Friday, 23 September 2016

የአማራ የፖለቲካ ንቅናቄ ለኢትዮጵያ ህልውና እጅግ አስፈላጊ ነው

2009/1/12 .. (2016/9/22)

ከተለያዩ ጽሁፎች እንደጠቀስኩት ለላእፉት 25 ዓመታት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ኢሚዛናዊ ሆኗል። በ1983 ኢህአዴግ ስልጣን ሲይዝ የኢትዮጵያ ብሄርተኛ (Ethiopian nationalist) የፖለቲካ መሪዎች ለ40 ዓመታት እርስበርስ በመፋጀት እራሳቸውን ጦራቸውንም አጥፍተው ነበር። ስለዚህ የሀገሪቷ ህገ መንግስት የተቋቋመው ሀገሪቷም የተስተዳደረችው በጎሳ ብሄርተኛ (ethnic nationalist) የሆኑ ፖለቲከኞች ነው። የፖለቲካ ኃይል በጠቅላላ በጎሳ ብሄርተኝነት እጅ ነው።

በዚህ ምክንያት በርካታ የሆነው የሀገር ብሄርተኛ ህብረተሰብ በፖለቲካ ዙርያ አልተወከለም። ለዚህ ነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ኢሚዛናዊ ነው ማለት የሚቻለው፤ የጎሳ ብሄርተኞች ከመጠን በላይ ውክልናና ድምጽ አላቸው ርዓዮት ዓለማቸውንም ያራምዳሉ፤ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ግን አልተወከሉምም ድምጻቸውም የሚገባው ያህል አይሰማም። ይህ ሁኔታ ነው ዛሬ በኢትዮጵያ የሚታየውን ከፍተኛ ጎሰኝነትና ዘረኝነት ያመጣው።

ጎሰኝነቱ ለሀገሪቷ ህልውና እጅግ አደገኛ መሆኑ ዛሬ ግልጽ ሆኗል። ለዚህ ያለን አንዱ ከባድ መረጃ የጎሳ ብሄርተኛው ፓርቲ ኢህአዴግን ምን ያህል በሁኔታው መስጋቱ ነው። ከኢህአዴግ አመራር መካከል ጎሰኝነት በሀገሪቷ ፖለቲካ በዝቶ ለስልጣናችንም አስጊ ስለሆነ ፓርቲያችንን ወደ አንድ የሆነ በጎሳ ያልተከፋፈለ ፓርቲ (ብአዴን ህውሃት ኦህዴድ ቅርቶ ማለት ነው) እንቀይር እያሉ ይገኛሉ። ሀገሪቷን ከዚህ አደጋ ለማውጣት የኢትዮጵያ ብሄርተኛ ጎራ የፖለቲካ ድርሻውን በድፍረት (25 ዓመታት እንቅልፍ በኋላ) መውሰድ አለበት።

እሺ ማን ናቸው የኢትዮጵያ ብሄርተኞቹ? ባሁኑ ዘመን ከበየ ክልሉ ቢገኙም በርካታዎቹ ከጎሳዊ ውህደት ያለበት ስፍራዎች እንደ አዲስ አበባና ሌሎች ትላልቅ ከተማዎች ይገኛሉ። በክልል ደረጃ ደግሞ ጠቅላላው የአማራ ክልል የሀገር ብሄርተኛ ነው። ይህንን እውነታ በምርጫ 1997 ቅንጅት ያሸነፈበት ቦታዎች መረዳት እንችላለን። ለማስተዋስ ያህል ኢህአዴግና ህብረት የጎሳ ብሄርተኝነት የሚበዛበት ቦታዎችን አሸነፉ፤ ቅንጅት ደግሞ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት የሚበዛበትን ቦታዎች አሸነፈ።

