Monday 16 April 2018

ለራሳችን ክብር የሌለን አልቃሾችና ለማኞች ነንን?

አንድ አመት በፊት ስለ ኢህአዴግ ማልቀስ አቁመን ወደ ተግባር እንግባ የሚል ጽሁፍ ጽፌ ነበር። ይቅርታ አድርጉልኝና ያንን መልዕክት በጠንከር ያለ ቋንቋ ልድገመው።

ላለፉት 27 ዓመታት እኛ «ተቃዋሚዎች» «የኢትዮጵያ ወዳጆች» «የኢትዮጵያ ብሄርተኞች» «ፍትህና ዴሞክራሲ ፈላጊዎች» ስለ ኢህአዴግ ወይንም ስለ ህወሓት እንደ ህፃኖች ስናለቅስ ስናማርር ለፈረንጆች አቤቱታ ስናቀርብ ቆይተናል። ውርደት አይደለምን? አናፍርም እንዴ? በአንድ ጎን ህወሓት የሀገሪቷን 6% ነው የሚወክለው እንላለን። ህዝቡ አይፈልጋቸውም እንላለን። ብሌላ ጎን ደግሞ በጠመንጃቸው፤ ማሰቃያቸው፤ ይሉኝታቢስ እነታቸው፤ ጉብዝናቸው፤ ብልጠታቸው፤ የውጭ ድጋፋቸው ወዘተ ምክንያት ይገዙናል እንላለን። አይገርምም 6% የሆነው ይህን ሁል መቻሉ 90% የሆነው እንደ ጅል መመልከቱ?

እስቲ አንዴና ለመጨረሻ እንወስን፤ ህወሓት 6% ወይንም ከነ አደርባዮቻቸው 10% በቻ ድጋፍ ነው ያላቸው? መልሳቸን «አይደለም» ከዛ በላይ በርከት ያለ ድጋፍ አላቸው ከሆነ ኢህአዴግ ብዙ ደጋፊ አለው ማለት ነው። ስለዚህ ኢህአዴግ የጥቂቶች መንግስት ነው ዴሞክራሲ የለም ወዘተ ማለት አንችልም። ግን በዚ አብዛኞቻችን የምንስማማ አይመስለኝም። በተለይ ሌት ከቀን ስለ ህወሓት ለምናለቅሰው በዚህ አንስማማም።

ስለዚ ለጥያቄው መልሳችን «አዎን ኢህአዴግ የትንሽ ሰው ድጋፍ ምናልባትም የትግሬ ብቻ ድጋፍ ነው አለው» ነው የሚሆነው። እንደዚህ ከሆነ ግን ለ27 ዓመታት በጥቂት ሰዎች ነው የምንገዛው ወደ ማለት ያስኬደናል! 10%ው 90%ውን ለ27 ዓመታት ገዝቷል! እንዴት ነው 10%ው 90%ውን የሚገዛው ካልን ደግሞ መልሱ አንድ ብቻ ነው። እጅግ አናሳ (minority) የሆነ ቡድን ብዙሃንን (majority) መግዛት የሚችለው በአናሳው ጥንካሬ ሳይሆን በብዙሃኑ ፈቃደኝነት ነው። ልድገመው፤ በብዙሃኑ ፈቃደኝነት ነው። ስለ 40%ው 60%ውን መግዛት አይደለም የምናወራው። ስለ 30%ው 70%ውን መግዛት አይደለም የምናወራው። 10%ው 90%ውን ገዝቷል። ያውም በመደብ በርዕዮት ዓለም ሳይሆን በጎሳ። የጎሳ አገዛዝ ብዙሃኑን ይበልጥ ሊያስነሳው ይገባ ነበር። አለመነሳቱ እንደ ፈቃድ ይቆጠር።

ስለዚህ ህወሓት ኢትዮጵያን ገዝታለች ካልን የማን ጥፋት ነው፤ የ10% የሆኑት «ገዥዎች» ወይንም 90% የሆኑት «ተገዦች»? ምን ጥያቄ አለው፤ ሃላፊነቱም መፍትሄውም ሙሉ በሙሉ የ90% የሆነው ብዙሃኑ ነው። ግን እኛ «ተቃዋሚዎች» ሙሉ በሙሉ አቅማችንን፤ ግዜያችንን፤ ወሬአችንንና ገንዘባችንን በአሳፋሪ መልኩ ስለ10% የሆኑት ስናለቅስ ነው የምናጠፋው። የችግሩ ምንጭና የመፍትሄው ምንጭ የሆነው ብዙሃን የሆንነው «ተቃዋሚ ጎራ» ላይ በሚገባው ከመስራት ፋንታ ችግሩ ባልሆነው ለመፍትሄ ዝግጁ ባልሆነው ላይ «እንሰራለን»። ያሳዝናል፤ ያሳፍራል፤ ለምን ለ27 ዓመታት ለውጥ እንዳልመጣ በትክክሉ ያስረዳል።

