Showing posts with label heart. Show all posts
Showing posts with label heart. Show all posts

Friday, 30 September 2016

ጥፋት አለብኝ ብዬ ካላመንኩኝ «ወያኔ» ነኝ!

2009/1/19 ዓ.ም. (2016/9/29)

ከዲያስፖራ እየኖርኩኝ ስጋዊ ምቾቴን አጠናቅቄ ህሊናዬ እየወቀሰኝ ሀገር ቤት ያሉትን ወንድሞች እህቶቼን ታገሉ እላለሁ። ሀግሬን እወዳለሁ እላለውንጂ ያሳደገችኝ ብትሆንም ለሷ ያለኝን ሃላፊነት ከተውኩኝ ቆይቻለሁ። ክጃታለሁ ጥያታለሁም። ሆኖም ግን ሀገሬን መበደሌ አይታየኝም። ስለሌሎችን ኅጢአትና በደል እጮሀለው እንጂ። ከአይኔ ያለውን ግንድ አላየውም የሌላውን ጉድፍ ብቻ ነው የሚታዬኝ።

ምሬቴ ትንሽ በመሆኗ ምክንያት አጥሬን መግፋት መብቴ ነው እላለሁ! ገፈዋለሁ፤ ከጎረቤት ጋርም እጣላለሁ፤ መንገድንም አጠባለሁ። ለሰፈሩ ችግር እያመጣሁኝ ነው። ግን የእለት ወሬዬ ስለ ቀበሌአችን ሹማምንት የምስና ባህሪ ነው። አይኔ ውስጥ ግንድ የለም።

እውነት ነው፤ ሲያስፈልግ ጉቦ ሰጣለሁ። መብቴን ለማስከበር ብቻ ሳይሆን የማይገባኝን ለማግኘትም። ምን ይደረግ፤ የሀገራችን እውነታ ነው ብዬ እራሴን አታልላለው። ግን መሪዎቻችን እንዴት ሞራል ቢስ ናቸው ብዬ አማርራለሁ።

አንዱ የኦርቶኦክስ መሰረታዊ እምነት ሁላችንም ለሁሉም ሰው ኅጢአት በተወሰነ ደረጃ አስተዋጾ እድርገናልና ሃላፊነት አለብን የሚል ነው። ኅጢአቶቻችን የተገናኙም የተወራረሱም ናቸው። ይህንን ለማብራራት ያህል የታወቀው ሩሲያዊ ደራሲ ፊኦዶር ዶስቶኤቭስኪ በ«ካራማዞቭ ወንድማማቾች» የጻፈውን ጥቅስ እንመልከት። ታላቁ የሃይማኖት አባት ዞሲማ ልጆቻቸውን ሲመክሩ እንደዚህ አሉ፤
«አንድ ሰው በዚህ ዓለም ከሚኖሩት በሙሉ የባሰ ኅጢአተኛ እንደሆነ ሲያምን፤ በተጨማሪም ከሁሉም ሕዝብ ፊት ጥፋተኛ እንደሆነ...፤ ለዓለምም ለያንዳንዱ ሰውንም ኅጢአት እና ጥፋት እንዳለበት ስያምን ነው የ(ክርስቲያናዊ) አንድነት ድላችንን ማስመዝገብ የምንችለው..።
«ሁላችሁም ልባችሁን በደምብ አዳምጡና ለራሳችሁ ሳትሰለቹ ንስሐ ግቡ። እስከ ተጸጸታችሁ ድረስ ኅጢአታችሁ የጎላ ቢመስላችሁም አትፍሩት...።
«በጸሎታችሁ እንደዚህ አስታውሷቸው፤ «አምላካችን ሆይ የሚጸልይላቸው የሌሏቸውንም ላንተ መጸለይ የማይፈልጉትንም አድናቸው» ብላችሁ ጸልዩ። እንደዚህም ቀጥሉ «አምላኬ ሆይ እኔ ከሁሉም የባሰ ርኩስ ነኛ፤...»»
በተጨማሪ ባለፈው ጽሁፌ የጠቀስኩት በጾቪዬት እስር ቤት የተሰቃዩት አለክሻንደር ሶልዠኒትሲን ከእስር ቤት ሆነው የጻፉትን እንደገና ልጥቀስ፤

