ባለፈው ጽሁፌ (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2019/03/blog-post_19.html) ግንቦት 7 እና ሌሎች «የዜግነት ፖለቲካ» ፓርቲዎች፤ አዴፓ እና አብን ግቦቻቸው የዜግነት ፖለቲካ እንደመሆኑ ጸጉር መቀንጠስ ትተው መተባበር ቢያንስ አለመጠላለፍ አለባቸው ብዬ ነበር። የሀገራችን ነባራዊ አደገኛ ሁኔታ ስለሚያስገድደን ማለት ነው።
ዋናው ግባችን የዜግነት ፖለቲካ (የዜግነት አስተዳደር ነው)። የጎሳ ፌደራሊዝምን አፍርሰን የብዝሃነት (multicultural and multilanguage) ፌዸራሊዥም ነው የሚበጀን ነው አቋማችን።
የዚህ ግብ ዋና ምክንያት ርዕዮት ዓለማዊ ሳይሆን መረጃ ላይ የተመሰረተ (empirical) ነው፤ የጎሳ ፌደራሊዝም የግጭት መንስኤ መሆኑን ለ28 ዓመት በአምባገነንትም በአንጻራዊ ነፃነትም አይተናል። ሚዛናዊ፤ ለዘብተኛ፤ ዓለም ዙርያ ተሞክሮ ያለው በዜግነት የተመሰረተ ክልሎችን በርካታ መብት የሚጸት ፌደራሊዝም እነዚህን ህልውናችንን ለማጥፋት የደረሱትን ግጭቶች ይቀንሳል። ለዚህ ነው የዜግነት ፖለቲካን የምንፈልገው፤ ግንቦት 7ም፤ አዴፓም፤ አብንም።
ይህን ግብ ለመምታት መደራጀት ግድ እንደሆነ ከምናልባት 50 ዓመታት ብኋላ እየገባን ይመስላል። ገንዘብ እየተሰበሰበ ነው ድርጅት(ቶች) እየተቋቋመ ነው። ይህ ግድ ነው። አሰምርበታለሁ፤ ግድ ነው። አልያ እልቂት ነው የሚጠብቀን።
ግን ወደ ግባችን ስንጓዝ የተለያየ መንገድ እንጠቀም ይሆናል። የተለያየ ስትራቴጂ እና ታክቲክ ማለት ነው። ለምሳሌ፤ አናንዶቻችን ለዘብተኛ አቋም እና በተለይ ለዘብተኛ አነጋገር እና ኮምዩኒካሽን ግድ ነው ጎሰኝነትን ለመቀነስ ብለን እናምናለን (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2019/03/blog-post_15.html)። ሌሎች ደግሞ ጠንቅረን መናገር እና መሟገት አለብን ይላሉ።
ይሁን፤ በዚህ ጉዳይ እንሟገት። ግን ግባችንን አንርሳ። አንጠላለፍ። አንዱ ግድ የሌላውን መንገድ ካልተጠቀምክ አልተባበርህም አይበል። ምን ይደረግ ሰው ነን ፖለቲካ ነው እና አቋም ይለያያል። በፖለቲካ ፍፁምነት የለም።
ግን ትብብር እና አለመጠላለፍ ግድ ነው። አለበለዛ አስፈላጊ የሆኑን ግዙፍ ድርጅቶች እና አቋሞችን ማቋቋም አንችልም፤ ይህ ማለት ግባችን አቅራቢያም አንደርስም፤ ይህ ማለት የጎሳ ፖለቲካ እንደምናየው ሀገራችንን እያቃጠለ ይቀጥላል።
No comments:
Post a Comment
ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!