Thursday 23 August 2018

ስለ አማራ ብሄርተኝነት ንቅናቄ ልሟገት

እስቲ በጠ/ሚ አብይ የተለምዶ አካሄድ (http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/08/blog-post_10.html) ልጀምር… የድሮ ንጉሦቻችን ታላቅ ውሳኔዎች ለመወሰን ዘንድ አማካሪዎቻቸውን ሰብስበው ጉዳዩን እየገለባበጡ ከጫፍ እስከ ጫፍ ተሟገቱበት እና ፈትሹት ይሏቸው ነበር። አማካሪዎቻቸው ሁሉንም የሚቃረኑትን ሀሳቦችን ወክለው እርስ በርስ ተከራክረው አሸናፊውን (አሸናፊዎቹን) ለንጉሡ ያቀርባሉ። ንጉሡ ይህን መረጃ ተጠቅመው ይወስናሉ። ይህ ትውፊታችን ነው።

በአማራ ብሄርተኝነት ፅንሰ ሃሳብ አልስማማም። ሆኖም ሃሳቡን በሚገባው ለመረዳት እና ለመፈተሽ ሃሳቡን ደፌ ለመሟገት እወዳለሁ። በአማራ ብሄርተኝነት እና ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ያለው ውይይት ትንሽ የረከሰ ነው ማለት ይቻላል። ውይይትም ማለት አይችላልም። በስድብ፤ ዘለፋ እና በመግባባት እጦት የተሞለ ነው። አንዱ ወገን (እዚህ ላይ እራሴን አካትቼ ነው የምናገረው) ለሌላው ወገን አይቆረቀሩምጅ("empathy" የለም)። የዚህ ጽሁፍ አንዱ አላማ ይህንን ለማስተካከል ነው።

ሌላው አላማ ይውይይት ነጥቦቹን ለማጠንከር ነው። ይህን ማድረግ የሚቻለው የሌላውን ወገን ክርክሮች ስንመለከት ጠንካራ ጎኑን (http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/03/blog-post_21.html) በማየት ነው። ፉክክር ላይ ደካማ ጎን ላይ እናተኩራለን። ገምቢ ውይይት ላይ ግን ጠንካራ ወገን ላይ ነው ማተኮር ያለብን። ስለዚህ ከአማራ ብሄርተኝነት መከራከርያ ነጥቦቻቸው ደካማ ወይንም ስሜታዊ ወይንም መሰረት የሌላቸውን ነጥቦች ትተን ምክንያት እና አቅም ያላቸውን ነጥቦች ማየት ይገባል።

ክዚህ ጽሁፍ ልመልሰው የምፈልገው ጥያቄ ይህ ነው፤ « ለመን በአማራነት መደራጀት አስፈለገ በኢትዮጵያዊነት መደራጀት አይሻልም ወይ?»። ለዚህ ጥያቄ አጭር መልሱ ይህ ይመስለኛል፤

1. የጎሳ ብሄርተኝነት አሁንም በኢትዮጵያ ዙርያ ሰፍኗል እያደገም እያለ ነው እነ ጠ/ሚ አብይ ለመቀነስ ምንም እየሞከሩ ቢሆንም። የጎሳ ብሄርተኝነት በደምብ ያልነገሰው ቦታ የአማራ ክልል ነው። ሌሎች ክልሎች በሙሉ ፖለቲካቸውን በጎሰኝነት እና ጎሰኝነት ብቻ አደራጅተዋል።

2. የዛሬው ሁኔታ ይህ በመሆኑ እና ሀገሪቷ ለ27 ዓመት በጎሳ አስተዳደር ፕሮፓጋንዳ መሞላቱ ለአማራው ህልውና እና ጠቃሚ ስልት (strategy) ሲባል ለአማራው በጎሳ ብብሄርተኝነት መልክ መደራጀት ይመረጣል በኢትዮጵያዊነት ወይንም አንድነት ከመደራጀት ይልቅ።

3. የአማራ ህዝብ ላለፉት 27 ዓመት ስለተጨቆነ እና የሀገራዊ ብሄርተኝነት ራዕይ አልሰራም የሚል አመለካከት አንዳንዱ ላይ ስላለ የአማራ ህዝብ የሀገራዊ ብሄርተኛ የሆኑት ድርጅቶችን ደግፍ ቢባልም በሙሉ ልቡ አይደግፍም።

