Thursday 15 September 2016

በፈቃዳችን ነው የምንገዛው

2009/1/4 ዓ.ም. (2016/9/14)

ይህን ነጥበ በተደጋጋሚ በተለያየ መንገድ ለማስረገጥ እወዳለሁ። የዛሬው የኢህአዴግ አገዛዝን የኢትዮጵያ ህዝብ አይፈልገውም የምንለው የዚህ አባባላችንን ሙሉ ትርጓሜ ልንረዳ ይገባል። የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ኢህአዴግን የማይፈልግ ከሆነ ኢህአዴግ የአናሳ ሰዎች አገዛዝ ነው ማለት ነው። አናሳ ድጋፍ ያለው መንግስት ያለ የሌላው ፈቃደኝነት ሊገዛ አያችልም። ልድገመው፤ የአናሳ ድጋፍ ያለው መንግስት ያለ ሌላው ፈቃድ ሊገዛ አይችልም! 

ስለዚህ «የኢህአዴግ አገዛዝን የኢትዮጵያ ህዝብ አይፈልገውም» ስንል የምንገዛው በገዛ የራሳችን ፈቃደኝነት በራሳችን ጥፋት በራሳችን ድክመት ነው ማለት ነው። ሌላ ትርጉም የለውም። የችግሩ ምንጭም መፍትዬውም ከኛ ነው። ኢህአዴግ እንደ በሩ ክፍት የሆነ ቤት ያገኘ ሌባ ነው። ወደ ቤታችን ብንመለስ ሰተት ብሎ ይለቃል። ታድያ መችሄ ነው ወደ ቤታችን የምንመለሰው?

«ድጋፉ አናሳ ቢሆንም ፖሊሱ ደህንነቱ የጦር ሰራዊቱም በሙሉ ከነሱ እጅ ናቸው» ይባላል የኢህአዴግን ኃይልና ጥንካሬ ለማስረዳት። ለማስረዳት ብቻ ሳይሆን ለድክመታንንና ለሽንፈታችን ምክነያት ለመፍጠር። ኢህአዴግን ለማሸነፍ እጅግ ከባድ መሆኑን ለመግለጽ። እንዲሁም ኢህአዴግ ስልጣን በመያዙ ሃላፊነታችንን ለመሸሽ። 

ግን ለዚህ መልሱ ቀላል ነው። መሳሪያው በማን እጅ ነው? በጣም አብዛኛው ፖሊስና ጦር ሰራዊት አማራ ኦሮሞና ከትግራይ ያልሆኑ ጎሳዎች ናቸው። ይህ ማንም ያማይክደው ሀቅ ነው። የፖሊስና የጦር ስራዊቱ አመራር ብቻ ነው ባብዛናው ህወሓቶች ወይም ትግሬዎች። መሳሪያ ደግሞ በአመራር እጅ ሳይሆን በተራ ወታደሩ እጅ ነው ያለው። ስለዚህ መሳርያው በአማራና በኦሮሞ እጅ ነው ማለት ይችሃላል!

እሺ ጡንቻውን ደግሞ ትተን በመንግስት መስርያቤት አብዛኛው ማን ነው። በዚህም ረገር ትግራዩ አናሳ ነው። ለመደምደም ያህል የኢትዮጵያ ስምንት በመቶ ሆነው የትግራይ ህብረተሰብ አገሩን በሙሉ ሊያስተዳድሩት አይችሉም። ሊያስተዳድሩም ሊቆጣጠሩም ሊከታተሉም አይችሉም።

ሌሎቻችን ሃላፊነታችንን ድክመታችንን ለማምለት ምክነያት ፈልገን «ትግራይ ብቻ ሳይሆን ከሌሎቹ ጎሳዎች አደርባዮች እየረዷቸው ነው» እንላለን። ታድያ አደርባዮቹና ትግራዩ ሲደመር አብዛኛ ነው? ከሆነ ኢህአዴግ አብዛኛውን የሚወክል ጥሩ መንግስት ነው ማለት ነው! ታድያ ነው?አይደለም። በእውነቱ የአደርባዩም ቁጥር ትንሽ ነው።

ታድያ እንዴት ነው ኢህአዴግ የሚገዛው። በሌሎቻችን ፈቃድና ትብብር ነው። ትብብር ማለት እያንዳንዳችን ለዚህ አገዛዝ ያለንን አስተዋጾ ተመልክትን አምነን ከመቀየር ይልቅ «ወያኔ ሴጣን ነው» እያልን ማልቀስ ነው። ለኢህአዴግ ስልጣን ለመያዝ ያለንን ሃላፊነት ማምለጥ የኛ የተቃዋሚ ችግር ላይ ከባዱንና አስፈላጊውን ስራ መስራት እንፈልጋለን። «ወያኔ ሴጣን ነው» ብለን መዝፈን ነው የሚቀለን።

ከአብዛኛው የፖለቲካ ጎራ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ነን ኢትዮጵያዊ ብሄርትኞች ነን የምንለው ለኢሃዴግ አገዛዝ ትልቅ ሃላፊነት አለብን። ኢህአዴግን በመጀመርያ የወለድነው እኛ ስለሆንን። በኃይለ ስላሴ ዘመን በቂ ለውጥ ባለማድረጋችን፤ የማይሆን «ፈረንጅ አምላኪ» ትውልድ ወልደን የራስ ማጥፋት ዘመቻ ማድረጋችን፤ የደርግን መንግስት ተቆጣትረን ትክክለኛ መስመር ባለማስያዛችን፤ በቀይ ሽብር እንደገና የራስ ማጥፋት ዘመቻ ማካሄዳችን፤ እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው ሻዕብያ ኢህአዴግና ኦነግ በ1983 የኢትዮጵያን ህልውና ብቸኛ ወሳኞች እንዲሆኑ ያደረጉት። ከዛም ለ25 ዓመት እርስ በርስ እየተጣላን ለህብረተሰቡ መጥፎ ምሳሌ እየሆንን አሳለፍን። ሃላፊነቱ ታድያ የኛ አይደለምን?

