Thursday, 18 October 2018

የአዲስ አበባ ህዝብ መደራጀት፤ እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ

ትላንት ሁለት የአዲስ አበባ ሰዎች በማይሆን ክስ ታስረዋል። ከሱም እንደገባኝ ከሆነ ወጣቶችን በ«አዲስ አበባ በከተማው ተወላጅ ነው መመራት ያለበት» መፈክር ዙርያ ማደራጀት ነው። ለዚህም አደረጃጀት ከፍልስቴም ኮንሱሌት ጋር ተባብረዋል ነው ሌላው ክስ። እነዚህ ስራዎች በፍፁም ህገ ወጥ አይደሉም እና መታሰር እንደሌለባቸው ግልጽ ነው። ሆኖም ትላንት እነዚህ እስረኞች በጭለማ ቤት እየተሰቃዩ (torture) ይገኙ ነበር። ዛሬ ደህና ፍርድ ሳያገኙ አይቀርም። መከራ ለነሱ ቢሆንም መሻሻል ነው።

በዚህ ግዳይ በርካቶች አቤቱታ እያቀረቡ ነው። ጥሩ ነው፤ እንደዚህ አይነት የማይሆን እስርን መቃወም አለብን። ግን እንደምናውቀው ፖለቲካችን ከመቃወም ወደ መስራት መሻገር አለበት። Proactive politics beats reactive politics anytime።

መሰራት ያለበት ስልታዊ አደረጃጀት ነው። በመጀመርያ ለምንድነው «ወጣቶችን» የምናደራጀው? ሰራተኛው የት አለ? ወዝ አደሩ የት አለ? የቢሮ ሰራተኛው የት አለ? ወላጆች የት አሉ? ጡረተኞች የት አሉ? መከከለኛ መደቡ የት አለ? ሃብታሙ የት አለ? «የተማረው» የት አለ? ምሁራኑ የት አለ? ልሂቃኑ የት አለ? ለምንድነው «ወጣቱ» (እውነቱን ለመናገር ስራ የሌለው ወጣት) ሸክሙን መሸከም ያለበት?

ይህ «ወጣትን» ማደራጀት ዘላቂነት እንደሌለው ይታወቃል። ሁሉም ህዝብ መሳተፍ አለበት ለእውነተኛ የዜግነት ፖለቲካ ወይንም የሲቪክ አደረጃጀት። ወጣቱ ተሳትፎ ሌላው ከሸሸ ዋጋ የለውም ብቻ ሳይሆን ጎጂም ሊሆን ይችላል። እንደ ሜኪናን በአራተኛ ማርሽ ማስጀመር ማለት ነው።

ሌላው ችግር ገና መደራጀቱ በተገቢው ሁኔታ አይጀምር እራስን ለጥቃት ማጋለጥ ነው። እኔ እንደሚገባኝ የአዲስ አበባ መደራጀት አላማ «የአዲስ አበባ ህዝብ መብቱ እንዲከበር» ነው። ከንቲባው የአዲስ አበባ ትውልድ ይሁን አይሁን አይደለም። የአዲስ አበባ ህዝብ መብት ከተጠበቀ ምርጫ ይኖራል እና ህዝቡ የፈለገውን ይመርጣል። ግቡ እንዲህ ግልጽ ሆኖ ካየነው እና ግቡ ላይ ካተኮርን 1) ስራችንን በትክክሉ እንሰራለን እና ይሳካልናል 2) ለጥቃት እራሳችንን አናጋልጥም!

አካሄዱ እንደሚመስለኝ እንዲህ ነው መሆን ያለበት፤

1) በጣም ሰፊ ተዕልኮ (vision and mission) ያለው ድርጅት ማቋቋም፤ ለምሳሌ «የአዲስ አበባ ህዝብ መብት እና ጥቅም ለማስከበር የሚሰራ» ድርጅት ማለት ነው። ሀ) ሰፊ ተዕልኮ ስለሆነ ለመጠቃት መጋለጡ አነስተኛ ነው የሚሆነው። ለ) ብዙ ሰዎችን በተለይም «መደራጀት» ሲባል የማይገባቸው ወይንም የሚፈሩትን ይጋብዛል። እናቶች፤ ወላጆች፤ መካከለኛ መደቡን። ሃብታሙን ወዘተ ይጋብዛል።

2) ከመፈክር በፊት መደራጀት። መጀመርያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ከፋይ አባላት ይኖረው። ከዛ በኋላ ነው መንቀሳቀስ። እንቅስቃሴው ከአቅም ጋር አብሮ መሄድ አለበት! እንቅስቃሴው ከአቅም ጋር አብሮ መሄድ አለበት! አቅም ሳይጎለበት መራመዱ ጥቃትን መጋበዝ ነው። የቅንጅት ታሪክ ይህን ነው የሚያስተምርን። ቅንጅት በመቶ የሚቆጠሩ መሪዎች እና አባላት ነበረው ከዛ ቀጥሎ እስከ ብዙሃኑ ድረስ ከሞላ ጎደል ባዶ መዋቅር ነበር። ጥቂት መሪዎች እና ብዙ ብዙሃን። መሃሉ ባዶ ነው። እነዚህ ጥቂት መሪዎች ሲጠቁ እና እርስ በርስ ሲጣሉ ማን ይተካቸው። መዋቅሩ እስከ ታች ባዶ ነበርና። ስለዚህ መጀመርያ መጠንከር ከዛ ወደ ዋና ስራ መግባት ነው ትክክለኛ አሰራር። ይመስለኛል።

የአዲስ አበባ ህዝብ ወይንም ጠቅላላ የኢትዮጵያ ህዝብ በተለያየ ወኪላዊ ድርጅቶች መደራጀት አለበት (በዜግነት ፖለቲካ ካመንን)። አለበለዛ ያው የጎሳ ፖለቲካ ማለትም የግጭት ፖለቲካ ነው የሚቀረን። ለሀገራችን ህልውና ቅድመ ሁኔታ ነው ማለት ነው። ስለዚህ ይህን ዋና ስራ በሙሉ ተሳትፎ በሰከን ያለ ብልጥ መንገድ እንስራው። ህዝብ በሙሉ እንዲሳተፍ እናድርግ።

«እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤ ስለዚህ እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ።»

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!