ከእስርቤታችን አልጋ የሆነው የበሰበሰው ገለባ ላይ ጋደም ብዬ ነው ለመጀመርያ ከውስጤ የበጎ መንፈስ የተሰማኝ። ቀስ በቀስ መረዳት የጀመርኩት ይህ ነው፤ ጥሩና ክፉን የሚለየው መስመር በሀገሮች፤ መደቦች፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችም መካከል አይደለም የሚያልፈው፤ ይህ መስመር የሚያልፈው በያንዳንዱ የሰው ልብ መኻል ነው። መስመሩ እድሜአችን በሙሉ ከውስጣችን ወደፊት ወደኋላ ይላል። በክፉ የተሞሉ ልቦችም ቢያንስ ቅንጣት ያህል ጥሩነት ይኖራል፤ ከሁሉም ጥሩ ከሚባለውም ልብ ከአንድ ጥጓ ትንሽ ክፉነት ይኖራል።
«በየቦታው እየዞሩ ያሉ ክፉ ስራ የሚሰሩ ክፉ ሰዎች ቢኖሩና እነሱን ከኛ መለየትና ማጥፋት ብቻ ቢሆን ኖሮ እንዴት ቀላል ነበር? ግን ጥሩና ክፉን የሚለየው መስመር ከያንዳንዱ የሰው ልጅ ልብ መካከል ነው የሚያልፈውና ማን አለ ከራሱ ልብ ቁራጭ ቆርጦ ለማጥፋት ፈቃደኛ ይሆነ?»
ሶልዠኒትሲን በመታሰራቸው፤ በእስር ቤት ለደረሰባቸው በደልና ስቃይ፤ ያሰሯቸውን የዘመኑን መንግስት መሪዎች፤ የፍርድ ቤት ዳኞች፤ የደህንነት አዛዦች፤ ወዘተ ብቸኛ ጥፋተኛ አድርገው ሊቆትሩ ይችሉ ነበር። ማንናችንም ደካሞች በሳቸው ቦታ ብንሆን እንደዛ ነበር የምናስበው።

ግን እየተሰቃዩም ቢሆን ይህን ቀላሉ የውሸት መንገድን ከመከተል እውነትን መረጡ። እውነትን ፈለገው ህሊናቸውን ተጠንቅቀው መርምረው የራሳቸውም ግድፈት እንዳለ ተገነዘቡ። ከነዛ ክፉዎች እንደማይሻሉ አመኑ።

ሶልዠኒትሲን በሁለተኛ ዓለም ጦርነት ጀግና ወትደር ነበሩ። ሀገሬን እንደዚህ አገልግዬ እንዴት በማግስቱ ለማይረባ ምክንያት እታሰራለሁ ነበር በመጀመርያ ያሰቡት። ግን ህሊናቸውን ሲመረምሩ ከጦር ሜዳ የሰሩትንና ሲሰራ አይተው ዝም ያሉትን ግፍ አስታወሱ። ሀገርን በመከላከል አሳበው ህሊናቸውን እንዴት እንደሸጡ አስተዋሉ። አብረዋቸው የታሰሩትንን የመንግስት ሰለቦች ሲመለከቱም ምንም ንጹ የሚመስሉትም በተወሰነ ደረጋ ተመሳሳይ የህሊና ሽያጭ እንዳካሄዱ ተገነዘቡ።

ከዝ ቀጥሎ የበደሏቸውን ሲመለከቱ በፊት የነበራቸው እነሱ ክፉ እኔ ንጹ የሚለው አስተሳሰባቸው ውሸት እንደሆነ ገባቸው። በዳዮቻቸውም እንደራሳቸው በተለላየ አታላይና የማይረባ ምክንያት ህሊናቸውን ሽተዋል። ስንቱ ናቸው በስመ ሀገር ወዳድነት እንደ ሶልዠኒትሲን አይነቱን የሀገር ከሃዲ ብለው ያሳሰሩት። እነዚህ «እውነት አማኞች» ርዕዮት ዓለማቸውን እንደ ሃይማኖት አድረገው የሚያምኑበት ስለሱ ምንም ለማድረግ ወደኋላ አይሉም ነበር። ሶልዠኒትሲን እነሱን ሲያዩ እራሳቸውን አዩ።

