Thursday, 13 October 2016

ኦርቶዶክስ ክርስትናና ፖለቲካ

2009/2/3 .. (2016/10/13)

«እግዚአብሔር በሁልም ስፍራ አለ በሁሉም ነገርም ይገኛል» (God is everywhere present and in all things) አንድ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት መሰረታዊ እምነት ነው። ይህ አባባል እግዚአብሔር የፈተራት ዓለም በሁለት በ«አለማዊ» እና በ«ሃይማኖታዊ» ስፍሮች እንዳልተከፈለች ይገልጻል። ወደ ቤተሰባችን፤ ስራችን፤ ንግዳችን፤ ዘፈናችን፤ መዝኒያናችን፤ ስፖርታችን፤ ትምህርትቤታችን፤ እርሻችን፤ ፖለቲካችንም ስንሄድ እግዚአብሔርንና እምነታችንን ትትን መሄድ አይቻላም! እግዚአብሔር በነዚ ስፍሮች ሁሉ አለና። ግድብ የለውም። ስለዚህ ፖለቲካና ክርስትና የተለያዩና የማይገናኙ ናቸው ማለት አይቻልም።

ስለዚህ ክርስትያኖች በፖለቲካ ልንሳተፍ እንችላለን። የማህበራዊ ኑሮ ፖለቲካን ስለሚይካትት ብንፈልግም ባንፈልጉም በተወሰነ ደረጃ ቢሆንም ፖለቲካ ውስጥ ተሳትፈናል። ሁለት ምሳሌዎች ልስጣችሁ፤ ቀረጥ መክፈል ማለት ገንዘብ ለመንግስት መስጠት ነው። የዚህን ገንዘብን አጥቃቀም የሚወስኑት ፖለቲከኞች ናቸው። በገንዘባችን ለሚያደርጉት ግን ተጠሪ ነን ግንዘባችን ነውና። በቀበሌ ወይም በማንኛውም የምንግስት መሥሪያቤት ስንገለገል ፖለቲከኞች የዘረጉትን የአስተዳድራዊ ዘዴ መቀበል ማለት ነው። ብለት ኑሮአችን ፖለቲካ አይጠፋም። ፖለቲካ አንዱ የህይወታችን ዘርፍ ነው።

ታድያ የአንድ ክርስትያን ፖለቲካዊ ኑሮ እንዴት መሆን አለበት? ይህን ለመመለስ በመጀመርያ አንዳንድ መሰረታዊ የሆኑ የክርስትና እምነቶች እንመልከት። ከላይ እግዚአብሔር ከሁሉም አለ የሚለውን አባባል ጠቅሽያለሁ። ቀጥሎ «በዐይነህ ውስጥ ያለውን ግንድ ሳትመለከት፤ በወንድምህ ዐይን ያለውን ጉድፍ ለምን ታያለህ» የሚለውን እስቲ እንመልከት። ባለንጀራችሁን እንደራሳችሁ ውደዱ ይበልጥ ደግሞ እኔ እንደምወዳችሁ ያህል ውደዱት ብሎ ክርስቶስ አዞናል። ይህን አባባልንም እንመልከት።

ሌላ አባባል፤ ቅዱስ ባስሊዮስ እንደዚህ አሉ፤ « የባለንጀራህ ሀጥያት ብቻ ከሆነ የሚታይህ ያንን ብቻ ከማየት ይልቅ በፊትም አሁንም የሚያደርገውን ጥሩ ነገሮች እንዳሉ ተገንዘብ። መፍረድን ትተህ ይህን ለማድረግ ስትሞክር ጭራሽ እርሱ ካንተ የተሻለ እንደሆነ ትረዳለህ።» ይህ አባባል ሁለት መሰረታዊ እምነቶታችንን ይገልጻል፤ እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉም ሰው ትንሽም ቢሆን ጥሩነት ስላለው በሌላ ሰው መፍረድ ተገቢ አይደለም።

