Monday 29 August 2016

የኢትዮጵያ ብሄርተኞች፤ አርፍደን ቢሆንም ነቅተናልን?

2008/12/12 ዓ.ም. (2016/8/18)

በመጀመርያ ለመላው ለኢትዮጵያ ህዝብ ይቅርታዬን ላቀርብ እወዳለሁ። የሀገሬ የኢትዮጲያ ወዳጅ በአንድ ኢትዮጵያ የማምን የኢትዮጲያ ብሄርተኛ እንደመሆኔ ለ60 ዓመት በላይ ሀገሬን በድያታለሁና። ፖለቲካዋ እንዲበላሽ ፈቅጄ ህዝቧ እንዲጎሳቆል አድርግያለውና።

ልጆቻችን ሀገራችንን የሚጠቅም የሙያ ትምህርት እንዲማሩ ብለን ወደ ፈረንጅ ሀገራት ስንልካችረው ተገቢውን ጥንቃቄ ሳናደርግ ቀርተናል ። በዚህ ምክንያት አባቶቻቸውን፤ ባህላቸውን፤ ትውፊታቸውን እንዲንቁ የሚያረግ ሀገር አጥፊ የሆነ ርዓዮት ዓለም እንደ ጣዖት እያማለኩ ተመለሱ። እኛም «የተማረ ይግደለኝ» እያልን ለሚያመጡት አደጋ ታውረን ተቀበልናቸው። 

ይህ እንዳለ ሆኖ ተገቢ የሆኑትን የመሬት የቋንቋ ወዘተ የፖለቲካ ጉዳዮችን በአግባቡ መመለስ እኛ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች አቅቶን ህዝብ ጨራሽ የሆነ የተማሪ ንቅናቄና የወታደር ጥምረት ስልጣን እንዲይዝ አደረግን። የኛ ኢትዮጵያ ብሄርተኛ የሆነውን ጎራ ከፖለቲካ ተሰደድን ወይም ኢዲዩ ነኝ፤ እህአፓ ነኝ፤ ደርግ ነኝ ወዘተ እያልን እርስ በርሱ ተለያየንም ተጨራረስንም። በመጨረሻ የወለድነው የደርግ መንግስት ሀገራችንን አመሰቃቅሎ ህዝብን በስመ ኢትዮጵያዊነት ገድሎ አንዳንድ ወገኖቻችንን ወደ እነ ሻእብያ፤ ህወሓት፤ ኦነግ ወዘተ አይነት የጎሳ ድርጅቶች እንዲሽሸጉ አድርጎ ሀገሪቷን ለነዚሁም አስረከበ። 

1983 ዓ.ም. ሲደርስ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት እንደ ፖሊቲካ ኃይል የመጨረሻ ወድቆ ተገኘ። በፖለቲካ ድርግት ወይም ንቅናቄ መልክ አልነበረም። በመጽሔትና ለቅሶ ቤት ብቻ ቀርቶ ነበር። የኢትዮጵያ ህልውና በኃይል ያላቸው የጎሳ ብሄርተኞች እንደ ህወሓት ተወሰነ። እኛ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች እራሳችንን በማጥፋት ሜዳውን ለነሱ ለወለድናቸው «የጠፉ ልጆች» ተውንላቸው። ታድያ ለዚህ ሁሉ ይቅርታ መጠየቅ አያስፈልግምን?!

ላለፉት የ60 ዓመታት የኢትዮጵያ የፖሊቲካ ችግሮችን የኢትዮጵያዊ ብሄርተኛ ወገንን ብቻ ጥፋተኛ ማድረግ ጉዳዩን ማቅለል እንደሆነ አላጣሁትም። ግን በኢትዮጵያ ብሄርተኞች ጥፋትና ድክመት ማተኮር የመረጥኩት አስተማሪ ስለሆነና የችግሮቹን መፍትሄ በግልጽ እንድናይና እንድንረዳ ስለሚጠቅመን ነው።