የመጨረሻ ግንዛቤአቸው ንስሃ መግባት እንዳለባቸው ነበር። ንስሃ ቢገቡ በራሳቸው ብቻ ሳይሆን በባልደረቦቻቸው በሙሉ የደረሰው እንደማይደርስ ገባቸው። በሶቪዬት ህብረት የሚገኙት ሀገራት በሙሉም ሰላምና እውነታዊ መንግስት ሊያገኙ የሚችሉት በዚህ አይነት መንገድ ብቻ እንደሆነ ተገነዘቡ። ሌሎቻችንም እንደዚህ አድርገን እንድናስብ ጋበዙን።

እሺ፤ የምጨረሻ ጥቅስ ከአባ ዶሮቴዎስ፤
«አንድ ሰው በእግዚአብሔርን ፊት እራሱን በደምብ ቢመረመረ ለሚደርስበት ያለው በደል ባተግባር፤ በሃሳብ፤ በንግግር፤ በፀባይ፤ ወይም በባህሪይ ሃላፊነት እንዳለበትና ከፊል ተጠቅያቂ እንደሆነ ይገለጽለታል።»
እንዲሁም ለኢትዮጵያ ችግሮች ሁሉ፤ የፖለቲካ ችግር ተጨምሮ፤ ሁላችንም ኢትዮጵያኖች አስተዋጾ አድርገናል ሃላፊነትም አለብን ብለን ማመን አለብን። ቀጥሎ ይህን ሃላፊነት ብንወታው ችግሩ ይፈታል ብለን ማመን አለብን። አባ ዶሮቴዎስ እንዳሉት እራሳችንን ተጠንቅቀን በኢግዚአብሔር ፊት እንመርምር። ይህ ወደ ሰላምና እውነት ብጨኛው መንገድ ነው።

Friday, 23 September 2016

የአማራ የፖለቲካ ንቅናቄ ለኢትዮጵያ ህልውና እጅግ አስፈላጊ ነው

2009/1/12 .. (2016/9/22)

ከተለያዩ ጽሁፎች እንደጠቀስኩት ለላእፉት 25 ዓመታት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ኢሚዛናዊ ሆኗል። በ1983 ኢህአዴግ ስልጣን ሲይዝ የኢትዮጵያ ብሄርተኛ (Ethiopian nationalist) የፖለቲካ መሪዎች ለ40 ዓመታት እርስበርስ በመፋጀት እራሳቸውን ጦራቸውንም አጥፍተው ነበር። ስለዚህ የሀገሪቷ ህገ መንግስት የተቋቋመው ሀገሪቷም የተስተዳደረችው በጎሳ ብሄርተኛ (ethnic nationalist) የሆኑ ፖለቲከኞች ነው። የፖለቲካ ኃይል በጠቅላላ በጎሳ ብሄርተኝነት እጅ ነው።

በዚህ ምክንያት በርካታ የሆነው የሀገር ብሄርተኛ ህብረተሰብ በፖለቲካ ዙርያ አልተወከለም። ለዚህ ነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ኢሚዛናዊ ነው ማለት የሚቻለው፤ የጎሳ ብሄርተኞች ከመጠን በላይ ውክልናና ድምጽ አላቸው ርዓዮት ዓለማቸውንም ያራምዳሉ፤ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ግን አልተወከሉምም ድምጻቸውም የሚገባው ያህል አይሰማም። ይህ ሁኔታ ነው ዛሬ በኢትዮጵያ የሚታየውን ከፍተኛ ጎሰኝነትና ዘረኝነት ያመጣው።

