Wednesday 15 August 2018

ከአንድ የ«አምራ ብሄርተኛ» ያደረግኩትን ቃለ ምልልስ

ከአንድ የ«አምራ ብሄርተኛ» ያደረግኩትን ቃለ ምልልስ ላቀርብላቹ እወዳለሁ። እኔ አስፋው ጠያቂው ሆኜ እንግዳዬ ደግሞ ግዮናዊት ሀገሬ ትባላለች እራሷን የአማራ ብሄርተኛ ብላ የምትሰይም የ28 ዓመት መምህርት ናት። ቆይታችን እንዲህ ነበር፤

አስፋው፤ ለቃለምልልስ ፈቃደኛ በመሆንሽ አመሰግናለሁ፤ እንኳን ደህና መጣሽ።

ግዮናዊት፤ ምንም አይደለም፤ እኔም አመሰግናለሁ።

አስፋው፤ እስቲ ስለ አማራ ብሄርተኝነት ርዕዮተ ዓለም ትንሽ ንገርኝ።

ግዮናዊት። የአማራ ብሄርተኝነት የአማራ ህዝብ ለአማራ ህዝብ መቆም አለበት የሚል ርዕዮተ ዓለም ነው። የአማራ ህዝብ ባለፉት 27 ዓመት፤ 40 ዓመት ማለት ይቻልም ይሆናል፤ ብዙ ግፍ እና ሰቆቃ የደረሰበት ነው። ክብሩን ከማጣት እስከ ቡድናዊ ግድያ (genocide) ተፈጽሞበታል። ከበየ ኢትዮጵያ ክልሎች ተፈኛቅሏል። ህዝቡ ተገድሏል። የመንግስት በጄቱ ተቀምቷል። አማራ ሀገር ከሁሉም ድኻ ሆኖ ግን በጨቋኝነት ይፈረጃል። እስካሁን እንደ ጨቋኝ ይታያል እንደ ህዝብ መቀጣት አለበት ተብሎ ይሰበክበታል። የአማራ ብሄርተኝነት ይህን ያለፈውንም፤ ያለውንም፤ ወደ ፊት የሚመጣውንም አማራ ላይ ጥቃት ለመቋቋም ነው የሚቆመው። ከዛ አልፎ ተርፎ የአማራ ህዝብ መደራጀት ያለበት እራሱን ለመከላከል ብቻ ሳይሆን ለመቋቋም እና ለመበልጸግ። ልጆቻችን እንዲማሩ፤ እርስ በርስ እንድንረዳዳ፤ ለራሳችን ልማት እንድናመጣ ወዘተ የሚታገል ርዕዮተ ዓለም ነው።

አስፋው፤ ግን እስቲ «አማራ» ከሌላው ይበልት ተጨቁኗል ማለት ይቻላል። ባለፉት 27 ዓመት ሁሉም ትግራይ ያልሆነ ተጨቁኛለሁ ይላል። ኦሮሞ በስመ ኦነግ። ጋምቤላ ለመሬቱ፤ አኟክ ጭራሽ ጄኖሳይድ ተፈጽሞበታል። ሲዳማ በየጊዜው ተመቷል። ወዘተ።

ግዮናዊት። አዎን ህወሓት ሁሉንም መትቷል ግን እንደ አማራ በየ ክልሉ የሚገደል የለም። እንደ አማራ የህዝብ ቁጥሩ እንዲመነምን የተደረገ የለም። እንደ አማራ በየ ክልሉ የሚፈረጅበት ጭቋኝ ተብሎ የሚረገጥ የለም።

አስፋው፤ አዎ ግን ሁሉም ጎሳ እንዲሁ የራሱ እሮሮ አለው እኮ።

ግዮናዊት፤ አይደለም፤ ሁሉም መንግስት ጭቁኖኛል ማለት ይችላል እንበል። በዚህ እንስማማ። ግን አማራ የተጠቃው በመንግስት ብቻ ሳይሆን በሌላው ህዝብም ነው። ይህ ነው ልዩነቱ። ሲገደል ሲፈናቀል መንግስት ብቻ አይደለም ይህን የሚያደርግ የነበረው። መንግስት «ጭቋኝ» ብሎ ሰየመው ከዛ በኋላ የተለያዩ ግለሰብ እና ቡድኖች ይህን ይዘው አማራን በየቦታ ያሰቃያሉ። ይህ ነው ልዩነቱ። አማራ የትጠቃው በመንግስት ብቻ ሳይሆን በህዝብም ነው።