ለምሳሌ በተደጋጋሚ የሚነሳው ጥያቄ «ከአናሳ ብሄር የመነጨው ኢህአዴግ ለ25 ዓመት ስልጣን እንዴት ሊይዝ ቻለ» ነው። የዚህንም ጥያቄ መልስ ካገኘን ነው ለውጥ ማምጣት የሚቻለው። ለዚህ ዋናው መልስ የኢትዮጵያ ብሄርተኛ የሆነው የፖሊቲካ ጎራ ከኢትዮጵያ የፖሊቲካ ሜዳ ስለጠፋ ወይም ኃይል አላባ ስለሆነ ነው። የጠፋው ደግሞ በህወሓት እጅ ሳይሆን በራሱ እጅ ነው። የተማሪ ንቅናቄው የለኮሰው አብዮትና የደርግ መንግስት የኢትዮጵያ ብሄርተኛ አመራርንና ልሂቃንን ሀገር ውስጥም ወደ ውጭም በታተናቸው። የኢትዮጵያ ብሄርተኛ የሆነው ብዙሃንም በደርግ ዘመን በነበረው ጭካኔ ተመርዞ «ፖሊቲካና ኮሬንቲ» እያለ ፖሊቲካን ዞር ብሎ ላለማየት ወሰነ።

በዚህ ምክነያት የኢትዮጵያ ፖሊቲካ ሚዛን አጣ እስከ ዛሬም አጥቷል። ይህ እጂግ ዋና ነጥብ ነው። በታወቀው የ1983 ዓ.ም. የለንደን ሰብሰባ የተደራጀ ኃይል የነበራቸው ጎራዎች ሻእብያ ኢህአዴግና ኦነግ ነበሩ። ቢዚህ ምክነያት የኢትዮጵያ የወደፊት አካሄድን የወሰኑት፤ እንደ ህገ መንግስት አይነቱን መሰረታው ስምምነቶች ያቀናበሩት፤ የተወሰኑት የጎሳ ብሄርተኛ ድርጅቶች ናቸው። የኢትዮጵያ ብሄርተኛው ጎራ በመደራጀትና በኃይል ማጣት ምክንያት አልተሳተፈም።

ይህ ሲሆን ኢህአዴግና ሌሎቹ ትልቅ ስህተት አድርገዋል። ደርግና የኃይለ ስላሴ መንግስት መውደቃቸውና የኢትዮጵያ ብሄርተኞች የተደረጀ ኃይል ማጣጣቸው የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት በብዙሃኑ ተቀባይነት እንዳጣ ያሳያል ብለው ገመቱ። ነገር ግን የተወሰኑ ወገኖች የኢትዮጵያ ብሄርተኝነትን ባለመፈለግ ደርግን ቢዋጉትም አብዛናው ህዝብ ደርግን የጠላው ስለ ሶሺአሊዝሙ ጭካኔው ወዘተ ነው። 

ሆኖም ይህ በኢትዮጵያ ብሄርተኝነት የሚያምን ግን ደርግን የማይወድ ህዝብ ብፖሊቲካ ድርድሩ አልትቆጠርም አልተሳተፈም አልተወከለምም። ይባስ ብሎ ኢህአዴግ ለ 25ዓመታት ዋና ስራውን የኢትዮጵያ ብሄርተኞች (ወይም «ትምክህተኛና ነፍጠኖች» ብሎ የሰየማቸው) የፖሊቲካ ወገን እንዳይነሳ ማድረግ ነበር። ይህ ሁኔታ የኢትዮጵያ ፖሊቲካን ኢሚዛናዊ አድርጎ የዛሬው የፖለቲካ ችግሮች አንዱ ምክንያት ሆኗል። ለመድግም ያህል የኢህአዴግ ጥረት ብቻ ሳይሆን የጎራው እርስ በርስ መፋጀትና ሌሎቹ ከላይ የተጠቀሱት የታሪክ ምክነያቶች ናቸው የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት የፖለቲካ ኃይል እንደመነምን ያደረጉት። 

በደምብ ማስተዋል ያለብን አናሳን የሚወክል አገዛዝ ህወሓት በተለይም አናሳ ጎሳን የሚወክል አገዛዝ ያለ ሌላው ህዝብ ፈቃድ መግዛት በፍጹም አይችልም። አናሳ ነውና በኃይል በመጨፍጨፍ በማሰር ወዘታ ብቻ ሊገዛ አይችልም። ስለዚህ ህወሓት የማይወክለው ህዝብ እርስ በርሱ እንዲጣላና እንዲከፋፈል ወይም በፖሊቲካ በፈቃደኝነት እንዳይሳተፍ የግድ ያስፈልገዋል። ይህ ካልገባን ወይም ካላመንን ኢህአዴግ በርካታውን የኢትዮጵያን ህዝብ ይወክላል ብለን አመነናል ማለት ነው! ይህን ደግሞ ኢህአዴግ እራሱ አያምንም።

