Friday 22 June 2018

ኤርትራ

የ1991 ኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ስለ ባድሜ ወይንም ድንበር አልነበረም። ጉዳዩ የስልጣን የበላይነት ነበር ተፎካካሪዎቹ ሻዕብያ እና ህወሓት ነበሩ።

ደርግ ከስልጣን ሲወርድ ጀምሮ ለሰባት ዓመት ህወሓት እና ሻዕብያ ከሞላ ጎደል አብረው ኢትዮጵያን ገዝተዋታል። አዎን የኢትዮጵያ መንግስት በህወሓት ነበር የሚመራው ግን በህውሓት ፈቃድ እና ድጋፍ ሻዕብያ እንደ «ሁለተኛ መንግስት» ይንቀሳቀስ ነበር። የኤርትራ መንግስት አካላት ከነ ደህንነት ክፍሉ ኢትዮጵያ ውስጥ በይፋም በስውርም ይሰራ ነበር ስልጣንም ነበረው። የኤርትራ መንግስት እና ባለ ሃብቶች በኢትዮጵያ መንግስት ፖሊሲዎች ታላቅ ሚና ይጫወቱ ነበር። ኤርትራ ከብሄራዊ ባንክ ገንዘብ ታገኛ ነበር። ኤርትራዊ ባለ ሃብቶች በምስና የባንክ ብድር፤ የምንግስት ኮንትራት፤ የቀረጥ ነጻ መብት ወዘተ ያገኙ ነበር። ኤርትራዊያን ቡና አለቀረጥ ከኢትዮጵያ ገዝተው ወደ ውጭ ሀገር ይሸጡ ነበር። ወዘተ፤ ምሳሌዎቹ ማስረጃዎቹ በርካታ ናቸው ተመዝግበዋል በአዲሱ የመንግስት ግልጽነት አካሄድ ደግሞ ይበልጥ ወደ ይፋ ይወጣሉ። ድምዳሜው ግን ከ1983 እስከ 1991 የኤርትራ መንግስት እና ኤርትራዊያን ባለ ሃብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ አግባብ ያልሆነ ተጽኖ እና ስልጣን ነበራቸው።

ግን ይህ ሁኔታ ሊቀጥል አይችልም ነበር። ምክንያቱም የሀገር ገዥ የነበረው ህወሓት ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ይፈልግ ነበር። የሀገር መንግስት ሆኖ ልምንድነው ሌላው ሁለተኛ ምነግስት የሚያስተናግደው? ህወሓት የኢትዮጵያን ስልጣንን እና ከኢትዮጵያ የሚገኘውን ጥቅም ለራሱ ይፈልግ ነበር። ኢህአዴግ ውስጥ ያሉት አጋር ፓርቲዎችም እንዲሁም ኢትዮጵያ ከኤርትራ ተጽኖ ነጻ መሆን አለበት እራሳችን ሙሉ በሙሉ መግዛት አለብን የሚል አቋም ነበራቸው። በዛው መጠን ሻዕብያ በኢትዮጵያ ያለውን ጥቅም እና ስልጣን መልቀቅ አልፈለገም። በዚህ ጉዳይ መደራደር አልተፈለገም ተፎካካሪዎቹ በጡንቻ መጋጠም ወሰኑ። በአጭሩ ይህ ነበር የህወሓት እና የሻዕብያ ግጭት እና የጦርነቱ ምንጭ።

ከጦርነቱ በኋላ በህወሓት እና ኢህአዴግ ክፍፍል ምክንያት ወደ «ጦርነትም ሰላምም የለም» ("no war no peace") ዘመን ገባን። ለምን እስከ መጨረሻ ሄደን አሰብን አልወሰድንም ሻዕብያን አላፈርሰንም የሚሉ ነበሩ። ስለዚህ የህወሓት የፖለቲካ ስምምነት ያንን ባናደርግም ኤርትራን በማግለል ሻዕብያን እንጎዳለን ሆነ። ሻዕብያ በኢትዮጵያ አሳቦ የሀገራቸውን ኤኮኖሚ እና የህዝብ ሞራል ይገላል እና ቀስ ብሎ ይወድቃል ነበር በኢትዮጵያ መንግስት የነበረው አስተሳሰብ። ከዛ በኋላ ከኢትዮጵያ ጋር በተሻለ መልኩ ለመደራደር ዝግጁ የሆነ መንግስት ኤርትራ ውስጥ ስልጣን ይይዝ እና ከነሱ ጋር እንደራደራለን ነበር የኢህአዴግ አቋም።

ስለዚህ ባጭሩ የ«ጦርነትም ሰላምም የለም» ፖሊሲ ሁለት አላማ ነበረው፤ 1) ሻዕብያን ከስልጣን ማውረድ ለኢትዮጵያ ወይንም ለህወሓት የሚመች መንግስት እንዲመጣ እና 2) ኤርትራ እንደ ሀገር ኃይሏ ከኢትዮያ አንጻር እንዲመነምን እና በዚህ ምክንያት ለኢትዮጵያ አመቺ የሆነ የድርድር ሁኔታ እንዲፈጠር።

