ ሜቱ ለባለንጀራው ትክክለኛ ፍትህ ሲያጎልበት ከማጽናናት ፋንታ ዞር ብሎ የማይጠይቀው ህዝብ። የቀበሌ ሹሞች ለልማት የመጣውን ገንዘብ ሲሰርቁ ለኔም ትንሽ ባካፈሉኝ የሚል ህዝብ። እንደዚህ አይነት ኢሰባዊ ድርጊቶች ቅርም የማይለው ህዝብ። ሙስና ምንም የማይመስለው ህዝብ። እርስ በርስ መተሳሰብ የጠፋበት ህዝብ። እንደ ጥሩ ምሳሌ የሆኑት መሪዎቹ ለገንዘብ ብሎ ምንም የሚያደርግ፤ የገዛ ወንድሙን ጎረቤቱን ዘመዱን የሚሸጥ። ልጁን ለገንዘብ ብሎ እየማቀቀች «ዶላር» እንድትልክ አረብ ሀገር የሚልክ ህዝብ። ስለ እድር የሚያግሮምርም የመሃበራዊ ኑሮ ጥቅም የጠፋበት ህዝብ። ማንነቱን ለማጥፋት የቸኮለ ህዝብ፤ ለፈረንጅ የሚሰግድ፤ ልጁን ወደ ውጭ ሀገር ለመላክ የፈለገውን የሚያደርግ፤ ቤት ቁች ብሎ የፈረንጅ ቅኝ ግዛት ማስፈጸምያ የቴሌቪዥን «ድራማ» ሲከታተል የሚውል የደነዘዘ ህዝብ። ወጣቶቹ ስለአርሴናል የሚገዳደሉ ህዝብ። ቤተ ክርስቲያኑ በሙስና የተሞላች፤ መስጊዷ የተከፋፈለች ህዝብ። የኢትዮጵያ ህዝብ በዚህ ሁኔታ ናትና በቅርቡ ምንም አይነት ፖለቲካዊ ለውጥ አይመጣም ብዬ ደምድሜ ነበር።

ግን ይሄው ዐመፅ ተጀመረ። ሆኖም የሚዘልቅ አይመስልም። ይህን የምለው ለመተንበይ አይደለም፤ ትንቢቴ ዋጋ እንደሌለው ታይቷል። ዐመፁ ይቀሽፋል የምለው ዐመፁ ወደ ጥሩ ነገር እንዲመራ፤ ፍሬአማ እንዲሆን ብዙሃኑም የፖለቲካ መሪዎችም በቂ ስራ እንዳልሰሩ ለማሳየት ያህል ብዬ ነው። እስካሁን ማንም የህዝቡን ጥያቄና ፍላጎት በተገቢው ደረጃ ያሰባሰበና ለውይይት ያቀረበ የለም። እስካሁን ብሶትና እሮሮ ብቻ ነው የሚሰማው። ብዙሃኑ ብሶቱንና እሮሮውን መግለጹ ተገቢ ነው ግን ከፖለቲካ መሪዎቹ ማቀናበርና ማወሃድ ከሌለ የትም አይደረስም።

በኔ እምነት ዐመፁን ያስነሳው የመጀመሪያ ደረጃ ምክንያት አድሎ ነው፤ በተለይ በዘር የተመሰረተ አድሎ። ህብረተሰብ ውስጥ ተቀላቅሎ አስተውሎ ለሚመለከት ይህ ሊያመልጠው አይችልም፤ የአብዛኛው ህዝብ እሮሮ ከአድሎና ሙስና ጋር የተያያዘ ነው። የፍትህ ጉድለት፤ የዴሞክራሲ ጉድለት፤ የጎሳ አስተዳደር፤ ወዘተ ሁለተኛ ደረጃ ምክንያቶች ነበሩ። ግን መፍትሄ ከተፈለገ እነዚህ፤ ፍትህ፤ ዴሞክራሲ ወይም ተጠሪነት፤ እኩልነት፤ ናቸው መሰረታዊ ጉዳዮቹ! ሙስናና አድሎ የኔዚህ ርዥራዦች ናቸው። ስለዚህ የህዝቡም የፖለቲካ መሪዎችም የምሁራንም ቱክረት እነዚህ ጉዳዮች ላይ ካልሆነ ትክክለኛ ለውጥ ሊመጣ አይችልም።

ዐመፁ እንደምጠብቀው ከበረደ ቀጥሎ ምን ይደረግ? ከዚህ በፊት እንደጻፍኩት መልካም አስተዳደርና መልካም ህብረተሰብ እንዲሆንልን የምንፈልገው በየ ጎራችን፤ ከምነግስት አስተዳደር ውስጥ ቢሆንም፤ በበኩላችን መልካም ስራ መስራትና ጥሩ ዜጋና ምሳሌ መሆን ነው ማድረግ ያለምን። ለውጥ የምንፈልገው አብዛኛ ከሆንን ሁላችንም ይህን ካረግን የምንፈልገው ህብረተሰባዊና መንግስታዊ ለውጥ ይመጣል።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!