ከዚህ በፊት እንደጻፍኩት የጎሳ ብሄርተኝነትን ከፖለቲካችን ለመቀነስ እና ለማጥፋት የዴሞግራፊ ለውጦች ማምጣት ግድ ነው (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2016/09/curbing-ethnic-nationalism-via_26.html)። ምከንያቱ ባጭሩ እንዲህ ነው...
የጎሳ ብሄርተኝነት ህዝብ ውስጥ በተለይ የኦሮሞ ህዝብ ውስጥ በደምብ እንደገባ ሁላችንም ገብቶናል። በልሂቃን ደረጃ ብቻ ሳይሆን በብዙሃን ደረጃም። ይህን ጎሰኝነት በስብከት እና ልመና ማጥፋት አይቻልም። የተም ሀገር የጎሳ ብሄርተንኘት አንዴ ከሰፈነ የሚቅንሰው ነገር ፖለቲካዊ ድርድር ሳይሆን የዴሞግራፊያዊ ለውጥ ብቻ ነው። በኢትዮጵያ የሚያስፈልገው የዴሞግራፊ ለውጥ በኦሮሞ እና ሌላው ኢትዮጵያዊ መካከል መቅላቀል እና ውህደት (integration and assimilation) ነው። ህዝቡ ተቀላቅሎ ተጋብቶ ተዋልዶ የቅይጥ ባህል እና ህዝብ መጨመር አለበት። በዚህ መንገድ የጎሳ ብሄርተኛው ጎራ እያነሰ ይሄዳል የፖለቲካ ኃይሉም ይመነምናል። ይህን የሚያስፈጽም አንድ ፖሊሲ ኦሮምኛ የህገር ሙሉ ቋንቋ ማድረግ ነው። ይህ ኦሮሞዎች ከኦሮሚያ ወደ ሌላው ኢትዮጵያ እንዲፈልሱ ይጋብዛል። ለምሳሌ ኦሮምኛ ለማስተማር ወደ አማራ ክልል ይመጣሉ። ይህ ፈልስት መቀላቀልን እና መወሃድን ያመጣል። ከላይ የጠቀስኩት ጽሁፍ ባጭሩ ይህን ነው የሚለው።
በቅርቡ ለማ መገርሳ ስለኦሮሞ ህዝብ ወደ ከተማ መፍለስ እናለበት ያሉት ነገር ከዚህ ጋር አብሮ ይሄዳል። ለምሳሌ አዲስ አበባ ዙርያ የሚኖረው ባብዛኛው ኦሮሞ ነው። አዲስ አበባ ባደገች ቁጥር በሜትሮፖሊታን ከተማው ያለው የኦሮሞ ህዝብ ቁጥር እየጨመረ መሄዱ አይቀርም። ከላይ በጻፍኩት አንጻር ይህ የኦሮሞ ህዝብ በአዲስ አበባ መብዛት አይቀሬም ብቻ ሳይሆን እንደ ጥሩ ነገር ነው መታየት ያለበት። ከተማው ህዝቡን ይቀላቅለዋል እና ያዋህደዋል። ይህ ውህደት የጎሳ ብሄርተኝነትን ይቀንሳል። ስለዚህ ኦሮሞዎችን ወደ አዲስ አበባ እና ሌሎች ከተሞች እንዲፈልሱ ያለው የኦዴፓ እቅድ ጥሩ ነው ማለት ይቻላል።
አሁን ከኛ ከኢትዮጵያ ብሄርተኞች ጎራ የሚጠበቀው ይህ እቅድ በምንፈልገው በአውንታዊ መስመር እንዲካሄድ ነው። «የጎሳ ጌቶዎች» ወይንም የአንድ ጎሳ ሰፈሮች እንዳይፈጠሩ፤ እውነታዊ ውህደት እንዲኖር፤ ሌላው ህብረተሰብ ኦሮምኛ እንዲማር፤ አድሎዋዊነት እንዳይኖር፤ ወዘተ መስራት አለብን። ሌላው ከኛ የሚጠበቀው ነገር የኦሮሞዎች መብት እና ፍላጎት በአዲስ አበባ እንደሚከበረው የሌሎች ዜጎች መብት እና ፍላጎት በኦሮሚያ እንዲከበር መሟገት እና ማስፈጸም ነው። አልፎ ተርፎ ኦሮሙማ (የኦሮሞ ባህል) በአዲስ አበባ እና መላው ኢትዮጵያ እንዲንጸባረቅ በመስማማት in exchange የጎሳ ፌደራሊዝም ሀገ መንግስቱ እንዲቀየር መሟገት እና መደራደር አለብን። ይህን ለማድረግ ታላቅ አቅም እና መደራጀት ይጠበቅብናል።
ነገሮችን ሁሉ በአውንታዊ መልኩ እንደ opportunity ማየት የአሸናፊነት ምልክት ነው። ኦዴፓ ኦሮሞን ወደ አዲስ አበባ እንዲሄድ እናበረታታለን ሲል እኛ እሰየው ብለን በሂደቱ ተሳትፈን እኛ የምንፈልገው መልክ እንዲይዝ ማድረግ አለብን። ከውጭ እያየን በፍርሃት ከማልቀስ ጉዳይ ውስጥ ገብተን መምራት ነው ያለብን።
ስለዚህ ለማ መገርሳ ልክ ነው፤ የዴሞግራፊ ለውጥ ግድ ነው። በዚህ መንገግድ ብቻ ነው መቀላቀል እና መዋሃድ የሚመጣው። በዚህ መንገድ ብቻ ነው አሁን በህብረተሰባችን የሰፈነው ጎሰኝነት ከረዥም ዓመታት በኋላ እንዲቀንስ እና እንዲጠፋ ማድረግ የሚቻለው።
No comments:
Post a Comment
ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!