Thursday, 9 August 2018

የበጎ አድራጎት ድርጅት እና ማህበር ህግ ይበልጥ ይጠንክር

እንደሚታወቀው ኢህአዴግ ዘጠኝ ዓመት በፊት ባሳወጀው ህግ በሰባዊ መብት፤ የብሄር ብሄረሰብ ጉዳዮች፤ የጾታ ልጆች አካል ጉዳተኞች ጉዳዮች ወዘተ የሚሰሩ በጎ አድራጎት ድርጅቶች (በአድ) ከ90% በላይ ገቢአቸውን ከሀገር ውስጥ ማግኘት አለባቸው። ህጉ ሲረቀቅ የተተቸው ምክንያት ኢህአዴግ የሰባዊ መብት ጥሰቶቹ በድርጅቶች እንዳይመረመሩ ኣና ዓለም አቀፍም ሀገራዊም አይን እንዳይበዛበት ነው። እውነትም ህጉ የተመሰረተው ዋና ምክንያት ይህ ነው።

ግን አሁን በመጣው የፖለቲካ ለውጦች መንግሥት የሰባዊ መብት መጣስን እየተወ ነው ለህብረተሰቡም ለድርጅቶችም የመተቸት እና የይግባኝ ማለት ነፃነት ሰጥቷል። እንደ ፍርድ ቤት አይነት መዋቅሮችም እየተሻሻሉ ነው። ፖለቲካውም ወደ ሰላም እየተቀየረ ነው። ስለዚህ ሀገር ውስጥ ያለው ህብረተሰብ ስለ ሰባዊ መብት ወይንም ሌላ ጉዳይ የሚሟገት ድርጅት በሰላም እና አለ ፍርሃት ማቋቋም ይችላል። የውጭ ሀገር ድርጅቶች ወይንም ገንዘባቸውን ከውጭ ሀገር የሚያገኙ ድርጅቶች አስፈላጊ አይደሉም።

አስፈላጊ ባይሆኑም ለምን ገቢያቸውን ከሀገር ውጭ የሚያገኙ ድርጅቶች ይከልከሉ፤ ህጉ ይቀየር እና ይፈቀድላቸው። በዛውኑ ውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊዎች የሚደጉሟቸው ድርጅቶች በነፃነት ማገልገል ይችላሉ። እንደዚህ የሚሉ አሉ።

ግን ይህ በዙ ሰው የማያስበውን ችግሮች ያመጣል። ብውጭ ገንዘብ የሚመሩ ድርጅቶች የሚያንጸባርቁት የለጋሾቻቸውን ፍላጎት እና አላማ ነው። የሚሰሩት ለኢትዮጵያ ህዝብ ሳይሆን ለለጋሾቻቸው ነው። የለጋሾቻቸው አላማ ደግሞ ከኢትዮጵያ ህዝብ ፈቃድ ውጭ ሊሆን ይችላል።

ለምሳሌ የውጭ ሀገር የፖለቲካ እና ባህል በኢትዮጵያ ሊያስፋፉ ይችላሉ። ጸረ ሃይማኖት ፍልስፍኖችን እና ርዕዮተ ዓለሞችን ሊያስፋፉ ይችላሉ። ጸንፈኛ ጎሰኝነትን ሊደግሙ ይችላሉ በኃይለ ሥላሴ ዘመን እንደተደረገው። ጸንፈኛ ሃይማኖትም እንዲሁ። በተለያየ መንገዶች የውጭ ሀገር ተጽዕኖ በሀገራችን ላይ እንዲጠነክር ማድረግ ይችላሉ። ይህ ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብን ሊከፋፍል እና ሊጎዳ ይችላል እና ኢትዮጵያን ከሌሎች ሀገር አንጻር ሊያደክማት ይችላል።

ማወቅ ያለብን በጎ አድራጎት ድርጅቶች በመጀመርያ ደረጃ የለጋሾቻቸው መሳርያዎች ናቸው እንጂ የበጎ አድራጎት ሰራተኞች አይደሉም። የውጭ ሀገር ድርጅቶች ወይንም ከውጭ ሀገር ገንዘብ የሚያገኙ ድርጅቶች የዛን ውጭ ሀገር መንግስት ወይንም ሌላ ለጋሽ ፍላጎት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ያንጸባርቃሉ። የዛን ሀገር የውጭ ጉዳይ መሳርያዎች ናቸው።

ግን እንደዚህ ቢሆንም የነዚህ ድርጅቶችን መልእክት መቀበል ፋንታ የኢትዮጵያ ህዝብ ይሁን እና ለምን ይከለከላሉ የሚሉ አሉ። እውነት ነው ህዝብ የመወሰን ነፃነት ሊኖረው ይገባል። ግን ጉዳዩ እንደዚህ ቀላል አይደለም። ለምሳሌ በፖለቲካ ውድድር አንዱ ፓርቲ የሌላው 10 እጥፍ ገንዘብ ካለው የገንዘብ ኃይሉ እንዲያሸንፍ ያደርገዋል። እያንዳንዱ ግለሰብ አንድ ምርጫ ያለው የህዝባ ምርጫ ቢሆንም ገንዘብ ታላቅ ሚና ይጫወታል። ይህ ገንዘብ ለማስታወቅያ እና ለጥቅም (ጉቦ) ይውላል እና በዚህ መንገድ የሰውን ምርጫ ይገዛል። ስለዚህ የገንዘብ ሚና በምርጫ ታላቅ ነው። የበጎ አድራጎት ድርጅቶችም ጉዳይ እንዲሁ ነው። ብር ያለው ህዝብ ላይ ይበልጥ ተጸዕኖ አለው። የሀገራዊ ድርጅቶችን ያፍኗቸዋል።

ሌላው ከውጭ ሀገር ወደ በጎ አድራጎት ድርጅቶች የሚመጣ ገንዘብ መከልከል ጥቅም የሀገሪቷ ህዝብ ድርጅት መደገፍ እና ማቋቋም እንዲለምድ ነው። ለምሳሌ ህዝቡ በልጆች አስተዳደግ ዙርያ ስራ ያስፈልጋል ድርጅት ያስፈልጋል ካለ እራሱ ከኪሱ አውጥቶ ድርጅት ይመስረት። ይህ ድርጅት ሙሉ ለ ሙሉ ህዝብን ይወክላል ማለት ይቻላል። ይህ ድርጅት ህዝብ የሚፈልገውን ያደርጋል እንጂ የውጭ ለጋሾች የሚፈልጉትን አያደርግም። ይህ ነው እውነት «ዴሞክራሲ» ተጠሪነት እና ሃላፊነት።

ስለዚህ በነዚህ ሁለት ምክንያቶች፤ 1) አላግባብ የውጭ ቅኝ ግዛት ተጽዕኖ እና 2) ሀገር በቀል ድርጅቶች እንዲጎለቡ እንዳይታፈኑ ያለው ህግ እንዳለ ይሁን። መሻሻል ካለበትም ሁሉንም በጎ አድራጎት ድርጅቶች ገንዘባቸው በሙሉ ከሀገር ውስጥ ማድረግ ነው።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!