አስፋው፤ ግን እኮ የአርሲ ኦሮሞን ብትጠይቀው የአማራ መንግስት ለ100 ዓመት ጨቁኖኝ ነበር ሰለዚህ እኔም በመንግስት ብቻ ሳይሆን በግለሰቦች ተጨቁኛለሁ ይላል። አማራ ብቻ አይደለም እንደዚህ አይነት ጭቆና ዘመን ያሳለፈው ይላል። የ«ተጨቆንኩኝ» እሽቅድድም አልሆነምን?

ግዮናዊት፤ ያየድሮ ታሪክ ነው ባለአባቶች መሬታቸውን ከተነጠቁ 44 ዓመት አልፏል። አማራ ላይ ግን አሁንም ነው ጥቃት የሚደረገው።

አስፋው፤ ግን የታሪካዊው ጭቆና አሁንም ርዝራዥ አለው ይሉናል። አማራው ጨቁኗል አሁንም የድሮ ጭቆናው ውጤት ነው የሚያገኘው ይላሉ። መቼም ወደ ኋላ እየተሄደ ሁሉም የግፍ ቆጠራውን ያደርጋል ከሁሉም እበልጣለሁ ይላል አይደለምን?

ግዮናዊት፤ በዚህ አንስማማም። የድሮ የድሮ ነው። ዛሬ ግን ከሁሉም ሰለባ አማራ ነው ብለን ነው በአማራ ብሄርተኝነት የምናምነው።

አስፋው፤ ጥሩ። ግን ከሌሎች ድጋፍ አትጠብቁ። ከኛ በሙሉ እናንተ ናችሁ የተጨቆናችሁት እንዲሏችሁ አትጠብቁ። በዛ መሰረት እንደረደራለን ብላችሁ አታስቡ።

ግዮናዊት፤ ይሁን የራሳቸው ጉዳይ በዚህ መስማማት አያስፈልግም። ግን ለኛ ለአማራ ህዝብ እኛ ዋና ተጨቋኝ እንደሆንን እናምናለን ይህንንም እንደ ምክንያት አድርገን ነው የምንደራጀው።

አስፋው፤ እሺ አማራው ተጎድቷል እየተጎዳ ነው። ለምንድነው በአማራነት መደራጀት የሚያስፈልገው ይህን ጥቃት ለመቋቋም? ለምን በኢትዮጵያ ወይንም በ«ኢትዮጵያ-አማራ» ስም መደራጀት ለዚህ አይበጅም? በኢትዮጵያ ስም ብንደራጅ አማሮች ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ለኛ ይቆሙ ነበር።

ግዮናዊት፤ ተጨቋኙ አማራ ነውና። ምን ሌላ ምክንያት አለው። በአማራነቱ እየተሰደበ እየተኮነነ እየተገደለ እያለ እራሱን በአማራነቱ መከላከል አለበት። ማን ሌላ ይከላከልለት? እራሱን ካደራጀ አይጠቃም። ሌላን ከጠበቀ ይጠቃል። ግልጽ ነው እኮ።

አስፋው፤ ማለት የፈለግኩት እንዲህ ነው። የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ እንውሰድ። ይህ ድርጅት እራሱን የ«ኢትዮጵያ ብሄረአዊ ንቅናቄ» ብሎ ቢሰይም አሁን የሚሰራውን መስራት አይችልም ነበር ያውም ሌሎችን አካቶ እና ተጨማሪ ኃይል አከማችቶ?

