Friday 3 August 2018

የበታችነት ስሜት

ሰላሳ አርባ ዓመታት በፊት ከሀገሩ የሚሰደድ ኢትዮጵያዊ ወደ ምዕራብ ሀገር ሲሄድ ከሀገሩ ይበልጥ «የሰለጠነ» እና «የበለጸገ» ሀገር አግኝቻለሁ ብሎ ያስቡ ነበር። የምዕራብ ሀገሮች በሀብት፤ በብልጽግና፤ በግብረ ገብነት፤ በቅልትፍና (efficiency)፤ በንፅህና ወዘተ ከኢትዮጵያ የላቁ መሆናቸው አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ያምን ነበር።

ሆኖም ግን ስደተኛው ምዕራብ ሀገሮችን ቢያደንቅም የሚተችባቸው ጉዳዮች ነበሩ። ለምሳሌ «ዘረኝነትን ያራምዳሉ» ይላል። በአዲስ ቅኝ ግዛት ታዳጊ ሀገራትን ያጠቃሉ ይዘርፋሉ። ኢትዮጵያ ለቅኝ ግዛት ስለማትመች እነ አሜሪካ ካዷት እና በደርግ አይነቱ አረመኔ መንግስት በማርክሲዝም እንድትገዛ አደረጉ። በተለያዩ ሀገራት ሕጋዊ የሆኑ መንግስታትን ይገለብጣሉ። ወዘተ። ኢትዮጵያዊ ስደተኛው ልሂቃኑም የምዕራብ ሀገሮችን በዚህ መልኩ ይከሱ ነበር።

በርካታ ስደተኞች እንደዚህ በማለት የምዕራብ ሀገሮችን ተችተው ሀገራቸው ኢትዮጵያ ችግሮች ቢኖሯትም ከነዚህ ሀገሮች በማንነት ደረጃ አታንስም ብለው ያምኑ ነበር። በዚህ ምክንያት የሀገር የማንነት የበታችንነት ስሜት (inferiority complex) ገና ብዙ አላደረባቸውም። በኢትዮጵያዊነቱ ያለው ኩራት ብዙ አልተቦረቦረም ነበር።

ግን ጊዜው ባለፈ ቁጥር ኢትዮጵያ «አልሻሻል» ስትል ባንጻሩ የምዕራብ ሀገሮች በብልጽግና እይናሩ እና አንዳንድ ልውጦች ሲያደርጉ የፕሮፓጋንዳ ስልታቸውም እየዳበረ ሲሄድ ኢትዮጵያዊ ስደተኛው በአሙሮው የምዕራቡን ዓለም እያበለጠ ሀገሩ ኢትዮጵያን እያሳነሰ ሄደ። ቀስ በቀስ የበታችነት ስሜት (inferiority complex) እያደረበት ሄደ። የህ የበታችነት ስሜት ወደ ሀገር ቤትም ገባ።

ወደ ምዕራብ ሀገር የተሰደደ ኢትዮጵያዊ ደህና ገቢ ማግኘት እና ሃብት ማከማቸት ቻለ። ስደተኛው ድሮ ቢገጥመውም ባይገጥመውም የሚያማርረው ዘረኝነቱ እየቀነሰ ሲሄድ አየ። ለነገሩ ዘረኝነቱ ድሮም ኑሮውን ከማሻሻል አልከለከለውም ነበር። አህን ግን ጭራሽ በጥቁርነቱ ስራ ከማጣት ማግኘት ጀመረ! ባሜሪካ ልጆቹ በጉብዝናቸው ብቻ ሳይሆን የጭቁን (ጥቅር) ዘር በመሆናቸው ስኮላርሺፕ ማግኘት ጀመሩ። የአሜሪካ ኑሮ ከድሮም ይበልጥ እየተመቸ ሄደ።