ጎሰኝነቱ ለሀገሪቷ ህልውና እጅግ አደገኛ መሆኑ ዛሬ ግልጽ ሆኗል። ለዚህ ያለን አንዱ ከባድ መረጃ የጎሳ ብሄርተኛው ፓርቲ ኢህአዴግን ምን ያህል በሁኔታው መስጋቱ ነው። ከኢህአዴግ አመራር መካከል ጎሰኝነት በሀገሪቷ ፖለቲካ በዝቶ ለስልጣናችንም አስጊ ስለሆነ ፓርቲያችንን ወደ አንድ የሆነ በጎሳ ያልተከፋፈለ ፓርቲ (ብአዴን ህውሃት ኦህዴድ ቅርቶ ማለት ነው) እንቀይር እያሉ ይገኛሉ። ሀገሪቷን ከዚህ አደጋ ለማውጣት የኢትዮጵያ ብሄርተኛ ጎራ የፖለቲካ ድርሻውን በድፍረት (25 ዓመታት እንቅልፍ በኋላ) መውሰድ አለበት።

እሺ ማን ናቸው የኢትዮጵያ ብሄርተኞቹ? ባሁኑ ዘመን ከበየ ክልሉ ቢገኙም በርካታዎቹ ከጎሳዊ ውህደት ያለበት ስፍራዎች እንደ አዲስ አበባና ሌሎች ትላልቅ ከተማዎች ይገኛሉ። በክልል ደረጃ ደግሞ ጠቅላላው የአማራ ክልል የሀገር ብሄርተኛ ነው። ይህንን እውነታ በምርጫ 1997 ቅንጅት ያሸነፈበት ቦታዎች መረዳት እንችላለን። ለማስተዋስ ያህል ኢህአዴግና ህብረት የጎሳ ብሄርተኝነት የሚበዛበት ቦታዎችን አሸነፉ፤ ቅንጅት ደግሞ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት የሚበዛበትን ቦታዎች አሸነፈ።

የሚቀጥለው ጥያቄ እንዴንት ነው ይህ ከሀገር ፖለቲካ የጠፋው የሀገር ብሄርተኛ ጎራ የሚገባውን ፖለቲካዊ ድርሻ መያዝ የሚችለው። በመጀመርያ ከታች ከመላው ህብረተሰብ (grassroots) ጀምሮ የአንድነትና የአንድ አላማ መንፈስ ልያድርበት ይገባል። ይህ ለማንኛውም ስኬት ቀድመ ሁኔታ ነው! ሰውው እንደዚህ «አንድ ልብ» ሲሆን ነው የፖለቲካ እርምጃዎች መውሰድ የሚችለው። በዛሬው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ህብረተሰቡ ማድረግ የሚችለው እንደነዚህ አይነት ነገሮች ነው፤ በተለያዩ መዋቅሮች (የመንግስት መስሪያቤቶች፤ የሰራተኛ መሐበራት፤ የገበያ መሐበራት፤ የተቃራኒ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ ኢህአዴግ፤ ወዘተ) ስርጎ መግባትና መቆጣጠር፤ የእምቢተኝነት እንቅስቃሴዎች፤ ሰላማዊ ሰልፎች፤ ወዘተ።

የኢትዮጵያ ብሄርተኞች እነዚህን እርምጃዎች ማካሄድ ይችላሉ ወይ? እንደ አዲስ አበባና ሌሎች ከተማዎች የተለያዩ አይነት ሰዎች ስለሚኖሩባቸው፤ ከተማ በመሆኑ የመሐበራዊ ኑሮ ውስን ስለሆነ፤ ሰውዉ በደምብ ስለማይተዋወቅ፤ የመንግስት ደህንነት አትኩሮ ስለሚከታተላቸው፤ ወዘተ እንድዚህ አይነት ስራዎች ለማኮናሆን ከባድ ነው።