ሃላፊነት ወስደን ምን እናድርግ። ሁሉም በበኩሉ ማድረግ የሚችለው አለ። ሆኖም ሁሉ ስራችን መፈከር መሆን ያለበት «ክፉ አታድርግ» ነው። ይህ ማለት አብዛኞቻችን በመሃበራዊ ኑሮው ክፉ ነገር ከማድረግ ብንቆጠብ፤ ከጎረቤቶቹ ጋር ተፋቅረን ብንኖር፤ ከስራ ባልደረቦቹ ጋር ብንግባባ፤ ለስራተኞቻችን ደግ ብንሆን፤ የተቸገሩትን በደምብ ብንረዳ፤ ወዘተ ለውጥ ወድያው ይመጣል። ኢህአዴግም ምንም ሊከላከለው አይችልም።

ዛሬ እነዚህ አይነት አዝማሚያ እያየን ነው። በአማራ ክልል ለምሳሌ አመራሩም ፖሊሱም ወታደሩም ክፉ ነገር አላደርግም የራሴን ህዝብ አልገልም አልጎዳምም ስላለ ነው የእምቢተኝነት ንቅናቄው እዚ የደረሰው። የብአዴን አመራር ፖሊስና ወታደር በመቅጣት ብቻ ሳይሆን በተለያየ መንገድ ህዝቤን እረዳለሁ፤ በትክክል አስተዳድራለሁ፤ አልጎዳም፤ ወዘተ ካለ ኢህአዴግ ከሌሎች ክልሎች አስተዳዳሪ ፖሊስና ወታደር ወደ አማራ አምጥቶ ለመቆጣጠር ቅንጣት አቅሙ የለውም። (አለው ካልን አናሳ መሆኑን አጣን ማለት ነው!) ለጊዜው ለማስፈራራት ያህል የብዙ ሰው መግደልና ማሰር አቅም አለው እያደረገውም ነው ግን ከተወሰና ደረጃ ማለፍ አይችልም። 

ኢህአዴግም በፖለቲካ የበሰለ ስልሆነ ይህን በደምብ ይገባዋልና በዚህ ማስፈራራትና ጭቆና ነገሩን ካላበረድኩኝ መቆጣጠር አልችልም ብሎ ያምናል። በተዘዋዋሪ ዛሬም የሚካሄደው ማስፈራራት የአማራ ከሃዲዎች ባይኖሩበት ሊካሄድ አይችልም ነበር። (ከሃዲዎቹንም እኛ ነን የወለድናቸው። ቁጥራቸው በርካታ ከሆኑ በአማራ ክልል በኛ መሃል ችግር አለ ማለት ነው የከሃዲ ፋብሪካ ሆነናል ማለት ነው! ከሃዲዎቹ ላይ ከማተኮር የሚፈጠሩበትን ምክንያት አጣርቶ ማስተካከል ነው ያለብን።)

ለአማራ ህዝብ ምክሬ እንደዚህ ነው። እርስ በርሳችሁ ሰላም፤ አንድነት፤ መታማመንና ፍቅር አዳብሩ። መሃበራዊ ኑሮአችሁ ያማረ ይሁን። የቀበለ አስተዳደርን በጥሩ ሁኔታ አስፈጽሙ። ካህናት የህዝቡን የህሊና ንቃትን አዳብሩ በስብከት ሳይሆን ይበልጥ ምሳሌ በመሆን። ውስጣችሁ ያሉትን ቅራኔ ያለባቸውን ቡድኖች እንደ የተለያዩ አናሳ ጎሳዎች በጥበብና በፍቅር ያዙም የጥፋት አካል እንዳይሆኑ ተንከባከቧቸው! በማህላችሁ ያሉትን የተጎዱ ስራ ያጡ ማደርያ ያጡ ወዘተን ተንከባከቧቸው። ሰላማዊ ሁኑ፤ የሰው ቤት ማቃጠል ንብረትንም ማውደም ይቅር። ይህ የህሊናም የፖለቲካም ጉዳት ብቻ ነው የሚያመጣው። ከፍተኛ አስተዳደር ቦታ ላይ ያላችሁ በትክክል አለ ሙስና አለጥፋት አለክፋት አስተዳድሩ። ፖሊስና ወታደሮች መትፎ ነገር አታድርጉ። ሄዳችሁ እሰሩ የሚል አለአግባባ የሆነ ትዛዝ ብታገኙ እምቢ ከማለት ሰውየውን አጣን ብላችሁ ተመለሱ! ወዘተ።

እንደዚህ አይነት እርምጃዎች ሁሉም ህብረተሰብ ማድረግ ይችላል በቀላሉም መንግስትን ይለውጣል። እግዚአብሔር ከኛ ጋር ይሁን ያጠፋውንም ይቅር ይበለን ለፈተናም ካኑ ወድያ እንዳንገዛ ብርታቱ ይስጠን።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!