Showing posts with label forced eviction. Show all posts
Showing posts with label forced eviction. Show all posts

Monday, 4 March 2019

ተረት ተረት፤ አዲስ አበባ የኦሮሞ ገቤሬዎችን አፈናቅሏል

1. የአዲስ አበባ ህዝብ ምንም ፖለቲካዊ ውሳኔ አድርጎ አያውቅም። በኢህአዴግ (ከነ ኦህዴድ) የተገዛ ህዝብ ነበር። ስለዚህ የአዲስ አበባ ህዝብ ማንንም አላፈናቀለም። አፈናቃይ ካለ ኢህአዴግ ከነ ኦህዴድ ነው።

2. ከአዲስ አበባ የተፈናቀሉት ባብዛኛው ኦሮሞ ቢሆንም የተወሰኑ አማሮች እና የሌላ ጎሳ አባላት ነበሩ።

3. ካአዲስ አበባ ውስጥ የተፈናቀሉት ደግሞ ከሁሉም ጎሳ ነበሩ። እነዚህ የአዲስ አበባ ተፈናቃዮች ከአዲስ አበባ ዙርያ የተፈናቀሉት ገበሬዎች ይበልጥ ተበድለዋል በደልን በገንዘብ ከተረጎምነው። ከካዛንቺስ 50 ካሪሜትር ቦታው የተፈናቀለው ምናልታብት ሁለት ሶስት ሚሊዮን ብር ነው ያጣው። ከቡልቡላ የተፈናቀለው ገበሬ የዚህ ሩብም አልከሰረም።

4. ገበሬዎች እና ሌሎች «ተፈናቀሉ» ስንል መንግስት የማይመጥን ትንሽ ካሳ ሰጥቷቸው በግድ ከመሬታቸው አስነሳቸው ነው። አድግራጊው የአዲስ አበባ ህዝብ ያልመረጠው የአዲስ አበባ መንግስት ውየንም አብዛኛው ጊዜ የኦህዴድ መንግስት ነው። ገበሬውን አነስተኛ ካሳ ሰጥቶት ለኢንቬስተር በከፍተኛ ዋጋ ሽጦ ትርፉን ኪስ አስገብቷል። ለዚህ የአዲስ አበባ ህዝብ ትጠያቂ አይደለም፤ ኢህአዴግ እና ኦህዴድ ናቸው።

5. ታላቁ ግን ማንም የማያነሳው ጉዳይ የሀገራችን የመሬት ፖሊሲ ነው። መሬት የመንግስት በመሆኑ ነው ገበሬዎችም ሌሎችም የሚፈናቀሉት እና «ተፈናቀሉ» የሚባለው። አዲስ አበባ ሲሰፋ (እንደ ከተማ ይሁን እንደ metropolis) ዙርያ ያሉት ገበሬዎች ዋና ተጠቃሚ ነበር መሆን ያለባቸው፤ ይሆኑም ነበር መሬት የግል ቢሆን። አዲስ አበባ ዙርያ ያሉት ገበሬዎች ከተማው እየሰፋ ስለሄደ መሬታቸውን በእጅግ ውድ ዋጋ ሊሸጡ እና ሊጠቀሙ ይችላሉ። ቡልጋ ያለው ገበሬ የመሬቱ ዋጋ አንድ ብር በካሬ ቢሆን ይው መሬት አዲስ አበባ ዙርያ መቶ ብር ሊሆን ይችላል። በዚህ መንገድ ነው የትም ሀገር ከተማ ሲሰፋ ዙራይ ያሉት ገበሬዎች ሎተሪ እንዳሸነፉ የሚቆጠረው። ግን ኢትዮጵያ ገበሬው መረቱን መሸት ስለማይፈቀድ እና መንግስት ሲፈልግ መንጠቅ ስለሚችል ከተማ ዙርያ ያለ ገበሬ ጭራሽ ይሰጋ! ስለዚህ በዚምህ ረገድ ጥፋቱ የአዲስ አበባ ህዝብ ሳይሆን የኢህአዴግ እና ኦህዴድ የመሬት ፖሊሲ ነው። አዲስ አበባ ዙርያ ያሉ ገበሬዎች በኢህአዴግ/ኦህዴድ ምክንያት በሚሊዮኖች የሚቆጥር ብር አጥቷልና!

