Showing posts with label proactive politics. Show all posts
Showing posts with label proactive politics. Show all posts

Thursday, 25 October 2018

የሀገራችን የኢትዮጵያ ድህነት «የንስሐ ፖለቲካ» ነው!

የንስሐ ፖለቲካ ምን ማለት ነው? «ንስሐ» በመጀመርያ ስህተትን መገንዘብ እና ማመን ማለት ነው። «ተሳስቻለሁ»፤ «አውቄም ሳላውቅም አጥፍቻለሁ»፤ «በድያለሁ»፤ «የውሸት መንገድ ተከትያለሁ» ብሎ ማመን ነው የመጀመርያ የንስሐ ተግባር።

ይህ ስህተትን ማመን ብዙ ጥቅም አለው። በመጀመርያ እውነትን እንድናውቅ እና እንድናምን ያደርጋል። ለምሳሌ አንድ ፖለቲከኛ በማርክሲዝም አምኖ ሰዎችን «ጸረ አብዮት» ናችሁ ብሎ ጨቁኗል እንበል። ይህ ሰው መሳሳቱን ሲያምን አብሮ ማርኪስዝም ውሸት ነው፤ እውነቱ ስብዓዊነት ነው ብሎ ያምናል ማለት ነው። ንስሐው እውነትን እንዲረዳ እና እንዲቀበል አደረገው።

ሌላው የንስሐ ጥቅም የመንፈስ እርካታ ነው። የስህተት እና ሓጢአት ሸክም ከባድ ነው። ይቅርታ ስንጠይቅ ይህ ግዙፍ ሸክምን እናወርዳለን ማለት ነው። ሸክሙ ሲወርድልን ስራችንን በአግባቡ እንድንሰራ ይጠቅመናል።

ሶስተኛ የንስሐ ትቅም ተጎጂን ማጽናናት ነው። የሰው ልጅ «ይቅርታ አድርግልኝ» ሲባል ልቡ ይለሰልሳል እና ይረካል። ከበቀል ወደ ሰላም ይመለሳል። ይህ የልብ እርካታ እዚህ ላይ አይቆምም። በዳዩ ይቅርታ ሲጠይቀው ተበዳዩም የራሱን ስህተቶች እንዲገነዘብ ይረደዋል። የራሱን ስህተቶች እንዲያምን እና ይቅርታ እንዲጠይቅ ይገፋፈዋል። በዚህ መንገድ የይቅርታ፤ መግባባት እና ቅራኔ መፍታት መንፈስ በማህበረሰቡ ይንሰራጫል።

ሌላው የንስሐ ትቅም ስህተትን አውቆ ማረምያውንም ማወቅ ነው። አንዴ ስህተታችንን ካመንን ለችግሩ መፍትሄውን ማግኘት እንችላለን። በተቃራኒው ስህተታችንን ካላመንን ችግራችንን መፍታት አንችልም። ይህ ሁላችንም የምናውቀው ነገር ነው። አንድ መሪ የተሳሳተ እርምጃዎች እየወሰደ እና ችግሮችን እያመጣ እያለ ስህተቱን ካላወቀ እና ካላመነ ችግሩ መቼም አይፈታም። ስህተትን ማመን የችግር መፍታት ቅድመ ሁኔታ ነው። ስለዚህ ስህተታችንን ካመንን መፍትሄ ይመጣል።

ስለዚህ የንስሐ ሁለተኛ ተግባር ለስህተታችን የፈጠረው ችግሩ መፍትሄ አግኝቶ በተግባር መዋል ነው። ይቅርታ ከጠየቅን እና ስህታችንን ላለመድገም ከማልን በኋላ እንደ ሁኔታው ካሳ እንሰጣለን። ካሳ ማለት የተፈጠረውን ችግር ማስተካከል ማለት ነው። ከሰረቅኩኝ መመለስ። ከጎዳሁኝ ማደስ። ከዋሸሁኝ እውነቱን መናገር፤ ካበላሸሁኝ ማስተካከ፤ ወዘተ። አልፎ ተርፎ እንደዚህ አይነት ስህተትን ደግሜ እንዳልሰራ ተገቢውን ጸሎት፤ ተግባር፤ ትምሕርት ወዘተ ማድረግ እና መፈጸም ነው ያለብኝ። ይህ ነው ችግሩን መፍታት ማለት፤ ማስተካከል እና እንዳይደገም የሚያስፈልገውን ነገሮችን ማድረግ።

