ቆቅ ሞቷን ጠራች ይባላል።
የኢትዮጵያ ብሄርተኞች በቂ እንዳልተደራጀን የታወቀ ነገር ነው። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አባላት ያላቸው ድርጅቶች ሊኖርን ይገባል ግን የለንም። በርካታ ሚሊዮኖች ብዙሃን አለን ግን ልሂቃን፤ መሪ እና ድርጅት ላይ እጅግ ደካማ ነን።
በተዘዋዋሪ የጎሳ ድርጅቶች ያው የጎሳ በመሆናቸው ትብብር እና አንድነት ስላላቸው ጠንካራ ናቸው። ሁከት እና ችግር ስለሚያጎለብታቸው እየጠነከሩም እየሄዱ ነው።
በዚህ ሁኔታ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ዋና ስራ መደራጀት እንደሆነ ግልጽ ነው። የህልውና ጉዳይ ነው። የዜግነት ፖለቲካችንን ካላራመድን እና ግዙፍ ድርጅቶች ካልፈጠርን እኛም ሀገራችንም እንጠፋለን። ጠ/ሚ አቢይ ቢፈልግም ይህን ሊያደርግልን አይችልም። እኛ የራሳችንን ድርሻ ካልሰራን እሱም አቅም ያጣል። ለነገሩ እስከ ዛሬም ሀገራችን ላሳለፈችው ችግር ዋና ምክንያት የኛ በሚገባው አለመደራጀት ነው።
በዚህ ሁኔታ፤ ደካማ ሆነን፤ ዋና ስራችን እራሳችንን ማጎልበት እና ማደራጀት በሆነበት ጊዜ ጠላቶች ማፍራት ጅልነት ነው። አሁን ሁሉንም የማቀፍ ጊዜ ነው። የጊዜ መግዥያ ጊዜ ነው። ጠ/ሚ አቢይ፤ የጎሳ ብሄርተኞች፤ ህወሓት ወዘተ ሁሉንም ተጠንቅቀን ይዘን ወዳጅ መስለን መገኘት አለብን። የመደራጀት ስራችንን መስራት ነው ያለብን። ብልህ ፖለቲካ ማለት ይህ ነው።
ለምሳሌ የአዲስ አበባ ሲቪክ ድርጅት ለማቋቋም ሲጀመር ስለ ከንቲባው አለማንሳት። ወይንም ማሞገስ። ጽሁፍ እና ፖስተሮች በአማርኛ ብቻ ሳይሆን በኦሮምኛም ማዘጋጀት። አዲስ አበባ ለአዲስ አበቤዎች አይነት መፈክር ትቶ በቀላሉ «ለአዲስ አበባ ነዋሪ ሁሉ መብት ማስከበር» ነው ተልዕኯችን ማለት ነው! ወዘተ። ሀሳቡ ግልጽ ይመስለኛል።
ግን ይህን ከማረግ ፋንታ እንደ ቆቛ እንጮሃለን! ምንም ሳይኖረን አፍ ብቻ እንሆናለን። ባለን ጊዜ አንዴ ከጎሳ ብሄርተኞች ጋር አሁን ደግሞ አንዳንዶቻችን ከጠ/ሚ አቢይ ጋር ግብ ግብ እንገባለን። ገና ለመታገል አቅም ሳይኖረን ጠላቶች እናፈራለን። ይህን ማቆም አለበን፤ የህልውና ጉዳይ ነው። የ50 ዓመት የፋራ ፖለቲካችንን ማቆም ካላቆምን ሌላ እድል የሚኖረን አይመስለኝም።
አካሄዳችን መሆን ያለበት መጀመርያ ኃይልን መሰብሰብ። ይህን ለማድረግ ባይጥመንም የሚያስፈልገውን ነገር ማድረግ። ከሁሉም ጋር አብሮ መስራት ያስፈልጋል። እራስን አለማጋለጥ ያስፈልጋል። ኃይልን ከሰበሰብን በኋላ ደፈር ያሉ አቋሞች መያዝ እና ስራዎች መስራት።
በመጨረሻ ማለት የምፈልገው... ምን አልባት በመጮህ፤ መተቸት እና በመውቀስ ህዝባችን እንዲማረር እና እንዲቆጣ አድርገን በቀላሉ ይደራጃል ብለን እናስብ ይሆናል? ለዚህ ይሆን ብዙዎቻችን ዋናው የመደራጀቱን ስራ ትተን 100% ጊዜአችንን በመተቸት እና መወንጀል የምናጠፋው?
ይህ ከሆነ በጣም የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው። አካሄድ ውድቅ እንደሆነ የ27 ዓመት ማስረጃ አለን! ለ27 ዓመት ህወሓት እና የጎሳ ብሄርተኞች ሲረግጡን ያሁሉ ሚሊዮን ህዝብ ሆነን አንዳች ግዙፍ ድርጅት ማቋቋም አልቻልንም። የወሬ፤ ጩሀት እና ትችት ፖለቲካ አልሰራም።
ህወሓት ከስልጣን የወረደው እነ ኢሳት ህዝቡ ሀውሓትን እንዲጠላ ስላደረጉ አይደለም። ህዝቡ በለቱ ኑሮ አይቷቸው ጠልቷቸዋልና! አልፎ ተርፎኦ ይህ ጸረ-ህወሓት ዘመቻ ምንም አይነት ጠንካራ ድርጅት አልፈጠረም። ያሁሉ ዓመታት ጩሀት በኋላ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ትንሿ ግንቦት 7ን ብቻ ነው ያፈራነው።
ስለዚህ የጩሀት ፖለቲካ አይሰራም። ህዝቡን በፕሮፓጋንዳ አማርሮ ማደራጀት እንደማይቻል አይተናል። ህዝቡ በእውን በኑሮው ተማርሯል። የፖለቲከኞች ስራ ይበልጥ ተማረሩልኝ ማለት ሳይሆን ማደራጀት እና ለምሬቱ ትክክለኛ መስመር ማብጀት ነው። የኛ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች የፖለቲካ ልሂቃን ይህን ማድረግ አልቻልንም። እስቲ አሁን እንሞክር።
No comments:
Post a Comment
ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!