ክርስቶስ «እኔ በልቤ የዋህና ትሑት ነኝ» ብሎ እኛም እንደሱ እንድንሆን አዞናል። ትሕትና የቀደመውና ዋናው ሀጥያታችን «ትዕቢት» ተቃራኒና መድሀኒት ስለሆነ የሃይማኖት አባቶች የምያተኩሩበት መልካ መግባር ነው። አባ ይስሐቅ ዘሶሪያ እንዲህ ብለዋል፤ «ጨው ለምግብ እንደሚሆን ትህትና ለሁሉ መልካ መግባር ይሆናል።»

የክርስትያን ፖለቲካ ኑሮ ከላይ በጠቀስኳቸው አባባሎች የሚያስተምሩን መልካ መግባሮች ነው መካተትና መመራት አለበት፤ 1) እግዚአብሔር ከሁሉም አለ፤ 2) የሌላውን ሀጥያት ከማየት ፋንታ የራሳችንን ሀጥያት አይተን ንስሃ እንጋባ እናርማቸውም፤ 3) ባለንጀራችንን ክርስቶስ እንደሚወደን እንውደድ፤ 4) በሰው አንፍረድ፤ ትሑት እንሁን ከትዕቢትና ትምክህት እንራቅ።

በዛሬው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ አንድ ክርስትያን እነዚህን እምነቶች ተከትሎ ምን ሊያደርግ ይገባዋል? አትፍረዱ፤ ትሑት ሁኑ፤ የራሳችሁን ሀጥያት ተመልከቱ፤ አብዛኞቻችን በፖለቲካ ዙርያ የሌላው ሰው፤ ወገን፤ ጎሳ፤ ፓርቲ ጥፋት ብቻ ነው የሚታየን። የኢህአዴግ፤ የህወሓት፤ የኦነግ፤ የሻእቢያ፤ የኢዴፓ፤ የደርግ፤ የኢሀፓ፤ የኃይለ ስላሴ፤ የዘንድሮ ተቃዋሚ፤ የዲያስፖራ፤ ወዘተ። አንድ ክርስትያን እራሱን ሳይመረምር የራሱን ጥፋቶች ተረድቶ ንስሀ ሳይገባ የማንንም፤ የኢህአዴግንም፤ ጥፋትና ስህተትን ላይ ማተኮር የለበትም።

ግን ምን የፖለቲካ ሀጥያት አለብኝ ብለን የምንጠይቅ ብዙ ነን። ከበርካታ ሰዎች ከገደለው ካሰቃየው ኢህአዴግ፤ ደርግ፤ ወዘተ ምኔ ሊወዳደር ይችላል። እስቲ ይህን ጥያቄ በምሳሌዎች ለመመለስ ልሞክር።

