የሰርቢያ እና የአማራ ታሪክ ብዙ ልዩነቶች አሉት። ግን አንድ ሁለት ተመሳሳይ ነገሮች አሉ፤
1. ልክ እንደ ኢትዮጵያ ዙርያ አማራው እንደተበታተነው ሰርቢያኖች ዩጎስላቪያ ዙርያ ከሌሎች ጎሳዎች በጣም በይበልት ተበታትነው ይኖራሉ። በርካታ አማራ በየ ክልሉ ይኖራል። ከኦሮሞ ክልል ውጭ የሚኖር የኦሮሞ ህዝብ ከዚህ አንጻር እጅግ አነስተኛ ነው።
2. ከዮጎስላቭ መሪ ቲቶ ሞት በኋላ የዩጎስላቪያ የተለያዩ ጎሳዎች ከሰርቦች በቀር ጎሰኝነታቸው እያየለ ሲሄድ ከሀገሪቷ እንገንጠል ማለት ሲጀምሩ ሰርቦቹ እንደ መልስ «ጠንካራ» ጸንፍ የያዘ በእሾኽ በእሶኽ የሚያምን መሪ ሚሎሴቪች ወደ ስልጣን አመጡ። የሚሎሴቪች ምሳሌ የአማራ ብሄርተኝነት ነው።
እዚህ ላይ አንድ ነጥብ… ስሎቦዳን ሚሎሴቪች «አክራሪ» ሰርብ ቢሆንም በምዕራባዊያን የተከሰሰበት ወንጀሎች ሃሰት ናቸው ማለት ይቻላል። የጎሳ ወንድሞቹን ሰርቦቹን ባሉበት እካካከልላቸዋለው ብሎ ነበር የሚዋጋው ልክ እንደ ሌሎቹ ጎሳዎች ክሮአቶች፤ ቦስኒያኖች፤ ኮሶቮች እንደ ሚዋጉት። ስለዚህ ያአማራ ብሄርተኞች እንደ ሚሎሴቪች ናቸው ማለት ወንጀለኞች ናቸው ማለት አይደለመ።
ሆኖም ሚሎሴቪች እና ደጋፊዎቹ ታላቅ የፖለቲካ ስህተት ነው የፈጸሙት። ሰርቢያኖቹ ሶስት ነገሮች አዩ፤
1. ስሎቬኒያኖቹ፤ ክሮአቶቹ፤ ቦዝኒያኖቹ እና ኮሶቮቹ ሁሉ መገንጠል እንደሚፈልጉ
2. እነዚህ በሙሉ ሰርቢያ ውስጥ ብዙ ነዋሪ የላቸውም ግን ሰርቢያኖች በነዚህ «ክልሎች» ብዙ ናቸው። መገንጠል ከመጣ ስሎቬኒያ፤ ክሮኤሺያ፤ ቦዝኒያ እና ኮሶቮ የሚኖሩ ሰርቦች ናቸው ዋና ሰለቦች ሀገር የለሽ የሚሆኑት። ሰርቢያ ውስጥ ብዙ ስሎቪኖች፤ ክሮአቶች፤ ቦስኒያኖች፤ ኮሶቮዎች ስለሌሉ እነሱ ግድ አልነበራቸውም መገነጣጠልን ይፈልጉታል።
3. የምዕራብ ዓለም በሙሉ ዩጎስላቪያ እንዲበታተን እና ሰርቦቹ እንዲንበረከኩ (ሩስያን ለመጉዳት እና የአውሮፓ ህብረትን ለማጠንከር) ነው የሚፈልገው።
የሰርቢያ ልሂቃን ይህን አይተው በዜዴ የሀገራቸውን ጥቅም አስከብሮ ከመስራት ፋንታ ለምሳሌ ስሎቪኒያን እና ክሮኤሺያን በስምምነት ለቆ አቁምን በቦዝኒያ እና ኮሶቮ ላይ ከማዋል ፋንታ ሁሉንም እንዋጋ አሉ። ሰርቢያ እንዳለ ምዕራብ አለሙን ሲዋጋ ማን እንዳሸነፈ እናውቃለን። አሁን በክሮኤሺያ የሚኖሩት ሰርቦች፤ በቦዝኒያ የሚኖሩት ሰርቦች እና በኮሶቮ የሚኖሩት ሰርቦች የዚህ ያልበሰላ ፖለቲካ አካሄድ ዋና ሰለቦች ሆነው ቀርተዋል። ሰርቢያም እጅግ ተጎሳቁላለች ሞራልዋ ሞቷል።