በአማራ ክልል ግን እነዚህ ችግሮች የሉም ወይም ያንሳሉ። ህዝቡ ባብዛኛው ለትውልድ የሚተዋወቅ ነው፤ አብዛኛውም ከገጠር ነው የሚኖረው። በደህንነት በኩልም መንግስት ብዙ አማራጭ የለውም። ኢህአዴግ በሀገሩ በአማራ ደህንነቶች ልቆጣጠር ካለ ይከዱታል። አንድ ልብ ማለት ይህ ነው፤ የገዛ ወንድሙንና ዘመዱን አያጠቃም። ከማጥቃት ፋንታ ለአዲስ አበባ ላሉት አዛዦቹ እያስመሰለም ቢሆን ከሀገሩ ህብረተሰብ ዘመዱ ጋር ይቆማል። ደህንነት አስፈጻሚዎቹን ከውጭ ክልሎች ላምጣ ከለ ደግሞ መንግስትን የሚያናጋ ጠባሳ የሚያመጣ የጎሳ ጦርነትን ይጋበዛል። ስለዚህ ህዝቡ ከተባበረ ከተማመነም «አንድ ልብ» ከሆነም ከሃዲዎቹም ውስን ከሆኑ የመንግስት ደህንነት ምንም ማድረግ አይችልም። በዚህ ምክንያቶች የአማራ ንቅናቄ ስኬታማ መሆን እድሉ ከፍ ያለ ነው።

የአማራ ንቅናቄ ተሳካ ማለት ደግሞ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች የፖለቲካ ኃይል በሚገባው ጨመረ ማለት ነው። ከሀገሪቷ ሁለቱ ትላልቅ ክልሎች አንዱ ከጎሳ ብሄርተኛው ኢህአዴግ እጅ ወጣ ማለት ነው። ስኬቱም እንደ አዲስ አበባ አይነቱን የኢትዮጵያ ብሄርተኛ የሚበዛበት ቦታዎች እንዲነሱ ይገፋፋል። ቅድም እንደጠቀስኩት ደግሞ ይህ የሀገር ብሄርተኛ ኃይል ሲጨምር የሀገሪቷን እሚዛናዊ የሆነውን የፖለቲካ ሁኔታ ወደ መስተካከል ይመራዋል። የጎሳ ፖለቲካ ያስፋፋውን ለሀገሪቷ አስጊ የሆኑትን ጎሰኝነትና ዘረኝነትንም እንድንቆጣጠርና እንድንቅንስ በሩን ይከፍታል። ባጭሩ ቢዝህ ምክንያት ነው የአማራ የፖለቲካ ንቅናቄ ለኢትዮጵያ ህልውና እጅግ አስፈላጊ የሆነው።

Wednesday, 14 September 2016

ከጎረቤቱ ጋር የተጣላ «ወያኔ» ነው!

2009/1/4 ዓ.ም. (2016/9/14)

የጎረቤታሞቾ ልጆች ይጣላሉ። አንዱ ሌላውን የትምህርት ቤት መጸሐፌን ሰረቀ ብሎ ይከሰዋል። ወሬው ወደ ወላጅ ጆሮ ይደርሳል። የተከሳሹ ቤተሰብ እንዴት ልጃቸው ልጃችንን ሌባ ይላል ብለው ጎረቤቶቻቸውን ይቀየማሉ። በዚህ ተነስቶ የሁለቱ ጎረቤታሞቾ ግንኙነት መበላሸት ይጀምራል። ሐሜትና ክስ መመላለስ ይጀምራሉ። በተዘዋዋሪም በቀጥታም መሰዳደብ ይጀምራሉ። አንዱ ሌላውን እንደ «ጠላት» ይቆጥራል። ጓደኞቻቸውም ይወግናሉ።

አብዮቱ ከነበልባል ወደ እሳት እየተፋፋመ ነው። አንዱ ቤተሰብ የጠላት ጎረቤታቸውን ልጅ ኢህአፓ ነው እያሉ ማስወራት ይጀምራሉ። ልጁ ታስሮ ይወሰዳል ይሰቃያል ይገደላልም። ታሪክ ልጁን የደርግ ሰለባ አድርጎ ይመዘግበዋል። እውነቱ ግን የጎረቤት ሰለባ መሆኑ ነው። ደርግ መሳርያ ብቻ ነበር።