አሁን ግን ይህ ያልተወከለው ህዝብ መሳተፍ የጀመረ ይመስላል። ከ25 ዓመት በኋላ በጎንደር በባህር ዳርና በመላው በአማራ ክልል የምናያቸው የህዝበ ሰልፎች የዚህ ምልክት ናቸው። እርገጥ ከዚህ በፊት የተለላዩ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ስሜትን ያቀፉ እንቅሳቅሴዎች ለምሳሌ እንደ ቅንጅት አይነት ኖረው ያውቃሉ። እነዚህ ግን ወደ ኋላ ሄደን ስናያቸው በአብዛኛው በከተማ ህዝብ የተመኩና ውስጣቸው የተከፋፈለ ንቅናቄዎች ነበሩና በነዚህ ምክነያቶች ኢህአዴግ በቀላሉ ሊያጠፋቸው ችሏል። ወይም በተለያዩ ብልጥ የመርህ መልሶች እንደ «ልማት እንሰጣቹሃለን ስልጣና ጥቅማችንን አትንኩ እንጂ» የሚለውን እያራመዱ ተቃዋሚዎች የህዝብን ድጋፍን እንዲያጡ አደረጉ።

የዛሬው በአማራ ክልል የሚካሄደው የነፃነት እንቅስቃሴ ግን ከዚህ ታሪክ የተማረ ይመስላል። የአማራ ክልል ህዝብ በደፈናው የኢትዮጲያ ብሄርተኝነት ስሜት ያለው ነው፤ በአማራ ክልል አክራሪም ይሁን ለዘብተኛ የጎሳ ብሄርተኝነት በሞላ ጎደል የለም። እንሆ ለ25 ዓመታት የኢህአዴግ አገዛዝ ዘመን ይህ ሰፊ የኢትዮጵያ ብሄርተኛ ጎራ ከሞላ ጎደል ከኢትዮጵያ ፕሊቲካ እራሱን አውጥቶ ይኖር ነበር። አሁን ግን ተነስቷልና የሚዘልቅ ከሆነ ኢህአዴግ በምንም መንገድ ልያቆመው አይችልም።

ለኢህአዴግ አዲስ አበባና ኦሮሚያ ይቀሉታል። በእነዚህ ቦታዎች የተለያዩ ህዝቦች መደቦችና ጎሳዎች አሉና ጠንከር ያለ ጭቆና በማራመድ መከፋፈልን (ኦነግ ሊያርድህ ነው ወይም አማራ ሊገዛህ ነው ወይም ንብረትህ ሊወድምብህ ነው እያለ) ጥርጣሬንና ፍረሃትን አስፍኖ የፖሊቲካን እንቅስቃሴ መግደል ይችላል። በአማራ ክልል ግን እነዚህ መስፈርቶች የሉምና መከፋፈሉ ቀላል አይደለም። ኢህአዴግ ትልቅ የጭቆና እርምጃ ከወሰደ ደግሞ አማራውን በጎሳነቱ ያስተባብረዋልና ይህ የጎሳ ጦርነት ይጋብዛል። ከጥቂት የህወሓት አክራሪዎች በቀር የኢህአዴግ አመራር ይህን በደንብ ይረዱታል አይፈልጉትምም።

ሆኖም ኢህአዴግ እስቲ እንደልማዳችን ወይም ለ25 ዓመታት እንዳረግነው የኃይል እርምጃ በመጀመርያ እንውሰድና ውጤቱን እንየው ብሏል። የኢህአዴግ  ለዘብተኞችም ለአክራሪው ወገን እርምጃህን ሞክር ግን ካልሰራ መሪው ወደኛ እጅ ይገባል ብለው ተስማምተዋል። ንቅናቄው ካልቆመ  በየአቅጣጫው ለውቶች ይጅምራሉ። እያንዳንዱ የመንግስት የህብረተሰብም መዋቅሮች ውስጥ በተለይ ጦር ስራዊት ውስጥ ታላቅ ለውጦች ይኖራሉ። ከላይ የጠቀስኩት የተበላሸው የኢትዮጵያ የፖሊቲካ ሚዛን መስተካከል ይጀምራል። ከስንት ዓመታት በኋላ ከሀገር ፖሊቲካ የጠፋው የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ጎራ ሃላፊነቱን ተቀብሎ ድምጹን ያስከብራል። ይህ ሁኔታ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ታላቅ ድል ይሆናል የሀገሪቷን ፖሊቲካ ሁሉን አቀፍ በማድረጉና ወደ እውነታን የሚያንጸባረቅ ትክክለኛው ሚዛን በማስተካከሉ። ነገር ገን ይህ ዕድል ካለፈን…

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!