የአማራ ብሄርተኝነት እሾኽ በ እሾኽ አመለካከትም እንዲሁ ይሆናል ብዬ እሰጋለሁ። በነ ኦሮሚያ፤ ቤኒሻንጉል፤ ደቡብ፤ ሶማሌ ወዘተ ክልሎች የጎሳ ብሄርተኝነት ጠንከር ያለ ነው። የነዚህ ክልል «ጎሳዎች» ከክልላቸው ወጭ በብዛት አይኖሩም። አሉ ግን ብዛታቸው ውስን ነው። አማራው ግን በሚሊዮን የሚቆጠር ከክልል ውጭ አለ።
አማራው ጠንክሮ በአማራነቱ ቢደራጅ እና ከሌሎች የጎሳ ድርጅቶች (ወኪሎች) ሲደራደር እነሱ ለሚያደርጉት እሾኽ በ እሾኽ (tit for tat) ልመልስ ከሆነ ውጤቱ ምን ይሆን። አማራው ምንም ጠንካራ ቢሆን ከግዴለሽነት ጋር መዋጋት አይችልም። ኦሮሚያ አማራው ዜጋ አይደለም ቢል የአማራው መልስ በአማራ ክልል ያሉትን ኦሮሞዎችን እንደዛው ማደረግ ነው። ግን ኦሮሞ ብሄርተኛው ግድ የለውም እንደዚህን ለመሰዋት ዝግዱ ነው።
አያችሁ ሁኔታው ሚዛናዊ አይደለም። Asymmetrical ነው። አማራ በየቦታው አለ ሌላው ግን ክልል ውስጥ ነው። ይህ ማለት ሁለቱ ወገኖች የሚጠቀሙበት የትግል ዘዴ መለያየት አለበት። የአኖሌ ሃውልት ገንብተሃል እና የጣይቱ ሃውልት ልገንባ (አዎ አኖሌ ታሪኩ ሃሰት ነው አውቃለው) ማለት የተሳሳተ ብድር መላሽ ፖለቲካ ነው።
አማራው ግን በኢትዮጵያዊነት ከተደራጀ በዛ ጥላ ስር በርካታ አማራ ያልሆኑም ይይዛል። እነዚህ ሰዎች ኦሮሚያ ውስጥ ውግያ ሳይፈጥሩ ግን በዘዴ ታላቅ የፖለቲካ ኃይል መያዝ ይችላሉ። ይህን ኃይል ተተቅሞ የጎሳ ብሄርተኝነትን የሚቀንሱ ፖሊሲዎችን ለማራመድ ድጋፍ አስፈላጊ ድጋፍ ይሰጣሉ። እነዚህ ፖሊሲዎች ለዓመታት ከሰሩ በኋላ የጎሳ ብሄርተኝነት ይቀንሳል። ከዛ በኋላ የጣይቱ ሃውልት ይሰራ ቢባል ማንም አያስቸግርም። ዘዴው እንዲህ ነው።
የሰርቦች እጣ ፋንታ እንዳይደርስብን። ስሜታዊ ፖለቲካ በጀግንነት እና ፍልፍና ሸፍነን አናራምድ። ከልባችን አለ bias ጉዳዩን በክፍት የሆነ አዕምሮ እናስብበት።
No comments:
Post a Comment
ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!