Monday 4 June 2018

የዘመናዊነት ዕቅድ (The Modern Project)

ይህ ከቀሲስ/መምህር ስቲፈን (እስቲፋኖስ) ፍሪማን ጽሁፍ (https://blogs.ancientfaith.com/glory2godforallthings/2014/01/10/the-modern-project/) በሰፊው የተረጎምኩት ነው። ቀሲስ ስቲፈን አሜሪካዊ (ምስራቃዊ ወይም ቃልቄዶናዊ) ኦርቶዶክስ ቄስ ናቸው። ከፕሮቴስታንትነት ወደ ኦርቶዶክስ እምነት «ከተመለሱት» በርካታ አሜሪካዊ ካህናት መካከል ናቸው። አሜሪካዊ በመሆናቸው ብቻ ሳይሆን በቀለም ትምሕርት እና በሃይማኖት ታሪካቸው ምክንያት ስለ በዘመናችን የነገሰው ዘመናዊነት ፍልስፍና በደምብ ያውቃሉ ለክርስትና ዋና ጠላት መሆኑንም ይገነዘባሉ። ሆኖም የዘመናዊነት ፍልስፍና የነገሰ ስለሆነ ሳናውቀው ሁላችንም በተወሰነ ደገጃ እንደተቀበልነው ያውቃሉ። ሰለዚህም ነው ቀሲስ ስቲፈን በዚህ ጉዳይ ዙርያ ብዙ የሚጽፉት። ጽሁፋቸው ለሁላችንም ገላጭ እና አስተማሪ ነው ብዬ አምናለው። ብሎጋቸውን ብታነቡ እጅግ ጠቃሚ ይሆናችኋል ብዬ አምናለው።

ሁለተኛ ዲግሪዬን በ«ቴኦሎጂ» በምማርበት ወቅት (1970 ዎቹ) «የዘመናዊነት ዕቅድ» ('the project of modernity') የውይይት ርዕስ የነበረበት ጊዜ ነበር። ይህ የዘመናዊነት ዕቅድ «ዘመናዊውን» ዓለም ('the modern world') ለመገንባት የሚሰሩትን ማህበራዊ፤ ፍልስፍናዊ፤ ፖለቲካዊ እና ሃይማኖታዊ ስራዎችን ያካትታል። በ17ኛ ክፍለ ዘመን የመነጨው «የብርሃን መብራት» ('the Enlightenment') ፍልስፍና አዲስ የአስተሳሰብ አይነቶች ወደ ምዕራባዊው ዓለም (ከዛ ቀጥሎ ወደ መላው ዓለም) አመጣ። ለምሳሌ ለ«ሀገር» የምንለው ፅንሰ ሃሳብ አዲስ ትርጉም እና አወቃቀር ፈጠረ። የክርስትና ሃይማኖትን በአዲስ መልክ ፈጠረ (ለምሳሌ ፕሮቴስታንትነት)። ከሁሉም በላይ ግን የሰው ልጅ ማንነትን ሌላ ትርጉም ሰጠው።

እኛ የዚህ ዘመን ሰዎች የዚህ ፍልስፍና ወራሾች ነን። የዘመናዊነት እና የዘመናዊነት ዕቅድ ልጆች ነን። ዛሬ ማንም ትምህርት የሌለውም ሰው «የዘመናዊነት ዕቅድ» ያመጣውን አስተሳሰቦችን ሳያውቀውም ቢሆን አድሮበታል አምኖበታልም። በትምህርት ቤትም በሚዲያም በሌሎች መንገዶች አስተሳሰቡን ወርሰነዋል። እኛ «የዘመናዊነት ዕቅዱ» ውጤቶቹ ሆነናል።

ዘመናዊነት ዕቅዱ የሰው ልጅን ማንነት ሲደነግግ እንደዚህ ይላል፤ « የሰው ልጅ በራሱ ብቻ የሚተዳደር ነፍስ ነው፤ ውሳኔዎቹ እና ስራው ብቻ ነው ማንነቱን የሚወስን»። ይህ ማለት፤

