Showing posts with label population. Show all posts
Showing posts with label population. Show all posts

Thursday, 7 February 2019

በህዝብ ቆጠራው ላይ የኦርቶዶክስ አማኝ ቁጥር ከታሰበው በታች ቢሆን ምን እንል ይሆን?

በሚመጣው የህዝብ ቆጠራ ላይ የኦርቶዶክስ አማኝ ቁጥር ከታሰበው ወይንም ከሚፈለገው በታች ቢሆን እንደ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ምን እንል ይሆን? ይህን መረጃ / ሰነድ ስናገኝ ምንድነው ማድረግ ያለብን?

በመጀመርያ ደረጃ ንስሃ ነው መግባት ያለብን። የኦርቶዶክስ አማኝ ቁጥር ከመነመነ ዋናው ጥፋት የኛ የኦርቶዶክስ ምዕመናን ስለሆነ። እምነታችን፤ ክርስቶስም፤ የሃይማኖት አባቶችም አስረግጠው ይነግሩናል፤ እኛ ጥሩ ክርስቲያኖች ከሆንን እንደ ብርሃን ሌሎችን ወደ ብርሃን፤ ወደ ቃሉ፤ ወደ ክርስቶስ እናመጣለን። በአንጻሩ ጥሩ ክርስቲያኖች ካልሆንን፤ ጭለማዎች ከሆንን፤ ሌሎችን ወደ ክርስትና እንዳይመጡ እናደርጋለን። አልፎ ተርፎ ከኛም ያሉትን እንዲወጡ እናደርጋለን።

ይህን እውነት በአጭሩ ለመግለጽ የሩሲያዊው ቅዱስ ሴራፊም (ሱራፌል) ዘ-ሳሮቭ  እንዲህ ብለዋል፤

«መንፈስ ቅዱስ እንዲያድርባችሁ ከፈቀዳችሁ ዙርያችሁ ያሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ይድናሉ።»

በዚህ ጉዳይ ላይ ለተጨማሪ ማብራርያ ይህን የታወቁት የቆጵሮስ (ሊማሱ ከተማ) ጳጳስ አታናሲዮስ ቃለ ምልልስ ያንብቡ፤ http://orthochristian.com/79957.html። «ክርስቶስን የማያውቁ ሰዎች መኖራቸው የኛ (የክርስቲያኖች) ጥፋት ነው» ይላሉ። ይህ መሰረታዊ እምነታችን ነው።

በመንፈሳዊ ህግ ኃጢአት የቦታ እና የጊዜ ግድብ የለውም። የሁላችንም ኃጢአት ሁላችንንም በተለያየ መንገድ ይነካል። ለምሳሌ፤ እንዴ ወንድሜን ከበደክሉኝ ችግሩ ከኔ እና እሱ መካከል ሆኖ አይቀርም። ይተላለፋል። ወንድሜ ተበሳጭቶ ሌሎችን ይበድላል። ቤት ሲሄድ ቤተሰቡ አክሩፎ ያገኙታል። እኔ ስለበደልኩት ህይወቱን በሙሉ ቁስሉን ተሸክሞ በቁስሉ ምክንያት አስተሳሰቡም ድርጊቶቹም ሊሳባ ይችላል። ቂም ሊይዝ ይችላል። ሰውን በጥርጣሬ ሊያይ ይችላል። በዚህ መንገድ የኔ ኃጢአት እንደ ተላላፊ በሽታ ይንሰራጫል።

ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ህግ ኃጢአት ከቦታ ቦታ ብቻ ሳይሆን ዘመናትን ይሸጋገራል ብለን እናምናለን። ይህ ማለት ኃጢአት ለትውልድ ይተላለፋል። ይህ የሃይማኖታችን መሰረታዊ እምነት ነው። የአዳም ኃጢአትን መውረሳችን ይህን ይገልጻል። ለአዳም ኃጢአት ሃላፊነት ባይኖረንም ውጤቱን ወርሰናል። እኛም ኃጢአት በመስራታችን እንዲሁም አስተላልፈንዋል። ለምሳሌ ከወላጆቼ የወረስኩት ችግርን ተሸክሜ ለልጆቼ በትወሰነ ደረጃ አስተላልፋለሁ። ችግሩ በሃሳብ ብቻ ሳይሆን በደምም (በዲኤኔአችን) ይተላለፋል።

