Monday 5 September 2016

የጎሳ ብሄርተኝነትን እንዴት እንቀንስ?

2008/13/1 ዓ.ም. (2016/9/5)

በመጀመርያ እኛ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ስለ ጎሳ ብሄርተኝነትና የጎሳ ስሜት ወይም የማንነት (ethnic identity) ስሜት በደምብ መረዳት አለብን። የጎሳ ስሜት የተፈጥሮ ጉዳይ እንዶሆነ ማመን አለብን። የሰው ልጅ ቤተሰቡን እንደሚወድ፤ መንደሩን እንደሚወድ፤ ጎሳውን ይወዳል። አንዳንዱ ጎሳውና ሀገሩ አንድ ስለሆነ ለጎሳውና ለሀገሩ ያለው ሲሜት አንድ ነው። አንዳንዱ ደግሞ ከብዙ ጎሳ ያለበት ሀገር ስለሚኖር ጎሳውና ሀገሩን ለይቶ ለሁለቱ የተለያየ ስሜት ይኖረዋል።

የጎሳ ስሜት ተፈጥሮ እንደመሆኑ ለመረዳት አይናችንን ከኢትዮጵያ ዞር አድርገን ዓለም ዙርያ ያሉትን ሀገሮችን እንመልከት። በታዳጊም በበለጸጉም፤ በምዕራባዊም በሌላውም፤ በአዲሱም በጥንታዊውም ሀገሮች የጎሳ ስሜት ሲንጸባረቅ እናያለን። ታሪካዊ ውይም ወቅታዊ ብሶቶች ቢኖርም ባይኖርም፤ የኤኮኖሚ ጥቅም ጉዳይ ቢኖርም ባይኖርም፤ ወዘተ የጎሳና የማንነት ስሜት አለ። ከዚህ ትንታኔ በዓለም ዙሪያ ያሉትን ምሳሌዎች አልደረድርም። ግን ይህ የጎሳ ጉዳይ ዓለም ዙሪያ መገኘቱ የሰው ልጅና ማኅበራዊ ውነታ እንደሆነ ያሳያል።

ታድያ ተፈጥሮ ከሆነ ምንድንነው የጎሳ ወይም የማንነት ስሜት ችግር።? ችግሩ የሚመጣው አንድ ሰው ጎሳውን ከሀገሩ (ወይም ከመላው የሀገሩ ህዝብ) ይበልጥ ሲወድና ሲያስቀድም ነው። በመጀመሪያ ትግራይ ነኝ ቅጥሎ ኢትዮጵያዊ» አይነቱ አባባል።) ይህ ሰው ከጎሳውን መውደድና በጎሳው መኩራት አልፎ ወደ የጎሳ ብሄርተኝነት (ethnic nationalism) ተሻግሯል ማለት ነው። እንደዚህ አይነቱ አስተሳሰብ ችግር እንደሆነ ለማስረዳት አንድ ምሳሌ ልስጥ፡ «የጎሳዬ ቋንቋ የአካባቢዬ የአስተዳደር፤ ትምህርት፤ ፖሊቲካ፤ ወዘተ ቋንቋ ይሁን» የሚለውን አቋም እንመልከተው። ጎሳው በአካባቢው የህዝብ ቁጥር በጣም አባዛኛ ከሆነ አቋሙ ትክክል ነው ማለት ይቻላል። ጥቂት ሰው ነው አለፍላጎቱ ይህን ቋንቋ መማር የሚኖርበት። ህዝቡ ባብዛኛው ተጠቃሚ ስለሚሆን ሀገርን የሚጎዳ አቋም አይደለም። በአንጻራዊው ደግሞ ይህ ጎሳ ከአካባቢው እጅግ አናሳ ነው እነበል። ይህ ማለት ለጥቂት ሰው ፍላጎት ተብሎ በርካታ ህዝብ በሌላው ቋንቋ በግድ ሊስተዳደር ነው። የዚህ ጎሳ ሕብረተሰብ «ምንም ይሁን ማንም ይጎዳ የኛ የጎሳ ፍላጎት ነው መቅደም ያለበት» የሚል ከሆነ ጎሳውን ከሀገሩ አስቀድመዋል። የጎሳ ብሄርተኝነት ማለት ይሄ ነው።

እንደዚህም ሆኖ የጎሳ ብሄርተኝነትን ስንቃወም መጠንቀቅ አለብን። በመጀመሪያ የጎሳ ብሄርተኛ የሆኑት ፖለቲከኞች የነሱን አቋም የሚቃዎሙትን እንደ ፖለቲካ መሳርያ በቀላሉ መጠቀም ይችላሉ። የጎሳ ብሄተኝነት ብዙ ግዜ ሆድ የባሰው ስልሆነ «የኛን አቋም የሚቃዎሙት የጎሳችን ጠላቶች ናቸው፤ መብቶቻችንንም እንዲከበር የማይፈልጉ ናቸው» ብለው በማናፈስ በቀላሉ የተከታዮቻቸውን ቁትር ይጭምራሉ። በሁልተኛ ደረጃ የጎሳ ብሄርተኛን አቋም መቀየር ከባድ ነው። ከጎሳ ብሄርተኝነት የተቀየሩ ሰዎች ጥቂትና በጣም የሚደነቁ ናቸው። እነሱም የተቀየሩት በክርክርና ብሙግት ሳይሆን ትህትና፤ ንፁህ ልብና ለዘብተኛ አቋም ያላቸው ሰዎች ስላጋጠሟቸውና እንደነዚህ አይነት ሰዎች እንደ ወንድሞቻቸው ማየት የህሊና ግዴታ ስለሆነባቸው ነው።