ዛሬ አንደኛው ግብ አልተመታም ግን ሁለተኛው ተመቷል ወይንም ከዚህ በላይ ሊመታ አይችልም። ማለተም ካሁን ወድያ ኤርትራን ለማድከም ተብሎ ይህ ፖሊሲ ቢቀጥል ጉዳቱ ከጥቅሙ ይበልጣል። ሻዕብያ እና ኤርትራ የሚማሩት ትምሕርትሮች ከነበሩ ተምረውታል። የኤኮኖሚ ችግር በቂ አይተውታል። ሻዕብያ መሪው ኢሳያስ አፈወርቂ ከህውየት እስኪለዩ መግዛት መቀጠሉ ግልጽ ሆኗል። ከዛ በኋላ ደግሞ ትርምስ የሚመጣ ይመስላል የሻዕብያን የመገንጠል ጦርነትን የማያስታውስ ጭቆና ብቻ የሚያስታውስ አዲስ ትውልድ ወደ ፊት እየመጣ ሲሄድ። ስለዚህ ነው የአብይ አህመድ መንግስት ይበቃል ወደ ሰላም እና ድርድር እንግባ ያለው። ትርምስ ሳይመጣ ጠላት ሀገሮች እጃቸውን አለ ቁጥጥር ኤርትራ ውስጥ መክተት ከሚጀምሩ በፊት ካሁኑኑ የቀረውን የወንድማማቾች ስሜትን ተጠቅመን እንደራደር ነው።

ይህ ጥሩ አካሄድ ይመስለኛል። እንዳልኩት የ «ጦርነትም ሰላምም የለም» ፖሊሲ በቂ ሰርቷል ምቀጠሉ ለኢትዮጵያ አይጠቅማትም። ከዚህ አልፎ ተርፎ የኤርትራ ችግር ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ የቅርብ የፖለቲካ ለውጦች የሁለቱን ሀገራት የኃይል ሚዛን እጅግ ወደ ኢትዮጵያ አመዝኖታል። በህወሓት ዘመን የኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠላው ከፋፋይ መንግስት ስለነበር ሀገሪቷን የተከፋፈለች ከሚገባት ደካማ ኃይል እንዲኖራት አድርጓል። በዛን ጊዜ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ድርድር ብትገጥም ውጤቱ ደካማ ነበር የሚሆነው። አሁን ግን ህዝቡ በሙሉ አንድ ስለሆነ እነ አብይ አህመንድ ወደ ድርድር ሲገቡ ያንን ሁሉ ኃይል ይዘው ስለሚገቡ ታላቅ ድል ማድረስ ይችላሉ። እንደ ድሮ የሻዕብያን ብልጠት መፍራት የለም። እንደ ድሮ ኤርትራ እና ኢትዮጵያ እንደ እኩለኛማቾች አደሉም። ኢትዮጵያ ታላቅ፤ ግዙፍ እና ባለ ኃይል ናት ኤርትራ እንደሚገባት የኢትዮጵያ አንድ አስረኛ ናት። ይህ ለድርድር ጥሩ ሜዳ ነው። በእውነታ የተመሰረተ ትክክል እና ዘላቂ ስምምነት እንዲኖር የሚያደርግ ሜዳ ነው።

ባጭሩ የጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ የ«ጦርነትም ሰላምም የለም» የሚለውን ፖሊሲ ያቆመው ምክንያት ጥቅሙ ስላለቀ እና ለኢትዮጵያ አሁኑኑ ከኤርትራ ጋር ድርድር መግባት አዋጪ ስለሆነ ነው። እዚህ ላይ ማለት የምፈልገው አንድ ነገር አለ። ለኔ ኤርትራ እና ኢትዮጵያ አንድ ናቸው። የኤርትራ ህዝብ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም ለማለት ሙሉ መብት አሉ በዚህ መብት አምናለሁ። ግን ለኔ ኤርትራኖች ሀገሬዎች ወንድሞቼ ናቸው። ከዛም አልፎ ከኢትዮጵያ የተገነጠሉት በኔ በኛ ጥፋት እንጂ በነሱ ክፋት አይደለም ብዬ ነው የማምነው። ስለዚህ ለኔ ይህ ድርድር ስለኤኮኖሚ ብቻ ሳይሆን ስለ ህዝባዊ ግንኙነተና ትሥስር ነው። የመለያየታችን ቁስሎች፤ ትዕቢቶች፤ ውሸቶች፤ ወዘተ የማስወገድ መጀመርያ ነው። እነ አብይ አህመድ ይህንን ለማድረግ እግዚአብሔር ይርዳቸው ይድራን!

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!