ግዮናዊት፤ አይችልም። ስሙ «ኢትዮጵያ» ከሆኑ ሁሉንም ማቀፍ ይኖርበታል ለአማራ የተለየ ጭቆና ብቻ መቆም አያችልም። ይህ «ኢትዮጵያዊ» ድርጅት የአማራ ህዝብ ለብቻ የጎደለውን ማሟላት አይችልም። የአማራን ርስት ማስመለስ አይችልም። ወዘተ።

አስፋው፤ ግን በዚህ መልኩ ይችላል። ኢትዮጵያዊ ድርጅት ከሆነ ሁሉንም ለተጨቆነው አማራ ለመቆም ማስተባበር ይችላል። ሁሉንም ለተጭቆነው ኦሮሞ ማስተባበር ይችላል። ይህ ከአማራ በቻ ይበልጥ ትልቅ ኃይል አደለምን?

ግዮናዊት፤ በቴኦሪ ደረጃ ጥሩ ይመስላል ግን በዚህ ዘመን ከአንድ ብሄር በላይ ሲቀላቀል መዘዙ ብዙ ነው። እስካሁኑም አልሆነልንም። አማራ አማራ አትበሉ እንባላለን። ይህ ደግሞ አይመቸንም።

አስፋው፤ እስካሁን አልሆነምን ተይው! የአማራ ብሄርተኝነትም እስካሁን አልሆንም። በደምብ ላልተሞከረ ነገር አልሆነም ማለት ሃሰት ነው። የአንድነት ድርጅቶች ያልተሳካላቸው በአንድነት ስለሚያምኑ አይደለም በእርስ በርስ የጎሳ ፍጭት አይደለም።

ግዮናዊት፤ ምንም ቢሆን እኛ አማሮች ለአማራ መስራት ነው የምንፈልገው።

አስፋው፤ ታድያ ይህ አቋማችሁ ከሌሎች ጎሰኞች እንደ ህወሓት ወዘተ ምን ይለያችኋል?

ግዮናዊት፤ ቅድም እንዳልኩት እኛ ለብቻ ይበልጥ ተጨቁነናል። አልፎ ተርፎ እኛ በኢትዮጵያዊነት እናምናለን። እንገንጠል አንልም። አማራ ኢትዮጵያዊ ነን ነው የምንለው። ይህ ነው ትልቁ ልዩነት።

አስፋው፤ በክልሌ ያለው አማራ «መጤ» ነው የሚለው የኦሮሞ ብሄርተኛውም እንዲሁ ነው የሚለው እኮ። ተበድያለሁ። መገንጠል አልፈልግም (መብቱ አይወሰድብኝ እንጂ) እና እኔ መጀመርያ ኦሮሞ ነኝ ቀጥሎ ኢትዮጵያዊ (የብሄር ፌደራሊዝም እስካለ አለ በለዛ ለቃለው!) ። እንዲሁ ነው የሚሉት። አሁንም ምን ይለያችኋል።

ግዮናዊት፤ እኛ ደግሞ ማንንም አንጨቁንም ከክልላችን ይውጣልን አንልም ብለንም አናውቅም። ይህ ነው ሌላ ልዩነታችን።

አስፋው፤ ግዮናዊት፤ ሌሎቹም እኮ ማንንም አንጨቁንም። ታሪካዊ ጭቆናን እናስተካክላለን ለምሳሌ በaffirmative action አይነት ነገሮች መሬተም ወደ ድሮ የተቀማበት በመመለስ ወዘተ። በክልላችን የኛ ቋንቋ ነው የሚሰፍነው እንላለን በመንግስት በትምሕርት ደረጃ ወዘተ። ሌላው ይህን ካልተቀበለ ይውጣ ከፈለገ ነው የሚሉት። በአማራ ክልልም የአማራ ብሄርተኝነት ከሰፈነ እንዲሁ እይደለም የሚሆነው? በአማራ ክልል ያለው አማራ ያልሆነው ህብረተሰብ ሁለተኛ ዜጋ አይሆንም?

