Tuesday, 25 October 2016

የአንድ ዲያስፖራ ኑዛዜ

2009/2/15 ዓ.ም. (2016/10/25)

በአንድ ዲያስፖራ የተጻፈ…

ችግርን ለመፍታት በመጀመሪያ የችግሩ ዋና ምክንያቶች በትክክሉ መገኘት አለባቸው። እነዚህ ምክንያቶች ተገኝተው ሲፈቱ ነው ዋናው ችግር የሚፈታው። የችግሩ ምክንያቶች ወይም ምንጮች በትክክሉ ካልተገኙ ችግሩ መቼም አይፈታም። ይህን ሁላችንም የምናውቀው እውነታን በመጀመርያ የምጠቅሰው እኔ ከሀገሬ ኢትዮጵያ የፖለቲካና መሃበረሰባዊ ችግሮች ምክንያቶች አንዱ ነኝ ብዬ ስለማምን ነው።

ከማልፈልገው መንግስት ለመሸሽ «ኑሮ ለማሸነፍ» ብዬ ያሳደገችኝን ሀገሬ ኢትዮጵያን ትችያት ወጣሁኝ። በምሳሌ ደረጃ ቤቴን ትቼ ወጣሁኝ ማለት ይቻላል፤ በጣም በመቸኮሌም የቤቴን ቁልፍ ለማንም በአደራነት አልተውኩም። ባዶና አለ ጠባቂ የተውኩትን ቤት ሌላ ሰው ገብቶ ማስተዳደር ጀመረ። የቤቱን እቃ በሚፈልገው መልክ አሸጋሸገ፤ የማይፈልገውን እቃ ሸጠ ወይም ጣለ፤ የሚፈልገውን አዲስ እቃ ደግሞ ገዛና አስገባ። እኔ ከሩቅ ከዲያስፖራ ሆኜ እመለከተለሁ አዝናለው እናደዳለው እጮሃለውም። ቤቴን በመጀመሪያው ባልተውኩኝ ኖሮ።

በርካታ የትምህርት ጓደኞቼ እንደኔ ውጭ ሀገር ናቸው። አቃቸዋለሁ፤ ጥሩ ችሎታ ያላቸው ደህና ሰዎች ናቸው። ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የበቁ የሀገራችን ምርጥ ተማሪዎች ነበሩ፤ ሀገሪቷን በደምብ ማገልገል የሚችሉ። ግን ዛሬ ሀገራቸውን ለቀው ውጭ ናቸው፤ አሜሪካንን ያገለግላሉ፤ ወይ ስዊድንን ያገለገላሉ። ታድያ እነዚህ ሁሉ ከሀገር ወጥተው ማን ነው የቀረው? እኔ ከሀገራችንን ከሚመሩት የተሻልኩኝ፤ እንደነሱ ክፉ ያልሆንኩኝ፤ ሀገር ወዳድ ነኝ ብዬ የማምን ከሆነ ከሀገሬ መውጣቴ ምን ይባላል። እራሴን አውጥቼ ሀገሬን ለክፉ ናቸው የምላቸው ሰዎች ትችያታለሁ ማለት ነው። ትልቅ ጥፋት አለብን።