በመንፈሳዊ ህግ ኃጢአት በሀገር ደረጃም ይታወቃል። የእስራኤል ህዝብ ለሀገራዊ ኃጢአታቸው የታዋቁ ናቸው በራሳቸው በኦሪት ታሪክም በወንጌልም ይህ ታሪካቸው ተዘርዝሯል። ሌሎች በርካታ ህዝቦች እንደ ህዝብ ወይንም ሀገር ለኃጢአቶቻቸው ዋጋ ከፍለዋል። ዛሬም እንዲሁ ነው (https://blogs.ancientfaith.com/glory2godforallthings/2015/06/27/dostoevsky-and-the-sins-of-the-nation/)።

ስለዚህ እንደ ግለሰብም እንደሀገርም ኃጢአቶቻችን በቦታ እና ጊዜ ይተላለፋል። ለዚህ ኃጢአቶቻችንን አምነን ንስሃ መግባት አለብን። ይህ መሰረታዊ የክርስትና እምነት ነው። እንኳን በኢትዮጵያ በዓለም ዙርያ ችግር ሲከሰት ወደ ራሳችን ተመልክትን «ምን አድርጌ ወይህም ምን ባለማድረጌ ነው ይህ የሆነው» ብለን እራሳችንን መጠየቅ አለብን።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ መእመን ቁጥር ከቀነሰ ወይንም ካልጨመረ እሄኑኑ ጥያቄ እራሳችንን መጠየቅ ነው ያለብን። አማራጭ የለንም። እውነቱ ይህ ነው። ለዚህ ችግር ሌሎችን ጥፋተኛ ማድረግ ኢ-ክርቲያናዊ አካሄድ ነው። እንደ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች «ጴንጤዎቹ»፤ «ሙስሊሞቹ»፤ ወይንም «ሴኩላሪስቶቹ» ናቸው ምእመኖቻችንን የወሰዱብን ማለት አንችልም። ወደራሳችን ብቻ ነው መመልከት ያለብን። እኛ ብርሃን ከሆንን ምንም አይሳነንም፤ ዓለም በሙሉ ወደ ክርስቶስ ይመጣ ነበር። እዚህ ላይ ነው ማተኮር ያለብን። ይመስለኛል።

Tuesday, 1 January 2019

የአማራ «ልሂቃን» እና የአማራ ህዝብ ቅነሳ

ማንም በማይክድበት ደረጃ በአማራ ክልል የተካሄደው የወሊድ ቅጥጥር (በተዘዋዋሪ የህዝብ ቁጥር ቅነሳ) ዘመቻ ከሁሉም ክልል በላይ በደምብ «ተሳክቷል»። ማለት የህዝብ ቁጥር ጭማሬ በደምብ እንዲቀንስ አድርጓል።

ይህ ለኔ እጅግ የሚያሳዝን ክስተት ነው። የአማራ ክልላዊ መንግስት በአማራ ልሂቃን ተደግፎ ያልተሟላ እና ኋላ ቀር የህዝብ ብዛት መጥፎ ነው የሚል ፍልስፍና ተሸክሞ የአማራ ክልልን ህዝባዊ አቅምን መንምኖታል። ህዝቡም በመርፌ የሚወገ የወሊድ መቆጣጠርያ መድሃኔት በmarketing እና coercion ኃይል እንዲጠቀም በማድረግ ከባህሉ፤ ከጤንነቱ እና ከራሱ (ከህሊናው) ጋር እንዲጣላ አድርጓል። ሌሎቹ ክልሎች ይህንን መርዛማ አካሄድ ላለመከተል ሲታገሉ የአማራ መንግስት እና ልሂቃን አዋቂ እና ተምረናል ባዮች ሙሉ በሙሉ capitulate አደረጉ። እውነትም «የተማረ ገደለን» (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2016/12/blog-post_7.html)።