በትምህርት ቤቱ ሰራተኞች መካከል ምንጩ የተረሳ የቆየ ጸብ አለ። ሰራተኞቹ ለሁለት ተከፍለዋል፤ ዋናው አስተዳዳሪው አንድ ወገን ይዟል፤ ምክትል አስተዳዳሪው ሌላውን ወገን ይዟል። ጦርነት አይደለም፤ ትምህርት ቤቱ ይሰራል ልጆቹም ይማራሉ። ግን ውስጥ ለውስጥ ችግር አለ፤ ትምህርት ቤቱ በሐሜትና ሹክሹክታ መንፈስ ተይዟል።

ኢህአዴግ ስልጣን በቅርብ ይዞ ለአብዮታዊ ዴሞክራሲ እንቅፋት ለሆኑትን «ነፍጠኖች» ከመንግስት ስራ እያባረረ ነው። ምክትል አስተዳዳሪው የሱ «ጠላት» ጎራ የሆኑትን በውሸት ትምክህተኞች ነፍጠኞች ብሎ ለመንግስት ይጠቁማቸዋል ከሰራም ይባረራሉ። ኢህአዴግ አባረራቸው ተብሎ ታሪክ የሚዘግበዋል። ግን ይህን ጉዳት ያደረሱባቸው ባልደረቦቻቸው ናቸው። ኢህአዴግ መሳርያ ብቻ ነበር።

ትምህርት አይሆነውም የሚባል ልጅ ከሰፈራችን አለ። ቤተሰቡም ዘመዶቹም ትምህርት ቤቱም ካህኑም አይረዱትምም አይረዱትም። ጭራሽ ይለቅፉታል ይሰድቡታል ይተቹታል። ልጁ እያደገ ሲሄድ ብሶትና ምሬት ያለው ከራሱ ጋር የተጣላ የዝቅተኝነት ስሜት ያለው ጎረምሳ ይሆናል።

ከምርጫ 97 በኋላ ሰላማዊ ሰልፎች እየተካሄዱ እያለ ፌዴራል ፖሊስ እየዞሩ ህዝብን እያሰሩ ነው። ይህንን ብሶት የተሞላው ልጅ ከሰፈርህ የሰልፉን አስተባባሪዎች የሆኑትን ጠቁምልን በቋሚነትም ጠቋሚያችን ሁንልን ብለው ይጠይቁታል። ልጁ ተስማምቶ በርካታ የሰፈር ልጆችን ይጠቁማል። እስረኞቹም ቤተሰቦቻቸውም ይሰቃያላኡ። የታሰሩት የተሰቃዩት ታሪክ ሲመዘገብ እንደ ኢህአዴግ ሰለቦች ይመዘግባቸዋል። ግን ጠቋሚው ባይጠቁማቸው ምንም አይደርስባቸውም ነበር። ልጁ አሁንም የሰፈሩ «ጠቋሚ» ትብሎ ይታወቃል።

ምርጫ 97 ሊደርስ አቅራብያ አቋማቸው ተመሳሳይ የሆኑት የተቃዋሚ ፓርቲዎች አንድ ግንባር ፈጥረው እራሳቸውን «ቅንጅት» ብለው ሰይመው ምርጫውን ይወዳደራሉ። አሸንፉም። መንግስት ግን አላሸነፋችሁም አመጽም ማስነሳት ሞክራችኋል ብሎ ያስራቸዋል። ከዓመት በላይ ታስረው ከእስር ቤት ሲወጡ ባመረረ የእርስ በርስ ጥል ይለከፋሉ። በጸባቸው ምክንያት የነፃነት ንቅናቄውንም እንዲፈርስ ያደርጋሉ። እርስ በርስ ቢጣሉም የነፃነት ትግሉን ብያከሽፉትም «ውያኔ» በድሎናል ብለው ያለቅሳሉ።