Tuesday, 2 October 2018

የአዲስ አበባ ተፈናቃዎች

የኛ የአዲስ አበባዎች አንዱ (ከብዙ) ድክመቶቻችን በዚህ ቪዲዮ ይገለጻል፤

https://www.youtube.com/watch?v=fhKBwe1wF2Y

ይህ ድክመት ከመሬታቸው የተፈናቀሉት ወንድሞች እይቶቻችን ጎረቤቶቻችንን ዞር ብለን አለማየት ነው። በመቶ ሺዎች «የብሎኬት ካሳ» ተሰጥተው ከቤታቸው ወደ ዳር ከተማ ባዶ የሆነ 70 ካራሜትር ተባርረዋል።

ሰፈር ከነ ማህበራዊ ኑሮ ተበታትነዋል። አብዮተኛ እርምጃ ተወስዶባቸዋል ማለት ይቻላል። ይህ ለተፈናቃዮች ብቻ ሳይሆን ለመላው የአዲስ አበባ ህዝብ ምን ያህል ጎጂ እንደሆነ ይታወቃል። "Social capital" ከሰረ፤ መተባበር ጠፋ፤ መተዋወቅ ጠፋ፤ መደጋገፍ ጠፋ፤ ማህበራዊ ግብረ ገብ ጠፋ፤ ኢ-ማህበራዊነት በዛ፤ ወንጀል በዛ ወዘተ።

አንዱ ለችግሩ መፍትሄ የመሬት ፖሊሲውን መቀየር ነው።

1. ካሁን ወድያ መንግስት መሬት መውሰድ የሚችለው ለመንግስት ጥቅም እንደ መብራት፤ ውሃ፤ መንገድ ወዘተ ይሁን። ካሳውም የ«ብሎኬት ዋጋ» ሳይሆን የመሬቱ ከነቤቱ የገበያ ዋጋ መሆን አለበት።

2. መሬት ለግል ጉዳይ እንደ ኢንቬስትሜንት ከተፈለገ ኢንቬስተሩ በግል ከመሬት ባለቤቶቹ መሬቱን ተደራድሮ ይግዛ። መንግስት ጣልቃ አይግባ። ገዥ እና ሻጭ ከተስማሙ ሁለቱም ደስተኛ ይሆናሉ። ኢንቬስተሩ የገበያ ዋጋ ስለከፈለ በመሬቱ አይቀልድም አዋጪ ነገር ላይ ያውለዋል። ሻጩም ተበድያለሁ አይልም በራሴ የወሰንኩትን አገኘሁኝ ብሎ ያምናል።

የሚጠቀም ሶስተኛ ወገኖችም አሉ። መላው የአዲስ አበባ ህዝብ ከመፈናቀል የሚያመጣው ጠቅላላ ህምሞች ይተርፋል። የመንግስት ሰራተኞችም ከሙስና ፈተና ይድናሉ። ማፈናቀል ወይንም የመሬት ፖሊሲው በጠቅላላ ካድሬዎች በረካሽ አፈናቅለው በውድ ለኢንቬስተር በመስጠት ሙስና የጋበዘ ስርዓት ነበር። ፖሊሲው ከተቀየረ ሁላችንም ከዚህ ሁሉ እንተርፋለን።

Friday, 21 September 2018

የተረሳው ጉዳያችን፤ የመሬት ፖሊሲ ሚና በጎሳ ፖለቲካ

ከዚህ በፊት ደጋግሜ ስለ የኢትዮጵያ የመሬት ፖሊሲ ችግር ጽፍያለሁ (http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/03/blog-post_47.html)። መሬት የግል ወይንም የአካባቢ ("local community" ለምሳሌ ወረዳ) ከመሆኑ ፋንታ የመንግስት መሆኑ ለህዝባችን እጅግ ጎጂ ፖሊሲ ነው ብዬ ነው የማምነው። ለዝርዝሩ ከላይ የጠቀስኩትን ጽሁፍ አንብቡ፤ ግን በአጭሩ መሬት የመንግስት መሆኑ የፈጠረው ችግሮች እንዲህ ናቸው፤

1. ገበሬው ለ«ጎበዝ ገበሬ» የሆነው ጎረቤቱ መሬቱን ሽጦ ወደ ከተማ መሄድ ባለመቻሉ ገጠር ቀርቶ በገጠር የመውለድ መጠን (birth rate፤ በገጠር አማካኙ ከስድስት ልጅ በላይ ነው) ልጅ ወለደ። ከተማ ቢሄድ ኖሮ ሁለት ልጅ (ሁለት አማካኙ ነው ለከተማ ነዋሪ) ይወልድ ነበር። ይህ ማለት የህዝብ ቁጥርን ባልተጠበቀና በኢተፈጥሮዊ (artificial) መንገድ ንሯል። ኢተፈጥራዊ ማለት ህዝቡ ወደ ከተማ እንዳይሄድ ነፃነቱ በመገደብ የጠፈጠረ ሁኔታ ስለሆነ ነው። ከግዳጅ የመጣ ክስተት ስለሆነ ነው።