1. በራሱ ብቻ የሚተዳደር ነፍስ፤ የሰው ልጅ የማንነቱ መሰረት በማወቅ እና ማሰብ ችሎታው የተወሰነ ነው። «የማሰብ እና ማወቅ ችሎታዬ ብቻ ነው የሰው ልጅ የሚአደርገኝ»። ከዚህ ቀጥሎ በፈቃዴ ከሌሎች ጋር መጋራት እችላለሁ ግን ማንነቴ በራሴ ብቻ ነው የሚወስነው። ከሌሎች ጋር ያለኝን ግንኙነትም እኔ ብቻ ነው የምወስነው። ይህ ነው በዘመናዊው ዓለም የምናየው የ«ግለኝነት» አኗኗር መሰረታዊ ሃሳብ።

2. ውሳኔዎቻችን እና ስራዎቻችን ማንነታችንን እና የህይወት ጉዞዋችንን ይወስናሉ፤ በዚህ ዓለም ያለኝ የማንነት ምደባ የራሴ አመራረጥ፤ ውሳኔዎች እና ያሳለፍኩት ልምዶች ናቸው የሚወስኑት። ውሳኔዎቼ ማንነቴን ይወስናሉ እና መሆን የምፈልገውን መሆን እንድችል ብቸኛ ሚና ይጫወታሉ። የኔ ምርጫ እና ውሳኔዎች ናቸው የህይወቴን ትርጉም እና ማን መሆን እንደምፈልግ የሚወስኑት።

እነዚህን ፅንሰ ሃሳቦች ካሰላሰልናቸው የዘመናችን ታሪክን ወሳኝ ነገር «ነፃነት» ለምን እንደሆነ በቀላሉ እንረዳለን። (ይህ «ነፃነት» የሚባለው የመወሰን እና የመምረጥ «መብት» ነው እንጂ እውነተኛው ነፃነት አይደለም።) የሰው ልጅ ማንነት ትርጉም ከላይ የተጻፈው ከሆነ ይህ «ነፃነት» የግድ ይሆናል። ይህን ነፃነት የሚገድብ ሁሉ የሰው ልጅ ህልውና እና ፍላጎት ጠላት ይሆናል። እንደ ፈለግኩኝ መምረጥ መወሰን ስችል ነው ፍላጎቴን ማምዋላት የምችል ሰው መሆን የምችለው።

ከላይ እንደጠቀስኩት ባሁኑ ዘመን እነዚህ አይነት አስተሳሰቦች ሳናውቀው ሰርቀው አዕምሮአችን ውስጥ ገብተዋል። ዓለም ዙርያ ታውቀዋል። እንደ «ነፃነት» እና «ምርጫ» አይነቶቹ ቃላቶት ምን ማለት እንደሆኑ ብዙሃኑ ተውሕዶታል። እነዚህን ቃላቶችን ስንጠቀም ሁሉም ሰው ትርጉማቸውን «ያውቃል»።

አንዳንድ የክርስቲያን ቡድኖች በተለይም የፕሮቴስታንት ንቅናቄ ይህን አስተሳሰብ አቀናብረው አንጸራጭተውታል። እነዚህ የክርስቲያን ቡድኖች ከአሜሪካ እና አውሮፓ ተነስተው የ«ዘመናዊ» ክርስትና ዓለም ዙርያ አስፋፍተዋል። በጥናታዊ ክርስትና ያልነበሩ አስተያየቶች እና ጥያቂዎችን አስፋፍተው የተለመዱ እንዲሆኑ አደረጉ። ለምሳሌ የህፃንነት ጥምቀት ጥያቄ፤ ዛሬ ሰው ለምን በህፃንነቱ ክርስትና ይነሳል የሚለው ጥያቄ ይጠየቃል። ልበ በሉ ለመጀመርያዎቹ ፕሮቴስታንቶች ይህ ጥያቄ አልነበረም ግን የተከሉት ዘር ወደዚህ አመራ። ጥያቄ የሆነው ምክነያት የህጻንነት ጥምቀት «ነፃነትን» ይሽራል ተብሎ ነው! «ህፃኑ እንዴት አለ «ምርጫው» ይጠመቃል። ለመጠመቅ ላለመጠመቅ ነፃነቱ ሊኖረው አይገባምን?» ይባላል! በዘመናዊነቱ ዕቅድ ምርጫን ወይም የራስ ውሳኔን የሚገድብ ነገር አደገኛ ነው ተብሎ ይሰየማል። በየ «ኤቫንጀሊካል» ፖሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን ክርስቲያን መሆን የ«ነፃ ምርጫ» ጉዳይ ነው ይባላል። «የውሳኔው ስዓት» ሰዎች ክርስቶርስን ጠቀብያለሁ የሚሉበት ጊዜ በዘመናችን ተለምዷል።

