Showing posts with label ሃይማኖት. Show all posts
Showing posts with label ሃይማኖት. Show all posts

Friday, 8 June 2018

ሃይማኖታዊዋ ትግራይ እንዴት በፀረ ሃይማኖት ፓርቲ ትመራለች?

የትግዳይ ህዝብ ረዥም ታሪክ እንዳለው ወግ እና ትውፊቱን እንደሚወድ እንደሚአከብር ይታወቃል። ለምሳሌ ሃይማኖቶቻቸውን የሚአስቀድሙ እንደሚአጠብቁ ይነገራል ይታያል። በክብረ በአልም በዘውትር ጊዜም አክሱምን የጎበኘ ክርስቲያን ይህንን ሊመሰክር ይችላል። የህዝቡ አምልኮት ልዩ እና ጠንካራ መሆኑ ይታያል።

ታድያ እንደዚህ አይነቱ ህዝብ እንዴትቢሆን ነው በ ፀረ ሃይማኖት የሆነ የፖለቲካ ኃይል የሚገዛው እንዴት ይህን ኃይል ለዓመታት ከሌሎች ለይቶ ይደግፋል የሚለው ጥያቄ እንዴት ነው የማይጠየቀው። ፀረ ሃይማኖት ስል ከህወሓት አባላት መካከላማኞች የሉም ማለቴ ሳይሆን ግን የፓርቲው ርዕዮት ዓለም ፀረ ሃይማኖት መሆኑ ግልጽ ነው። አጀማመሩም እንደዚሁ ነው ዛሬም እንደዚህ ነው። አንድቀላል ምሳሌ ስለ ጎሰኝነት ያላቸው አመለካከት ቀትታ ከማርክሲዝም የመጣ ነው። የ «ጨቋኝ ተጨቋኝ» አመለካከታቸውም እንደዚሁም። እነዚህ «ከ ሃይማኖት ነፃ» የሆኑ አመለካከቶች ሳይሆኑ ፀረሃይማኖት ፀረ ትውፊት ናቸው።

እርግጥ ሃይማኖታዊ ትውፊት አክባሪ የሆነ ህብረተሰብ እንዴት በፀረ ሃይማኖት ወይም ሃይማ ኦት የለሽ ገዥ መደብ ወይም ልሂቃን ይመራል የሚለው ጥያቄ ትግራይን ብቻ ሳይሆን መላ ኢትዮጵያን ይመለከታል። ከኦርቶዶክስ ክርስቲያን አንፃር መልሱ ቀላል ነው፤ የህዝቡ የኛ ሐጢአት ነው ምክንያቱ። በጾቪዬት እስር ቤት የተሰቃዩት አለክሻንደር ሶልዠኒትሲን ከእስር ቤት ሆነው የጻፉትን እንደገና ልጥቀስ
ከእስርቤታችን አልጋ የሆነው የበሰበሰው ገለባ ላይ ጋደም ብዬ ነው ለመጀመርያ ከውስጤ የበጎ መንፈስ የተሰማኝ። ቀስ በቀስ መረዳት የጀመርኩት ይህ ነው፤ ጥሩና ክፉን የሚለየው መስመር በሀገሮች፤ መደቦች፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችም መካከል አይደለም የሚያልፈው፤ ይህ መስመር የሚያልፈው በያንዳንዱ የሰው ልብ መኻል ነው። መስመሩእድሜአችን በሙሉ ከውስጣችን ወደፊት ወደኋላ ይላል። በክፉ የተሞሉ ልቦችም ቢያንስ ቅንጣት ያህል ጥሩነት ይኖራል፤ ከሁሉም ጥሩ ከሚባለውም ልብ ከአንድ ጥጓ ትንሽ ክፉነት ይኖራል።
በየቦታው እየዞሩ ያሉ ክፉ ስራ የሚሰሩ ክፉ ሰዎች ቢኖሩና እነሱን ከኛ መለየትና ማጥፋት ብቻ ቢሆን ኖሮ እንዴት ቀላል ነበር? ግን ጥሩና ክፉን የሚለየው መስመር ከያንዳንዱ የሰው ልጅ ልብ መካከል ነው የሚያልፈውና ማን አለ ከራሱ ልብ ቁራጭ ቆርጦ ለማጥፋት ፈቃደኛ ይሆነ?
እያንዳንዶቻችን ልብ ውስጥ ያለው ክፋት ተጠራቅሞ ነው በመሪዎቻችን ላይ የሚታየው።