ይህ ስደተኛ ኑሮው «እየተሳካለት» በሄደ ቁጥር አሜሪካ በሱ አይን ይበልጥ እያማረች ሄደች። ፍትሐዊና መሐበራዊ ስነ ሥርዐቱን ከድሮም ይበልጥ ማደነቅ ጀመረ። ለሴቶች፤ ለልጆች፤ ለጥቁሮች ወዘተ ያለው «መብት» እና ጥንቃቄ ከኢትዮጵያ ጋር ሲያነጻጽረው ይገርመዋል። በፖለቲካ ደረጃ «ዴሞክራሲ» አምላኩ ሆነ «ሲኤንኤን» (CNN) መላዕክቱ ሆነ። በአንጻሩ ኢትዮጵያ በስደተኛው አይን እየቀነሰች እየወረደች ሄደች። አልሻሻል አለች እየባሰችም ሄደች። ስደተኛው ሀገሩን በጎበኛት ቁጥር ከአሜሪካ ጋር እያንጻጸረ ዘመዶቹን ያደነቁራል። በአሜሪካ እና ኢትዮጵያ ያለውን ልዩነት ለማሳየት ያህል ዘመዱን ከ«ሀገር ቤት» ለመውጣት በርካታ አስር ሺዎች ዶላር ይከፍላል።

ዛሬ በኛ በኢትዮጵያውያን የዝቅተኘት መንፈስ በደምብ አድሮብናል ማለት ከእውነት የራቀ አይመስለኝም። ግን ይህ መንፈስ እውነትን ነው የሚያንጸባርቀው? እውነት ዝቅተኛ ህብረተሰብ ነን? ወይም ሀገራችን ዝቅተኛ ነው? ይበልጥ ታላቅ የሆነው ጥያቄ ሙሉ ሰው ለመሆን ወይንም በዘመኑ ቋንቋ «መሻሻል» ከፈለግን እንደ ምዕራቡ ዓለም መሆን ይኖርብናል? ምናልባት ዘፈናችን ጭፈራችን ምግባችንን ለትዝታ ብለን ጠብቀን በሌላው በሙሉ እንደነሱ እንደ ምዕራባዊያን መሆን ይኖርብን ይሆን?

እዚህ ላይ በቀለም ትምሕርት ከምንማረው በሚዲያ ከምንሰማው ፕሮፓጋንዳና ተራ «እውቀት» ወጥተን እናስብ። በአዲሱ ቅን ግዛት የተገዛውን አእምሮአችንን ነፃ እናውጣው የብዥታ መነጽራችንን እንጣል። በመጀመርያ እስቲ ምንድነው «ስልጣኔ» ብለን እንጀምር። ጥያቄውን በምሳሌ ኃይል ለመመርመር ታዋቂውን የሮሜን ስልጣኔን እንመልከት።

በክርስቶስ ዘመን በርካታ አይሁዶች ወደ ሀገራቸውን ወርሮ የገዛው ሮሜ ይፈልሱ ነበር። አንድ አይሁድ ወደ ሮሜ ሲሄደ ዛሬ ኢትዮጵያዊ ከሀገሩ ወደ አሜሪካ እንደመሄድ እናመሳስለው። ሮሜ ሀብታም ነበረች። «ስደተኞችን» መጤዎችን ትቀበላለች ታስተናግዳለች ታበለጽጋለች። ውጣ ውረድ ቢኖረውም መጤዎች የሮሜ ዜጋ የመሆን እድል አላቸው። የሮሜ ዜግነት አንደ ይሁዳ ዜግነት በጎሳ በብሄር በደም የተወሰነ አይደለም ማንም የሮሜ ዜጋ መሆን ይችላል። የሮሜ ፍርድ ቤቶች በደምብ ይሰራሉ በተለይ ለሮሜ ዜጎች እውነተኛ ፍትሕ ይሰጣሉ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ችግር ባጋጠመው ቁጥር አይሁዶች ሲገሱት ሲሉ የሮሜ ዜግነቱን ተጠቅሞ ፍርድ ይጠይቃል! በሮሜ ፍርድ ቤት ትክክለኛ የፍርድ ሂደት እንደሚጠብቀው ስለሚያውቅ ነው። የሮሜ መንግስታዊ አስተዳደር ፍፁም ባይሆንም ከሌሎች አንጻር «የሰለጠነ» ነበር። «ዴሞክራሲ» አይነት ከነ ምክር ቤት አለው። በሮሜ የማሕበራዊ ብረ ገብ አለ። የሴቶች «መብቶች» ከሌሎች ሀገሮች ከይሁዳ ይልቅ የተከበሩ ናቸው። በስነ ሥርዓት  በኩልም ሮሜ የስለጠነች ናት። መንገዶቿ ንፁ ናቸው። መንገደኛ ለመንገደኛ ጎረቤት ለጎረቤት አገልጋይ ለባለጉዳይ ያለው ግንኙነት በጥቅም የተሳሰረ ሰላማዊና የተቀላጠፈ (efficient) ነው። የድሮ «ሮሜ» ስልጣኔ እንደዚህ ይመስላል።

