Wednesday 11 April 2018

የኢትዮጵያ ፖለቲካ እውነቶች (እንደሚመስለኝ)

እስቲ በነዚህ እውነታ የሚመስሉኝን ነጥቦች ዙርያ እነወያይ፤

1. ድሮ የነበረን የልሂቃን (elite) እራሱን አጠፋ። በኃይለ ሥላሴ መንግስት የነበረው ልሂቃን በአብዮት ምክንያት ተባረረ ተገደለ ተበታተነ። የኃይለ ሥላሴ ልጆች  የሆኑት አብዮቱን የመሩት አዲስ ልሂቃን በአብዮቱ ዘመን እርስ በርስ ተፋጅተው ተላለቁ። የተረፈው የደርግ ልሂቃን በደካማ ርዕዮት ዓለም እና አስተዳደር በተጨማሪ በዓለም ፖለቲካ ክስተቶች ምክንያት ፈራረሰ። ሻእብያ ህወሓትና ኦነግ ኢትዮጵያን ሲቆጣጠሯት የበፊቱ የልሂቃን በተለይ በሀገር ብሄርተኝነት (የጎሳ ብሄርተኝነት ተቃራኒ) የሚያምነው የልሂቃን ቡድን ጠፍቶ ነበር። ኢትዮጵያ የቀራት አቅም (capacity) ያለው ልሂቃን ጎሰኛ ወይም የጎሳ ብሄርተኛ ጎራው ብቻ ነበር። እስካሁን የሀገር ብሄርተኛ ልሂቃኑ ከነበረው ጉዳት በቂ አላገገመም።

2. የዚህ የልሂቃን ቡድን መፍረስ ያለፉት 27 ዓመት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሁኔታ ላይ ከምናስበው በላይ ከባድ አስተዋጾ አድርጓል። በበፊቱ ልሂቃን ቡድን መፍረስ ምክንያት ነው ለ27 አመት የ«ተቃዋሚ» ጎራው ደካማ ሆኖ የቀረው። ተቃዋሚዎች ነፃነት ባለበት በውጭ ሀገርም መደራጀት ያልቻሉበት ምክንያት ልሂቃኑ ስለፈረሰ በቂ የልምድ የሰው ኃይል የመደራጀት ልምድ የታሪቅ ምሶሶ እና የተመሳሰሉት የልሂቃን ውጤቶች ስለሌለው ነው። በዚህ ምክንያት ነው ቢያንስ 70% እስከ 90% ከብዙሃኑ ድጋፍ ማግኘት የሚገባው ተቃዋሚ ለ27 ዓመት ብዙ ማድረግ ያልቻለው። ለተቃዋሚ ድክመት ሌላው የሚሰጠው ምክንያት የኢህአዴግ ጫና ከዚህ አንጻር እንደ ዋና ምክንያት ሊቆጠር አይችልም።

3. በሀገር ውስጥም በሀገር ውችም ያለው የተቃዋሚ ድክመት ምክንያት  የፖለቲካ ለውጥ ከተቃዋሚ ፓርቲና ቡድኖች ሳይሆን ከብዙሃኑና ከኢህአዴግ ውስጥ ነው እየመጣ ያለው። (ተቃዋሚዎች ምንም ሚና አልተጫወቱም ለማለት ሳይሆን ከሚገባው አነስተኛ ሚና ነው የተጫወቱት አቅማቸው ውስን ስለሆነ።) እንደሚታየው የቅርብ ዓመታቱ የህዝብ ተቃውሞ የልሂቃን ማበረታጭያና ድጋፍ በጣም ያንሰዋል። ይህ የልሂቃን ወይም የመሪ እጥረት እጅግ አሳሳቢ ነው።

4. «አዲሱ ትውልድ መሪዎችን አልፎ ትቶ ሄዷል» ሲባል እውነት አይመስለኝም ነበር። ግን የዛሬው ትውልድ «ፖለቲካ ኮሬንቲ ነው» የሚባለውን አልፏል አባባሉንም ጭራሽ አያውቀውም። ኢህአዴግ ለ27 ዓመት ሳይቀየር የገዛበት አንዱ ምክንያት የበፊቱ ትውልድ ባለፉት አብዮቶች ተማሮ ተቃጥሎ በፖለቲካ ነክ ጉዳዮች በሚገባው መጠን ስላልተሳተፈ ነው። አሁን ግን ያ ዘመን አልፎ አዲሱ ተውልድ ለመሳተፍ ፍርሃት የለውም። አንዴ በእጽ በኳስ በገንዘብ ወዘተ ቢደነዝዝም ፖለቲካ ውስጥ እየተሳተፈ ነው። ነገር ግን አባት አያት አስተማሪ መሪ ታሪክ ትውፊት ይጎለዋል የበፊቱ ትውልድና ልሂቃን ስላላወረሰው።