ይህ ካደረግን በጠቅላላው የተበላሸውን አስተካከልን ማለት ነው። ወደ እውነት መመለስ ነው። «ወደ ራስ (እውነት ማለት ነው) መመለስ ነው»።

ንስሐን በዚህ መልኩ ከተረዳነው «የንስሐ ፖለቲካ» ጥቅሙን እና አስፈላጊነቱን መገንዘብ ቀላል ይመስለኛል። በአጭሩ ለማስቀመጥ ያህል፤ ንስሐ መግባት የችግርን መፍታት ቁንጮ ነው። ፖለቲካችንም የመሃበራዊ ሁኔታችንም በርካታ የምናውቃቸውም የማናውቃቸውም ችግሮች አሏቸው። እነዚህን ችግሮችን ምንጮቻቸውን ሳናውቅ ወይን ሳናምን እንፈታቸዋለን ማለት ሃሰት ነው። ችግሮቹ የሚፈቱት መጀመርያ ችግር እንደሆኑ ካመንን፤ የራሳችንን ድርሻ ካመንን፤ ይቅርታ ከጠየቅን፤ መፍትሔ ከፈለግን እና እራሳችንን ከቀየርን ነው። ሌላ መንገድ በሙሉ አይሰራም። አልፎ ተርፎ ይህንን መንገድ ካልተከተልን ችግሮቻችን ይቀጥላሉ እየባሱም ይሄዳሉ።

የንስሐ ፖለቲካ በተግባር በታላቅ የፖለቲካ መድረክ ያየነው በጠ/ሚ አብይ አህመድ ስራዎች ነው። ጠ/ሚ አብይ ለአለፉት የኢህአዴግ ጥፋቶች «እንደ ግለሰብ» ተሳስችያለሁ ብለው ይቅርታ ጠይቀዋል። ንስሐ ገቡ ማለት ነው። ይህ በማድረጋቸው በርካታ ስኬቶች አምጥተዋል፤

1. ስህተታቸውን ተገነዘቡ እና አመኑ። ችግሮችን በአግባቡ ስለተረዱ ወደ መፍትሄ መሄድ ችለዋል።

2. ተጎጂውን በሙሉ ይቅርታ በመጠየቃቸው ህዝቡ የመንፈስ እርካታ እንዲያገኝ አድርገዋል። ብሶት እና ቂም በመጠኑ መቀነስ ችለዋል።

3. ሌሎቻችንም ለራሳችን ጥፋቶች ይቅርታ እንድንጠይቅ አስተምረውናል። ስህተታችንን አምነን የጎዳናቸውን አዝናንተን ወደ መፍትሄ እንድንሄድ ገፋፍተውናል። መሪአችን እንዲህ ካደረገ እኛም እንችላለን ነው።

4. አንጻራዊ የብሄራዊ ሰላም አምጥተዋል። ጠ/ሚ አብይ ይቅርታ በመጠየቃቸው አብዮት እና ሁከት እንዳይመጣ አድርገዋል። ሰው ይቅርታ ጠይቆ ይቅር ብሎ በሰላም እንዲኖር ገፋፍተዋል። የ«እውነት እና እርቅ» (truth and reconciliation) አይነት ሂደት ወደፊት እንዲጀመር ሜዳውን አብጅተዋል።

5. ይቅርታ፤ ትህትና እና ሃላፊነት መውሰድን በማንጸባረቃቸው የህዝብን እምኔታ አገኝተዋል።

የጠ/ሚ አብይ የ«ንስሐ ፖለቲካ» ከሞላ ጎደል በታላቁ ስኬታማ ሆኗል። አንድ ወይንም ሁለት ዓመት በፊት የአምባገነናዊ አገዛዛችን በዚህ መልኩ አለ አብዮት እና አለ ሁከት ይቀየራል ብንባል ሁላችንም አናምንም ነበር። የማሆን ነገር ነው እንል ነበር። ይህ ያልጠበቅነው ታላቅ ድል አለ «ንስሐ ፖለቲካ» አይሳካም ነበር።