4. ሀገሪቷ በጎሳ ብሄርተኝነት ስለጥለቀለቀች ከአማራ ውጭ ለሀገራዊ ብሄርተኝነት ያለው ድጋፍ እጅግ ዝቅተኛው ነው የሚሆነው። የነ ለማ ቡድን ኢትዮጵያ ብሄርተኛ ቢሆንም ፖለቲካ ውድድር ቢካሄድ (እንደ ምርጫ) የኦሮሞ ብሄርተኞች በቀላሉ እነ ለማ ቡድንን ያሸንፏቸዋል። ሰለዚህ በመጨረሻ የሀገራዊ ብሄርተኛ ፓርቲዎች ከአማራ ውጭ ኢሚንት ድጋር ይኖራቸዋል በአማራ ክልል ደግሞ ደካማ ድጋፍ ይኖራቸዋል። ስለዚህ ሀገር ዙርያ ሲደመር የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ንቅናቄው ደካማ ይሆናል ከጎሳ ብሄርተኝነት አንፃር። የጎሳ ብሄርተኝነት በደምብ አይሎ አሸናፊ ሆኖ ይገኛል።

5. ይህ ብዙ ድጋፍ የሌለው የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ፓርቲ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነትን የሚደግፈው ህብረተሰብ ከነ አማራውን በሚገባው መወከል አይችልም ኃይሉ ከጎሳ ብሄርተኞች እጅግ ደካማ በመሆኑ። በድርድር ጠረጵዛ፤ ፓርላማ፤ ወይንም በፖለቲካ ኃይል ሙግት የሀገራዊ ፓርቲው ይጨፈለቃል።

6. ገን አማራው በአማራ ብሄርተኝነት ስር ከተደረጀ ለአመታት የተከማቸውን ብሶት እንደ ኃይል ተጠቅሞ ጠንካራ አማራውን በማንኛውም ደረጃ መወከል የሚችል ድርጅት ይገነባል። አሁን ባለው የጎሳ ብሄርተኝነት ያጥለቀለቀው የሀገራችን የፖለቲካ ሁኔታ የአማራ ህዝብን የብሶት ስሜት እንደ ኃይል ተጠቅሞ ጠንካራ እና ቋሚ ድርጅት ማቋቋም ለአማራው ህልውና ግዴታ ነው።

7. ጠንካራ የአማራ ፓርቲ ከተቁቁመ ሌሎች የጎሳ ፓርቲዎችን በኃይል ሚዛን ይይዛቸዋል። ምክንያቱም የአማራ ብሄርተኛ ፓርቲው የጎሳ ፓርቲ ቢሆንም አማራ ጎሰኝነት በባህሪው ከኢትዮጵያ ብሄርተኝነት የተቆራኘ ስለሆነ። በዚህም ብምክንያት የአማራ ብሄርተኝነት ፓርቲው ከክልል ውጭ ላሉት አማሮች ያገለግላል።

እኔ እንደሚመስለኝ የአማራ ብሄርተኝነት ንቅናቄ መኖር ምክንያት ባጭሩ ይህ ነው።

እስካሁን ባየሁት የተለየዩ ሰዎች አስተያየት ሌሎች የክርክር ነጥቦች ይነሳሉ። ለምሳሌ «አምራ ከሁል ተጨቁኗል»፤ «ሌላው ሲደራጅ ልምን አማራ ይጠየቃል»፤ «በአማራ ብሄርተኝነት ምን አገባችሁ»፤ «ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች በአማራ ትከሻ ላይ ነው የተቁቁሙት»፤ «የአንድነት ኃይሎች አማራን ዘርፈውታል ነግደውታል»፤ «የአንድነት ኃይሎች ሌቦች ናቸው» ወዘተ። እነዚህ ስሜታዊ፤ ከመሰረተ ጉዳዩ ውጭ፤ ወይንም ሃሰት የሆኑ የክርክር ነጥቦች ስለሆኑ አልተጠቀምኳቸውም ክርክሩን ያደክማሉ እና።

ስለዚህ የአብን ከአንድነት ይልቅ በአማራነት መደራጀት ምክንያት እንዲህ ነው። እስቲ ህልችሁም በሁለቱም ወገን ያላችሁ ይህን አንብቡ እና እናንተም ከአቋማችሁ ተቃራኒ የሆነውን ወገን ይዛችሁ መከራከር ሞክሩ። እንዲህ እያደረግን ወደ መስማማት ወይንም በሰላም ላለመስማማት ደረጃ (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2016/10/blog-post.html) እንደርሳለን ብዬ እገምታለሁ።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!