Tuesday 14 August 2018

ተረት ተረት፤ የትግራይ ገዥ መደብ አገዛዝ እና የ«አማራ ገዥ መደብ» አገዛዝ አንድ ናቸው

«የትግራይ ገዥ መደብ አገዛዝ እና የ«አማራ ገዥ መደብ» አገዛዝ አንድ ናቸው»። ይህ ተረት ተረት (myth) በበርካታ ሰዎች ሲደጋገም ወደ እውነታ እያማራ ነው። በቅርቡ ባደረጉት ኑዛዜአቸው የቀድሞ ጠ/ሚ ታምራት ላይኔም ደግመውታል። «የአማራ ገዥ መደብ ብይ አማራ ብዙሃን እንደነገዱት ነው ህወሓት የትግራይ ገዥ መደብ በትግራይ ብዙሃን የነገዱት» ብለዋል። ይህ አስተያየት እጅግ የተሳሳተ ነው።

የሁለቱ አገዛዞች መሰረታዊ ልዩነት ይህ ነው፤ በደርግ እና በንጉሳዊው ስርዓት ጎሳ፤ ዘውግ፤ ብሄር አይነት ጽንሰ ሀሳቦች በህግ ደረጃ አልነበሩም። አገዛዙ በህግ ደረጃ ከጎሳ እና ከጎሰኝነት ውጭ ነበር። በህወሓት አገዛዝ ግን ጎሳ እና ጎሰኝነት በህግ የተደነገገ ነው። ጎሰኝነቱ በልምድ ወይንም በባህል ደረጃ ሳይሆን ህጋዊ ነው። ይህ መሰረታዊ ልዩነት ነው።

በኃይለ ሥላሴ መንግስት ማንኛውም ግለሰብ በጎሳ ምክንያት ከመንግስታዊ ስልጣን እና ሹመት አይከለከልም ነበር። አይከለከልም ብቻ ሳይሆን ጎሳው ጭራሽ እንደ ጉዳይ አይነሳም፤ በህግ እና ስረዓት ደረጃ ጎሳ የሚባል ጸንሰ ሀሳብ የለም። በዚህም ምክንያት በኃይለ ሥላሴ መንግስት በርካታ ከተለያዩ ጎሳ የሆኑ ባለ ስልጣኖች ነበሩ።

ሆኖም የአስተዳደር ቋንቋው አማርኛ ነበር። ይህ ከጅማ ለተወለደው ኦሮሞ መሰናከል ነበር። የገዥ ስረዓቱ ንጉሳዊ ነበር። ይህ ከኮንሶ የተወለዱት ባዕዳዊ ስረዓት ነበር። በነዚህ አይነት ምክንያቶች አማራ ያልሆኑ ወደ ስልጣን ለመቅረብ ከአማራ ይልቅ ይከብዳቸው ነበር ማለት ይቻል ይሆናል። አማራ ቋንቋውን በማወቅ ከሌላው ይበልጥ እድል ነበረው ማለት ይቻላል። እንዲሁም የአዲስ አበባ ተወላጅ ይበልጥ እድል ነበረው ማለት ይቻላል። በዚህ ደረጃ በተለያዩ የጎሳ ተወላጆች የስልጣን እና ሹመት እድል ልዩነት መኖሩን መካድ አይቻልም። ግን ይህ ልዩነት የታሪክ አጋጣሚ ነው እንጂ በህግ የተደነገገ አልነበረም። ስለዚህ አማራ ያልሆነው ቢከብደውም ወደ ስልጣን መምጣት ይችል ነበር። አድሎ ነበር ግን አድሎው ህጋዊ አልነበረም ስለዚህ ሊቀለበስ የሚችል አድሎ ነበር።

የህወሓት አገዛዝ ግን መሰረቱ ጎሰኝነት ነበር። ህወሓት የትግራይ ድርጅት ለትግራይ ህዝብ ነው። አማራው በአማራነቱ ቦታ የለውም። ቋንቋ ባለመቻሉ ወይንም የፖለቲካ ባህሉን ባለማወቁ ሳይሆን በአማራነቱ ምክንያት ስልጣን ሊይዝ አይችልም። በህወሓት ዘመን አድሎ መቀልበስ የማይችል የጎሳ የደም አድሎ ነበር።

ይህን የ«ትግራይ ገዥ መደብ» እና የ«አማራ ገዥ መደብ» አገዛዝ ልዩነት ስንመለከት አንድ ትልቅ ትምሕርት እንማራለን። ይህ ስለ የጎሳ አገዛዝ አደገኝነት ነው። ጎሳ የትውልድ የደም ጉዳይ ስለሆነ በመሰረቱ ህዝብን የሚለይ እና አድሎ (discrimination) የሚያመጣ ነው። በዚህ ምክንያት ነው የጎሳ አገዛዝ የግጭት (conflict) ፋብሪካ የሚሆነው።

የጎሳ መብቶችን ለማስተናገድ የጎሳ አስተዳደርን ከመጠቀም ወይንም የጎሳ መብቶች በህግ ከማወጅ የቋንቋ እና የባህል መብቶችን ማደንገድ ይሻላል። ቋንቋ እና ባህል ማንም መማር መቀየር የሚችለው ስለሆነ መሰረታዊ አድሎ የላቸውም። በዚህ ምክንያት በአድሎ የተነሳ የተጨቋኝ ስሜቶችን አያዳብርም ስለዚህ ግጭትን አያበዛም።

ይህን ተመስርተን ነው የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ጸንፈኛ ነው የምንለው። ዓለም ዙርያ ሀገራት የቋንቋ እና ባህል መብቶችን በህጋቸው ያስተናግዳሉ። የጎሳ መብቶችን በዚህ መንገድ ያስተናግዳሉ። ግን የትም ሀገር ጎሳን በህጋቸው አያስተናግዱም። በጎሳ እና በቋንቋና ባህል ያለውን ልዩነት በግጭት መጋበዝ አኳያ በድምብ የታወቀ ስለሆነ ነው እንዲህ የሆነው። ግን ኢትዮጵያ ብቸኛዋ ጎሳን በህግዋ ውስጥ ያካተተች ናት። ለሀገራችን ህልውና ይህን መቀየሩ አስፈላጊ ነው።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!