ቤተ ክርስቲያን ስለ ገብረ ግብ የምታስተምረውም በዘመናዊነት ዕቅዱ ምክንያት በጥርጣሬ ላይ ወድቋል። ዘመናዊ ሰዎች እራሳቸውን «ካቶሊክ»፤ «ኦርቶዶክስ»፤ «ጴንጤቆስጣል»፤ «ፕሬስቢቴሪያን» ወዘተ ብሎ ቢሰይምም ቤተ ክርስቲያናቸው ስለ ግብረ ገብ ወይም ስነ መግባር ኑሮዋቸው መወሰን የለባትም ብለው ያምናሉ። እራሳቸውን «ካቶሊክ» ብለው ቢሰይሙም በካቶሊክ እምነት አይገዙም። ለምሳሌ አብዛኞች አሜሪካዊ ካቶሊኮች ቤተ ክርስቲያናቸው በተለይ ስለ ቤተሰብ እና ጋብቻ የምታስተምረውን ሌሎችም ትምህርቶቿንም ይክዳሉ! ከቤተ ክርስቲያናቸው እምነቶች የሚፈልጉትን ይመርጣሉ የግል ምርጫዬ ነው የነፃነት ጉዳይ ነው ብለው ያምናሉ። ግን ይህ «የግል ሃይማኖታቸውን» በራሳቸው «ነፃነት» እና ምርጫ «ካቶሊክ» ብለው ይሰይማሉ። በዚህ አስተሳሰብ «ካቶሊክ»፤ «ኦርቶዶክስ»፤ «ሉቴራን» ወዘተ ሰው የሚመርጠው ማንነት ነው እንጂ ማንነትን እና ህይወትን የሚወስን ጉባኤ አይደለም።

የዘመናዊነት ዕቅዱ የጥንታዊ ክርስትና ጠላት ነው።

በጥንታዊ አመለካከት የሰው ልጅ ለራሱ ብቸኛ ወሳኝ አይደለም። በዚህ ዓለም የምንገኘው ከራሳችን ሌላ በሆነው በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው። ህይወታችን የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። የህይወታችን አላማው፤ ትርጉሙ እና አቅጣጫው በእግዚአብሔር የተሰጠ ነው። የሰው ልጅ የሚያደርገን እና ዋጋ የሚሰጠን በእግዚአብሔር ምሳሌ መፈጠራችን ነው እንጂ ውሳኔዎቻችን ወይም የመወሰን አቅም ስላለን አይደለም። የሁላችንም ታናሾች አቅም የሌላቸው፤ ችሎታ የሌላቸው፤ ከአልጋ ተኝተው መንቀሳቀስ የማይችሉት፤ ወዘተ በኢግዚአብሔር ምሳሌ በመፈጠራቸው ክብር እና ዋጋ አላቸው።

ማንነታችን በህይወት ምርጫዎቻችን እና ውሳኔዎቻችን ብቻ አይደለም የሚወሰነው። ህይወታችን እና ማንነታችን ከእግዚአብሔር ያገኘነው ስጦታ ነው። እሰረታዊ ማንነታችን በተወሰነ ደረጃ የተመደበ ነው። ይህ ማንነት በክርስትና ህይወት የሚገለጽ እና የሚለወት ነው እንጂ አንድ ሰው በግሉ የሚፈጥረው አይደለም። ምርጫዎቻችን እና ውሳኔዎቻችን ሚና ይጫወታሉ ግን ከእግዚአብሔር ውሳኔ ስር ነው ሚናቸው። ዞሮ ዞሮ የእግዚአብሔር ፍጥረቶች ነን ስለዚህ ውሳኔዎቻችን ትርጉም ያላቸው ከሱ ጋር ባለን ግንኝነት ነው።