ግዮናዊት፤ አይሆንም ብቻ ነው ማለት የምችለው። አሁን በአማራ ክልል ያሉ የኦሮሞ ዞኖች ውስጥ ነዋሪዎቹ ሙሉ ነፃነት አላቸው በቋንቋቸው በፍላጎታቸው መተዳደር። አገውም እንዲሁ።

አስፋው፤ ስለዚህ አማራው በክልሉ ያሉትን «አናሳ ብሄሮችን» አይጨቁንም የመጨቆን ባህሪውም የለውም እንበል። ጥሩ። ግን ሌሎቹም እንደዚህ እያሉ ግን በደል ያደርሳሉ። ለምሳሌ በኦሮሞ ክልል የአማርኛ ትምሕርት ይቀራል ቢባል አንቺ እንደ ጭቆና ታዪው ይሆናል ግን ኦሮሚያ ቋንቋችን እንዳይሸረሸር ነው ይላል። አማራው በአማራነቱ መደራጀቱ ይህን ጉዳይ እንዴት ያደርገዋል?

ግዮናዊት፤ የአማራ ድርጅት ለዚህ መልስ ይኖረዋል። ከኦሮሚያ ለሚኖረው አማራው መብት ይቆማል ይታገላል።

አስፋው፤ ከመፈክር አልፎ በተግባር ያልሸው ምን ማለት ነው?

ግዮናዊት፤ በአማራ ክልል እንደዛው አይነት ፖሊሲ እናመጣለን። በኛ ኦሮሞ ዞኖችም ትምሕርት ቤት በአማርኛ ብቻ ማድረግ ነው።

አስፋው፤ ግን አማራ በብዛት በየክልሉ አለ። በዚህ ብድር በመመለስ (tit for tat)ተሸናፊ አማራው ነው የሚሆነው። ልክ እንደ ሰርቢያኖች በዩጎስላቪያ በኢትዮጵያ የጎሳ ግጭት ከተነሳ አማራው ነው ከሁሉም በላይ የሚጎዳው አይደለም?

ግዮናዊት፤ አማራው በደምብ ከተደራጀ ሁሉንም አማራ በየ ቦታው ያለውንም መጠበቅ ይችላል። ጦር ይኖረዋል ሄዶ ይከላከላል።

አስፋው፤ የአማራ ጦር አዲስ አበባ ሄዶ የአዲስ አበባ አማራዎችን መብት ሊጠብቅ ነው? ሻሸመኔ ሄዶ አማራውን ሊጠብቅ ነው? ይህ አጉል ፉከራ ከእውነታ የራቀ አይደለም።

ግዮናዊት፤ አዎን ዝም ብዬ የኛ የአማራ ብሄርተኞች ስሜታዊ መልስ ነበር የሰጠውህ! ትክክለኛ መልስ እንዲህ ነው፤ አማራው ተደራጅቶ ሲጠነክር ሌሎች ክልሎች/ብሄሮች ይጠነቀቃሉ ከጸንፈኝነት ይቆጥባቸዋል። ከግጭት ይልቅ ወደ win-win ያመጣቸዋል ነው።

አስፋው፤ ሁሉም አሸናፊ አካሄድ ቢቻል ኖሮማ እስካሁን እናደርገው ነበር! የጎሳ አስተዳደር የሁሉም አሸናፊ ሳይሆን የዚህ ተቃራኒ የሆነው የሁሉም ግጭት ውጤት ነው የሚያመጣው። ያለፈው 27 ዓመት ይህን አሳይቶናል ብለሽ አታምኝም?

ግዮናዊት፤ አዎን ለዚህም ነው የአማራ ብሄርተኞች የጎሳ ፌደራሊዝምን የምንቃወመው። የአማራ ብሄርተኝነት ንቅናቄ (አቤን) አቋሙም እንዲሁ ነው የጎሳ አስተዳደርን ለመቀየር።

አስፋው፤ እንዲህ ከሆነ እንዴት ጠንካራ አማራ ከጎሳዊ ግጭት ያድነናል ትያለሽ? ላለፉት 27 ዓመት በዚህ ክፉ "experiment" እንዳየነው የጎሳ አስተዳደር በጎሳዎች መካከል ግጭት ያመጣል። በሺዎች የሚቆጠሩ ግጭቶች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ህይወት አልፏል፡ እኔ ሀገር አልባ ሆኛለው።

ግዮናዊት፤ ምን ማለትህ ነው?