እሺ አሁን እውነታው ከተገለጸልን እንዴት ነው ወደ ፊት መራመድ ያለብን የሚለውን እንዳስስ። የመጀመርያው የችግር መፍትሄ ችግር እንዳለ ማወቅና ማመን ነው። ህወሓት ስልጣን የያዘው አልፎ ተርፎ ህወሓት/ሻእብያ ኢትዮጵያን ከደርግ በኋላ የተቆጣጠሩት በኛ ጥፋት ነው። የሌላ የማንም ጥፋት አይደለም። በመጀመርያ ደረጃ እንደ ኮሙኒዝም አይነቱ የማይሆን የምዕራብ ፍልስፍና አስተማርናቸው። ከዛ ቀጥሎ እኛ አንዴ አድሃሪ፤ ኢህአፓ፤ ምኤሶን፤ ኢዲዩ፤ ደርግ ወዘተ ስንባባል ስንገዳደል ነው እነዚህ በመሃል ገብተው ባዶ የሆነውን የምንግስትን ጎራ የተቆጣጠሩት። ከዛም በኋላ ህወሓት ሀገራችንን አጥበቃ የተቆጣጠረው እኛ «ተቃዋሚዎች» ከነ ፓርቲዎቻችን፤ ድርጅቶቻችን፤ ጋዜጦቻችን፤ ሚዲያዎቻችን ተባብረን መንቀሳቀስ ስላልቻልን ነው።

የህወሓት ጉብዝና፤ ብልጠት፤ «ወርቃማነት» አይደለም የግዛት ዘመናቸውን ለ27 ዓመታት እንዲቀጥል ያደረገው። አባቶቻችን ትውፊታችን በራሳችን እንድንተማመን በሚገባው እንድንኮራ ነው ያሳደጉን። እንደ አንድ ኩሩ ኢትዮጵያዊ 10% ድጋፍ ያለው ህወሓት በጉብዝና ሌሎቻችንን ያሽከረክራል ማለት በፍፁም አልችልም። አልችልም ብቻ ሳይሆን እውነትም አይደለም።

በተዘዋዋሪ ሰዎቻችን የህወሓትን አገዛዝ «አፓርታይድ» (apartheid) ሲሉ እጅግ አፍራለው። የደቡብ አፍሪካ ነጮች በ ትምሕርት፤ እውቀት፤ የአገዛዝ ስልት ወዘተ ከጥቁሮቹ እጅግ የተለዩ ነበሩ። በደቡብ አፍሪካ ነጮችና ጥቁሮች ያለው አይነት ልዩነት ነው በህወሓት ደጋፊዎችና በሌሎቻን ያለው ብሎ የሚያምን አለ? አለ? ይቅርጣ አድሩጉልኝ ግን እንደዚህ የሚያምን በኢትዮጵያዊነቱ የማያምን የማይኮራ የበታችነት ስሜት ያለው ነው። ተሳስቻለሁ?

ወደ ዋናው ነጥብ ልመለስና ምን ያህል ያለንበት ሁኔታ እራሳችን የፈጠርነው እንደሆነ ለማየት እስቲ በመንግስት አስተዳደራችን ማን ማን እንዳለ እንመልከት። በየ መንግስት መስርያቤት ከቁልፍ ቦታዎች በቀር በጣም አብዛኛው የስራ ቦታ በትግሬ ያልሆኑ ነው የተቆጣጠረው። አስቡት 6% ሆነው በየቦታ መሆን አይችሉም። በርካታ ትግሬዎች ደግሞ መንግስት ከመስራት ንግድ ዓለሙን ይፈልጉታል። ስለዚህ መንግስታችን በአብዛኛው በሌሎቻችን ነው የሚስተዳደረው። ጦር ሰራዊቱም ከመሪዎቹ በቀር በኦሮሞ፤ አማራና ደቡብ ነው የተሞላው። አዛዡ ትግሬ ቢሆንም መሳርያው ከሌላው እጅ ነው! ይህ ሆኖ በምን ተአምር ነው በህወሓት ደጋፊዎች ወይም «ትግሬዎች» ነው የተገዛነው የሚባለው?!