አንድ አስተማሪ የቤተ ክርስትያን ተረት ልንገራችሁ… በአንድ ወክት የቤተ ክርስትያን አመራርና ካህናት በከባድ የመንፈሳዊ ፈተና ተይዘው ነበር። በካህናቱ መካከል የእምነት ጉድለት፤ የስነ መግባር ጉድለት፤ የሙስና ብዛት፤ ወዘተ ይታይ ነበር። እጅግ ከባድ ዘመን ነበር። በዚህ ጊዜ አንድ ደህና ኑሮ ያላት ሴት ወይዘሮ ወደ አንድ የታወቁ መንፈሳዊ አባት ለራስዋ ጉዳዮች ምክር ለማግኘትና ንስሀ ለመግባት ትሄዳለች። ከኚህ አባት ጋር ቁጭ ብላ መወያየት ስትጀምር ግን ዋና ጉዳይዋን ትታ ስለ ቤተ ክርስቲያን አመራሮችና ካህናት ችግር ብቻ ታወራለች ታጉረመርማለችም። የምታማክራቸው አባት በትዕግስት አቤቱታዋንና ወሬዋን እስክትጨርስ ድረስ አዳመጧት። ሁሉንም ተችታና ኮንና ጨረሰች። ቀጥሎ እኚህ ታላቅ አባት ልጆች እንዳሏት ጠየቋት። አዎን ሁለት ሴቶችና ሁለት ወንዶች አሉኝ አለች። ከነዚህ ወንድ ልጆችሽ አንዱ ቄስ ቢሆንስ ብለው ጠየቋት። በፍጹም፤ እንዴት ይሆናል ብላ ተቆጣች። እንዴት ለልጀ ገንዘብም እውቀጥም የሌለውን ስራ እመኝለታለሁ አለች! ታድያ የራስሽ ልጆች ካህን እንዲሆኑ ካልፈለግሽ ማን ነሽ በፈቃዳቸው ካህን እንሆናለን ያሉትን የምትኮንኙ ብለው ታላቁ አባት ወቀሷት አስተማሯትም።

ሀገር ችግር ላይ በሆነበት ጊዜ መሸሽ ክህደት ነው ማለት ይቻላል። እኔ ሀገሬን ከድጂያታለሁ ለማለት ወደኋላ አልልም። ጥፋትንና ድክመትን ማመን የመጀመሪያ የችግርን መፍታት እርምጃ ነው። አንድ ሰው ቤተሰብ ውስጥ ችግር ካለ ቤተሰብነቱን ክዶ ሸሽቶ አይሄድም። ልጀ ካስቸገረኝ ልጄ አይደለህም ብዬ አላባርረውም። ካባረርኩት ካድኩት ማለት ነው። ሀገርም እንደዚህ ነው። ሀገር ወዳድ ነኝ ማለትና ሀገር ችግር ላይ ስትወድቅ መሸሽ ተጻራሪ ናቸው!

እውነት ነው፤ አንዳንዴ ሽሽት ግድ ነው። ድንግል ማርያም ልጇን ክርስቶስን ይዛ ሸሽታለች። ግን ሽሽቱ አላማን ለማሳካት ነው እንጂ ለመሸሽ አይደለም። እውነቱን ለመናገር እኔ ግን ወደ ዲያስፖራ የመጣሁት ለመሸሽና የሀገሬን ችግር ለሌሎች ለመተው ነው። ለሀገሬ አላማ ኖሮኝ አይደለም። ኢትዮጵያ ያሉት ታግለውልኝ ደህና መንግስት ሲያመጡ እመለሳለሁ ብዬ ነው። ግን ያም ቢሆን የምመለስ ይመስላችኋልን? ከሃዲ ነኝ፤ እውነት ነው፤ ጥፋቴን አምናለሁ።

ግን ሀገሬን እውዳለሁ፤ ፖለቲካዋ እንደዚህ ወይም እንደዛ መሆን አለበት፤ መሃበረሰቧም እንደዚህ ወይም እንደዛ መምሰል አለበት፤ ህዝቡ መሰልጠን አለበት፤ መንግስትም አሰራሩ እንደዚህ መሆን አለበት ብዬ አስባለሁ እለፈልፋለውም። ሀሳብና ወሬ ብቻ ሀገር ወዳድ የሚያደርግ ይመስለኛል።