አምባገናናዊ መንግስት በካላሉ ካስቀመጥነው «አምባገነን» የሚባለው የአብዛኛው የህዝብ ድጋፍ ስለሌለው ነውና የራሱን ፍላጎት ህዝቡ ላይ ስለሚጭንባቸው ነው። አብዛኛውን ቢወክልማ ምን «አምባገነን» ያስብለዋል። ኢህአዴግ አምባገነናዊ ነው ካልን የትንሽ ሰው ቁጥር ድጋፍ ነው ያለው ማለት ነው። የትንሽ የሰው ቁጥር ድጋፍ ያለው መንግስት ደግሞ አብዛኛ የሆነውን ህብረተሰብ መግዛት የሚችለው ይህ ህዝብ እርስ በርስ ለመከፋፈልና ለመገዛት ፈቃደኛ ከሆነ ብቻ ነው! «ፈቃደኛ» የሚለውን ቃል የተጠቀምኩት አውቄ ነው። ምክንያቱም አንድ ህብረተሰብ «ተከፋፈል» ትብሎ መታዘዝ አይቻልም። እራሱ ነው ልከፋፈል ውይም አልከፋፈል ብሎ የሚወስነውና።

ይህ መከፋፈል ነው ኢህአዴግን እስካሁን በስልጣን ላይ ያቆየው። ስለዚህ የኢህአዴግ ኢትዮጵያን እስካሁን መግዛት ሃላፊነቱን መሸከም ያለበት በገዛው ፈቃድ የተከፋፈለው የአገሪቷ ህብረተሰቡ ነው። 

ከላይ ያስቀመጥኳቸው ምሳሌ ታሪኮች ይን ይገልጻሉ። እርስ በርስ ሲጣላ ሲጠላ ሲቃረን የዋለ ህዝብ እንዲህ ይላል «ለጎረቤቴ ወይም ለወንድሜ ያለኝ ጥላቻ ለአምባገነኑና ለአምባገነኑ ጭካኔ ካለኝ ጥላቻ ይበልጣል፤ አምበገነኑ ይግዛኝ!» ታድያ የፖለቲካ ችግር ምንጭና ሃላፊነት ዬት ነው? ከ«ዎያኔ» ነው ወይስ ከኛ ኢትዮጵያ ህዝብ ነው?። ከኛ እንደሆነ ግልጽ የሆነ ይመስለኛል። የችግሩ መንጭም እኛው ነን፤ ሃላፊነቱም የኛው ነው፤ መፍትሄውም ከኛው ነው።

የታወቁት የሶቪዬት (የሩሲያ) ጸሃፊ አሌክሳንደር ሶልዠኒትሲን ለረጅም ዓመታት በ«ጉላግ» ከሚባለው የሶቪዬት «የሞት» እስር ቤቶች በፖለቲካ ምክንያት ታስረው ነበር። የሶቪዬት የኮምዩኒስት አምባገነናዊ መንግስት እስከ 20 ሚሊዮን ሰዎች (ከ160 ሚሊዮን የህዝብ ቁጥር) ወደነዚህ የጉልበት ስራ የስቃይና የሞት እስርቤቶች ልኮ ነበር።

ሶልዠኒትሲን ጀግና የሆኑ ሀገራቸውን ያገለገሉ ወታደር ነበሩ። ቢሆንም መንግስቱና በተለይ ሹማምንቱን ወቀስክ ተብለው ታሰሩ። ከእስር ቤት ሆነው እንደማንኛውም የህሊና እስረኛ «ለምን ታስረርኩኝ» «ምን አይነት ጭካኞች ናቸው» የሚሉትን ሃሳቦች ያንሸራሽሩ ነበር። ግን ከእስር ቤት ሆነው ስለ እስራ ዘመናቸው ሲመዘግቡ ከታች የተጠቀሰውን ታላቅ ሃሳብ ተገለጸላቸው፤ በታወቀው «የጉላግ አርኪፔላጎ» መጸሃፍ ሳፉት (ትርጉም የኔ ነው)፤

ከእስርቤታችን አልጋ የሆነው የበሰበሰው ገለባ ላይ ጋደም ብዬ ነው ለመጀመርያ ከውስጤ የበጎ መንፈስ የተሰማኝ። እውነቱን ቀስ በቀስ እንደዚህ እንደሆነ መረዳት ጀመርኩኝ፤ ጥሩና ክፉን የሚለየው መስመር የሚያልፈው በሀገሮች፤ በመደቦች፤ በፖለቲካ ፓርቲዎችም መካከል አይደለም፤ ይህ መስመር የሚያልፈው በያንዳንዱ የሰው ልብ መኻል ነው። መስመሩ እድሜአችን በሙሉ ከውስጣችን መለስ ከለስ ይላል። በክፉ የተሞሉ ልቦችም ቢያንስ ቅንጣት ያህል ጥሩነት ይኖራቸዋል፤ ከሁሉም ጥሩ ከሚባለውም ልብ ከአንድ ጥጓ ትንሽ ክፋት ይኖራታል።