ይህን ሁሉ የምለው እኛ 90% የሆንነው ብዙሃኑ ነው ኢህአዴግ መንግስት ሆነው ለ27 ዓመታት እንዲቆዩ ያደረግነው። እኛ «ተቃዋሚዎች» የራሳችንን ጎራ ማስተካከል ስላልቻልን ነው። እንኳን መተባበር ጭራሽ በደምብን መነጋገር ስላልቻልን ነው። የፖለቲካ ብስለት ስለሌለን ነው። እንደ ልሂቃን ባለፉት 50 ዓመታት እርስ በርስ ተገዳድለን ሀገሪቷን አቢዮት በአቢዮት አድርገን ፈራርሰን ገና ስላዳንን ነው።

ለዚህ አባባሌ መልስ ሊኖራችሁ ይሆናል። የኢህአዴግ ጭቆና ነው «ተቃዋሚ» ጎራውን ያደከመው ትሉ ይሆናል። እረ። ኢህአዴግ ነው ዲያስፖራው ድርስ መጥቶ ተቃዋሚው እርስ በርስ እንዲጣላ ያደረገው?! ተአምርተኞች ናቸው! በነፃነትና ምንም እግዳ በሌለባቸው ሀገሮች ተቃዋሚው ላለፉት 27 ዓመት በሚገባን ደረጃ መደራጀት አልቻልንም ማለት ይቻላል። ተለይም ተቃዋሚው የ90% ህብረተሰቡ ድጋፍ አለው ካልን የተቃዋሚው ውጤት ከዜሮ በታች ነው ማለት ማጋነን አይደለም። ዛሬ ከ27 ዓመት በኋላ የተቃዋሚው ሁኔታ ጭራሽ ብሶበት ነው የሚገኘው። ምናልባት ከ ኢሳት፤ ግንቦት 7፤ አሁን ደግሞ ቄሮ በቀር ትንሽም ሚና መጫወት የሚችል ስብስብ ወይንም ድርጅት የለም። ቄሮ ተሽሎ ቢገኝም የነዚህም ድርጅቶች አቅም እጅግ ትንሽ ነው። አልፎ ተርፎ ስለ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የውስጥ መረጃ ያላችሁ የኢህአዴግ ሚን ሳይሆን የተቃዋሚዎች ሚና ነው በእርስ በርስ አለመስማማታቸው በርካታውንአስተዋጾ ያደረገው።

እና ይህ የተቃሚው ጎራ በተለይ የተቃዋሚ ልሂቃኑ ድክመት ነው ኢህአዴግን ለ27 ዓመት በስልጣን ያዋለው ማለት ይቻላል። እንደዚህ ከሆነ ለውጥ የምንፈልገው ገንዘባችንን፤ ንግግራችንን፤ ጊዜያችንን፤ ጠቅላላ አቅማችንን በህወሓት ላይ በማልቀስ ነው ማዋል ያለብን ወይንም የራሳችንን ጎራ በማስተካከልና በማጠንከር ነው? ጥያቄ የለውም፤ ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ ስለኢህአዴግ በማልቀስ ያጠፋነውን ግማሽ ጊዜ እኛ ላይ በመስራት አውለን ቢሆን ኖሮ እስካሁን ጠንክረን ለውጥ አምጥተን ነበር።

