Friday 10 August 2018

ጠ/ሚ አብይ አህመድ፤ የድሮ ሰው

ዓመት በፊት ማንኛውም ኢትዮጵያዊን ምን አይነት የፖለቲካ ለውጥ ትፈልጋለህ ቢባል፤ «ዴሞክራሲ፤ ነፃነት፤ ፍትህ፤ እኩልነት» ይል ነበር። ጠ/ሚ አብይ ስልጣን ሲይዙ እንደዚህ አይነት መልእክቶች እና መፈክሮች ነበር የሚጠበቅባቸው። ግን እሳቸው «ፍቅር፤ ሰላም፤ ይቅር ማለት» አሉ። መንፈሳዊ መረጋጋትን ከፖለቲካ መረጋጋት አስቀደሙ። ይህን የድሮ ሰው ብቻ ነው የሚለው፤ የዘመኑ ሰዎች ምን ማለት እንደሆነም ሊገባን ያስቸግረናል።

ጠ/ሚ አብይ የፖለቲካ ለውጡን ሲጀምሩ በሀገራችን መልካም አስተዳደር እና ብልጽግና እንዴት እንደሚያመጡ ይነግሩናል ብለን ሁላችንም እንጠብቅ ነበር። በነዚህ ጉዳዮች ሲናገሩ ግን እኛ ካሰብነው አልፎ ሄዱ። እሳቸው እንኳን ለኢትዮጵያ ለምስራቅ አፍሪካ ቀጥሎም ለጠቅላላው አፍሪካ ምሳሌ የሚሆን እና የሚያስተምር መልካም አስተዳደር እና ብልጽግና እናመጣለን አሉ! እኛ ስለሀገራችን ኢትዮጵያ ብቻ ነው ያሰብነው። በዛሬ ዝቅተኛ ሞራላችን ከሀገራችን ውጭ ምሳሌ መሆን እንደምንችል በፍጹም አናስብም። ጠ/ሚ አብይ ግን ዛሬ የጊዜያዊ ድክመቶች ቢኖራትም ኢትዮጵያ የአፍሪካ መሪ ናተና ይህንን ተእልኮዋን አንረሳም ብቻ ሳይሆን እናሟላለን አሉ። እንዲህ ሲሉ 60 ዓመት በፊት የነበሩ ጀግና የኢትዮጵያ ልሂቃን የማዳምጥ መሰለኝ!

ጠ/ሚ አብይ አብዛኞቻቸው ትንተናቸውን የሚጀምሩት የኢትዮጵያ ታሪክ እና ወግ በመጥቀስ ነው። ለምሳሌ ስለ «ፍቅር፤ ሰላም፤ ይቅርታ» ሲያወሩ ወጋችን ነው ብለው ነው። ታሪካችን ጥላቻ፤ ጦርነት፤ እና ቂም በደምብ እንዳለበት አልተሳኑም ግን የታሪክ እና ወጋችን የመጨረሻ ግብ እና ፍጻሜ ፍቅር፤ ሰላም እና ይቅርታ እንደሆነ ያውቃሉ። በድክመታችን ላይ ሳይሆን በጥሩ ጎናችን ያቶኩራሉ። በዚህ ዘመን ማን እንዲህ ይላል? በዚህ ዘመን ብዙዎቻችን በዝቅተኛ መንፈስ የተሞላን ስለሆነን ከታሪክ እና ወጋችን ጥሩ ነገር አይታየንም። ግን ጠ/ሚ አብይ ታሪክ እና ወጋቸውን በሚገባው በእውነተኛ ፍቅር ነው የሚያዩት።

በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ሁላችንም የጠበቅነው ጠ/ሚ አብይ መንግስት ካሁን ወድያ በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገባ ያደርጋሉ ነው። ምናልባትም ይህን በይፋ ለህዝብ ይናገራሉ ነው። ግን እሳቸው እንደገና ከጠበቅነው አልፈው ቤተ ክርስቲያንን ነፃ መተው ብቻ ሳይሆን ወደ መርዳት ገቡ! መንግስት ላበላሸው ሃላፊነት አለበት ማስተካከል አለበት ብለው በሲኖዶሶቹ እርቅ እንዲኖር ምኞታቸውን ተናገሩ። መናገር ብቻ ሳይሆን ስልጣናቸውን እንደ ህሊና ግፊት በመጠቀም እርቁ እንደፈጸም አስተዋጾ አደረጉ። ጭራሽ ካልሆነ እግራችሁ ላይ ወድቄ እንድትታረቁ እለምናችኋለሁ አሉ! ማናችንም ይህን አልጠበቅንም።

