ካአማራ ክልል ውጭ የተወለድን አማራዎች እና አማራ ክልል የተወለዱ አማራዎች ትንሽ የትውውቅ ጉድለት ያለን ይመስለኛል። በተለይም የአዲሱ የኢህአዴግ ዘመን ትውልድ በዚህ ዙርያ የመረጃ እጦት አለው። በዚህ ጽሁፍ ይህንን የመረጃ እጦት ለማስተካከል እና መተዋወቅን ለማምጣት ነው የምሞክረው።
እኔ ከ«ነፍጠኛ» ቤተሰብ ነው የተወለድኩት። አያቶቼ፤ ቅድመ አያቶቼ፤ ቅድመ ቅድመ አያቶቼ የትወለዱት ከምዕራብ ሃረርጌ «ጨርጨር» ከሚባለው አካባቢ ነው። አያቶቼ ከጎጃም፤ ከአማራ ሳይንት፤ ከወሎ እና ከመራቤቴ ነበር «ነፍጠኛ» ሆነው ወደ ሃረር የመጡት።
«ነፍጠኛ» ምን ማለት ነው? ወታደሮች ከነቤተሰቦቻቸው፤ መሬት የሚፈልግ ብዙሃን ገበሬ፤ አዲስ መሬት የሚፈልግ ባላባት/ባለሃብት፤ ለአስተዳደር ስራ የተገመገመ ግለሰቦች፤ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚፈልጉ ካህነት ወዘተ። እነዚህ በሙሉ አጼ ምኒልክ አካባቢውን ከተቆጣጠሩት አብረው ወይንም በኋላ የገቡ ናቸው። የመጡበት ደግሞ ከተለያየ ቦታ ነው ግን አብዛኛው የአማርኛ ተናጋሪዎች ነበሩ።
ነፍጠኛው አንዳንዱ በደሞዝ እና ንግድ ይተዳደር ነበር። ብዙዎቹ (እንደ የኔ ቤተሰብ) ለመተዳደርያ ተብሎ መንግስት መሬት ሰጣቸው። ከፊሉ መሬት ባዶ ሰው ያልሰፈረበት የማይጠቀምበት ነበር። ሌላው ደግሞ ሰዎች (ገበሬዎች) የሚኖሩበት ነበር። የኔ ቤተሰብ መሬቶች ሁለቱም አይነት ነበራቸው የመሬታቸው ስፋት ደግሞ እጅግ ትልቅ ነበር። መሬታቸው የተነጠቀባቸው ነባር ገበሬዎቹ በአብዛኛው ጭሰኛ ወይንም ገባር ሆኑ። አልፎ ተርፎ በምዕራብ ሃረርጌ በርካታው የመንግስት እና አስተዳደር ስራ የተሰጠው ለነባሩ ሳይሆን ለነፍጠኛች ነበር። ሁሉም ሳይሆን አብዛኛው እንዲህ ነበር።
ስለዚህ የነባሩ ህብረተሰብ ቁጭቱ ባጭሩ ሁለት ነበር፤ በገዛ መሬቱ ጭሰኛ መሆኑ እና በ«ወራሪ» መስተዳደሩ። በወራሪ መስተዳደር ኢትዮጵያ ውስጥ የተለመደ ነበር በየ ጊዜው መግዛት መገዛት ስለነበር ኦሮሞም ምዕራብ ሃረርጌ የገባው በወረራ ስለነበር (ግን ከመቶ አመታት በፊት)። ሆኖም ብዙ ጊዜ ወራሪው ከነበሩ ጋር ከጊዜ በኋላ ይወሃዳል። ግን በኔ አያቶች ዘመን የሃይማኖት ልዩነት ስለነበር በቂ ጊዜም ስላልቆጠረ በምዕራብ ሃረርጌ በነፍጠኛው እና ነባሩ ብዙ ውህደት አልተካሄድም።
ይህ እንደሆነ በኔ እይታ እኛ እንደ ነፍጠኞች እና የነፍጠኞች ልጆች ሁለት ነገሮች ማድረግ ነበረብን። አንዱ ከገበሬዎች የተነጠቀውን መሬት መመለስ ከቻለ ከነ ካሳ ሲሆን ሁለተኛው ስረዓቱ በሚፈቅደው ደረጃ የነባሩ ቋንቋ እና ባህል በትምሕርት እና አስተዳደር ደረጀ እንዲንጸባረቅ ማድረግ።