በዘመናዊነት ዕቅዱ እና በጥንታዊው አመለካከት ያለው ጦርነት በደምብ የሚታየው በተለይም በምዕራቡ ዓለም በስነ ህይወት (biology) እና የሰው ግንኝነት ዙርያ። ጥንታዊ የክርስትና አመለካከት ስነ ህይወታችን፤ ማለትም ሰውነትና አካላችን ወዘተ፤ የተሰጠን ነው። እንደ አባት፤ እናት፤ ወንድም፤ እህት ወዘተ ያለን ከሰው ጋር ያለን ግንኙነቶችም የተሰጡን ናቸው። ጾታ ምርጫ አይደለም። ቤተሰብም የደም ተፈጥሮ ነው እንጂ በምርጫ አይደለም። በባለና ሚስት መካከል ወይም ሌሎች ወሰባዊ ግንኙነቶች የተሰጠ አላማ አላቸው እንጂ የግል ፍላጎት ማምዋያ አይደሉም። ግን የዘመናዊነት ዕቅዱ «ነፃነትን» እና «ምርጫን» እንዲሰፍኑ ማድረግ ነው የሚፈልገው። የሰው ተፈጥሮ እውነት ነው ግን ወሳኝ አይደለም ይላል (ለዚህም ነው ዛሬ አንዳንዶች ጾታቸውን የሚመርጡት)። ቤተሰብ የምርጫ ጉዳይ ነው የምንፈልገውን ግንኙነቶችን እንመርጣለን። የደም ትሥሥር የተሰጠ መሆኑ እና በደም ትሥሥር ምክንያት ሃላፊነቶች መኖራቸው በምዕራባዊ ሀገራት መንግስታት እና ፍርድ ቤቶች እየተካደ ነው። ለዚህም ነው በእግዚአብሔር ፈቃድ የተጸነሰው ከ«ነፃነት» ጋር መወዳደር ያልቻለው እና ጽንስን ማስወረድ የሰፈነው።

ዛሬ «እውነት» የሚባለው ነገር አሻሚ ሆኗል። የኔ እውነት ካንተ እውነት ይለያል ግን ሁለቱም እውነቶች ናቸው ይባላል። እውነትም የምርጫ ጉዳይ ሆኗል። አንድ የሆነ እውነት የለም ይባላል። በዚህ ዘመናዊ ዓለም እውነት አንድ ነው ማለት እንደ ጭቆና ነው የሚቆጠረው። የጥንታዊ ክርስትና አስተያየት ከነ ህግ እና እምነቱ የማይመች እና መጥፋት ያለበት ሆኖ ነው የሚታየው። ዘመናዊው ዕቅድ «ለምን እግዚአብሔርንም በራሳችን ምርጫ በራሳችን ምናብ አንፈጥረውም አንወስነውም» ይለናል።

መጨረሻው

ከመጀመርያ ጀምሮ ለ400 ዓመታት በላይ የዘመናዊው ዕቅድ የጥንታዊ ክርስትናን ተዋግቶ ከሰው ልጅ ከህዝብ ማስወገድ ነው አላማው። የዘመናዊነት ጥያቄ «እግዚአብሔር እንዴት ነው የፈጠረን» ሳይሆን «ዓለምን ምን እንዲመስል ነው የምንፈልገው?» ነው። የዓለም ሁኔታ የሰው ምርጫ ጉዳይ ነው ብሎ ነው የሚያምነው። ስለዚህ ነው የዘመናዊ ዕቅዱ ልጅ የሆነው የፕሮቴስታንት ስነ መለኮት (ቴኦሎጂ) የክርስትናን ትውፊት እና ወግን ከመመርመር እና ማጥናት ይልቅ ወንጌልን በራሱ ምናብ መተርጎም የፈለገው።

ማርቲን ሉተር «በመጻሐፍት ብቻ» ('Sola Scriptura') የሚባለው የፕሮቴስታንት አቋምን ሲፈጥር ማንም ሰው መጸሀፍ ቅዱስን አንብቦ አለ እርዳታ አለ ቤተ ክርስቲያን አለ ሃዋርያት በትክክሉ ይተረጉመዋል ለማለት ነው። ማርቲን ሉተር የሮሜ ጳጳስን ወይም የሮሜ ቤተ ክርስቲያን ችግሮችን በመቃወም ስበብ ክርስትናን በራሱ ውሳኔ እና ምርጫ መቅረስ ፈለገ። በዝህ መልክ ይህ «በመጸሐፍት ብቻ» የሚባለው አስተያየት በመጀመርያ ቤተ ክርስቲያንን እና ትውፊቷን ለመለየት የተጠቀሙበት መሳርያ ነበር። ግን ባልታሰበበት (ግን ሊታሰብበት) መልክ ይህ አስተሳሰብ ሰዎች መጸሀፍ ቅዱስን በግላቸው እንተርጉም እያሉ ከአንድ ከሉተር ከሁለት የሉተር ተፎካካሪ ዝዊንግሊ ወደ 30 ሺ አተረጓገም (ዛሬ ዓለም ዙርያ ያሉት የፕሮቴስታንት ቡድኖች ቁጥር) ደርሷል።