ጠ/ሚ አብይ ለሀገራችን ባህላዊ ሃይማኖቶች ታላቅ ክብር አላቸው። እኛ የዘመኑ ሰዎች እንዚህን መዋቅሮች ከፖለቲካ ውጭ የሆኑ ኋላ ቀር ነገሮች ይመስሉናል። እሳቸው ግን ለሀገራችን ደህንነት እና ጤንነት አስፍላጊ እና መሰረታዊ እንደሆኑ ይገባቸዋል። እነሱን ትቶ ኢትዮጵያዊነት በአሸዋ የተመሰረተ ቤት እንድሆነች ያውቃሉ ይናገራሉ ያስተምራሉ። እንደዚህ አይነት አስተሳሰብ ከልሂቃኖቻችን ድሮ ነው የጠፋው።

ጠ/ሚ ዱባይ ሄደው ከአረብ ህብረት መሪ ጋር ሲወያዩ አረቡ ልንረዳችሁ አስበናል ምናልባትም ትምሕርት ቤቶች በኢትዮጵያ ለማቋቋም እያሰብን ነው አሉ። ጠ/ሚ አብይ እሺ አላሉም። ወይንም ጥሩ ነው ግን የኤኮኖሚ ኢንቬስትሜንት ይሻለናል አላሉም። እናንተ እምነታችሁን እያጣችሁ ስለሆነ እኛ አረብኛ ተምረን ሃይማኖትን መልሰን እናስተምራችኋለን አልዋቸው (https://www.youtube.com/watch?v=b3GUI1rD9-M)! እዩ በራሳቸው እና በሀገራቸው ምን ያህል እንደሚተማመኑ። ማናችን በዚህ ዘመን ያለነው ኢትዮጵያዊ እንደዚህ እናስባለን? ይህ የጠ/ሚ አብይ ንግግር ኢትዮጵያን በትክክለኛ በሚገባት ቦታ የሚያስቀምጥ ነው። እውነትም ነው። ግን ስንቶቻችን እንደዚህ አይነት አስተሳሰብ ከልባችን ይገባን ይሆን?

ጠ/ሚ አብይ መንግስታቸው ለፈጸማቸው በደሎች በቡድናቸው በኢህአዴግ ስም ሳይሆን በግላቸው ይቅርታ ጠይቀዋል። ይቅርታ የሚጠይቅ ሰው በራሱ የሚተማመን ነው (http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/07/blog-post.html)። በራሱ የማይተማመን ሰው ወይንም የዝቅተኛ መንፈስ ያለው ሰው ይቅርታ ማለት ድክመቱን ለሁሉም የሚገልጥ ይመስለዋል። ጠ/ሚ አብይ ግን ትንሽ ይቅርታ ሳይሆን ለኢህአዴግ ኃጢአት በሙሉ ግዙፍ ይቅርታ ጠየቁ።

ከዚም አልፎ ከተለያዩ በአንድ ወቅት እንደ ጠላት የሚቆጠሩ ሰዎች ጋር በሂሊና ነፃነት ይገናኛሉ ይወያያሉ። ከኢሳያስ አፈዎርቂ፤ አብዴል እል-ሲሲ፤ ግንቦት ሰባት፤ ታማኝ በየነ፤ ጀዋር መሃመድ፤ የተለያዩ የህወሓት ሹማምንት ወዘተ በሰላም ተገናኝተው በህዝብ ፊት አብሮ ይቀርባሉ። ከነዚህ ጋር አብሮ መታየቴ እና መወያየቴ ማንነቴን በግምት ያስገባዋል እና አጉል እተቻለሁ ብለው አያስቡም። ይህም በራስ የመተማመን ምልክት ነው። ምንም አይበረግገዋቸውም። ከማንም ጋር መነጋገር እችላለሁ "on my own terms" ነው አስተሳሰባቸው።

ጠ/ሚ አብይ በራሳቸው የሚተማመኑት በሰው ልጅነታቸው ብቻ ሳይሆን ከፖለቲካ አንጻር በኢትዮጵያዊነታቸው ሙሉ በሙሉ ስለሚኮሩ ነው። በዚህ በኩል የድሮ ሰው ናቸው። እንደ በምኒልክ ዘመን የነበሩት ከአውሮፓዊያን ጋር በእኩልነት ሳይ በበላይነት ስሜት የሚደራደሩ። እንደ በኃይለ ሥላሴ ዘመን ለኢትዮጵያ በዓለም ደረጃ እንደሚደራደሩት አልፎ ተርፎ ለአፍሪካ የሚዋጉት። የሰለባነት አስተሳሰብ (victim mentality)፤ በዝቅተኝነት መንፈስ (inferiority complex)፤ በልመና፤ ሌሎችን መለመን ወይንም እንደ ሌሎች መሆን መፈለግ የለም። ይህ አስተሳሰብ ድንቅ ነው በአሁኑ ዘመን ከሀገራችን ብዙ የማይገኝ ነው። ግን ኢትዮጵያ እንደገና እንደዚህ አይነት እንደ ጠ/ሚ አብይ አይነቱን ሰው ማፍረት መቻሏ ተመስገን ነው። ሁላችንም የሳቸውን አስተሳሰብ (mindset) ያኑርብን። የሀገራችን ብጎ ህልውና ከዚህ ነው የምጀረውና።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!