እንደሚመስለኝ ከዚህ ታላቅ ትምሕርት መማር ያለብን «ኢትዮጵያ ብሄርተኝነት»፤ «አንድነት» ወይን የ«ዜግነት ፖለቲካ» የምናራምደው ጎራ ነን። ደጋግሜ እንደጻፍኩት ይህ የፖለቲካ ጎራ በርካታ የሀገራችን ፖለቲካ ችግርን ያመጣ ነው። በጃንሆይ ዘመን ተሃድሶ ማድረግ ባለመቻሉ፤ ግማሹ ማርክሲስት ሆኖ አብዮት እና ሁከት በማምጣቱ፤ እርስ በርስ በመጨራረሱ፤ በኢህአዴግ ዘመን አብሮ ስርቶ ተገቢ የተቃዋሚ ኃይል ማደራጀት ባለመቻሉ፤ ወዘተ (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/07/blog-post_15.html)። እስከ ዛሬ የ«ኢትዮጵያዊነት ኃይሉ» መቢገባን ደረጃ መደራጀት አልቻልንም። ግንቦት 7 ነው ያለው ግን እሱም ከሚገባው እጅግ ትንሽ እና አቅም ያነሰው ድርጅት ነው። የሀገራችን እምብዛም ብዙሃን በ«ኢትዮጵያዊነት» የሚያምን ሲሆን ልሂቃኑ እና ፖለቲከኛው ይህን ብዙሃን ወክሎ ሊያደራጅ አልቻልም። የልሂቃኑ የክሽፈት ታሪኩ ተጭኖታልና።

የንስሐ ፖለቲካ ይህን የተጫነውን መንፈስ ያወርድላታል ብዬ አምንዳለው። ልክ እንደ ለነ ጠ/ሚ አብይ እንዳረገው። እንደ ግንቦት 7 አይነቱ ድርጅት ወደ ኋላ ሄደው እንደ ድርጅት፤ መሪዎቻቸው እንደ ግለሰብ፤ እራሳቸውን ፈትሸው ያደረጉትን ስህተቶች አምነው በይፋ ቢናገሩ ይበጃል። ስህተቱ ትንሽም ሊሆን ይችላል፤ ቅራኔን መፍታት አለመቻል ይሆናል። ግን ይህ ፍተሻ እጅግ ጠቃሚ ነው የሚሆነው። መማርያ ይሆናል።

ታሪክን በአግባቡ ፈትሾ ያሉን ችግሮች ከየት እንደተነሱ ማወቅ አስፈላጊ ነው። ይህ ሲደረግ የሁላችንም ጥፋት ይታያል። ችግሩን በህወሓት ብቻ መለጠፍ ተገቢ አይደለም እውነትም አይደለም። እንደዚህ አይነት የህጻን አስተያየት ነው ችግሮቻችን በአግባቡ እንዳይታወቁ እና እንዳይፈቱ የሚያደርገው። የራስ ሃላፊነትን ማምለጫ መንገድ ነው። ለሀገራችን ችግር ሁላችንም ትልቅ ሚና ተጫውተናል፤ በመስራትም ማለመስራትም። ይህ መታመን እና መነገር ያለበት ይመስለኛል። ይህን ካደረግን ችግሮቻችንን በደምብ አውቀን ትክክለኛውን መፍትሄዎችን እናገኛለን። በህዝቡም እምኔታ እናገኛለን። ከስህተት መማር እና መሻሻል ባህል እናደብራለን። የትህትና ባህል እናደብራለን። የሃላፊነት መውሰድ ባህል እናዳብራለን። ጠ/ሚ አብይ እንደሆኑት ስኬታማ እንሆናለን።