ሁለቱንም ማድረግ ስላቃተን ደርግ መጥቶ የሁላችንንም መሬት ወሰደ ጭሰኛውንም ባላባቱንም የመንግስት ጭሰኛ አደረገ! የቋንቋ እና ባህል «እኩልነትንም» ማስፋፋት ሞከረ። የነፍጠኛ ዘመን አበቃ። በደርግ ዘመን የነፍጠኛውም ልጆች የነባሩም ልጆች በመንግስት አይን እኩል ሆኑ። በነገራችን ላይ በርካታ የነፍጠኛ ልጆች በተማሪ ንቅናቄው ተሳትፈው ለደርግ መምጣት ታላቅ አስተዋጾ አድርገዋል።
ኢህአዴግ ስልጣን ሲይዝ እና የጎሳ አስተዳደር እና ጎሰኝነትን ሲሰብክ ከነ «ጨቋኝ አማራ» የሚለው ትርክት እኛ የነፍጠኛ ልጆች በከባድ ተጠቃን። የቅርብ ዘሞደቼ በአማራነታቸው ብቻ ከመረሸን ለጥቂት ነው የተረፉት። ታሪኩንም ለመናገር ከብዷቸው ብዙ አይናገሩትም ነበር።
በጠቅላላ አማራው እና ሊላው እንደ «መጤ» እና «ክርስቲያን» የሚሰየመው ጉዳት የደረሰበት አካላዊ ብቻ አይደለም። ከሞላ ጎደል በሀገሩ ሁለእኛ ዜጋ ሆነ። በመንግስት ደረጃ በተለያየ መንገድ በቢሮክራሲውም በፍትህም (በፍርድ ቤት) ይጨቆናል። በማህበራዊ ኑሮ ደረጃም በየጊዜው ዛቻ እና ማስፈራርያ ያጋጥመዋል። ሙስሊም ካሎንክ መሬትህን ልቀህ ውጣ ይባላል። በየጊዜው ዘረፋ እና ግድያ ይፈጸማል። በየ ጊዜው ነገሮች ሲብሱ ፌደራል ፖሊስ ውየን ጦር ስራዊት ገብተው ወንጀለኞቹን ይረሽኗቸዋል። ግን በሌላው ጎን መንግስት ጎሰኝነትን በመስበክ ጸንፈኛ ጎሰኛ እና ሙስሊሞችን ያበረታታል። «መጤዎቹ» በጨርጨር ለ120 ዓመት በላይ የኖሩ የዛሬ ኑሮዋቸው በቢለዋ ስል ላይ ነው። በጣም ብዙዎቹ ገና 20 ዓመት በፊት ይህ ሀገራቹህ አይደለም ተብለናል ብለው ወደ አዲስ አበባ ወጥተዋል። ቀሪዎቹ በከፊል ፍርሃት ነው የሚኖሩት።
ይህ ነው ባጭሩ የአንድ ነፍጠኛ ልጅ ቤተሰብ እና ሀገር ታሪክ። እኔ አሁን ጨርጨር አልኖርም። ተመልሰህ ትኖራለህ ወይ ብባል አይመስለኝም። በአድነት ይሰማኛል እንዲሰምኝ ይደረጋል። የቋንቋ ጉዳይ አይደለም። ኦሮምኛን መቻል ግድ ነው ባይሆንም አምንበታለው። ግን አማራ በመሆኔ በመንግስት ደረጃም በ27 ዓመት የጎሰኝነት ስብከት ምክንያት በማህበረሰብ ደረጃም እንደ ሁለተኛ ዜጋ እንዳ በአድ ነው የምታየው።
ግን የደብረ ማርቆስ አማራ ይህን ስሜት አያውቀውም። በደርግ ወይንም ኢህአዴግ ወይንም በሌላ ምክንያት ከደብረ ማርቆስ ተሰድዶ አሁን ልመለስ ቢል ሀገር አለው! በአድነት እንዲሰማው የሚያደርግ የለም። መንግስትም ህዝብም ይቀበለዋል። ሀገሬን ልርዳ ቢል ልጃችን እንኳን ደህና ተመለስክ ነው የሚባለው። ሄዶ ቢኖር እንደ ማንኛውም ዜጋ በእኩልነት ይኖራል። «መጤ» አይባልም።
