Thursday, 7 February 2019

በህዝብ ቆጠራው ላይ የኦርቶዶክስ አማኝ ቁጥር ከታሰበው በታች ቢሆን ምን እንል ይሆን?

በሚመጣው የህዝብ ቆጠራ ላይ የኦርቶዶክስ አማኝ ቁጥር ከታሰበው ወይንም ከሚፈለገው በታች ቢሆን እንደ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ምን እንል ይሆን? ይህን መረጃ / ሰነድ ስናገኝ ምንድነው ማድረግ ያለብን?

በመጀመርያ ደረጃ ንስሃ ነው መግባት ያለብን። የኦርቶዶክስ አማኝ ቁጥር ከመነመነ ዋናው ጥፋት የኛ የኦርቶዶክስ ምዕመናን ስለሆነ። እምነታችን፤ ክርስቶስም፤ የሃይማኖት አባቶችም አስረግጠው ይነግሩናል፤ እኛ ጥሩ ክርስቲያኖች ከሆንን እንደ ብርሃን ሌሎችን ወደ ብርሃን፤ ወደ ቃሉ፤ ወደ ክርስቶስ እናመጣለን። በአንጻሩ ጥሩ ክርስቲያኖች ካልሆንን፤ ጭለማዎች ከሆንን፤ ሌሎችን ወደ ክርስትና እንዳይመጡ እናደርጋለን። አልፎ ተርፎ ከኛም ያሉትን እንዲወጡ እናደርጋለን።

ይህን እውነት በአጭሩ ለመግለጽ የሩሲያዊው ቅዱስ ሴራፊም (ሱራፌል) ዘ-ሳሮቭ  እንዲህ ብለዋል፤

«መንፈስ ቅዱስ እንዲያድርባችሁ ከፈቀዳችሁ ዙርያችሁ ያሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ይድናሉ።»

በዚህ ጉዳይ ላይ ለተጨማሪ ማብራርያ ይህን የታወቁት የቆጵሮስ (ሊማሱ ከተማ) ጳጳስ አታናሲዮስ ቃለ ምልልስ ያንብቡ፤ http://orthochristian.com/79957.html። «ክርስቶስን የማያውቁ ሰዎች መኖራቸው የኛ (የክርስቲያኖች) ጥፋት ነው» ይላሉ። ይህ መሰረታዊ እምነታችን ነው።

በመንፈሳዊ ህግ ኃጢአት የቦታ እና የጊዜ ግድብ የለውም። የሁላችንም ኃጢአት ሁላችንንም በተለያየ መንገድ ይነካል። ለምሳሌ፤ እንዴ ወንድሜን ከበደክሉኝ ችግሩ ከኔ እና እሱ መካከል ሆኖ አይቀርም። ይተላለፋል። ወንድሜ ተበሳጭቶ ሌሎችን ይበድላል። ቤት ሲሄድ ቤተሰቡ አክሩፎ ያገኙታል። እኔ ስለበደልኩት ህይወቱን በሙሉ ቁስሉን ተሸክሞ በቁስሉ ምክንያት አስተሳሰቡም ድርጊቶቹም ሊሳባ ይችላል። ቂም ሊይዝ ይችላል። ሰውን በጥርጣሬ ሊያይ ይችላል። በዚህ መንገድ የኔ ኃጢአት እንደ ተላላፊ በሽታ ይንሰራጫል።

ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ህግ ኃጢአት ከቦታ ቦታ ብቻ ሳይሆን ዘመናትን ይሸጋገራል ብለን እናምናለን። ይህ ማለት ኃጢአት ለትውልድ ይተላለፋል። ይህ የሃይማኖታችን መሰረታዊ እምነት ነው። የአዳም ኃጢአትን መውረሳችን ይህን ይገልጻል። ለአዳም ኃጢአት ሃላፊነት ባይኖረንም ውጤቱን ወርሰናል። እኛም ኃጢአት በመስራታችን እንዲሁም አስተላልፈንዋል። ለምሳሌ ከወላጆቼ የወረስኩት ችግርን ተሸክሜ ለልጆቼ በትወሰነ ደረጃ አስተላልፋለሁ። ችግሩ በሃሳብ ብቻ ሳይሆን በደምም (በዲኤኔአችን) ይተላለፋል።

በመንፈሳዊ ህግ ኃጢአት በሀገር ደረጃም ይታወቃል። የእስራኤል ህዝብ ለሀገራዊ ኃጢአታቸው የታዋቁ ናቸው በራሳቸው በኦሪት ታሪክም በወንጌልም ይህ ታሪካቸው ተዘርዝሯል። ሌሎች በርካታ ህዝቦች እንደ ህዝብ ወይንም ሀገር ለኃጢአቶቻቸው ዋጋ ከፍለዋል። ዛሬም እንዲሁ ነው (https://blogs.ancientfaith.com/glory2godforallthings/2015/06/27/dostoevsky-and-the-sins-of-the-nation/)።

ስለዚህ እንደ ግለሰብም እንደሀገርም ኃጢአቶቻችን በቦታ እና ጊዜ ይተላለፋል። ለዚህ ኃጢአቶቻችንን አምነን ንስሃ መግባት አለብን። ይህ መሰረታዊ የክርስትና እምነት ነው። እንኳን በኢትዮጵያ በዓለም ዙርያ ችግር ሲከሰት ወደ ራሳችን ተመልክትን «ምን አድርጌ ወይህም ምን ባለማድረጌ ነው ይህ የሆነው» ብለን እራሳችንን መጠየቅ አለብን።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ መእመን ቁጥር ከቀነሰ ወይንም ካልጨመረ እሄኑኑ ጥያቄ እራሳችንን መጠየቅ ነው ያለብን። አማራጭ የለንም። እውነቱ ይህ ነው። ለዚህ ችግር ሌሎችን ጥፋተኛ ማድረግ ኢ-ክርቲያናዊ አካሄድ ነው። እንደ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች «ጴንጤዎቹ»፤ «ሙስሊሞቹ»፤ ወይንም «ሴኩላሪስቶቹ» ናቸው ምእመኖቻችንን የወሰዱብን ማለት አንችልም። ወደራሳችን ብቻ ነው መመልከት ያለብን። እኛ ብርሃን ከሆንን ምንም አይሳነንም፤ ዓለም በሙሉ ወደ ክርስቶስ ይመጣ ነበር። እዚህ ላይ ነው ማተኮር ያለብን። ይመስለኛል።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!