አስፋው፤ አንቺ ከደብረ ማርቆስ ከአማራ ክልል በመሆንሽ የኛን ከአምራ ከአዲስ አበባ ውጭ የምንኖረውን አማሮች ታሪክ አትረድቱም። ከኔ ቤተሰቦች ሀገር በምዕራብ ሀረርጌ በጣም ብዙ አማሮች ሁለተኛ ዜጋ ላለመሆን ለህይወታቸው ሁልጊዜ ላለመስጋት ብለው ወደ አዲስ አበባ ተሰድደዋል። ይህ የሆነው ከ1983 ጀምሮ ነው። እስካሁን። ትውልድ ተሰድዷል ሀገር አልባ ሆኗል። ልጆች ሀገሬ ነው ብለው መጎብኘትም አይችሉም። በአካል መሄድ ይችላሉ ግን ሀገርህ አይደለም ስለሆነ የቦታው መንፈስ ዋጋ የለውም። የጎሳ አስተዳደርን በዚህ በተጨባጭ መንገድ ጉዳቱን አይተነዋል ደርሶብናል። ምናልባት እናንተ አምራ ክልል ያላችሁ ምንም ቢደርስባችሁ ሀገር አልባ አልሆናችሁም። የረሳችሁ ከሃዲዎች ናቸው የሚጨቁኗችሁ የነበሩት። ግን ሀገር አላችሁ ዛሬ በነፃነት ዘመን ሀገር አላችሁ። እኛ ግን የለንም። ሰለዚህ ስለ የጎሳ አስተዳደር ጉዳት እናውቃለን። ይህን አውቀን ነው አማራ እራሱን ማደራጀት ለኛ ዋጋ እንደሌለው የምናውቀው።

ግዮናዊት፤ አሳዛኝ ነው ግን መቼስ መደራጀታችን ይጠቅሟችኋል። ቢያንስ በገንዘብ እና ሌላ ነገር ድጋፍ ልንሰጣችሁ እንችላለን።

አስፋው፤ እስቲ ወደ ሌላ ርዕስ እንሂድ… ለምንድነው የአማራ ብሄርተኝነት የሚያስፈልገው ብሄ ስጠይቅሽ በመጀመርያ እና አጥብቀሽ የነገርሽኝ ስለ አማራ ላይ የደረሰው በደል ነው። ሌሎችንም ሳናግር ስለ አማራ ብሄርተኝነት አንድ ገጽ ከጻፉ 70% ስለ አማራ መጨቆን ነው። ይህ የ«ጭቁን» ስነ ልቦና (victim mentality) እንዲሰፍንብን አያደርግም? ይህ አይነት አስተሳሰብ ደግሞ ጎጂ አይደለም እንደ ጥቁር አሜሪካኖች፤ አቦሪጊኖች፤ ኦሮሞ ብሄርተኞች ወዘተ ማንነታችን ከመጨቆን ጋር አቆራኝቶ ወደ ታች አይጎትተንምን?

ግዮናዊት፤ እውነት ከሆነ ተጨቆንኩኝ ማለት ምን ጉዳት አለው? እውነት ነው። መካድ የለበትም። እውነቱን ካላመንን ደግሞ ወደ ፊት ሊደገም ይችላል አጥፊዎቹም ላይማሩ ይችላሉ እኛም ይቅር ማለት ያቅተን ይሆናል።

አስፋው፤ እውነት እማ እውነት ነው። ይካድ አይደለም የምለው። ምን ላይ እናተኩራለን ነው ጥያቄው። አዎን ጥቁር አሜሪካኖች እጅግ ተጨቁነዋል። ግን ያንን ከማመን አልፎ ማንነታቸውን ከመጨቆን ጋር አያይዘው ምንም ነገር ጉዳይ ላይ መጨቆናቸውን እንደ ምክንያት ሰበብ ይጠቀማሉ። (ያው በጅምላ እያወራን ነው ነገሩን ለማቅለል)። ስለዚህ እራሳቸውን አቅም አልባ (disempower) አድርገዋል። ለሚደርስባቸውም ሊሚያደርሱትም ሃላፊነት መውሰድ አቅቷቸው ሃላፊነቱም ምክንያቱም ሁል ጊዜ ጭቆና ይሆናል። ይህ ህብረተሰቡን እንዴት እንደጎዳው እናውቃለን። አምራ ብሄርተኛው ዛሬ ሲያወራም እንዲሁ ነው የሚሰማኝ። ስለደረሰበት ጭቆና በደምብ አሳምሮ ይናገራል። ምን ይመስልሻል?