የደብረ ማርቆስ አማራው በኢህአዴግ ዘመን እንደ ማንም በፖለቲካ ተጨቁኛለሁ ሊል ይችላል። በአማራነቴም ተጨቁኛለሁ ማለት ይችላል። ግን ማንም ደብረ ማርቆስ ሀገርህ አይደለም ውጣ ያለው የለም። አብዛኞቹ የጨቆኑት ደግሞ «የራሱ» ሰዎች በገንዘብ ወይንም ርዕዮተ ዓለም የተገዙ ነበሩ። ህወሓት ደብረ ማርቆስ መጥቶ በቀጥታ አልገዛም፤ በወኪል (proxy) ነው ያደረገው። ከሞላ ጎደል አማራው ስለ ህወሓት ብሎ አማራውን እንዲጨቁን ነው የተደረገው። ከሃዲዎች ብዙ ነበሩ። ይህ በደብረ ማርቆስ ልጅ በአማራነቱ እንዲያፍር ሳያረገው አይቀርም። በትንሹ ህወሓት ተገዛሁኝ ብሎ ተገቢ ህፍረት ይሰማዋል። የራሴ ወንድሞች ካዱኝ ብሎ ያስባል። በራሱ መተማመን እና በራሱ በማንነቱ መኩራት እየከበደው ሄዷል።
አያችሁ የሁለቱ ታሪክ ልዩነቶች። ብዙ ነው። ሁለቱም በአማራነታቸው ቢጨቆኑም ታሪካቸው ይለያያል። የጨርጨሩ አማራ የችግሩን አመጣት ይረዳል። ቅድመ አያቶቼ ባደረጉት ነው ብሎ ይገበዋል። አሁን የሚደረገው ተገቢ ባይሆንም አመጣጡ ይገበዋል። ግን የደብረ ማርቆስ ልጁ አይገባውም። ቤተሰቡ ነፍጠኛ ሆኖ አያውቅም ነፍጠኝነት ምን እንደሆንም ላያውቅ ይችላል። የገበሬ፤ ወዛደር ወይንም ነጋዴ ልጅ ነው ማንንም አስገብሮ አያውቅም። ግን አማራ ነፍጠኛ ትምክህተኛ ነው ተብሎ ተጭቆኔ። እድል አጋጥሞት ከመንደሩ ወጥቶ ከፍተኛ ትምሕርት ከገባ የሚጠሉት ኦሮሞ እና ትግሬ ብሄርተኞች ያጋጥሙታል። ዘሮቼ ምን አድርገው ነው ይላል? ታሪኩን ያውቅ ይሆናል ግን በቀጥታ የሱ ታሪክ ስላልሆነ በተወሰነ ደረጃ ለጉዳዩ ባይተዋር ነው።
አሁን የደብረ ማርቆሱ ልጅ በአማራነትህ ተጨቁነሃል በአማራነትህ ተነሳ ሲባል አዎን አለምክንያት ተጨቁኛለሁ ብሎ ሊነሳ ይችላል። ግን የሃረጉ አማራ ምክንያቱን ይበልጥ በግል ደረጃ ያውቀዋል። የጭቆናው ምክንያት ተገቢ አይደለም ሃረር ለኔም እኩል ሀገሬ ነው ቢልም የችግሩ የታሪክ አመጣጡን ያውቀዋል። በዚህ ምክንያት ምናልባትም ስለ መፍትሄው ሲያስብ ሰከን እና ለዘብ ያለ አመለካከት ይኖረዋል። አልፎ ተርፎ ስተት ከተፈጠረ የሚጠብቀው ጉዳት እጅግ ከባድ እንደሆነ ስለሚያውቅ ከወደ ጽንፈኝነት መንቀዥቀዥ ይቆጥበዋል። የደብረ ማርቆሱ ልጅ ግን ከፖለቲቃ ቀውስ በቀር ምንም አይደርስበትም። አይታረድም። ሀገር አለው። የማንነት ኩራቱን ነው መመለስ የሚፈልገው።
ይህ ወደ መጨረሻ የሳፍኩት በሙሉ ግምቴ ነው። እንስቲ እናስብበት እንወያይበት። ይህ የኔ አመለካከት ብቻ ነው። ግን በአማራ ውጭ እና አማራ ውስጥ የተወለዱ አማሮች መከከል የታሪክ እና የልምድ ልዩነቶች በደምብ እንዳሉ ማወቅ አስፈላጊ ነው። መግባባት እና መናበብ እና መተባበር እንድንችል ስለዚህ መወያየት ግድ ይመስለኛል።
No comments:
Post a Comment
ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!