Saturday, 29 December 2018

ልሂቃኖቻችን ዛሬም የምዕራባዊነት እስረኞች…

እምብዛም ልሂቃን እና ምሁራኖቻችን ዛሬም በምዕራባዊነት አምልኮ የተለከፍን ነን። እንግሊዝን፤ ጀርማንን፤ አሜሪካንን ገልብጦ እንዳለ ወደ ኢትዮጵያ ከማምጣት ውጭ ሃሳብ የለንም። ምናልባት የኢትዮጵያ ህዝብ ሙሉ ለሙሉ እንደ ምዕራብ ሀገር ለመሆን ዝግጁ ባለመሆኑ ጉዞውን ቀስ በ ቀስ እንጀምራለን እንል ይሆናል። ግን ግቡ አንድ ነው፤ ኢትዮጵያን እንደ «ፈረንጅ» ሀገር ማድረግ ነው።

ይህ አካሄድ ለኔ unimaginative ብቻ ሳይሆን ለሀገራችን የማይሆንም ነው ብዬ አምናለሁ። የኢትዮጵያዊነት ምሁራ ዶናልድ ሌቪን እንደሚያስታውሱን፤
"The vitality of a people springs from feeling at home in its culture and from a sense of kinship with its past. The negation of all those sentiments acquired in childhood leaves man adrift, a prey to random images and destructive impulses…"
ለኔ፤ በግሌ፤ ኢትዮጵያን እስክስታ፤ እንጀራ፤ ወዘተ ያላት ፈረንጅ ሀገር ማድረግ ትርጉም የለውም። ማንነትን ማጣት ነው። ባህላዊን እሴቶችን ማጣት ነው። አብሮነትን አጥተን ብጨኞችን መሆን ነው። ፍቅር አጥተን ነግ በኔዎች መሆን ማለት ነው። እምነት አጥተን እምነት የለሾችን መሆን ማለት ነው። ለኔ ይህ ትሩጉም የለውም።

ግን ልሂቃን እና ምሁራኖቻችን የሀገር ወጋችን ገብቷቸው አክብረውት መራመድ ያቃተን ምክንያት ይገባኛል። በመጀመርያ ወጋችንን በደምብ አላከበርንም። በጃንሆይ ዘመን የነበረው የፍትህ እጦት እና ጭቆና (በምንም ደረጃ ቢሆንም) የመጀመርያ ሀገር በቀል ፈረንጆቻችን እንዲወለዱ አደረገ። በሃይማኖት ተቋሞቻችን የነበረው ግብዝነትም እንዲሁ ጥላቻ ፈጠሮ ምሁራን ወደ ማርክሲዝም እንዲሄዱ ጋበዘ። ይህ ለምሁራኖቻችን ፈረንጅ አምላኪነት አንዱ ምክንያት ነው።

ሌላው ምክንያት ዘመናዊ ትምሕርት አሰጣጡ ነው። ሶሻል ሳየንስ ተማሪዎቻችን ከሞላ ጎደል የሚማሩት የዘመኑ ርዕዮት ዓለም ነው። ርዕዮት ዓለሙ እንደ እውነት ነው የሚሰበክላቸው አብዛኞቹ አለ ጥያቄ ይቀበሉታል። እንደ ምሁራን መቀጠል ከፈጉ ደግሞ ምርጫ የላቸውም። ከዘመኑ ርዕዮት ዓለም የተለየ አስተሳሰብ በባልደረቦቻቸው እንዲናቁ እና እንዲዘለፉ ነው የሚያደርጋቸው። ስራቸውንም ያጣሉ ማንም ዩኒቨርሲቲ ወይም ሌላ ተቋም አይቀጥራቸውም። ስለዚህም የዘመኑን ርዕዮት ዓለምን እንደ ጣኦት ያመልኩታል።

ሶስተኛው ምክንያት የኢትዮጵያ ነባራዊ ችግሮች ናቸው። አስተዋይ ያልሆነ ሰው ሃብታሙ እና ምቾት የተሞላውን ምዕራብ ዓለም ከኢትዮጵያ ጋር አወዳድሮ ምዕራብ ነው ትክክል ይላል። ማስተዋል የማይችል። ጠልቆ ማሰብ እና ማየት የማይችል። መሳደቤ አይደለም፤ እኔም ወደ እንደዚህ አይነት ቀላል ድምዳሜ ተስቤ አውቃለሁ።

ስለዚህ ዛሬ በኢትዮጵያ ታላቅ የምሁራን እና ልሂቃን እጥረት (deficit) አለ። እምብዛሙ ውጭ ሀገር የሚያየውን ፎርሙላ ወደ ሀገር ማምጣት ብቻ ነው የሚታየው። ማንነቱን አጥቷል። ማርክሲዝም ይሁን፤ «ሊበራሊዝም» ይሁን፤ ሶሻሊዝም ይሁን፤ «ማርኬት ኤኮኖሚ» ይሁን፤ ሴኩላሪዝም ይሁን፤ ፌሚኒዝም ይሁን፤ ዴሞክራሲ ይሁን ለምሁራኖቻችን ጣኦት ሆነዋል። ለምን ኢትዮጵያዊነት እንደሚያሰኝንም አላውቅም። አሜሪካዊ መሆን ይሻለናል ማንነታችን አሜሪካዊ ከሆነ።

ፋንታሁን ዋቄ እንዳለው ታላቅ paradigm shift ያስፈልገናል። አቢይ አህመድም ደጋግመው እንደሚሉት የሀገራዊ እሴቶቻችንን ተምረን አቅፈን እንራመድ። እሴቶቻችንን እንፈተሽ እና እናሟላ። አንድ አጭር ምሳሌ ልስጥ፤ ሃይማኖታዊ መቻቻል (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/04/blog-post_3.html)። የሀገራችንን ወግ የማያውቅ የሀገራችን ሃይማኖቶች መቻቻልን አያውቁም ይላል። ወይን መቻቻል የሚችሉት መሰረታቸውን ትተው ባህል ብቻ ሲሆኑ ነው ይላል። ግን ከላይ እንደጠቀስኩት ጽሁፌ በኦርቶዶክስ ክርስትና ለምሳሌ ከመቻቻል አልፎ ፍቅር ነው ዋናው መርህ! ሙስሊሙን መቻል (አሉታዊ ነገር ነው tolerate) የለብኝም መውደድ ነው ያለብኝ! ግን አብዛኞች ምሁሮቻችን መቻቻልን ከምዕራባዊነት እና ሴኩላሪዝም ያያይዙታል! ይህ ትንሽ ምሳሌ ነው። ወጋችንን እንፈትሽ። የምዕራብ ርዕዮት ዓለም እስረኞች አንሁን። ለራሳችን ማንነት ክብር እና ፍቅር ይኑረን። እራሳችንን እንወቅ።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!