አልፎ ተርፎ የ«ንስሐ ፖለቲካ» ከባህል እና ከወጋችን አብሮ የሚሄድ በመሆኑ ድል የመሳካት እድሉ ከፍ ያለ ነው። «ህዝባችን የዴሞክራሲ ባህል የለውም» ይላሉ የዘመኑ ምሁራናችን። «ገና መማር አለብን እና የስነ ልቦና ለውጥ ያስፈልጋል» ይባላል። ለኔ ይህ አስተያየት የሚመነጨው ከሀገራችን ባህላዊ እሴቶችን በአግባቡ አለማወቅ እና አለመፈተሽ ነው። ከ«ምዕራብ ዓለም» የጫነብን ፕሮፓጋንዳ ማመን ነው ይህ አስተያየት የሚመጣው። ግን የጢ/ሚ አብይ ስኬታማ ስራ የሚያሳየው የኛ የትህትና፤ የይቅርታ፤ የንስሐ፤ እሴቶች በፖለቲካችን ታላቅ አውንታዊ ሚና መጫወት እንደሚችሉ ነው። ሌላ (የምዕራብም) ሀገር መፈጸም የማይቻል ድል ነው የጠ/ሚ አብይ አካሄድ ያመጣው! የት ሀገር ነው መሪ ለሌላ የፈጸመው ሳይሆን ለራሱ ስህተቶች ይቅርታ የሚጠይቀው? የት ሀገር ነው እንደዚህ በቀላሉ ህዝቡ ይቅርታውን የሚቀበለው?! የት ሀገር ነው ትህትና ያሚያንጸባርቅ መሪ የሚወደደው? ይህ አካሄድ ሀገራችን የሰራው ምክንያት ከሃይማኖቶቻችን ቀጥታ የመጡ እሴቶችንም ስለተጠቀመ ነው። ስለዚህ የንስሐ ፖለቲካ በመሰረታዊ ደረጃ ኢትዮጵያዊ አካሄድ ነው። የኢትዮጵያዊነት ፓርቲዎች፤ ይህን የንስሐ ፖለቲካ እንስራበት!

Thursday, 18 October 2018

የአዲስ አበባ ህዝብ መደራጀት፤ እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ

ትላንት ሁለት የአዲስ አበባ ሰዎች በማይሆን ክስ ታስረዋል። ከሱም እንደገባኝ ከሆነ ወጣቶችን በ«አዲስ አበባ በከተማው ተወላጅ ነው መመራት ያለበት» መፈክር ዙርያ ማደራጀት ነው። ለዚህም አደረጃጀት ከፍልስቴም ኮንሱሌት ጋር ተባብረዋል ነው ሌላው ክስ። እነዚህ ስራዎች በፍፁም ህገ ወጥ አይደሉም እና መታሰር እንደሌለባቸው ግልጽ ነው። ሆኖም ትላንት እነዚህ እስረኞች በጭለማ ቤት እየተሰቃዩ (torture) ይገኙ ነበር። ዛሬ ደህና ፍርድ ሳያገኙ አይቀርም። መከራ ለነሱ ቢሆንም መሻሻል ነው።

በዚህ ግዳይ በርካቶች አቤቱታ እያቀረቡ ነው። ጥሩ ነው፤ እንደዚህ አይነት የማይሆን እስርን መቃወም አለብን። ግን እንደምናውቀው ፖለቲካችን ከመቃወም ወደ መስራት መሻገር አለበት። Proactive politics beats reactive politics anytime።

መሰራት ያለበት ስልታዊ አደረጃጀት ነው። በመጀመርያ ለምንድነው «ወጣቶችን» የምናደራጀው? ሰራተኛው የት አለ? ወዝ አደሩ የት አለ? የቢሮ ሰራተኛው የት አለ? ወላጆች የት አሉ? ጡረተኞች የት አሉ? መከከለኛ መደቡ የት አለ? ሃብታሙ የት አለ? «የተማረው» የት አለ? ምሁራኑ የት አለ? ልሂቃኑ የት አለ? ለምንድነው «ወጣቱ» (እውነቱን ለመናገር ስራ የሌለው ወጣት) ሸክሙን መሸከም ያለበት?