ዛሬ የኢትዮጵያ መሰረታዊ ችግር የህዝብ ብዛት አይደለም። ከመሰረታዊ ችግሮች መካከል የመሬት ፖሊሲው (መሬት የመንግስት መሆኑ) እንደ ችግር ይበልጠዋል። የህዝብ ብዛት እንዲህ እንዲጨምር ያደረገው ገበሬው መሬቱን ሽጦ ወደ ከተማ መምጣት ስለማይችል የኢትዮጵያ ህዝብ ለ40 ዓመታት artificially ገጠር እንዲቆይ ተደርጓል። ገበሬው በነጻነት መሬት መሸጥ መለወት ቢችል ኖሮ ዛሬ 80-85% የገጠር ነዋሪ ከሚሆን ወደ 60% ደርሰን ይሆን ነበር። የገጠር ህዝብ ስድስት ልጅ ይወልዳል የአዲስ አበባ ህዝብ ሁለት ልጅ ይወልዳል። 40% የከተማ ነዋሪ ሆኖ ከስድስት ፋንታ ሁለት ልጅ በአማካኝ ሲወልድ የህዝብ ቁጥራችን እንዲህ አይጨምርም ነበር። ስለዚህ ልክ እንደ ቻይና በማኦ ዘመን የመሬት ፖሊሲው ነው የዝብ ቁጥራችንን artificially እንዲንር ያደረገው። አሁን ታድያ መሰረታዊ ችግሩን አምኖ ለመቅረፍ ከመሞከር symptomኡን ለማከም እንሞክራለን። ይህ ታላቅ ጥፋት ነው።

በሁለተኛ ደረጃ አንድ ህዝብ የሚወልደውን ልጅ መጠን እራሱ የራሱን ጥቅም አይቶ በholistic እና organic መንገድ ቢቆጣጠር ነው የሚሻለው (በስነ ልቦና እና ማህበራዊ ሰላም ደረጃ)። ከተሜ ሲሆን፤ ቆይቶ ሲያገባ፤ ወዘተ እራሱ አስቦ መወሰን ይጀምራል። በመንግስት እና ኤንጂኦ ኃይል በግፊት እና ጫና በቅኝ ግዛት መልክ ከተመጣበት ችግሩን በደምብ ሳያውቀው ወደ አደገኛ የወሊድ ቁጥጥር ይገባበታል። ከዛ ዛሬ የምናየው backlash ይመጣል። ሴቶች መውለድ አቃተን ይላሉ። ልጆች ጠፉ ይባላል። ወዘተ። የብአድ መፍትሄ ብዙ ጊዜ መፍትሄ አይደለም።

ሶስተኛ፤ መላ ኢትዮጵያም አማራም ለህዝብ ቁጥር እድገት በቂ ቦታ አላት። አልተጨነቀችም። ሌሎች የመንግስት ፖሊሲዎች ናቸው ችግሮቹ። አልፎ ተርፎ አንዱ ላለፉት አመታት የኤኮኖሚ እድገት ያመጣው ግበአት የህዝብ ብዛት ነው። የ100 ሚሊዮን ገበያ እና ሰራተኛ ኃይል ቀላል አይደለም። ጥቅም አለው። ይህ በአማራ ክልል እና ልሂቃን የታሰበበት አይመስለኝም። ውሳኔዎችን በ one track mind ሆነው ነው የወሰኑት።

አራተኛ፤ በዛሬው የጎሳ ችግር ሁኔታ ዴሞግራፊ ወሳኝ ነገር ነው። የአማራ ክልል ህዝብ ቁጥር ቀነሰ ማለት በአንድነት የሚያምነው ህዝብ ቁጥር ቀነሳ ማለት ነው (አማራው ከሞላ ጎደል እንዳለ ከአንድነት ኃይሉ ውስጥ ስለሆነ)። ዛሬ ይህን ሃቅ መካድ አይጠቅምም። ይህ ፖለቲካዊን ይቀይራል። መሃሉን ያደክማል ጎሰኝነትን የሚያራምድ ፖለቲካን ያጠነክራል። ፖለቲካው ይዛባል። የአማራ ክልል መንግስት እና ልሂቃን ይህን እንደ አንድ ግበአት አለማሰባቸው እጅግ ያሳፍራል። ወይ ክፋት ወይንም ጅልነት ነው፤ ይቅርታ አድርጉልኝ። ነባራዊ እውነታን አለመቀበል ነው። ለጎሳ ፖለቲካ ተብሎ የህዝብ ቁጥር እንዲንር ይደረግ ማለቴ እንዳልሆነ መችሄስ ግልጽ ይመስለኛል። ግን ሁሉ ነገር መታየት አለበት እና ሚዛናዊው መንገድ መከተል አለብን ነው የምለው።