ጎረቤቴ ለ«ኢንቬስተር» ተብሎ መሬቱን ሲነጠቅ ረዳሁትን? ትንሽም ነገር አደረግኩለት?የምፍረአቸውን የሰፈሬን ዱሪዬዎችን ለመርዳትና ጥሩ መስመር ለማስያዝ ያረግኩት ነገር አለ? ወይም የራሳቸው ጉዳይ ብዬ ዞር ብዬም አላያቸውም። ችግር እስኪያመጡ። በፖለቲካ ዙሪያ «ኦሮሞ» ሲባል በልቤ ፍርሃትና ጥርጣሬ አይሰፍንም? ነው በንጹ ልቦና ጉዳዩን እመለከታለሁ? «እነሱ ከሚገዙን ወያኔ ይግዛን» ብዬ አስቤ አላቅምን? ግን አንድ ቀንም «ከነሱ» ጋር ቁጭ ብዬ ተወያይቼ አላቅም። ከጎረቤቶቼ ጋር ድሮ ተጣልቼ አሁንም አልተቀየምኳቸውም? በዚህ ጥላቻ ምክነያት እንኳን ለፖለቲካ ለውጥ ለምንም ነገር ከነሱ ጋር መተባበር አልችልም አይደ? ከባልደረባዬ ምሁር በትንሽ አስተሳሰብ ልዩነት ምክነያት ጠላቶች አልሆንም? እንኳን አብረን ለመስራት መተያየትም አንፈልግም አይደለምን? ስራተኞቼን እንደ ሰው ቆጥሬ አላውቅም እሁድ ቤተክርስትያን ለመሄድም እድል አልሰጣቸውም! ዘላለማዊ ቂም አልፈጠርኩባቸውም? ኢህአዴግ ይህንን ቂም ተጠቅሞ እነዚህን ሰራተኞቼን እኔን ለመግዳት ወይም የኔን አቋም ለማዳከም መጠቀም አይችልምን? የማይገባኝ ጥቅም ለማግኘት ጉቦ ሰጥችሄ አላውቅምን? ከስራ ቦታዬ በኔ ሃሳቦች የማይስማሙትን አልኮንንም? ሰራተኞች ሲሳሳቱ ችግራቸውን ከመረዳት ፋንታ አልፈርድባቸውም? ልጄ ውትድርና ገብቶ የማያምንበትን ክፉ ድርጊቶች እንዲያደርግ ይታዘዛል ያደርጋል። ልጄ ነው የሚጦረኝ እና እንደዚህ አይነቱን ጉዳይ ለሱ በማንሳት ላበሳጨው አልፈልግም እላለሁ። ታድያ እንደ የኢግዚአብሔር ልጅ ሃላፊነቴን አልካድኩምን?

እራሳችንን በደምብ ከመረመርን እነዚህ አይነቶቹ ሀጥያቶች እንዴት ከኛ ወደ ህብረተሰቡ፤ ከህብረተሰብ ወደ መንግስታችን እንደሚተላለፍ እንደሚያንጸባርቅ ልንገነዘብ እንችላለን። ክርስትያኖች የሁላችንም ኃጢአት የተገናኘው እንደሆነ እናምናለን። ለሌሎችንም ኃጢአት ሃላፊነት እንዳለብን እናምናለን። አባቶች ይህን ተጠንቅቀው ነው የሚያስተምሩን። ከላይ እንደምሳሌ የጠቀስኳቸው ኃጢአቶች እንዴት አሁን ካለው የምንግስት ስረዓት ባህሪ ጋር እንደሚገናኙ ግልጽ እንደሆነ ተስፋ አለኝ።

ክርስትያን በመሆኔ መጠን ለነዚህ ኃጢአቶች ንስሃ ገብቼ እየወደኩኝ እየተነሳሁኝ እያስተካከልኩኝ መኖር ነው የሚጥበቅብኝ። የፖለቲካ ኑሮዬም እንደዚህ ነው መሆን ያለበት። የምደግፈው የፖለቲካ አቋም፤ አመለካከት፤ ፓርቲ፤ ርዕዮተ ዓለም፤ ወዘተ ከክርስትያንነቴ ስር ነው መሆን ያለባቸው። እንደ ክርስትያን እስከኖርኩኝ ድረስ ፖለቲካው እራሱን ያስተካክላል።

ሆኖም ማንም ሰው አጥፊና ክፉ ነበር የሚያደርግ መንግስት ወይም ተቋምን መታገል የለበትም ማለት አይቻልም። እያንዳንዱ የራሱን ልብ ያውቃልና ልታገል ቢል በሱ ልፈርድ አልችልም፤ ግን ትግሉ ውጤታማ እንዲሆን በመጀመርያ የራሱን ልብና ገበና መፈተሽ አለበት። ሳይፈትሽ ሌላውን ለማስወገድ ብቻ ከታገለ ትግሉን አያሸንፍም። ወይም ይባስ ያሸንፍና ከታገለው የባሰ ሆኖ ይገኛል። ይህን እውነታ ሃይማኖታችን ያስተምረናል። እውነታም ስለሆነ በታሪክ በትደጋጋሚ ሲከሰት አይተናል! ስለዚህ በመጀመርያ ክርስትያን እንሁን፤ ሙሉ ክርስትያን እንሁን። ከሆንን ሌላው እራሱን ያስተካክላል።

