ስሜታዊ መሆን አይበጅም... ይህን የፍፁም ፈቃዱ ትክክለኛ ትንታኔ ያንብቡ።
(https://www.facebook.com/fitsum.fikadu.96/posts/2138544319567816)
ቁምነገሩ ጦርነቱን ማሸነፍ ነው
በቅድምያ በአደጋው ለተጎዳነው ሁሉ ፈጣሪ መፅናናት ይሁነን እላለሁ።አዎ እርሱው ፈጣሪ ኢትዮጵያዬን እንዲህ ካለው ሃዘን ሁሌም ይጠብቅልን እያልኩ በሰሞኑ የፖለቲካችን ፈተና ዙሪያ እንዲህ እንደሚከተለው ልል ወድጃለሁ።
የዶ/ር አብይ ቡድን ማለቴ ቲም ለማ ሃገርን አንድ ለማድረግ ከፍተኛ ትግልና ውጥረት ውስጥ ሆኖ ይታየኛል።ጁሃር (ኦነግ፣ ቄሮ) እነርሱን (ማለትም ቲም ለማን) ከኦሮሞ ህዝብ ጋር ለማጣላት ጠንክሮ እየሰራ መሆኑን አምናለሁ። እነርሱም ይህ ስለገባቸው ህውሃትን ቀስ በቀስ ድባቅ የመቱበትን ያንኑ የተለመደ ለዘብተኛ የሚመስል ግን ውስጠ ወይራ አካሄዳቸውን እየተገበሩበት ይገኛሉ። እነዚህ ብልህ መሪዎች መሬት እስከሚይዙ ድረስ ለህውሃት ተገዢና ተልመጥማጭ መስለው እንዴት አዘናግተው በጡረታ ስም ገሸሽ በማድረግ ከዚያም ጊዜ ጠብቀው እነዛኑ አይነኬ መሣይ የህውሃት መሪዎች ወደ ማሰር ውስጥ እንደገቡ ሳስብ፤ ይሄ በስሜት የሚነዳው ህዝባችን በሚፈልገው ፍጥነት ባለመሄድ ውስጥ ውጤት እንዳለ ያሳዩኛል።የእነዚህ ሰዎች አካሄድ ልክ እንደ ሺቭ ኬራ አባባል ዓይነት ነው።ማለትም፦ አሸናፊነት ማለት እያንዳንዱን የጦር ግንባር ማሸነፍ ማለት ሳይሆን ጦርነቱን ማሸነፍ ማለት ነውና።
ጁሃር በዚህም በእዛም ብሎ፤ "እኛ ከየኦሮሞ ህዝብ ጥቅምና አጀንዳ ይልቅ የምናስቀድመው የኢትዮጵያ ህዝብን አጀንዳና ጥቅም ነው" ብለው ዛሬውኑ በአደባባይ እንዲናገሩ ለማድረግ ያልወጋጋቸው ቦታ የለም። ም/ቱም ለእርሱ እንዲህ ማስባል ማለት እነርሱን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እስካሁንም በጥርጣሬ እያያቸው ካለው ከቄሮና ፅንፈኛ የኦሮሞ ብሄርተኞች ጋር ሙሉ ለሙሉ ማቆራረጥ እናም ቦታቸውን (ምርጫ ባስፈለገ ጊዜም ሆነ በአዘቦቱ ጊዜ) በኦነግ ማስቀማት ብሎም የእራሱን ርካሽ ተወዳጅነት በአክራሪ ኦሮሞ ብሄርተኞቹ መካከል ያለስጋት ማስፈን መሆኑን ስለሚያውቀው ነው።በከፍተኛ ፈተናና ጫና ውስጥ ያሉት ኢትዮጵያውያኑ ብልሆቹ መሪዎች ግን ገብቷቸዋልና፤ ቪዥናቸውን ከዳር ማድረስ እንዳለባቸው ስለሚያውቁ መረጋጋት ያለበትን በማረጋጋትና ባላንስ በመስራት ስራ ላይ ናቸው።
ኢትዮጵያውያኑ መሪዎች አዲስ አበባን ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ብቻ በእኩል እንድትሆን እንደሚመኙ ግልፅ ማሳያው እኮ፤ መጀመሪያውኑ የኮንዶሚኒየም ዕጣ ማውጣታቸው ነው።ከዚህ በተጨማሪም አገር ሰላም ብሎ የኮንዶሚኒየም እጣ ያወጣው ደግሞ የኦዴፓ አባላቸው ማለትም ታከለ ሆኖ ሳለ ወዲያውኑ የጁሃር ጫጫታ ወደ ደም ማፋሰስ ሊሻገር መሆኑ ሲገባቸው፤ ፅንፈኞቹን ለማረጋጋትና የኦሮሞን ህዝብ ለማሳመኛ የሚሆናቸውን ጊዜ ለመግዛት የሆነ ዓይነት መግለጫ "በሌላኛው" የኦዴፖ ገፅ አውጥተው ጉዳትን ተከላክለዋል። ዳሩ ግና በስሜት የሚንቀለቀለው የህዝባችን አካል ጠረጠራቸው። እነርሱ ግን ምንተዳቸው፤ ግባቸው የብሄር ፖለቲካን ከኢትዮጵያ ምድር ለመጨረሻ ጊዜ ማጥፋት ነውና፤ ይኸው ውጥናቸው ሲሳካ ለሁሉ ምላሽ ይሆነናል በሚል ተስፋ አሁንም ዋና ስራቸው ላይ ናቸው። አዎ በብሄር ፖለቲካ ሃገራቸውን እንዲህ ቁምስቅሏን በማሳየት እያንገላታት ያለውን ኢህአዴግንም ሆነ ኦዴፓቸውን ፍርስርስ አድርገው በህብረብሄራዊ ፓርቲ መተካት ደግሞ፤ የለዘብተኛ መሳይ አካሄዳቸው የመጨረሻ ግብ በዚያውም የጁሃርም ሆነ የኦነግ አሊያም የወላጃቸው የህውሃት ወይም ደግሞ የሌሎች ዘረኛ መሰሎቻቸው ሁሉ ሃሳቦች ግብአተ መሬት እንዲሁም የኢትዮጵያዬ ትንሳዔ መሆኑ ገብቷቸዋልና፤ ለስኬቱ ትግልና ጫና ውስጥ ናቸው። እኛስ የት ነን?
No comments:
Post a Comment
ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!