ሆኖም አሁን የህወሓት ስልጣን በሚገባው እየመነመነ ስለሆነ የትቭራይ ህዝብ ስለማንነታቸው ስለ ሃይማኖት እና ትውፊታቸው ስለ ፀረ ሃይማኖት መሪዎቻቸው እራሳቸውን ለመመርመር ጥሩ ጊዜ ይመስለኛል። የትግራይ ህዝብ በመጀመርያ ኮሙዩ ኢስት ነው ወይንም ሃይማኖተኛ። ልጎቹ ሃይማኖት የለሽ ገንዘብ እና ስልጣን አምላኪዎች ሆነው እንዲያድጉ ነው የሚፈልጉት? መሪዎቻቸው እየወደቈየተነሱምቢሆን ሃይማኖታዊ ቢሆኗይሻልም ወይ። ይህ ነው ወይም ካርል ማርክስ ወዘተ ነው የ ትግራይ ትውፊት? እነዚህን ጥያቄዎችን ለመጠየቅ ትክክለኛው ጊዜ ይመስለኛል።

እኔ በትክክሉ ይር ትግራይ ሰው ባልሆንም እንደ ኢትዮጵያዊነቴ ይበልጥ እንደ ኦርቶዶክስ ክርስቲያን መሆኔ ይህ ጉዳይ የ ኤርትራም ተመሳሳይ በማርክሲስት ሻብያ መገዛቱ ጉዳይ እጅግ ያሳዝነኛል። እነዚህ ቦታዎች ለክርስትናችን ቁልፍ ምናልባትም ምንጭ ቦታዎች ናቸው። እንዴት ሐጢአተኞች ብንሆን ነው ወደ ፀረ ሃይማኖታዊ አገዛዝ የሸጥናቸው። እግዚአብሔር ይቅር ይበለን።

Wednesday, 21 March 2018

«ሴኩላሪዝም»

ትንሽ አመታት በፊት አንድ የመንግስት ስራተኛ የሆነ ዘመዴ የኦርቶዶክስ መዝሙር ከመስሪያቤት ኮምፕዩተሩ ላይ ማዳመጥ ክልክል እንደተደረገ ነገረኝ። ለምን ብዬ ስጠይቀው ክርስትያኑም ሙስሊሙም የሚፈልገውን መዝሙር፤ ስብከት፤ ትምሕርት እያዳመጠ እና ኮምፕዩተሩ ላይ ሥዕል እየለጠፈ የሰራተኞች እርስ በርስ ግጭት ሊፈጥር ይችላል ተብሎ ተከለከለ አለኝ። የሚገርመው ነገር ግን 1) ከመስሪያቤቱ እንደዚህ አይነት ግጭቶች አልነበሩም እና 2) ክልከላው በተራ ትዛዝ ሳይሆን ከከፍ ያለ የአስተዳደር ደረጃ በመመርያ ምልክ የተላለፈ ነበር። የመመርያው ርዕስ ደግሞ «ሴኩላሪዝም» ነበር።

ይህን ታሪክ ስሰማ እጅግ አዘንኩኝ። መቼ ነው መንግስቶቻችን፤ ምሁሮቻችን እና ልሂቆቻችን የምዕራብ ዓለም ርዕዮት ዓለምና ፍልስፍና ይዘው አገራችን ላይ መጫን የሚያቆሙት? ካለፉት የ100 ዓመታት ታሪካችን አይማሩምን?

እስቲ «ሴኩላሪዝም» ባጭሩ ምን እንደሆነ እንመልከት። «ሴኩላሪዝም በዓለማችን እግዚአብሔር የለም/አይሳተፍም ብሎ ማሰብ ነው»። ሴኩላሪዝም እግዚህብሔር ሊኖር ላይኖርም ይችላል ግን ከዓለማችን ከሕይወታችን ከለት ኑሮአችንም አይሳተፍም የሚለው አመለካከት ነው። እግዚአብሔር ካለ እዛው ከዙፋኑ ወይንም ገነቱ ተቀምጦ ይመለከተናል። በሃይማኖት እና በእግዚአብሔር በግል ምርጫችን ልናምንባቸው የምንችል የእምነት ሥርዓቶች ናቸው። በሀሳብ ደረጃ ነው የምናምንባቸው ካላሰኘን ደግሞ ከሀሳባችን እናስወግዳቸዋለን!

ይህ አስተሳሰብ በተለያየ መንገድ ወደ ክርስትያን የሆነውን አስተሳሰብ ገብቷል። «ዓለማዊ» እና «መንፋሳዊ» የምንላቸው ቃላት በተሳሳተ መንገድ እንጠቀማለን። ዓለማዊ ስንል ስራችን፤ ትምሕርታችን፤ ገበያችን፤ ንግዳችን ወዘተ ነው። እግዚአብሔር እነዚ ነገሮች ውስጥ እንዳለ አናምንም። ስለዚህም ነው በነዚህ የህይወት ዘርፎቻችን ኢ-ክርስትያናዊ ነገሮች እያደረግን እያለን አማኞች ነን የምንለው። እሁድ እሁድ ግን ቤተ ክርስትያን ሄደን ወደ መንፈሳዊስ ዓለም እንሸጋገራለን። እዛ ጨዋ ነን፤ ጥሩ ስነ መግባር አለን፤ ጭንቀቶቻችንን አስተንፍሰን ወደ ዓለማችን እንመለሳለን።