መፍትሄው ምንድነው? የወሊድ መቆጣጠርይ ይከልከል ወዘተ አይነት የማይሆን ነገር አደለም የምለው፤ ከአንዱ ጸንፍ ወደ ሌላው! መንግስት ለወሊድ መቆጣጠርያ marketing እና እርዳታ ይተው ነው የምለው። በዚህ ዘርፍ የሚሰሩ ኤንጂኦዎች ይከልከሉ። የታወቁ ጉዳታቸው ያነሰ የወሊድ መቆጣጠርያ መንገዶች ይሸጡ ግን ህዝቡ ላይ አይጫኑ። ህዝቡ አለ ጫና እና ግፊት በorganic እና holistic መንገድ የራሱን ግላዊ ውሳኔ ያድረግ። አለ ጫና እና ግፊት። ይህ መፍትሄ ሁለት ግቦች ይኖሩታል፤ 1) የህዝቡ ስነ ልቦና እና የማህበረሰቡ ስነ ልቦና ይገጋጋል እና ይጠበቃል እና 2)  የህዝብ ቁጥር ጭማሬ ከፍ ይላል፤ ወደ naturally መሆን ያለበት ደረጃዎች ይሄዳል እና ከሌሎች ክልሎች ብዙ አያንስም። በአጭሩ የክልሉ ፖሊሲ ከጫፍ ወደ ሚዛን ይመለሳል ነው (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/04/blog-post_6.html)።

Friday, 21 September 2018

የተረሳው ጉዳያችን፤ የመሬት ፖሊሲ ሚና በጎሳ ፖለቲካ

ከዚህ በፊት ደጋግሜ ስለ የኢትዮጵያ የመሬት ፖሊሲ ችግር ጽፍያለሁ (http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/03/blog-post_47.html)። መሬት የግል ወይንም የአካባቢ ("local community" ለምሳሌ ወረዳ) ከመሆኑ ፋንታ የመንግስት መሆኑ ለህዝባችን እጅግ ጎጂ ፖሊሲ ነው ብዬ ነው የማምነው። ለዝርዝሩ ከላይ የጠቀስኩትን ጽሁፍ አንብቡ፤ ግን በአጭሩ መሬት የመንግስት መሆኑ የፈጠረው ችግሮች እንዲህ ናቸው፤

1. ገበሬው ለ«ጎበዝ ገበሬ» የሆነው ጎረቤቱ መሬቱን ሽጦ ወደ ከተማ መሄድ ባለመቻሉ ገጠር ቀርቶ በገጠር የመውለድ መጠን (birth rate፤ በገጠር አማካኙ ከስድስት ልጅ በላይ ነው) ልጅ ወለደ። ከተማ ቢሄድ ኖሮ ሁለት ልጅ (ሁለት አማካኙ ነው ለከተማ ነዋሪ) ይወልድ ነበር። ይህ ማለት የህዝብ ቁጥርን ባልተጠበቀና በኢተፈጥሮዊ (artificial) መንገድ ንሯል። ኢተፈጥራዊ ማለት ህዝቡ ወደ ከተማ እንዳይሄድ ነፃነቱ በመገደብ የጠፈጠረ ሁኔታ ስለሆነ ነው። ከግዳጅ የመጣ ክስተት ስለሆነ ነው።