እሺ፤ አቅማችንን በመገንባት እና እራሳችንን በማጠንከር ላይ ማጥፋት አለብን ስል ምን ማለት ነው። መደራጀት አለብን። አንዳንዴ እኛ ኢትዮጵያዊያን ተቃዎሚዎች ምን እያስበን እንደሆነ ግራ ይገባኛል። በሌሎች በአምባገነን መንግስት የሚመሩ ሀገሮች «ተቃዋሚ» የሚባለው ጎራ ድርጅት ወይንም ድርጅቶች፤ ገንዘብ፤ አቅም፤ ሚዲያ ወዘተ አለው። በዓመት በሚሊዮኖች የሚቆጠር በጀት ያላቸው ማለት ነው። እኛ ግን ከዚህ አንጻር ምንም የለንም። ስለተከፋፈልን ብቻ አይደልም። «አንድ ጎራ ነን አንድ አቋም ዓለን» የምንለውም አልተደራጀንም። እርስ በርስ እንፋጃለን። መነጋገርም ያቅተናል። ይህን ለማስተካከል ወይይት ያስፈልጋል። አንድ ሁለት ስብሰባ ሳይሆን ለወራት ለዓመታት የሚዘልቁ ተከታታይና ውጤታማ ውይይቶች። እንደዚህ ከባድ ስራ ነው የመደራጀት ሂደት። የግለሰብም የቡድንም አቅም መገንበት (capacity building) ያስፈልገናል። በተለይ በታላቅ እንቅፋት የሆነን ቅራኔ መፍታት (conflict resolution) ድክመታችን ላይ ብዙ መስራት አለብን። የፖለቲካ ስልታችንን ማዳበር አለብን። ብዙ ስራ ነው። ብዙ ብቻ ሳይሆን ለለውጥ ቅድመ ሁኔታ የሆነ ስራ ነው።

አይ ይህን ከባድ ስራ ከምንሰራ ስለ ህወሓት ማልቀስ ይሻለናል። ስለ ህወሓት ክፉነት በቂ ከዘፈንን ህዝቡ ተነሳስቶ መንግስትን ይገለብጣል ትሉ ይሆናል። የዚህ አይነት አመለካከት ምን ለበለው? በመጀመርያ ለ27 ዓመታት ያልሰራ አስተሳሰብ ነው። መቼም አንድ ነገር ደጋግመህ አድርገሀው ካልሰራ መቀጠሉ ሞኝነት ነው። ሁለተኛ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ የህወሓትን ክፋት በቂ አያውቀውም ማለታችን ነው?! እንደዚህ ካልን ደግሞ ህዝቡ ወይ ደደብ ነው ወይንም የህወሓት ከፋት እስከዚህም ነው ማለት ነው! ግን እንደዚህ የምናስብ አይመስለኝም። ህዝባችን ስለ ሀውሓት አገዛዝ ችግር ብበቂ ሁኔታ ይገበዋል ብቻ ሳይሆን ይኖረዋል። የሚያውቀውን ከምንደግምለት መፍትሄ ሀሳቦች ብንሰጠው ይመረጣል።

እዚህ ላይ ለመናዘዝ ያህል እኔም እንደዚሁ ስለኢህአዴግ የማማርር አልቃሽ እንደነበርኩኝ ልንገራችሁ። ከቅንጅት ምርጫ በፊት በየ ውጭ ሀገር መንግስታትና መሪዎች ቢሮ እየዞሩ «ወደ ምርጫችን ታዛቢ ላኩ» ከዛ «መንግስታችንን የሚቃወም መግለጫ ስጡ» ከዛ «መአቀብ አድርጉ» ከሚሉት አንዱ ነበርኩኝ። ግን የቅንጅት መፈራረስ እራሴን ጥያቄዎች እንድጠይቅ አደረገኝ። ችግራችን ኢህአዴግና የውጭ መንግስታት ሳይሆኑ እኛ ተቃዋሚዎች እንደሆንን ገባኝ። ኢህአዴግ በስልጣን ላይ የቆየው በብልጠቱም በውጭ መንግስታት ድጋፍም ሳይሆን በመጀመርያ ደረጃ በኛ በተቃዋሚዎች ድክመት ነው የሚለውን ድምዳሜ ላይ ደረስኩኝ።

የውጭ ሀገር መንግስታትም ኤንጂኦችም ግለሰቦችም ስለ ኢትዮጵያ ሁኔታ ላለመጠየቅ ላለማነጋገር ወሰንኩኝ። እራሳችንን የማንችል እንደ በታቾች እንደሚያዩን ተገነዘብኩኝ እነሱ ጋር መሄድ እንደ ውርደት መሆኑ ተሰማኝ። በተለያዩ ምክንያቶች የነዚህ ፍልጋት ከኢትዮጵያውያን ፍላጎት የሚጻረር እንደሆነ ተረዳሁኝ። እነዚህ ሁሉም ለጥቅም ይህን ወይንም ለርእዮተ ዓለም ኢትዮጵያ እነሱ እንደሚፈልጉት እንድትሆን ነው የሚፈልጉት። እራሳችንን እንዳንችል ነው የሚፈልጉት። በአዲሱ ቅኝ ግዛት እንዲቆጣጠሩን ነው የሚፈልጉት እራሳቸውን እንደ ኝጹሃን አድርገው ቢያቀርቡም። እነሱን በኢትዮጵያ ጎዳይ ውስጥ ማስገባት ማንነትን መሸጥና እዳ መፍጠር ነው። ለኢትዮጵያ ትክክለኛው መፍትሄ ከራሷ ህዝብ ነው የሚመጣው የሚለውን ድምዳሜ ላይ ደረስኩኝ ዞር ብዬ የውጭ ሀገር ሰው ስለ ኢትዮጵያ አላናግርም አልኩኝ።