ግዮናዊት፤ አዎ ስለ victim mentality እና ክብር ማጣት አውቃለሁ። ግን ይህን በኛ አማራ ብሄርተኞች አላይም። ሰለባ ሆነናል እና እንደገና እንዳይደገም መደራጀት እና መስራት አለብን ነው ጉዳዩ።

አስፋው፤ ጥሩ ነው የበታችነት ስሜት ከሌለ። ግን አይመስለኝም። የድሮ አማራ ቢበለም ተበድያለሁ አይልም ጸጥ ብሎ እራሱን ይጎላብታል እንጂ። ሽንፈትን በፍፁም አያምንም፤ ቢያውቀውም አያምንም። ይቅርታ ጠይቁኝ አይልም። የድሮ አማራ በትንሽ ቁጥር የሆኑ ህወሓቶች ተገዛሁኝ በገዛ ሀገሬ ተጨቆንኩኝ አይልም። ይህ እማ ጉድ ነበር የሚባለው! መቼም አያምነውም። የራሴ ጥፋት ነው ብሎ ወደ ራሱን ማስተካከል ቶሎ ይሻገራል። የዛሬው ትውልድ ግን ህወሓት እንዲህ አድርጎናል እያለ ይደጋግማል። እነ ይሄንን እንደ ታላቅ የአዕምሮ ሽንፈት ነው የማየው። ይቅርታ አድርጊልኝ እንጂ ያሳፍረኛል። ዝም ብለን ስራችን ነበር መስራት ያለብን።

ግዮናዊት፤ ታድያ አሁን ስራችንን እየሰራን ነው። ግን ልክ ነህ ቢያንስ ባሁኑ ወቅት ስለበደል ማውራት አቁመን ወደ ስራ መግባት አለብን።

አስፋው፤ ሌላ ጉዳይ… ምንድናቸው እነዚህ ከመካከላችሁ ሆነው ጸንፈኛ ሃሳቦች የሚያራምዱት። የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ዋጋ የለውም እስከ ኢትዮጵያ ፈርሳለች የሚሉ አሉ። አንቀጽ 39 ችግር የለውም የሚሉ አሉ። በጠቅላላ በጎሳ ብሄርተኝነት የሚያምኑ አሉ ከአማራ ጨቋኝ ነው ከሚለው ትርክት በቀር። እነዚህ የአማራ ብሄርተኝነት ምልክቶች ናቸው?

ግዮናዊት፤ ባጭሩ አይደሉም። የሰው ልጅ በተለያየ ምክንያት ወደ ጸንፍ ይሄዳል። አንዳንዱ በስነ ልቦና ምክንያት በደል ወይንም ጭቆና በዝቶበት። እንደምታውቀው ደግሞ ምሁራኖቻችን የጸንፈኝነት ችግር አላቸው። ቀላል መፍትሄ እንደ ዝክተኝነት ይቆጥሩታል። ከባድ እና ውስብስብ መፍትሄ እንደ ሊቅነት ይመስላቸዋል። ለዚህ ነው ወደ ጽንፍ የሚሄዱት እንጂ የአማራ ብሄርተኝነት እንደዚህ አይነቱን ነበር አያምንም። ኢትዮጵያ ከሌለች እማ ምን ዋጋ አለው? ለኛ የአማራ ብሄርተኝነት ኢትዮጵያዊነትን ማጠንከርያ መሳርያ ነው። እንጂ ሌላ ፍልስፍና አይደለም።

ውይይቱ ብሌላ ቀን ይቀጥላል…

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!