5. ከውጭ ሀገር ሆኖ የፖለቲካ ወይም ማህበረሰባዊ ንቅናቄ ቡድን ድርጅት ፓርቲ አቋቁሞ መተጋል እስካሁን ውጤታማ አልሆነም ማለት ይቻላል። ወይንም አነስተኛ ውጤት ነው ያፈራው። ሰዎች እየሞከሩ አይደለም ማለት አይደለም። ከድሮ ጀምሮ እስካሁን እንደነ ኢሳት አይነት ትልቅ ሙከራዎችና ስኬቶች አሉ። ግን ከላይ እንደጠቀስኩት ኢህአዴግ የ10% ደጋፍ ድርጅት ነው ካልን እነዚህ ስኬቶች ከሚገባው እጅግ አነስተኛ ናቸው። ስለዚህ ይህ የውጭ ድርግታዊ ትግል አስፈላጊ ነው ቢባልም ዋናው ውጤታማው ትግል አይደለም።

6. ሀገር ውስጥ ያለ የይፋ ተቃውሞ በግለሰብ በቡድን በድርጅት በፓርቲም ይሁን ለ27 ዓመት በሁለት ምክንያቶች ደካማ ሆኖ ተገኝቷል። ከላይ እንደጠቀስኩት ዋናው ምክንያት የልሂቃን እጥረት ተቃዋሚዎች የመተባበር የአብሮ መስራት የቅራኔ መፍታት የመደራጀት ስልቶች እንዳይኖረን አድርጓል። ልድገመው፤ ይህ ነው ዋናው የተቃዋሚ ድክመት ምክንያት። የኢህአዴግ ጫና ሁለተኛ ደረጃ ምክንያት ነው። ሆኖም በተለይ ላለፉት 10 ዓመት ኢህአዴግ ተቃዋሚን (እንደ ቻይና) ጨርሶ ለማጥፋት ሲወስን ተቃዋሚዎች በጣም ተጎድተዋል። ዛሬ ግን ድርጅቶች ቢጎዱም በህዝብ ደረጃ ተቃውሞ ምን ያህል አዋጪ እንደሆነ ይታያል የዛሬውንም ለውጥ ያመጣው ይህ የብዙሃኑ ተቃውሞ ነው። ስለዚህ ብዙሃኑ በዚው ከቀጠለ የፖለቲካ ለውጡ እየተንከባለለ እንዲቀጥል ያደርጋል። ይህ ተቃውሞ ስኬታማ ሆኗል አሁንም ስኬታማ ይሆናል። ግን እንደገና ልበለው እየጨመረ ሲሄድ መሪ ያስፈልገዋል።

7. ያለፉት አራት ዓመታት የብዙሃኑ ተቃውሞ በዋነኝነት ስለ «የጎሳ አድሎ»  ነው። ህዝቡ በ«ትግሬ አድሎ» (በተጨማሪ በ«አደርባይ አድሎ») ተማረናል እያለ ነው ሰልፍ የሚወጣው። እርግጥ የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ ነፃነት ይኑር መሬታችን አይነጠቅ ወዘተ የሚሉ መፈክሮች ይሰማሉ ግን የህዝብ ጥያቄ ቢደረግ አድሎ በዋነኝነት እንደሚጠቀስ የታወቀ ነው። ይህ አስተሳሰብ ደግሞ ከድኻ እስከ ሀብታም ከወዝ አደር እስከ ነጋዴ ይሰማል።(በአንድ በኩል ከፍቅር ሰላምና ፍትሕ ይልቅ ትኩረቱ የትግሬ አድሎ ላይ መሆኑ ያሳዝናል ግን እውነቱ ይህ ነው።)

