ጃዋር መሃመድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሱ እና ለሌሎች ያቀረበለት የሠራተኞቹ ጎሳ ሰነድ (https://www.facebook.com/Jawarmd/posts/10104092557488783) አሳይቶናል።
ጥሩ ነው። ይህ ጉዳይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ መነሳቱ አይቀርም እና መወያየቱ ጠቃሚ ነው።
ሆኖም ይህ ሰነድ የተሟላ አይደለም። የሠራተኞቹ ብሄርን ነው ወይንም የትውልድ ወይንም የመኖርያ ክልልን ነው የሚያሳየው ግልጽ አይደለም። የተጻፉት ክልሎች ናቸው፤ «ሌላ»፤ «ደቡብ ክልል»፤ «ኦሮሞ ክልል»፤ «አማራ ክልል» እና «ትግራይ ክልል» ነው።
ግን ይህን አይተን ሠራተኞቹን በመጡበት ክልል ነው ያስቀመጧቸው ለማለት ይከብደናል ሌሎች ክልሎች በተለይ አዲስ አበባ ክልል ስለሌሉበት! «ክልል» ብለው ጻፉት እንጂ «ብሄር» ማለታቸው ነው ከሆነ ደግሞ ለምን እንደዛ አላሉትም ማለት ይቻላል። አየር መንገዱ ሠራተኛ ሲቀጥር ብሄሩን እንደ መረጃ ያስቀምጠዋል ወይ የሚለው ጥያቄም ይነሳል።
ስለዚህ ስለዚህ ሰነድ ከመወያየታችን በፊት ሙሉ መረጃ ያስፈልጋል። ያንን ከአየር መንገዱ ወይንም ከአቶ ጃዋር (ነግረውት ከሆነ) ካላገኘን ዋጋ የለውም።
ግን በጠቅለል ያለ መልኩ ስለ «ኮታ» (በጎሳ፤ በጾታ ወይንም በመደብ የሥራ ወይንም የትምሕርት እድል መመደብ) ያለኝን አመለካከት ልግለጽ… ጠቃሚ ከሆነ። ይህ አካሄድ አደገኛ እና ህዝብን የሚያከፋፍል መሆኑ ምንም ጥያቄ የለውም። የግጭት ምንጭ መሆኑ ኢትዮጵያም የትም የታየ ነው።
ሆኖም አድሎ የትም ቦታ ያለ ነገር ነው። ኦሮምያ ያደገች አማርኛ በደምብ የማትችል ሴት ለአየር መንገድ የአስተናጋጅ ስራ ስትወዳደር በአማርኛ ጉድለቷ ትቸገራለች። ብቁመቷም ልትቸር ትችላለች። ምናልባት በተፈጥሮ ሳቂታ ከሰው ጋር በቀላሉ የምትግባባ ላትሆን ትችላለች። መልኳም «እስከዚህ» ሊሆን ይችላል። ወዘተ። ብዚህ ዓለም «እኩልነት» የለም። የሰው ልጅ አብዛኛውን ማንነቱን ይወርሳል በትንሹ ነው የራሱ ሚና ያለበት።
እንዲህ ሆኖ መንግስት ወይንም ሌላ ተቋማት እኩልነት ውየን "fairness" ለማምጣት ጣልክቃ ገብተው ኮታ ቢጠቀሙ ይጠቅማል ወይ? እኔ የሚሻለኝ መሰረታዊ ችግሮቹ ላይ ብናተኩር ነው። የቋንቋ ችግር ካለ ይፈታ። የአድሎ ችግር ካለ ይፈታ። ቁጥር ላይ ማተኮሩ ወይንም ኮታ እንዳ አንድ መሳርያ መጠቀሙ ጉዳቱ ከጥቅሙ ያይላል ብዬ ነው የምገምተው።
ይህን ለማየት ለጀዋር ጽሁፍ የቀረቡትን አስተያየቶችን ማየት ይበቃል! ጉድ ነው ግን ያልተጠበቀ አይደለም። እስቲ ጉዳዩን ሰክን ብለን እናስብበት። በደመነፍስ አንግባበት።
በመጨረሻ ስለ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ትግሬ ብቻ ሆኗል የሚለው ዘፈን አንድ ነገር ብል ደስ ይለኛል። ትግሬዎች አላግባብ ተቀጥረው ይሆናል ቢሆንም አይገርምም እንደማንኛውም መስሪያቤት አየር መንገዱም ብዙ ሰው የሚቀጥረው በትውውቅ ነው። በህወሓት አገዛዝ ዘመን ይህ የትውውቅ ድር (network) ወደ ትግሬዎች ማዳላቱ ምንም አይገርምም። መሰረታዊ ችግሩ የህወሓት አገዛዝ ነው እንጂ ትግሬዎች አለአግባብ መቀጠራቸው አይደለም። መሰረታዊው ችግር ከተፈታ ሌላውም ይፈታል።
እኔ የትግሬ አድሎ አለ ብዬ ማልቀስ ድሮም ወድጄ አላውቅም (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/04/blog-post_16.html)። ማልቀስ እና ማማረር ሽንፈት ነው የበታችነት እና የዝቅተኝነት ስሜትን (inferiority complex) ያዳብራሉ። ሃላፊነት-ቢስ ያደርጋሉ። ሰውን ተግባራዊ ስራ ከመስራት ወሬ ብቻ እንዲሆን ያደርጋል። Empower ከማድረግ disempower ያደርጋል። ይህን ችግር አንድ በደንብ የሚያሳየን ነበር አሁንም ህወሓት ከስልጣን ከወረደ በኋላ ሰዎች ስለ ትግሬ አድሎ በማሰብ ጊዜአቸውን ሲያባክኑ ነው። ወይንም ስለ በረከት ስምዖን ሲያወሩ። አዎ ሰው ቅስለኛ ነው ግን ክብሩንም ያጣ ይመስለኛል።
No comments:
Post a Comment
ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!