የጎሳ ብሄርተኝነትና ጎሳን ከሀገር ማስቀደም ምን ችግር አለው የሚሉ አሉ። የጎሳ ብሄርተኝነት ለሀገር ህዝብ ያለውን ጉዳት ባጭሩ ለማስረዳት ስለኢትዮጵያ ትንታኔ የሚሰጡ ምሁር ክሪስቶፈር ካላፓም አንድ ግዜ የጻፉትን ገላች አባባል ልጥቀስ፡ «በአንድ ሀገር የሚያራርቁና የሚያለያዩ ኃይሎች ከሚያገናኙና የሚያዋህዱ ኃይሎች ካየሉ ለሀገር ህልውና አስጊ ይሆናል» (ትርጉሙ የኔ ነው)። እያንዳንዱ ጎሳ በጎሳ ብሄርተኝነት ላይ ካቶከረ ሀገሩ ሀገር መሆኑን ቀርቶ የቅራኔ፤ ሹክሹክታና ጦርነት ስፍራ ይሆናል። ሁሉም ለራሱ ብቻ ስለሚያስብና ስለሚታገል። ለዚህ ነው የጎሳ ብሄርተኝነት ሀገርን እጅግ የሚጎዳው።

የዛረው የኢትዮጵያን ሕገ መንግሥትን የመሰረተውና ላለፉት 25 ዓመታት ሀገሪቱን የመራው ኢህአዴግ ይህ የጎሳ ብሄርተኝነትን ጉዳት አልገባውም። ለነገሩ አባዛኛው የኢህአዴግ አባላት የጎሳ ብሄርተኞች ስለነበሩ አይፈረድባቸውም። (በሌላ ጽሁፍ እንደተቀስኩት የኢትዮጵያ ብሄርትኛ ነኝ የሚለው እርስ በርሱ ተፋጅቶ 1983 .. ሲደርስ የፖለቲካ ሜዳው በጎሳ ብሄርተኞች ብቻ ቁጥጥር ስር ወድቆ ነበር። ጥፋቱም መፍትሄውም ከእኛ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች እንደሆነ አንርሳ ለማለት ነው።) «የጎሳ መብት» ብለው የሰየሙት ሃሳብ በተግባር ላይ ሲውል ሁሉ ጎሳዎች የሀገር ባለቤትነት ስለሚሰማቸው የሀገር ፍቅር ያድርባቸዋል ብለው ሰበኩ። ነገር ግን ሕገ መንግስቱም አስተዳደሩም የመንግስት መፈክሮችም ይጎሳ ብሄርተኝነት እንዲጥነክርና እንዲያከር ነው ያበረታታው! የመንግስት ድርጊቶች በሙሉ የህዝብ መለያየቱ፤ የጎሳ ውድድርና ቅራኔዎች እንዲሰፉ ነው ያደረገው። የዚህ አካሄድ ውጤት እጅግ ጎጂ መሆኑን ከኢህአዴግ ዓመራር ውስጥ ያሉም በርካታ አባላት ተገንዝበውትም መፍትሄ እየፈለጉለት ነው (ለስልጣናቸው አስጊ እንደሆነ ስለተረዱ)። ይህን ግንዛቤያቸውን የሚያሳየው ዓስር ዓመት በፊት የተጀመረው «ልማት» የሚለው መፈክር ነው። ይህ መፈክርና ቀጣይ መርህዎች የተፈጠሩበት አንድ ምክንያት የጎሳ ክፍፍል በአደገኛ ደረጃ እያየለ ስለሆነ ሀገሩን አንድ የሚያረግ ህብረ ጎሳዊ የሆነ መፈክር ያስፈልጋል ተብሎ ነው። ኤኮኖሚው ቢያድግም ልማትም ቢስፋፋም የጎሳ ብሄርተኝነቱ ጭራሽ እየሰፋ መሄዱ ለሁሉም ተመልካች ግልፅ ነውና ለዚህም ነው አንዳንድ ይኢህአዴግ ክፍሎችን ያሳሰባቸው።

