እንደ አብዛኛው ውሸት «አዲስ አበባ የሰፋችው ኦሮሞ ገበሬን በማፈናቀል ነው» የሚለው የተወሰነ እውነታ አለው። አዎን በኢህአዴግ አገዛዝ በአዲስ አበባ ዙርያ ያሉ ገበሬዎች ለመሬታቸው ከሚገባው እጅግ ዝቅተኛ የሆነ ካሳ ተከፍሏቸው በግዴታ ከመሬታቸው ተባረዋል። ግን ይህ ሙሉ ታሪኩ አይደለም።
እንደሚታወቀው በሀገራችን መሬት የመንግስት ነው የሚል አሳዛኝ ህግ ነው ያለው። ይህ ህግ ሲተገበር ስናይ መንግስት ባሰኘው ጊዜ የከተማም ይሁን የገጠር መሬት ከነዋሪዎች ይወስዳል። ሲወስድ ደግሞ የሚከፍለው ካሳ የ«ገበያ» ዋጋ ሳይሆን መንግስት እራሱ የሚተምነው እጅግ አናሳ ካሳ ነው። ልምሳሌ አዲስ አበባ ውስጥ ለ«ልማት» ተብሎ መሬትን መንግስት ሲወስድ የሚከፍለው ካሳ የቤትና የጊቢው አብሮ ዋጋ ሳይሆን የቤቱ (የግንቡ) ዋጋ ብቻ ነው። ለምሳሌ 100 ካሬ ላይ ቤት አለኝ ከሸጥኩት 500,000 ብር ያመጣል እንበል። መንግስት ሊወስደው ከፈለገ ግን የቤቱ ግምብ ዋጋ ብቻ እራሱ (ሶስተኛ ወገን ሳይሆን) ገምቶ ምናልባት 50,000 ብር ከፍሎኝ በግድ ይወስደዋል። በገጥር ደግሞ እንደ ክልሉ እና ዞኑ ቢለያይም አንድ ምሳሌ ልስጣችሁ። መንግስት ከገበሬ መሬቱን ሲወስድ የሶስት ዓመት ገቢውን ለካሳ ይከፍለዋል። ገጠር መሬት መሸጥ ባይኖርም የዚህ መሬት ዋጋ ከዚህ በላይ እንደሚሆን መገመት ይቻላል። የሶስት ዓመት ገቢ ሳይሆን ቢያንስ የአስር ነው መታሰብ የነበረበት።
ከዚም አልፎ ተርፎ ይግባኝ የለም። መንግስት አንዴ ትፈናቀላላችሁ ካለ ይህን ውሳኔ መታገል አይቻልም። ከመሬት ንትቅያው በስተጀርባ ያለው የገንዘብ እና የፖለቲካ ኃይል እጅግ ከባድ ነው። የኢህአዴግ ባለሟሎች አሉ፤ ኢነቬስተር ዩኖራል፤ ጉቦኛ መንግስት ሰራተኛው አለ፤ ባለ ስልጣን አለ። ባለ መሬቱ ከነዚህ ጋር መጋፋት አይችልም እና ተዛዙ ሲመጣ እሺ ጌታዬ ብሎ መንግስት የሚሰጠውን ካሳ ተቀብሎ መሄድ ነው።
ይህ ሁኔታ ያለው በመላው ሀገሪቷ ነው በአዲስ አበባ ብቻ አይደለም። ከመሬታቸው አለ አግባብ የሚፈናቀሉት ኦሮሞ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ሁሉ ናቸው። ገበሬዎች ብቻ ሳይሆን ከተሜዎችም ናቸው። አዲስ አበባን ከመሬታቸው የሚፈናቀሉትን ካየን ከአዲስ አበባ ዙርያ ካሉት ገበሬዎች ይልቅ የከተማው ተፈናቃይ ነው ይበልጥ መፈናቀል የሚጎዳው። ለምን? አራት ኪሎ 100 ካሬ ላይ የሚኖር ቤቱን ከነ ጊቢው ቢሸጠው አንድ ሚሊዮን ያገኝበት ነበር 50,000 ተሰጥቶ ይባረራል። ገበሬው ግን ሰፋ ያለ መሬት ቢኖረውም ከከተማ ሩቅ በመሆኑ ዋጋው ያን ያህል ውድ አይደለም በሚሰጠው ካሳ እና በመሬቱ እውነተኛ ዋጋ ያለው ልዩነት እንደ ከተማው መሬት አይሆንም። ስለዚህ አዲስ አበባ እና ዙርያ ሁሉም በመንግስት ከመሬታቸው የተፈናቀሉ ቢጎዱም በአማካይነት የከተማው ከገበሬው ይበልጥ ተጎድቷል።
በመጨረሻ ማን ነበር እነዚህን ገበሬዎች የሚያፈናቅለው ብለን ከጠየቅን የኦሮሚያ የኦህዴድ ቀበሌ እና ውረዳ ሰራተኞች እና የነሱ አዛዦች ናቸው። ለምሳሌ ባለ ሃብት ወይንም የአዲስ አበባ መንግስት በኢህአዴግ ድጋፍ መጥተው የለገጣፎን ባለስልጣኖች መሬት እንፈልጋለን ይላሉ። እነዚህ የኦህዴድ ባለ ስልጣኖች አላማቸው ትንሽ ካሳ ለገበሬው ሰጥቶ በትልቅ ዋጋ ለአዲስ አበባ ወይንም ለባለ ሃብት መስጠት እና በመካከል ከዋጋ ልዩነቱ ጉቦ መብላት ነው። አዲስ አበባ ውስጥም ይህ ነበር አሰራሩ። በጠቅላላ ላለፉ 27 ዓመት መሬት ለመንግስት ሹማምንት ታላቅ የጉቦ የገቢ ምንጭ እና ለኢህአዴግ ታላቅ የካድሬ መያዣ መንገድ ነበር። ስለዚህ አዲስ አበባ ሳይሆን የራሱ የኦህዴድ ካድሬ ነው አዲስ አበባ ዙርያ ያለውን ኦሮሞ ገበሬ አለ አግባብ ያፈናቀለው። አዲስ አበባ ናት ያፈናቀለቻቸው ማለት ሃሰት ነው።
ሙሉ እውነታው ይህ ነው፤ አዲስ አበባ ዙርያ ሳይሆን አዲስ አበባ ውስጥም ሀገር ዙርያም በየቀኑ ዜጎቻችን ከመሬታቸው አለ አግባብ እና አለ በቂ ካሳ ይፈናቀላሉ። የሚፈናቀሉት ደግሞ ኦሮሞዎች ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ነው። ችግሩ በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ መካከል ሳይሆን የመሬት የመንግስት ነው የሚለው ፖሊሲ (http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/03/blog-post_47.html) ነው። መሬት የግል ቢሆን እነዚህ ገበሬዎች በነፃነት በሚያስደስታቸው ዋጋ መሬታቸውን ሽጠው ነበር።
No comments:
Post a Comment
ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!