8. ከሌሎች ጉዳዮች ይልቅ የትግሬ አድሎ ህዝቡን ያማረረው ምክንያት የጎሳ አስተዳደር ያመጣው ወይም ያበራታታው የጎሰኝነት ስሜት ነው። በኃይለ ሥላሴ ወይም በደርግ ዘመን በመደብ በዝምድና በትውውቅ በፓርቲ አድሎ ነበር። ግን በዛን ጊዜ የህዝብ ተቃውሞ በመሬት ፍትሕ ነፃነት ተመስርቶ ነበር። ትኩረቱ አድሎ ላይ አልነበረም። ለምን ብትሉ በሰው ልጅ ተፈጥሮ የጎሳ አድሎ ከመደብ ወይም ከፓርቲ አድሎ ይበልጥ ያማርራል። በዚህ ምክናይት ነው ለረዥም ዓመታት እንደተጠበቀው ህወሓትን ስልጣን ላይ ያቆየው የጎሳ አስተዳደር አሁን ከስልጣን የሚያባርረው ወይም ለውጥን የሚያመጣ የሆነው። ይህንም በማወቅ ነው ኢህአዴግ ላለፉት አምስት ዓመት እራሱን ከጎሰኝነት ወደ «ኢትዮጵያዊነት» ማሸጋገር የሚሞክረው።

9. ከላይ እንደጠቀስኩት ዛሬ የምናየው የፖለቲካ ለውጦች ሁለት ዋና ምንጮች አላቸው፤ 1) የብዙሃኑ ተቃውሞ እና 2) ከኢህአዴግ ውስጥ የመጣ ለውጥ። ሁለቱም ወሳኝ ናቸው። እስካሁን በኢህአዴግ ውስጥ የሚመጣው ለውጥ በነ ለማ መገርሳ የሚመራው «የለማ ቡድን» ነው የሚካሄደው እንበል። የለማ ቡድን በኢህአዴግን ሰርጎ ገብቶ ከውስጥ ሆኖ ድርጅቱን የመቆጣጠርና የመቀየር ስራ ነው የያዘው። ቡድኑ ተቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አቢይን እስከማሾም ያበቃው ከኦህዴድ ብአዴን ድህዴን ምናልባትም ከህውሓት ደጋፊዎች ተሳታፊዎች ስላሉት ነው። ይህ ቡድን በርካታ የፖለቲካ ልምድ አቅምና እውቀት አለው ተፈትኗልም። ለዚህ ነው ከ«ተቃዋሚው» ጎራ ሲነጻጸር የለማ ቡደን ለለውጥ የሚጫወተው ሚና የሚበልጠው። ተቃዋሚው ከላይ በጠቀስኳቸው የታሪካዊ ምክንያቶች ደካማ ስለሆነ። የለማ ቡድን ለውጥ ማምጣት ከሚፈልጉት የልሂቃን ቡድኖች ብቸኛ አቅም ያለው ነው።  የቡድኑ ስራ ለሀገራችን በዋና አስፈላጊነት መያዝ አለበት።

10. ኢትዮጵያ የሚኖር ለፖለቲካ ለውት መታገል እፈልጋለሁ የሚል ተቀናቃኝ ልሂቅ ምሁር ወይንም ማንም ሰው አንድ ትልቅ ሚና መጫወት የሚችለው አንዱን የኢህአዴግ ፓርቲ ውስጥ በመግባት ነው። የለማ ቡድን ኢህአዴግን ለመቆጣጠር በርካታ የሰው ኃይል ያስፈልገዋል። ኦህዴድ ብአዴን ደህዴን ውስጥ ያሉትን የዚህ ሥርዓት ደጋፊዎች አክራሪዎችን በሰው ቁጥር ኃይል መብለጥ ማሸነፍ አለባቸው። እስካሁን የደረሱበት ደረጃ የደረሱት ቀስ በቀስ የነሱን ደጋፊዎችና ተሳታፊዎች ቁጥር እየጨመሩ እና ሌሎችን እያሳመኑ እየለወጡ ነው። አሁንም የለማ ቡደን ወደ ፊት ለመራመድ ከነሱ ሀሳብ የሚጋራ ስራ መስራት የሚችል የሰው ኃይል ያስፈልገዋል። የሰው ቁጥር ብቻ ሳይሆን ሀሳብ መስጠት ስራ ማስፈጸም በጠቅላላ አቅም የሚገነባ የሰው ኃይል ያስፈልገዋቸዋል። በዚህ መንገድ ነው የለማ ቡድን ኢህአዴግንም አልፎ ተርፎ ጦር ሥራዊቱንም ደህንነቱንም መቆጣጠር የሚችለው።