ሀገር ወዳድ ሆኜ ግን እንዴት ነው ተግባሬ ያንን የሀገር ፍቅርን ሊያንጸባርቅ የሚችለው? ልጆቼን እንኳን ቋንቋቸውን አላስተማርኳቸውም። ሀገረ ወዳድነት ይህ ነው? ያውም «አላስተማርኳቸውም» የሚለው ቃል በቂ አይገልጸውም፤ አላስተማርኳቸውም ሳይሆን እንዳይማሩ ከልኪያቸዋለሁ። ሌላው ሁሉ መጤ፤ ሂስፓኒኩ፤ ቻይናው፤ ሶማሌው፤ ጣሊያኑ፤ ወዘተ ቋንቋውን ከቤት እየተናገረ ልጆቻቸው በተዘዋዋሪ ቋንቋቸውን ይችላሉ። እኔ ግን ከቤቴ በደምብ የማልችለውን እንግሊዘኛ (ወይም ጀርመን ስዊድኛ ወዘተ) እየተናገርኩኝ ልጆቼ ቋንቋቸውን እንዳይችሉ አረጋለሁ። ባህላቸውን ወጋቸውንም ላይላዩን ብቻ ነው የማስተምራቸው። እውነቱን ለመናገር ልጆቼን ፈረንጅ እንዲሆኑ አድርግያለሁ። ኢትዮጵያዊ ትውልድ በኔ ቆሟል። ታድያ ምን አይነት ሀገር ወዳድ ነኝ?

ወደ ክህደቴ ልመለስና… እርግጥ እራሴን ለማጽናናት ያህል አንዳንድ ግዜ ለክህደቴ ስበቦችና አጉል ምክንያቶች እፈጥራለሁ። አንዱ «ከሀገሬ ብቆይ እታሰር ነበር» ነው። «ህሊናዬን ሽጥቼ ካልሆነ ሀገሬ መስራት አልችልም።» ታድያ ሀገር ቤት ያሉት ወገኖቼ በሙሉ ወይ ታስረዋል ወይ ህሊናቸውን የሸጡ አደርባዮች ሆኖዋል ማለት ነው? ወይ ፍርድ! በአንድ በኩል ገዥው መንግስት የአናሳ ህዝብ ነው እላለሁ። በሌላው በኩል ሁሉንም ይቆጣጠራሉ እላለሁ። እነዚህ የሚጻረሩ ሀሳቦች ናቸው! እውነቱ እንደዚህ ነው፤ አብዛኛው ህዝብ ክፉ ላለማድረግ ከወሰነ ከተባበረ በሀገሪቷ ያለውን ክፋት ይጠፋ ነበር። እራሴን እንደዚህ ማታለል አልችልም፤ ከሀገሬ ሆኜ ለሀገሬ በርካታ ጠቃሚ ነበር አፈራ ነበር።

አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ክሀገሬ የሸሸሁት ኑሮ አሸንፌ ቤተሰቤን ለመርዳት ነው ብዬ እራሴን ማጽናናት እሞክራለሁ። ከቅዠቴ ስነቃ ግን ለዚህም አጉል ምክንያት መልስ አለኝ። ሀገር የሚያድገው ገንዘብ ሲያገኝ ነው ወይም ህዝቡ በእውቀትና ችሎታ ሲበለጽግ ነው? ጃፓን ምንም ተፈጥሮ ሃብት ሳይኖራት ህዝቧን በእውቀትና ችሎታ እንዲበለጽግ አድርጋ ነው ያደገችው። ሳውዲ ደግሞ በተፈጥሮ ሃብት ምክንያት በገንዘብ ሃብታም ሆና ግን በህዝብ ደሃ ናት። ገንዘብ ለቤተሰቤ መላክ ምን ያህል ሀገሪቷንም እነሱንም ይጠቅማል? እርገጥ አንዳንድ ቤተሰብ ገንዘቡን ለዘላቂ ነገር ለትምህርት ለንግድ ወዘተ ይጠቅምበታል። በርካታው ደግሞ ለለት ኑሮ ይጠቀምበታል። ምንም ቢሆን ገንዘቤ እኔን አይተካም ሊተካም አይችልም ይተካል የሚለው አስተሳሰብም ጎጂ ነው። ማንም በድጎማ አይበለጽግም። ይህ ከሀገር ለመሸሽ ምክንያቴ ሊሆነ አይገባም።

አዎን ለክህደቴ ምንም ስበብ የለም። አምኛለሁ። ንስሀ ገባለሁም። እግዚአብሔር ሀገር ቤት እንድመለስና ከወገኖቼ አብሬ ደስታቸውንም ችግራቸውንም እንድካፈል ብርታቱ ይስጠኝ። እራሴንም ማታለል እንዳቆም ይርዳኝ። አሜን።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!