በየቦታው እየዞሩ ያሉ ክፉ ስራ የሚሰሩ ክፉ ሰዎች ቢኖሩና እነሱን ከኛ መለየትና ማጥፋት ብቻ ቢሆን ኖሮ እንዴት ቀላል ይሆን ነበር! ግን ጥሩና ክፉን የሚለየው መስመር ከያንዳንዱ የሰው ልጅ ልብ መካከል ነው የሚያልፈውና ማን አለ ከራሱ ልብ ቁራጭ ቆርጦ ለማስወጣት ፈቃደኛ ይሆነ?

በዚህ አባባላቸው ሶልዠኒትሲን የሚሉት የአምባገነናዊ ስረዓት የገዢና የመሪ ውጤት ሳይሆን የያንዳንዱ ሰው ድክመትና ጠፋት ውጤት ነው። ይህ አስተማሪ አባባል የዛሬውን የኢትዮጵያ ፖልቲካ ሁነታ በደምብ ይገልጻል።

ቅድም እንዳልኩት ኢህአዴግ አናሳ ድጋፍ ነው ያለው። በተጨማሪ ከለሎች አምባገነናዊ ስረዓት አናሳነቱ የተለየ ነው። ለምሳሌ የሶቪዬት መንግስት አናሳ ድጋፍ ቢኖረውም ይህ ደጋፍ በጎሳ የተመሰረተ አልነበረም። ስለዚህ የሶቪዬት ህዝብ ተጨቆኛለሁ ሲል በራሴ ወገን በሶቪዬቶች ነው የተጭቆንኩት ብሎ ነበር የሚያስበው። የኢህአዴግ አገዛዝ ግን አናሳ ብቻ ሳይሆን በጎሳ የተመሰረተ ነው። ህገ መንግስቱም አስተምረውም እንደዚህ ነው። ህዝቡም እንደዚህ ነው የሚመለከተው። የሰው ልጅ ባህሪ ደግሞ በራሱ ወገን ቢገደል ይሻለዋል በሌላ ወገን ወይም ጎሳ ከሚጨቆን! ስለዚህ የኢህአዴግ የጎሳ አገዛዝ ከሌላው አማገነናዊ ስረዓት ይበልጥ ህዝብ ቅራኔና አመጽ የተጋለጠ መሆን ነበረበት።

ይህን አመዛዝነን ከተረዳን ለኢህአዴግ በስልጣን መቆየት እኛ ኢትዮጵያዊያን ዋና ምክንያት መሆናችንን ይገባናል። አንድነት ያለው ህብረተሰብ ብንሆን እርስ በርስ ብንስማማ ብንተሳሰብ ብንፋቀር ኢህአዴግ ድሮ ወድቆ ነበር። በተጨማሪ ማለት የምንችለው ኢህአዴግ በኃይል ሊገዛን አይችልም በኃይል ገዝቶንም አያውቅም! በኛ እርዳታ፤ ትብብርና ፈቃድ ነው እየገዛን ያለው። የኛ ጥፋትና ሃጥያት ነው የኢህአዴግ አገዛዝ ምሶሶ። ስለዚህም ኢህአዴግን የፈጠርነው የምናቆመውም እኛ ከሆንን የምናፈርሰውም የምናጠፋውም እኛው ነን የምንሆነው። ውግያና ተመሳሳይ ቀውጥ አያስፈልግም፤ ከጎረቤቴ ጋር አልጣላም ማለት ብቻውን በቂ ነው። እንደዚህ ካረግን የኢህአዴግ ይፈርሳል። እርግጠኛ ነኝ በርካታ የኢህአዴግ አባላትም ያንን ሸክማቸውን የሚያወርዱበትን ቀን በጉጉት የጠብቁታል!