2 comments :

  1. ምን? ምን? "መጀመሪያ ክርስቲያን እንሁን"???? "ሌላው እራሱን ያስተካክላል"???? አልገባኝም። የርስዎ አስተያየት ሲገባኝ ሰው ራሱን ሳያጸዳ ስለ አገር ጉዳይ መናገር የለበትም ነው የሚሉን:: ታዲያ ዝምብለው ፖለቲካ ለንጹሃን ብቻ ነው ለምን አይሉንም

    ReplyDelete
  2. ጥሩ ጥያቄ ነው። ከጻፍኩት ያችን ጥቅስ ብቻውን ከተነበበ እርሶ እንዳሉት ሊተረጎም ይችላል። ግን...

    ክርስቶስ «አስቀድመህ ከዓይንህ ምሰሶውን አውጣ፥ ከዚያም በኋላ ከወንድምህ ዓይን ጉድፉን ታወጣ ዘንድ አጥርተህ ታያለህ» ይለናል ደግሞ «ወንድምህም ቢበድልህ በግሉ ምከረው ከሰማህ መልካም።ካልሰማህ ሁለት ሦስት ሰው ይዘህ ምከረው» ይላል።

    ትርጓሜው እስከሚገባኝ እንደዚህ ነው። አብዛኛው የሰው ልጅ የሌሎችን ጥፋት መገንዘብና መፍረድ አያቅተውም፤ የራሳችንን ስህተቶች ማየት ነው የሚያቅተን የማንፈልገውም። በተጨማሪ የሌላውን ስህተት ላይ ስናቶኩር የራሳችንን ስህተቶች ያስረሳናል፤ ይበልጥ አብዛኛው ጊዜ የሌላውን ላይ የምናቶኩረው ከራሳችን ጥፋት ለመሸሽ ነው! ስለዚህም ነው የሃይማኖት አባቶች እራሳችን እንድንመረምርና ሌሎችን ላይ እንዳንረርድ የሚያስተምሩን።

    ሌላው እምነታችን ደግሞ እንደዚህ ነው፤ ክርስቶስ «የዓለም ብርሃን ናችሁ» ብሎናል። «የሰላምን መንፈስ ስትቀበሉ ዙሪያችሁ በሺህ የሚቆጠሩ ይድናሉ» አለን የሩሲያ ኦርቶዶክስ አባት ቅዱስ ሴራፊም ዘሳሮቭ። ከመናገርና መስበክ ይልቅ (አስፈላጊ ቢሆኑም) ጥሩ መሆንና ጥሩ ምሳሌ መሆን ነው ዓለምን የሚቀይረው ማለት ነው። ሁላችንም ጥሩ ክርስቲያን ብንሆን እፖለቲካ ችግር አይኖርም። ይህ አተሳሰብ ህልም ነው ማለት ይቻላል። ነው እንዴ! የፖለቲካ ምርጫም ህልም ነው ማለት ነው። የኔ አንድ ድምጽ ከሚሊዮኖች ማህል ምን ዋጋ አለው ብለን ሳንመርጥ የምንቀር አለን። እንደዚሁ አስቦ ሁሉም ባይመርጥ ምን ይኮን ነበር። ሰውዉ የሚመርጠው አንድ ድምጼ ልዩነት ያመጣል ብሎ ነው።

    ለማጠቃለል ሁለት ነገሮች አሉ፤ መጀመሪያ በሚገባው ጥንቃቄ ራስን መመርመርና የራስን ጥፋት ማስወገድና ጥሩ ምሳሌ በመሆን ዙሪያችን ያሉትን መቀየር።

    ReplyDelete

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!