ይህ «ወጣትን» ማደራጀት ዘላቂነት እንደሌለው ይታወቃል። ሁሉም ህዝብ መሳተፍ አለበት ለእውነተኛ የዜግነት ፖለቲካ ወይንም የሲቪክ አደረጃጀት። ወጣቱ ተሳትፎ ሌላው ከሸሸ ዋጋ የለውም ብቻ ሳይሆን ጎጂም ሊሆን ይችላል። እንደ ሜኪናን በአራተኛ ማርሽ ማስጀመር ማለት ነው።

ሌላው ችግር ገና መደራጀቱ በተገቢው ሁኔታ አይጀምር እራስን ለጥቃት ማጋለጥ ነው። እኔ እንደሚገባኝ የአዲስ አበባ መደራጀት አላማ «የአዲስ አበባ ህዝብ መብቱ እንዲከበር» ነው። ከንቲባው የአዲስ አበባ ትውልድ ይሁን አይሁን አይደለም። የአዲስ አበባ ህዝብ መብት ከተጠበቀ ምርጫ ይኖራል እና ህዝቡ የፈለገውን ይመርጣል። ግቡ እንዲህ ግልጽ ሆኖ ካየነው እና ግቡ ላይ ካተኮርን 1) ስራችንን በትክክሉ እንሰራለን እና ይሳካልናል 2) ለጥቃት እራሳችንን አናጋልጥም!

አካሄዱ እንደሚመስለኝ እንዲህ ነው መሆን ያለበት፤

1) በጣም ሰፊ ተዕልኮ (vision and mission) ያለው ድርጅት ማቋቋም፤ ለምሳሌ «የአዲስ አበባ ህዝብ መብት እና ጥቅም ለማስከበር የሚሰራ» ድርጅት ማለት ነው። ሀ) ሰፊ ተዕልኮ ስለሆነ ለመጠቃት መጋለጡ አነስተኛ ነው የሚሆነው። ለ) ብዙ ሰዎችን በተለይም «መደራጀት» ሲባል የማይገባቸው ወይንም የሚፈሩትን ይጋብዛል። እናቶች፤ ወላጆች፤ መካከለኛ መደቡን። ሃብታሙን ወዘተ ይጋብዛል።

2) ከመፈክር በፊት መደራጀት። መጀመርያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ከፋይ አባላት ይኖረው። ከዛ በኋላ ነው መንቀሳቀስ። እንቅስቃሴው ከአቅም ጋር አብሮ መሄድ አለበት! እንቅስቃሴው ከአቅም ጋር አብሮ መሄድ አለበት! አቅም ሳይጎለበት መራመዱ ጥቃትን መጋበዝ ነው። የቅንጅት ታሪክ ይህን ነው የሚያስተምርን። ቅንጅት በመቶ የሚቆጠሩ መሪዎች እና አባላት ነበረው ከዛ ቀጥሎ እስከ ብዙሃኑ ድረስ ከሞላ ጎደል ባዶ መዋቅር ነበር። ጥቂት መሪዎች እና ብዙ ብዙሃን። መሃሉ ባዶ ነው። እነዚህ ጥቂት መሪዎች ሲጠቁ እና እርስ በርስ ሲጣሉ ማን ይተካቸው። መዋቅሩ እስከ ታች ባዶ ነበርና። ስለዚህ መጀመርያ መጠንከር ከዛ ወደ ዋና ስራ መግባት ነው ትክክለኛ አሰራር። ይመስለኛል።

የአዲስ አበባ ህዝብ ወይንም ጠቅላላ የኢትዮጵያ ህዝብ በተለያየ ወኪላዊ ድርጅቶች መደራጀት አለበት (በዜግነት ፖለቲካ ካመንን)። አለበለዛ ያው የጎሳ ፖለቲካ ማለትም የግጭት ፖለቲካ ነው የሚቀረን። ለሀገራችን ህልውና ቅድመ ሁኔታ ነው ማለት ነው። ስለዚህ ይህን ዋና ስራ በሙሉ ተሳትፎ በሰከን ያለ ብልጥ መንገድ እንስራው። ህዝብ በሙሉ እንዲሳተፍ እናድርግ።

«እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤ ስለዚህ እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ።»