11. ለውጥ የሚመጣው በብዙሃኑ ተቃውሞና በለማ ቡድን የሚባለው የኢህአዴግ ተሃድሶዎች ነው ብለናል። የብዙሃኑ እንቅስቃሴ ከደከመ በህወሓት የሚገዙት የኢህአዴግ አክራሪዎች ከለማ ቡድን ያይላሉ። የለማ ቡድን ከደከማና የብዙሃኑ ትግል ከቀጠለ ወደ መሪ አልባ አብዮት እንሄዳለን። ሁለቱም የማንፈልጋቸው ውጤቶች ናቸው። ስለዚህ የብዙሃኑም ትግል የለማ ቡድንም መጠንከር አለባቸው ግን መናበብ መቀናበርም አለባቸው። ልድገመው፤ መናበብ መቀናበርም አለባቸው።

12. የኢትዮጵያ ልሂቃን ምሁራን ላለፉት 50 ዓመታት በትክክሉ ያልተደረገውን የፖለቲካ ውይይት ዛሬውኑ ጀምሮ ማድረግ አለባቸው። ላለፉት 50 ዓመታት ጊዜአችንን ወይ ኃይለ ሥላሴን ወይ ደርግን ወይ ኢህአዴግን ስንወነጅል እንጂ ሃሳቦች ስንገነባ አይደለም ያጠፋነው። የተቃዋሚው ድክመት ምክንያት አንዱ ይህ ነው። አሁንም እነዚህን ውይይቶች ማድረግ ግድ ነው። አሁን የፖለቲካ ውድድር ጊዜ ሳይሆን የሀገር መገንባት ጊዜ ነው። ሊዚህ ስራ ደግሞ ጣት መጠቆም መተቸት መጯጯህ ሳይሆን መወያየት መግባባት መተማመን መስማማት ነው የሚያስፈልገው። ለዚህ ውይይት ሀገር ውስጥም ውጭም ያለነው ትልቅ ሚና መጫወት እንችላለን።

13. የዛሬው የኢትዮጵያ ጦር ስራዊት በአብዛኛው ኦሮሞ አማራ እና ደቡብ ነው። የትግሬ ወታደር ቁጥር አናሳ ነው እየመነመነም ነው። መሪዎቹ ባብዛኛው የህወሓት ደጋፊዎች እንደሆኑ እናውቃለን ግን ጠመንጃው በሌላው እጅ ነው። በዚህ ምክንያት ጦር ስራዊቱ ለተወሰነ ጊዜ በላይ ሀገሩን በአስጨኳይ ጊዜ አዋጁ ተመስርቶ ሊያፍን አይችልም። ጦር ስራዊቱ ህዝቡን የሚጨቁንበት ጊዜና መጠን በጨመረ ቁጥር ውጥረቱ በጨመረ ቁጥር እርስ በርሱ ልዩነቶች እየበዙ ይሄዳሉ የጎሳ ክልልፍ ያድርበታል። የስራዊቱ መሪዎች ይህንን ያውቁጣል በትንሽ ጊዜ ሀገሪቷን ጠቆጣጥረን ወደ ጊቢዎቻችን መመለስ እንችላለን ብለው ነው ተስፋ የሚያደርጉት። ግን የዝቡ ተቃውሞ እንዳለፉት አራት ዓመት ከቀጠለ ጦር ስራዊቱ ግድ ወደ ኋላ መመለስ ይኖርበታል። ስለዚህ የጦር ስራዊቱ በመሪነት በህወሓት ደጋፊዎች መቆጣጠሩ አሁን ብዙ ትርጉም የለውም።

14. የማንም ሀገር ደህንነት ጎራ የኢትዮጵያም ተጨምሮ አስቸጋሪ ነው። ደህንነት በባህሪው ስነ መግባር ቢስ የሆነ በህብረተሰቡ ብሶት የላቸውን ሰዎች ወደሱ ይጋብዛል ይቀጥራል። የሁላችንም ኃጢአት ክምችት በደህንነት ድርጅቶች ይታያል። ግን ደህንነት አለ ፖለቲካ ጎራው እጅግ ደካማ ነው። አሁን የፖለቲካው ጎራ በነ ለማ ቡድን እየተቀየረ ነው። የህዝብ ትግልና የለማ ቡድን ስራ በዚሁ ከቀጠለ ጦር ሰራዊቱም ወደ ባራኩ ይመለሳል። ሁለቱ ጎራ ዎችን ከተቆጣጠርን ደህንነት አቅም የለውም እሱም ግድ ይለወጣል።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!