2. የገጠር ህዝብ ቁጥር ንሮ የገበሬ መሬት አንሶ ልጆች የሚወርሱት አጥተው አሁን ታላቅ የገጠር ወደ ከተማ ፍልሰት ተከስቷል። ለ40 ዓመት ቀስ በቀስ ፍልሰት ከመሆኑ ፋንታ የገጠሩ ሰው ለ40 ዓመታት ከገጠር ተጠራቅሞ አሁን ባንዴ ወደ ከተሞች እየመጣ ነው። ይህ ሁኔታ ከተሞቻችንን አስጨንቋል።

3. ገበሬዎች ቢጎብዙም ገንዘብ ቢኖራቸውም መሬት መግዛት ባለመቻላቸው የግብርና ስራውን ማስፋፋት አልቻለም። ማደግ አልተፈቀድለትም። በዚህ ምክንያት «የሰው አቅማቸው» (human capital) እንዳያድግ ተደርጓል። ለምሳሌ እንደ የግብርና የሙያ፤ የንግድ ሙያ፤ የአስተዳደር ችሎታ አይነቱን እንዳያዳብር ተደርጓል።

4. ገበሬው ሽጦ መሄድ ባላመቻሉ መሬቱን ለትውልድ እያከፋፈለ መሸንሸን ሆነበት። መሬቱ ተሸንሽኖ የያንዳንዱ ገበሬ መሬት አንሶ አንድ ቤተሰብም ማስተዳደር የማይችል ሆኗል። በዚህ ምክንያት ገበሬዎች ለድርቅ እና ርሃብ ተጋለጡ። የምግብ ዋስትና እጥረት እንዳለ ነው።

5. ጎበዝ ገበሬዎች መሬት ገዝተው መስፋፋት ባለመቻላቸው እና ደካማ ገበሬዎች ለጎበዞቹ መሸጥ ባለመቻላቸው የእርሻ ውጤት ዝቅተኛ ሆኖ ቈርቷል። ይህ ደግሞ የእህልና የምግባ ዋጋ ግሽበት አምጥቷል።

ከላይ የጠቀስኳቸው ባብዛኛው በኤኮኖሚ ዙርያ የሆኑ ነጥቦች ናቸው። ግን የመሬት ፖሊሲው ሌላ ታላቅ የፖለቲካ እና ማህበረሰባዊ ተጽዕኖ አለው።

ባጭሩ፤ የመሬት ፖሊሲው አንዱ የጎሳ አስተዳደሩ ምሶሶ ነው። መሬት የ«ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች» ነው ሲባል ለ27 ዓመት የተተረጎመው የአማራ ክልል መሬት የ«አማራ ብሄር» ነው፤ የኦሮሚያ ክልል መሬት የ«ኦሮሞ ህዝብ» ነው ወዘተ እየተባለ ነው። ትርጉሙም የህገ መንግስቱን ጽሁፍም መንፈስም የተከተለ ነው።

«መጤ» እና «ነባር» የሚሉት ጽንሰ ሃሳቦች በማህበረሰቡ በዚህ መሬት ፖሊሲ ይደገፋሉ። የ27 ዓመታት የመፈናቀል ዘመቻዎች የተካሄዱትም በዚህ ምክንያት ነው። ግን ህጉ የመሬት ባለቤትነት የግለሰብ ወይንም የቅርብ አካባቢ ሰዎች ቢያደርግ ኖሮ የ«መጤ» እና «ነባር» አስተሳሰብን ይቀንስ ነበር ነአ ቀስ በቀስ ያጠፋ ነበር። ለዚህ አስተሳሰብ የህግ ሽፋን እንዳይኖረው ያደርጋል። ተፈናቃዮች ለመብታቸው በፍርድ ቤት መታገል እንዲችሉ ያደርጋቸው ነበር።

ስለዚህ ዛሬ ያለውን ጎሰኝነትን ለመታገል እና ቀስ ብሎ ከጎሳ ፌደራሊዝም ወደ ህብረ ባህላዊ አገዛዝ ለመሄድ ይህን የመሬት ፖሊሲ መመልከትና መቀየር ጠቃሚ ይመስለኛል።