የሚቀጥለው ጥያቄ እንዴንት ነው ይህ ከሀገር ፖለቲካ የጠፋው የሀገር ብሄርተኛ ጎራ የሚገባውን ፖለቲካዊ ድርሻ መያዝ የሚችለው። በመጀመርያ ከታች ከመላው ህብረተሰብ (grassroots) ጀምሮ የአንድነትና የአንድ አላማ መንፈስ ልያድርበት ይገባል። ይህ ለማንኛውም ስኬት ቀድመ ሁኔታ ነው! ሰውው እንደዚህ «አንድ ልብ» ሲሆን ነው የፖለቲካ እርምጃዎች መውሰድ የሚችለው። በዛሬው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ህብረተሰቡ ማድረግ የሚችለው እንደነዚህ አይነት ነገሮች ነው፤ በተለያዩ መዋቅሮች (የመንግስት መስሪያቤቶች፤ የሰራተኛ መሐበራት፤ የገበያ መሐበራት፤ የተቃራኒ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ ኢህአዴግ፤ ወዘተ) ስርጎ መግባትና መቆጣጠር፤ የእምቢተኝነት እንቅስቃሴዎች፤ ሰላማዊ ሰልፎች፤ ወዘተ።

የኢትዮጵያ ብሄርተኞች እነዚህን እርምጃዎች ማካሄድ ይችላሉ ወይ? እንደ አዲስ አበባና ሌሎች ከተማዎች የተለያዩ አይነት ሰዎች ስለሚኖሩባቸው፤ ከተማ በመሆኑ የመሐበራዊ ኑሮ ውስን ስለሆነ፤ ሰውዉ በደምብ ስለማይተዋወቅ፤ የመንግስት ደህንነት አትኩሮ ስለሚከታተላቸው፤ ወዘተ እንድዚህ አይነት ስራዎች ለማኮናሆን ከባድ ነው።

በአማራ ክልል ግን እነዚህ ችግሮች የሉም ወይም ያንሳሉ። ህዝቡ ባብዛኛው ለትውልድ የሚተዋወቅ ነው፤ አብዛኛውም ከገጠር ነው የሚኖረው። በደህንነት በኩልም መንግስት ብዙ አማራጭ የለውም። ኢህአዴግ በሀገሩ በአማራ ደህንነቶች ልቆጣጠር ካለ ይከዱታል። አንድ ልብ ማለት ይህ ነው፤ የገዛ ወንድሙንና ዘመዱን አያጠቃም። ከማጥቃት ፋንታ ለአዲስ አበባ ላሉት አዛዦቹ እያስመሰለም ቢሆን ከሀገሩ ህብረተሰብ ዘመዱ ጋር ይቆማል። ደህንነት አስፈጻሚዎቹን ከውጭ ክልሎች ላምጣ ከለ ደግሞ መንግስትን የሚያናጋ ጠባሳ የሚያመጣ የጎሳ ጦርነትን ይጋበዛል። ስለዚህ ህዝቡ ከተባበረ ከተማመነም «አንድ ልብ» ከሆነም ከሃዲዎቹም ውስን ከሆኑ የመንግስት ደህንነት ምንም ማድረግ አይችልም። በዚህ ምክንያቶች የአማራ ንቅናቄ ስኬታማ መሆን እድሉ ከፍ ያለ ነው።

የአማራ ንቅናቄ ተሳካ ማለት ደግሞ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች የፖለቲካ ኃይል በሚገባው ጨመረ ማለት ነው። ከሀገሪቷ ሁለቱ ትላልቅ ክልሎች አንዱ ከጎሳ ብሄርተኛው ኢህአዴግ እጅ ወጣ ማለት ነው። ስኬቱም እንደ አዲስ አበባ አይነቱን የኢትዮጵያ ብሄርተኛ የሚበዛበት ቦታዎች እንዲነሱ ይገፋፋል። ቅድም እንደጠቀስኩት ደግሞ ይህ የሀገር ብሄርተኛ ኃይል ሲጨምር የሀገሪቷን እሚዛናዊ የሆነውን የፖለቲካ ሁኔታ ወደ መስተካከል ይመራዋል። የጎሳ ፖለቲካ ያስፋፋውን ለሀገሪቷ አስጊ የሆኑትን ጎሰኝነትና ዘረኝነትንም እንድንቆጣጠርና እንድንቅንስ በሩን ይከፍታል። ባጭሩ ቢዝህ ምክንያት ነው የአማራ የፖለቲካ ንቅናቄ ለኢትዮጵያ ህልውና እጅግ አስፈላጊ የሆነው።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!