2. የገጠር ህዝብ ቁጥር ንሮ የገበሬ መሬት አንሶ ልጆች የሚወርሱት አጥተው አሁን ታላቅ የገጠር ወደ ከተማ ፍልሰት ተከስቷል። ለ40 ዓመት ቀስ በቀስ ፍልሰት ከመሆኑ ፋንታ የገጠሩ ሰው ለ40 ዓመታት ከገጠር ተጠራቅሞ አሁን ባንዴ ወደ ከተሞች እየመጣ ነው። ይህ ሁኔታ ከተሞቻችንን አስጨንቋል።

3. ገበሬዎች ቢጎብዙም ገንዘብ ቢኖራቸውም መሬት መግዛት ባለመቻላቸው የግብርና ስራውን ማስፋፋት አልቻለም። ማደግ አልተፈቀድለትም። በዚህ ምክንያት «የሰው አቅማቸው» (human capital) እንዳያድግ ተደርጓል። ለምሳሌ እንደ የግብርና የሙያ፤ የንግድ ሙያ፤ የአስተዳደር ችሎታ አይነቱን እንዳያዳብር ተደርጓል።

4. ገበሬው ሽጦ መሄድ ባላመቻሉ መሬቱን ለትውልድ እያከፋፈለ መሸንሸን ሆነበት። መሬቱ ተሸንሽኖ የያንዳንዱ ገበሬ መሬት አንሶ አንድ ቤተሰብም ማስተዳደር የማይችል ሆኗል። በዚህ ምክንያት ገበሬዎች ለድርቅ እና ርሃብ ተጋለጡ። የምግብ ዋስትና እጥረት እንዳለ ነው።

5. ጎበዝ ገበሬዎች መሬት ገዝተው መስፋፋት ባለመቻላቸው እና ደካማ ገበሬዎች ለጎበዞቹ መሸጥ ባለመቻላቸው የእርሻ ውጤት ዝቅተኛ ሆኖ ቈርቷል። ይህ ደግሞ የእህልና የምግባ ዋጋ ግሽበት አምጥቷል።

ከላይ የጠቀስኳቸው ባብዛኛው በኤኮኖሚ ዙርያ የሆኑ ነጥቦች ናቸው። ግን የመሬት ፖሊሲው ሌላ ታላቅ የፖለቲካ እና ማህበረሰባዊ ተጽዕኖ አለው።

ባጭሩ፤ የመሬት ፖሊሲው አንዱ የጎሳ አስተዳደሩ ምሶሶ ነው። መሬት የ«ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች» ነው ሲባል ለ27 ዓመት የተተረጎመው የአማራ ክልል መሬት የ«አማራ ብሄር» ነው፤ የኦሮሚያ ክልል መሬት የ«ኦሮሞ ህዝብ» ነው ወዘተ እየተባለ ነው። ትርጉሙም የህገ መንግስቱን ጽሁፍም መንፈስም የተከተለ ነው።

«መጤ» እና «ነባር» የሚሉት ጽንሰ ሃሳቦች በማህበረሰቡ በዚህ መሬት ፖሊሲ ይደገፋሉ። የ27 ዓመታት የመፈናቀል ዘመቻዎች የተካሄዱትም በዚህ ምክንያት ነው። ግን ህጉ የመሬት ባለቤትነት የግለሰብ ወይንም የቅርብ አካባቢ ሰዎች ቢያደርግ ኖሮ የ«መጤ» እና «ነባር» አስተሳሰብን ይቀንስ ነበር ነአ ቀስ በቀስ ያጠፋ ነበር። ለዚህ አስተሳሰብ የህግ ሽፋን እንዳይኖረው ያደርጋል። ተፈናቃዮች ለመብታቸው በፍርድ ቤት መታገል እንዲችሉ ያደርጋቸው ነበር።

ስለዚህ ዛሬ ያለውን ጎሰኝነትን ለመታገል እና ቀስ ብሎ ከጎሳ ፌደራሊዝም ወደ ህብረ ባህላዊ አገዛዝ ለመሄድ ይህን የመሬት ፖሊሲ መመልከትና መቀየር ጠቃሚ ይመስለኛል።