Friday, 6 April 2018

የህዝብ ብዛት

የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር በዝቷል በተለያዩ መንገዶች የህዝብ ቁጥር እድገትን መቀነስ አለብን ሲባል እጅግ አዝናለሁ። በተለይ የኛ ምሁራን ልሂቃን እንደዚህ ሲሉ ስለ ሀገራችን ህልውና እሰጋለሁ። ሀገራችን ብዙ የፖለቲካ የኤኮኖሚ የመሐበረሰብ ችግሮች አሉትና ከነዚህ ሁሉ የሰው ቁትር መብዛት «ችግር» ከተባለም ትንሹ ነው። የሰው ቁጥር አለ አግባብ ጨምሯል ከተባለም ምክንያቱ የእርግዝና መከላከያ እጦት ሳይሆን ሌሎች የኤኮኖሚና የፖለቲካ ችግሮች ናቸው።

እስቲ አንዳንድ እውነታዎች እንመልከት፤

1. በገጠር ሴቶች በአማካይ ስድስት ልጆች ይወልዳሉ። በአዲስ አበባ በአማካይ ሁለት ልጆች ይወልዳሉ። ላለፉት 43 ዓመት የመንግስታችን የመሬት ፖሊሲ ህዝባችን ከገጥር እንዳይወጣ አድርጓል። ምክንያቱም አንድ ገበሬ ገጠርን ትቶ ወደ ከተማ መምጣት ከፈለገ መሬቱን መሸጥ ስለማይችል ከሞላ ጎደል ባዶ እጁን ወደ ከተመ መምጣት ስለሚሆንበት አያደርገውም። በዚህ ምክንያት 43 ዓመት በፊት የህዝባችን 85% የገጠር ነዋሪ ነበር አሁንም ወደ 80% የገጠር ነዋሪ ነው። የመሬት ፖሊሲው ባይኖር ይህ ቁጥር ዛሬ ምናልባት 60% ይሆን ነበር። እንደዚህ ቢሆን ኖር 80% ፋንታ 60% ነበር ስድስ ልግ የሚወልድው 20% ፋንታ 40% ሁለት ልግ ይወልዳል። በዚህ ምክንያት የጠቅላላ የህዝብ ቁጥር እድገት ይቀንስ ነበር።

2. ሀብት ምቾት ድሎት ከትመት (urbanization) በጠቅላላ ብልጽግና (development) በጨመረ ቁጥር የቤተሰብ መጠን ይቀንሳል። ይህ ንድፈ ሐሳብ (theory) ሳይሆን ያለፈው የ100 አመት የዓለም ታሪክ የመሰከረው እውነታ ነው። በሀገርም በህብረተሰብም ደረጃ ይህ እውነታ ይታያል። ሀብታም ሀገሮች ብዙ አይወልዱም ከነሱም የሚወልዱት ካልበለጸጉ ሀገሮች የመጡ መጤዎች ናቸው። ማንኛውም ሀገር አማካይ ሀብቱ በጨመረ ቁጥር የቤተሰብ መጠኑ ይቀንሳል። ስለዚህ በኢትዮጵያም «ብልጽግና» በጨመረ ቁጥር የሚወለደው ቁጥር ይቀንሳል። ስለዚህ አሁን እንቀንሰው ብሎ መርሯሯጥ አያስፈልግም።

3. የህዝብ ብዛት ሀብት ነው። የምዕራብ ሀገሮች ፍልሰትን (immigration) የሚጋብዙት ምክንያት የሰው እጥረት ስላላቸው ኤኮኖሚያቸው እየተጎዳ ስለሆነ ነው። የአዲስ አበባ ኤኮኖሚ የሚንርበት አንዱ ምክንያት ከገጠር ወደ ከተማ ያለው ፍልሰት ነው። የሰው ኃይልና የሸማች (consumer) ቁጥር በመጨመረ ቁጥር የኤኮኖሚ እንቅሳሴ ይጨምራል። በውጭ ግንኙነት አንጻርም ብዙ ህዝብ ያለው ሀገር በዓለም ላይ ያለው ኃይልና ሚና ይጨምራል። የኢትዮጵያ የዝብን ቁጥር በአባይ ግድብ ላይ ያለው ሚና ትንሽ አይደለም። ስለዚህ የህዝብ ብዛት እንደ እንቅፋት ብቻ መታየት የለበተም።