ይህ ግን የውሸት ክርስትና ነው። በእምነታችን እግዚአብሔር በሁሉም ቦታ በሁሉም ነገር አለ። «እኔ የቅርብ አምላክ ነኝ እንጂ የሩቅ አምላክ አይደለሁም። ሰው በስውር ቢሸሸግ፥ እኔ አላየውምን? ሰማይንና ምድርንስ የሞላሁ እኔ አይደለሁምን? ይላል እግዚአብሔር።» ኤር 23:23-24።

ስለዚህ ትምሕርት ቤት ብሄድ፤ መስሪያ ቦታ ብሄድ፤ እርሻዬ ላይ ብሆን፤ ትራንስፖርት ላይ ብሆን፤ መጠጥ ቤት ብሄድ፤ በሁሉም ቦታ እግዚአብሔር አለ። ሕይወታችንን እግዚአብሔር ያለበትና የሌለበት ብለን ልንከፋፍለው አንችልም። በሁሉም ቦታ በሁሉ ደቂቃ ከኛ ጋር ነውና።

ይህ የሚያሳየን የሰው ልጅ ክርስትያንም ሴኩላሪስትም አብሮ ሊሆን አይችልም። ብዙዎቻችን ወደዚህ ስህተት ብንገባም ሊሆን የማይችል ነገር ነው። ለክርስትያኖች እግዚአብሔር ልኬት የለውምና። በተጨማሪ ሴኩላሪዝም እግዚአብሔርን ከለት ኑሮአችን ማጥፋት ስለሚፈልግ የክርስትና ተቃራኒ ብቻ ሳይሆን ጠላት እንደሆነ ግልጽ ነው።

«እናንተ ኦርቶዶክሶች፤ ሙስሊሞች፤ ፕሮቴስታንቶች አብሮ መኖር አትችሉም። ስለዚህም (እግዚአብሔራን ተክቼ!) ከላያችሁ ሆኜ አስተዳድራችኋለሁ» ይላል ሴኩላሪዝም / ሴኩላሪስቱ። «እኔ ነኝ ስልጡኑ፤ ከማንም ጋር የማልጋጨው፤ ከሁሉም ጋር የምግባባው፤ ሁሉንም የማከብረው» ይላል። እውነቱ ግን ሴኩላሪስቱ እንደዚህ ሲል ሁሉንም በሰላም ለመጠበቅ ሳይሆን አላማው ይህን አስመስሎ «እግዚአብሔር የለም» የሚባለውን ሃይማኖትን ለማስፋፋት ነው። እግዚአብሔር ከአዕምሮአችን ብቻ ነው ያለው እንጂ ከስራ ቦታችን፤ ገበያ ቦታችን፤ መንገዶቻችን፤ ሚዲያዎቻችን፤ ከለት ኑሮአችን የለም ብለን ካመንን ቀጥሎ እግዚአብሔር የትም የለም ማለት የሚቀጥለው ቀላል እርምጃ ነውና!

በተጨማሪ እግዚአብሔር ከለት ኑሮአችን ከሌለ የማህበረሰብ የአገራችን ድንጋጌዎች ከየት ሊመጡ ነው? ከሴኩላሪዝም ርዕዮት ዓለም ከ«እግዚአብሔር የለም» ሃይማኖት ሊመጡ ነው! አያችሁ ሴኩላሪዝም እራሱን ገለልተኛ አድርጎ እንዴት «እግዚአብሔር የለም» ሃይማኖትን ሰተት ብሎ እንደሚያሰፍን።

ኢትዮጵያ የሃይማኖት አገር ናት። ታሪካችን ትውፊታችን ከዚህ የተያያዘ ነው። ማንነታችን ይህ ነው። ሴኩላሪዝም ደግሞ የህን አፍርሶ «እግዚአብሔር የለም» ሃይማኖትን ነው ማስፈን የሚፈልገው። ይህ ሂደት እንዴት እንደሚሰራ ለማወቅ የምዕራብ ዓለሙን ያለፈውን 400 መቶ ዓመት ታሪክ መመልከት ነው። ስለዚህ ሴኩላሪዝም ኢ-ኢትይጵያዊ እንደሆነ ተረድተን ወደ አገራችን ሰተት ብሎ እንዳይገባ መጠንቀቅ አለብን። በተለይ ደግሞ ወደ ልባችን ሰተት ብሎ እንዳይገባ መጠንቀቅ አለብን።