ግን «የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም» እና ዛሬም የጥንታዊ ክርስትና አለች የዘመናዊነቱን ዕቅድን የስጋው መውግያ ናት። የዘመኑ ሚዲያ ቫቲካንን አትኩረው ያያሉ ገና ለገና መሰረቷን ሸርሽራ ትጨርሳለች እጇን ሙሉ በሙሉ ለዘመናዊነቱን ዕቅድ ትሰጣለች ብለው። በሩስያ ከሞት የተነሳችው ኦርቶዶክስ እምነት ደግሞ ከፖለቲካዊ «አምባገነን» ጋር የተያያዘ እና «ኋላ ቀር» ብለው ይሰይሙታል! ጦርነት ነው!

ዛሬ የጥንታዊ ክርስትና መንገድ ከባድ ነው። አታላዩ መንገድ ዝም ብሎ ጸረ የዘመናዊው አብዮት መሆን ነው። ከዘመናዊነት ዕቅዱ እኩል እንደ አማራጭ መወዳደር። ግን ክርስትና እንዳዚህ ካረገች እጇን ለዘመናዊው ዕቅድ ሰጠች ማለት ነው። ሌላ «ምርጫ» ሆነች ማለት ነው። ግን ጥንታዊ ክርስትና የምርቻዎቻን ውጤቶች አይደለንም ህይወቶቻችን በእግዚአብሔር ጸጋ እና ስጦታ ነው የሚወሰነው ሁሉም ነገር ከእግዚአብሔር አኳያ ነው የምንመለከተው ነው። የቤተ ክርስቲያን ተውፊት የለ የተሰጠ ነገር ነው እንጂ ምርጫ አይደለም። ስለዚህ እራሱን እንደ አንድ አማራጭ አያቀርብም ሊያቀርብም አይችልም።

የጥንትዊ ክርስትና መንፈስ ስለ በራስ መምርጥ ሳይሆን እራስን ባዶ ማድረግ። ማለት የራስን ፍላጎት ትቶ የእግዚአብሔርን ፍላጎት ማወቅ እና ማክበር። እጅን ለእግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ መስጠት። ጥንታዊ ክርስትና ህይወት የተሰጠ እንደሆነ ይረዳል። የተፈጥሮ የደም ትሥሥር፤ ቤተ ሰብ እና ዝምድና ተጭባጭ ናቸው እና ህይወታችን ላይ ተገቢ ሚና ይጫወታሉ ሃላፊነት ይሰጡናል። ዓለም እንደዚህ ትሁን እንደዛ ትሁን ብለን ማለም ከለት ለለት ከባድ የሆነ የክርስትና ኑሮአችን እንድንርቅ እንድንሰንፍ ፈተና ነው። የዓለም ድሃ ይረዳ እያልኩኝ እየተፈላሰፍኩኝ ድሃ ባለንጀራዬን ዞር ብዬ አላየውም! ግን የዘመናዊነት ዕቅድ እንደዚህ ነው የሚያስበው። ዓለምን አሻሽላለው ይላል። ከ«ነፃነት» በደምብ ማትረፍ የሚችሉትን ባለ ሃብቶች እና በትምሐርት ጎበዞች በደምብ አትርፈዋል። ግን ይህ የዘመናዊነት ዕቅድ ፉከራ ባዶ ነው ህይወታችንን በራሳችን መወሰን ስለማንችል። እራሳችንን ከእውነታችን በላይ ታላቅ አርገን ብናስብም መጨረሻ ላይ ሞት ምርጫችንን አያከብርም! ምናልባትም የዛሬው ታላቅ አሽሙር የዘመናዊነት ዕቅዱ የ«መሞት መብት»ን ማራመዱ ነው አለመሞት ምርጫ እንደሆነ!

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!