ለዚህም ነው አይሁዶችም ሌሎችም ወደ ሮሜ የሚፈልሱት ሃብቱን እና ስልጣኔውን ፈልገው። ልክ እንደ ኢትዮጵያውያን ወደ አሜሪካ እንደምንፈልሰው «ህይወትን ለማሻሻል» ወደ በአድ ሀገር ይሄዱ ነበር። ግን ሮሜ የይሁዳ ቅኝ ገዥ ነበረች! አይሁዶች ወደ የሚገዛቸው ሀገር ነበር የሚሄዱት። ወደ ዓለምን በሙሉ በጉልበቷ የተቆጣጠረቹ ሮሜ ነበር ለተሻለ ኑሮ ብለው የሚሄዱት። ግን አይሁዶቹንም ሌሎች መጤዎችንም የሮሜ ስልጣኔ  ክፋነቷን እንዳያዩ አድርጓቸዋል አሳውራቸው። ለነሱ ሮሜ የብልጽግና ሀገር እንጂ የክፋት ሀገር አልነበረትም። ሮሜ ሀገራቸው ይሁዳ የሌላት ነገሮች ሁሉ አላት። በዚህ ምክንያት በራሳቸው ባህልና ማንነት ዝቅጠኝነት ተሰማቸው እንደ ሮሜዎች መሆነ ፈለጉ ወደ ሮሜ ህብረተሰብ ተቀላቀሉ።

ይህ ምሳሌ ስለ «ስልጣኔን» ምን ያስተምረናል? ለብዙዎቻችን ስልጣኔ ሀብት ማለት ነው። ሀብት ካለ ሌሎች ጉድለቶች አያታዩንም። ስልጣኔ «ቴክኖሎጂ» ይመስለናል። የሮሜ የከተማው ቧምቧ እና ፍሳሽ ስራ አይሁዶችን ይገርማቸው ነበር። ስልጣኔ ቅልጥፍና (efficiency) ይመስለናል። የሮሜ የመነግስት መዋቅሮች በተለይ ጦር ሰራዊቱ ግቡን በቀላሉ ያስፈጽም ነበር። ስልጣኔ ፍትሕ ነው። ስልጣኔ ግብረ ገብ እና ስነ መግባር ነው።

እነዚህን ሁሉ ስንመለከት ግን ባጭሩ ስልጣኔ ማለት ነግ በኔን በደምብ ማወቅ ነው። አካባቢዬን አላቆሽሽም ሌሎችን መንገደኞችን ውድጅያቸው ሳይሆን ንፁ አካባቢ ስለሚበጀኝ እኔ ካላቆሸሽኩኝ ሌሎችም ስለማያቆሽሹ ነው። እኔ መኪና የማሽከረክረው ሕግ አክብሬ ነው ሌሎች የመንገድ ተጠቃሚዎችን ስለምወዳቸው ሳይሆን ሁላችንም በትክክል ካሽከረከርን ሁላችንም በፍጥነንት እና በሰላም የምንፈልግበት ቦታ ለመድረስ ስለሚያመችን ነው። መንግስቴ ለደሆች እርዳታ እንዲያደርግ እወዳለሁ ሰላምን ለመጠበቅ እኔም ነገ ብወድቅ እርዳታ እንዳገኝ። ወዘተ። ይህ ነው ስልጣኔ ባጭሩ። ሮሜም አሜሪካም የትም ህዝብ ሰላምና ሀብት እያገኘ ሲሄድ ለራሱ ለግል ምቾቱ የሚሆን አሰራሮች ስነ ምግባሮች እየገባው በተግባር መዋል ይጀምራል።

ግን ይህ ስልጣኔ ከጥሩነት፤ በጎነት፤ ሰላም ወዳድነት እና ከፍቅር ጋር አይገናኝም። ነግ በኔ በጎነትም ፍቅርም አይደለም። «የሰለጠነ» ራስ ወዳድነት ነው። ማንም ከጊዜ በሚያመጣው ልምድ በኋላ የሚደርስበት ነው። ማንም ደግሞ ችግሮች ሲያጋጥሙት ካልተመቸው የሚተወው ነው። ሮሜ ለራሷ የሰለጠነች ነበር ለሌሎች ሀገሮች ግን የክፋት መዓበል ነበረች። ዛሬ አሜሪካም አውሮፓም ሌሎችም ለራሳቸው የሰለጠኑ ናቸው ግን ከጠረፍ ውጭ አይደሉም።