የጎሳ ብሄርትኝነት በሀገራችን ምንም በዝቶ ቢሆንም መፍትሄ አለው። ዋናው መፍትሄ የሕዝባዊ «ውህደት» (integration) የሚያራምዱ መርህዎችን ማካሄድ ነው። ኢትዮጵያ እስካሁንም እንድ ሀገር ሆና ያለችው በታሪኳ የውህደት አጋጣሚዎች ነው። ጎሳዎችዋ በተለያየ መንገድ ስለተቀላቀሉ የተቀላቀለው ኃይል ሀገሪቱን አንድ አድረጎ ይዟታል። የሃማኖት፤ የመልክዓ ምድር፤ የግሳ (በፍልሰት)፤ ወዘታ ውህደቶች ናቸው ኢትዮጵያን አንድ ሀገር ያረጓትና እነዚህም ናቸው እስካሁን የጠበቋት።

ማንኛውም የመንግስት መርህ ከፖለቲካ እውነታ ጋር ካልተያያዘ አይሰራምም ጎጂም ይሆናል! ዛሬ እድሜ ለ25 ዓመታት በመንግሥት ደረጃ የጎሳ ብሄርተኝነትን መስፋፋት የኢትዮጵያ ጎሳዎች ከድሮ ይልቅ ተራርቀዋል። ለምሳሌ በኦሮሚያ ክልል የአማርኛ ትምህርት ባብዛኛው ስለማይሰጥ ብዙ ኦሮሞ ወጣቶች አማርኛ ሳይችሉ ትምህርት ቤት ይጨርሱና ከሌላ ክልል መማርም መስራትም ያቅታቸዋል። ይህ በገዛ ሀገራቸው መወሰናቸው ደግሞ ካላቸው ይበልጥ ጎሰኝነት እንዲሰማቸው ያደርጋል። የዚህ መፍትሄ ኦሮምኛን እንደ አማርኛ የኢትዮጵያ የሀገሩ ቋንቋ ማድረግ ነው። ከዚህም አልፎ ተርፎ ሌሎች ክልሎች፤ በተለይ የጎሳ ብሄርተኝነት ጠላት የሆነው የአማራ ክልል፤ በተቻለ ቁጥር በትምህርት ደረጃ ኦሮምኛ እንዲያቀርብና ተማሪዎቹ በደምብ አድርገው እንዲማሩት ማድረግ ነው። ይህ መርህ እርግት ወጪ ይኖረዋል ግን ጥቅሙ መለካት የማይቻል ነው። ኦሮምኛ በመስፋፋቱ የሚመጣው የስነ ልቦና ለውጥና በአማራና ኦሮምያ መካከል የፍልሰት ጭማሬ ሁለት የዚህ መርህ ውጤቶች ይሆናሉ። በዚህ አካሄድ የጎሳ ብሄርተኝነት እጅግ ይቀንሳል።

ከዚህ አያይዤ ማለት የምወደው በጎሳ ብሄርተኝነት የማይታማው ጎሳ አማራ ስለሆነ ይህን ጉዳይ ለመፍታት ከሌላው ጎሳ ይበልጥ ሀላፊነት አለበት። (ላለፉት 25-45 ዓመት ለመተኛቱም መካስ አለበት!) ስለዚህም በሀገር ደረጃ ኦሮምኛ ለማስፋፋት ሁኔታዎች ባይመቹም የአማራ ክልል ብቻውን በትምህርት ቤት ደረጃ የኦሮምኛ ትምህርት እንዲካሄድ እንደ ዋና እቅድ ማድረግ አለበት። ይህ ተግባር ለምላው ሀገሪቱ ታላቅ አስተዋሶ ይኖሮዋል።

ሶስት ሌሎች ውህደትን የሚጨምሩና የጎሳ ብሄርተኝነትን የሚገድቡ መርህዎች ጠቅሼ በሌላ ጽሁፍ አብራራቸዋለሁ። እነዚህ 1) በክልሎች መካከል ፍልሰት፤ 2) እንደ ትላልቅ ከተማዎች፤ አማራ ክልል፤ ወዘተ ውህደትና የሀገር ብሄርተኝነት የሚበዛባቸው ቦታውችን ኤኮኖሚ ማዳበር ሰውው ወደነዚህ ቦታዎች እንዲ ፈልስ፡ 3) የሀገሩን የሰው ቁጥር አከፋፈል (demography) ሚዛን እንዳይዛነፍ መጠንቀቅ። ለምሳሌ የሀገር ብሄርተኝነት የሚበዛባቸው ቦታዎች እንደ አዲስ አበባ በህዝብ አለመውለድ ምክንያት የህዝብ ቁጥሩ ከሌላው ዓንጻር እንዳይቀንስ መጠንቀቅ።

በመጭረሻ ማስረገት የመፈልገው ነጥብ ያለፈው የ25 ዓመት ኢሚዛናዊ የሆነ የኢህአዴግ የጎሳ ብሄርተኝነት አካሄድ በኢትዮጵያ በርካታ ጉዳት ቢያመጣም ማስተካከል ይቻላል። ሙሉ ሀላፊነቱ ግን የኛ የሀገር ብሄርተኞች ነው። 


1 comment :

  1. I hope our elites are of the same mind!

    ReplyDelete

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!