4. ኢትዮጵያ ገና ብዙ የህዝብ ቁጥር ማስተናገድ የምትችል ሀገር ናት። ካላት ለም መሬትና ሌሎች የተፈጥሮ ምንጮች አንጻር ምናልባት እስከ 200 ሚሊዮን ትችላለች። ጃፓን የኢትዮጵያ አራት እጥፍ ሰው በካሬ ኪሎሜትር አላት። ስለዚህ ኢትዮጵያ ትጨናነቃለች ብለን ልንሰጋ አይገባም።

ከዚህ አልፎ ተርፎ እንደ ኦርቶዶክስ ክርትያን የህዝብ ቁጥርን «መቆጣጠር» የሚባለው ነገር ያሳስበኛል። በተለይ የወሊድ መቆጣጠርን ማስፋፋት ያሳስበኛል። እንደዚህ አይነት ጉዳይ ውስጥ መግባት ትዕቢትን ነው የሚጋበዘው። እራሳችንን እንደ አምላክ እንድናይ ይፈትነናል። ከእግዚአብሔር የሰጠንን የተፈጥሮ ተልእኮ እንድንወጣ ይፈትነናል። ለዚህም ነው የሃይማኖት አባቶቻችን በሙሉ የቃወሙታ። ይህን መጠቀም ከሰው ተልእኮና ማንነት ይጋጫል ማጣት ነው ይላሉ። እርግጥ ካህናት በእረኝነት ሚናቸው በአንዳንድ አጋጣሚዎች የሃይማኖት ልጆቻቸውን እንዲጠቀሙ ሊፈቅዱ ይችላሉ ግን በጠቅላላ ከተቻለ አይመከርም። የስጋ ግንኙነትና መውለድ በተፈጥሮ የተገናኙ ናቸው ማለያየት ለሰው ልጅ ጎጂ ነውና።

ይህን እያወቅን የህዝብ ቁጥር እድገት እንዲቀንስ ተግባራዊ ስራዎች እናካሄድ ማለት ይከብደኛል። በተለይ በወሊድ መቆጣጠርያን በመጠቀም እንቀንስ ማለት ይከብደኛል። ለተጠቃሚው መንፈስ ጎጂ ነው ብዬ የማምነው ነገርን ማስፋፋት ህሊናዬ አይፈቅድልኝም። ሰዎች በገዛ ፍቃዳቸው ቢጠቀሙ ልፈርድባቸው አይገባም አልችልም «መብታቸው» ነው። ግን እንደ መንግስት መርህ ይህን ማስተዋወቅና ማስፋፋት ጎጂ ነው ብዬ ነው የማምነው። የቤተሰብ መጠንን ይቀንሳል ግን የመንፈሳዊ ጉዳቱ በምዕራቡ ዓለም የምናየው ኢትዮጵያ ውስጥ ማየት አልፈልግም። አዎ ዛሬ በሀገራችን በደምብ ተስፋፍቷል ግን መንግስት ከዚህ ጉዳይ እራሱን ቢያወጣ እወዳለሁ።

አልፎ ተርፎ ከላይ እንደጠቀስኩት በኔ እምነት የህዝብ ቁጥራችን አሳሳቢ ጉዳይም አይደለም። ክትመት ብልጽግና በጨመሩ ቁጥር የህዝብ ቁጥር እድገት ይቀንሳል። ቻይና ለ40 አመት ህዝቧ እንዳይወልዱ አድርጋ አሁን የህዝብ ቁጥራችን አንሶ አሳስቦናል ትላለች! እንማር!

ሀገራችን ገና «አልሞላችም»። ስለዚህ ትኩረታችንን ወደ ሌሎች የኤኮኖሚ የፖለቲካ የመሐበረሰብ ጉዳዮች ይሁን። እነዚህን ጉዳዮች በማሸነፍ የህዝብ ብዛት ጉዳያችንም በራሱ ይስተካከላል።