ስለዚህ ይህ ሀገር የሰለጠነ ነው የኔ ሀገር አይደለም ብለን የበታችነት ስሜት ሊኖረን ይግባል? በፍፁም! ስልጣኔ ማንንነት አይደለም። ስልጣኔ ይመጣል ይሄዳል በዓለም ታሪክ በተለያዩ ቦታዎች ተገንብቷል ፈርሷል። ስልጣኔ ከፍቅርና በጎነት አይገናኝም። የሰው ማንነት ግን በጎነት፤ ፍቅር፤ ሰላም ወዘተ ነው። ስለዚህ የሰው ልጅ እነዚህን የሚሽህ እስከሆነ መቼም የበታችነት ሊሰማው አይገባም! ከፍቅር ይልቅ «ብልጭልጭን» ሲያመልክ ነው ችግሩ የሚመጣው።

ይህን ተክትሎ እንደ ምዕራቡ ዓለም መሆን አለብን ብሎ ማሰቡም ተገቢ አይደለም። ለምን ብትሉ የምዕራባዊያን ርዕዮት ዓለም ከኢትዮጵያዊነት ትውፊትና ማንነት 180 ዲግሪ የተቃረነ ነው። የምዕራባዊ አስተሳሰብ የሰው ልጅ የዓለም ቁንጮ አድርጎ ያስቀምጠዋል። እግዚአብሔር የለም ወይንም ምንም ሚና አይጫወትም ይላል። ኢትዮጵያዊ ግን በትውፊታችን ፈጣሪ ነው በአምሳሉ የፈጠረን ብለን እናምናለን ሁሉ ነገራችንም ከዛ ይከተላል። ለዚህም ነው የጠ/ሚ አብይ አህመድ የይቅርታ፤ ፍቅር እና ሰላም መልዕክቶችን በደስታ እና ጉጉት የምንቀበለው። እንደዚህ አይነቱ መልዕክት የተም ምዕራብ ሀገር እንደ ህፃንነት ነበር የሚታየው። ስለ ልማት፤ ነፃነት፤ መብት ነው የምዕራብ ሀገር ውይይት። እግዚአብሔር የለምና።

ታሪክ ረዥም ነው። 500 ዓመት በፊት ቻይና ከሁሉም «የሰለጠነች» ነበር። 60 ዓመት በፊት ቻይና ወደ 40 ሚሊዮን ህዝቦቿን ገደለች ግማሽ ሀገሪቷ በርሃብ እየተሰቃየ ነበር። 2000 ዓመት በፊት ስሜን አውሮፓ በሮሜዎች ዘንድ የያልሰለጠና የአረመኔ ስፍራ ነበር። ዛሬ ደግሞ ከዓለም በሙሉ የሰለጠው ጎራ ይባላል። 60 ዓመት በፊት ኢትዮጵያ በዓለም ደረጃ ታላቅ ክብር ነበራት። ዛሬ እንደ ለማኝ ትታያለች። እኛ ኢትዮጵያዊያን ይህንን ብናስታውስ ጥሩ ይመስለኛል።

እውነት ስልጣኔ ፍቅር እና ሰላም ነው። የኛ የኢትዮጵያዊያን በዚህ ረገድ ከማንም ልናንስም ልንበልጥም እንችላለን የኛ ፋንታ ነው። ግን የሰው ልጅ በመሆናችን ከማንም አናንስም አንበልጥምም። የዝቅተኛ ስሜታችንም በምንም መለክያ ተገቢ አይደለም። እጅግ ጎጂም ነው። ሌላውን ምዕራባዊያንም ለመገልበጥ መሻህ ዋጋ የለውም ጎጂ ነው። ማንነታች ከፈጣሪያችን የተሰጠን ነውና ምንም የምናፍርበት ሊሆን አይገባም። እርግጥም ለሌሎች ምሳሌ ሆነን መገኘት ነው ያለብን ድሮ ሆነን እናውቃለን አሁንም የማንሆንበት ምክንያት የለም።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!