ስለዚህ ስለህወሓት ማልቀስ ስለውጭ ሀገራትን መለመን አውቀዋለሁ እና ከንቱ ነው ብዬ ነው ያማምነው። ደግሞ ከላይ እንደጠቀስኩት የ27 ዓመት ልምዳችን እንዳማይሰራ አሳይቶናል! ከዚህ በላይ መረጃ አያስፈልገንም።

የዚህ ጽሁፍ አርስት «ክብር» የሚለውን ቃል ይጠቅሳል። ስለእውነት ያቀፈ ክብር ነው የማወራው እንጂ ስለ በባዶ ቤት መኮፈስ አይደለም። በባህላችን ክብር ትልቅ ነገር ነው። አንዱ የክብር ማሳያ እራስን ከሌሎች እኩል አድርጎ ማየትና የበታችነት ስሜት አለመኖር ነው። እኛ «ተቃዋሚዎች» 90% ህዝባችንን «ወክለን» ስለ 10% የሆነውን ህወሓት ማልቀስ ሀወሓቶች ከኛ የሚበልጡ ፍጡሮች ናቸው ማለት ነው። ለራሳችን ክብር ካለን እንደዚህ ማለት የለብንም። ውርደት ነው። በሁለተኛ ደረጃ የሀገራችንን ችግር እንዲፈቱልን የውጭ ሀገር ሰዎችን መለመንም እንደ ውርደት ማየት ይቻላል። አዎን እንደ ስልት ብቻ ልናየው እንችላለን ግን ለወደፊት አደገኛ ሊሆን ይችላል። የኛ በተለይ የምሁራኖቻችን ጭንቅላት ለ60 ዓመት በምዕራብ ዓለም ፍልስፍና እየተገዛ ነውና ካልተጠነቀቅን ሳናውቀው የአዲሱ የቅኝ ተገዢዎች (የአእምሮ ቅኝ ግዛት) ልንሆን እንችላለን። ስለዚህ ክብራችንን ጠብቀን የችግራችን ዋና ምክንያትን ማለት እራሳችንን እንዋጋ እናስተካክል

በራስን ማክበር ዙርያ ሌላ ነገር ልጠቅስ እወዳለሁ። ህወሓት፤ ሻእብያ፤ ኢህአዴግ ሁሉም እኛ «ኢትዮጵያዊ ነን» የምንለው የወለድናቸው ድርጅቶች ናቸው ማለት እውነትም ነው ክብራችንን የሚጠብቅ አባባል ነው። ከ«ውጭ» መጥተው ወረሩን ከሆነ እራሳችንን እንደ የውጭ ኃይል ተሻናፊ እንቆጥራለን። ግን በኛ ድክመት ከኛ ነው የመነጩት ማለት ችግሩን ይኛ አደረግነው ማለት ነው መፍሄውንም የኛ ሆነ ማለት ነው። ይህ የሚያጎለብት (empower) አስተሳሰብ ነው ወደ መፍትሄ የሚያደርሰን አስተሳሰብ ነው።

ጽሁፉ ረዘመ! ለማጠቃለል ህወሓት እኛ በስተታችን የፈጠርነው ልጅ ነው። ህወሓት በስልጣን የቆየው የሚቆየውም በኛ ፈቃድና ድክመት ነው እንጂ በራሱ የተለየ ብልጠትና «ጉብዝና» አይደለም። የኛ ድክመት ለ50 ዓመታት ልሂቃኖቻችን እርስ በርስ በመፋጀት እራሳቸውን ስላጠፉ ነው። በዚህ ድክመታችን አትኩረን ከሰራን እና እራሳችንን ካሸነፍን ለሀገራችን የሚበጅ የፖለቲካ ለውጥ በቀላሉ ይመጣል።


No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!