Thursday 5 April 2018

የአሜሪካ መንግስት ከኢትዮጵያ መንግስት ይሻላል?

ባለፉት 18 ዓመታት በተለያዩ የአሜሪካ ጦርነቶች ምክንያት ወደ አንድ ሚሊዮን አካባቢ ሰዎች ሞተዋል። በርካታ ሀገሮች ተበጥብጠዋል መንግስታት ተገልብጠዋል ህብረተሰብ ተጎሳቅሏል። ሆኖም በርካታ ኢትዮጵያዊያን በተለይ ምሁራን ልሂቃን ሀገራችን «እንደ አሜሪካ በሆነች» እንላለን።

ይህ አባባላችን ምን ማለት እንደሆነ እንመርምር። በምርመራችን ሂደት ግረ መንገድ ስለ ራሳችን ስለ አቋማችን ማንነታችን አንዳንድ ቁም ነገሮች እንማራለን። ይህ ትምሕርት ለሰላምና ፍትሕ ያለንን ትግል አስፈላጊ ነው ያጠነክረዋልም።

እስቲ ስለ አንድ መጠነኛ የመርካቶ ነጋዴ የሆነ ኢትዮጵያዊ እናስብ። እድሜ ለህዝብ ብዛት ለኤኮኖሚ እድገት ንግዱም ገቢውም እያደገ ነው። ከመንግስትም ከሌላም ወገን እንቅፋቶች ቢያጋጥሙትም እንደ ጓዶቹ ብልህ ነውና ለንግዱ ለንብረቱ ብዙ ስጋት የለውም። ሆኖም አጋጣሚው ሲፈቅድ የተወሰነ ገንዘቡን ወደ ውጭ ሀገር ያወጣል። ኑሮው የተመቸ ቢሆንም ሀገሪቷ የሰላም የፍትሕ የፖለቲካ ችግሮች እንዳሏት ያቃል ያምናል። ግን ቱክረቱ የለት ኑሮው ላይ ነው። እንደማንኛውም ሰው ለኑሮ ይሯሯጣል ጥዋት እስከ ማታ ይሰራል። የሥርዓቱ ተበዳዮች የታሰሩትን የተገደሉትን መሬታቸውን የተቀማባቸውን አንዳንዴ ቢረዳም ብዙ ሊያያቸው አይፈልግም። እንዳሉ ቢያውቅም «ምን ይደረግ በተቻለ ቁጥር ከፖለቲካ መራቅ ነው» ብሎ ይኖራል።

እስቲ አንድ በአሜሪካ ያለ ኢትዮጵያዊ ስደተኛን እንመልከት። አሜሪካ መጥቶ ታግሎ በትምሕርቱ ገፍቶ ጥሩ ገቢና መአረግ ያለው ስራ ከያዘ ቆይቷል። የአሜሪካ «መካከለኛ መደብ» አባል ሆኗል። ባለቤቱም ትሰራለች ቤት መኪኖችም አላቸው ልጆቻቸው ይማራሉ በቅርብ ከፍተኛ ትምሕርትቤት ይገባሉ። ኑሮ ተመችቷቸዋል። አሜሪካ ተመችቷቸዋል። አዎ አንዳንዴ ስለ ዘረኝነት ስለወንጀል ይማረራሉ ግን እነዚህ ነገሮች ሕይወታቸውን አልነኩም። እንደ ፈረንጆች «አሜሪካ ታላቅ ሀገር ናት» ይላሉ። ስለ የኢራቅ ጦርነት ሰለቦች ወይም ሌሎች የአሜሪካ መንግስት ተጎጂዎች ብዙ አያስቡም፤ ምን አገባቸው። የለት ኑሮ በቂ ነው።

ግን ይህ «ኢትዮ-አሜሪካዊ» ኢትዮጵያ የሚኖረውን ነጋዴ ይተቸዋል። «እንዴት ዙርያህ ሰው እየተጭቆነ እየተገደለ እየተበደለ ዝም ዝም ብለህ ትኖራለህ» ይላል! እራሱ ግን  ለአሜሪካ መንግስት የሚሰጠው ቀረጥ ሀገሮችን ለመውረር ህዝብን ለመግደል ሲውል ዝም ይላል። እንቋን አሜሪካን መተቸት «አሜሪካ ጥሩ ሀገር ናት» ይላል። አልፎ ተርፎ «ኢትዮጵያ እንደ አሜሪካ ትሁን» ይላል!

ከዚህ ምንድነው መማር የምንችለው? በመጀመርያ የሰው ልጅ «ሲመቸው» ሲደላው ያለውን ችግር የሀገርም የግለሰብም የባለንጀራውም ችግር አይመለከትም። ለሰው ልጅ ድሎቱ ያሳውረዋል። ይህ እውነታ በፖለቲካ ደረጃ ሲንጸባረቅ ዓለም ዙርያ ይታያል። የቻይና መንግስት ኤኮኖሚውን በማፋጠን ህዝቡን ዝም አሰኛለሁ በሚል መርህ (policy) ነው ላለፉት 35 ዓመታት የሰራው። በኢትዮጵያም ይህ የፖለቲካ መርህ በ«ልማታዊ አስተዳደር» ስም ይራመዳል። ግን በጎሳ ፖለቲካ ሥርዓቱ ምክንያት ህዝቡን ዝም አላሰኘም። ከላይ እንደጠቀስኩት በአሜሪካም ድሎት ህዝቡን የመንግስት ግፎችን እንዳይመለከት ያደርጋል። ስለዚህ ለኢትዮጵያ ሰላምና ፍትሕ የምንፊልገው ይህን የሰው ባህሪ እና በፖለቲካ ያለውን ሚና አውቀን ነው መርህዎቻችን ስልቶቻችን መወቀር ያለብን።

ሁለተኛው ትምሕርት፤ የኢህአዴግ መንግስት ከሌሎች ያዓለም መንግስታት ተለይቶ «ሴጣን» አለመሆኑ ነው። አዎን መጥፎ መንግስት ነው ለ27 ዓመታት የፈጸመው ግፎች ተመዝግቧል። ሆኖም የኢህአዴግ ማንነትና አሰራር ውስብስብ ነው በቀላሉ «ሴጣን» ነው ማለት እውነቱን አለመገንዘብ ነው። ለዚህም ነው እንደ የ«ለማ ቡደን» አይነቱ ከኢህአዴግ ውስጥ ገብቶ ሰርቶ የደረሰበት ደረጃ የደረሰው። በጭፍን «ሴጣናዊ» መንግስት ቢሆን እንደዚህ አይነት ስራ ሊሰራበት አይችልም ነበር። ግን እንደማንኛውም መንግስት ስልጣን ዋናው አላማ ቢሆንም ለስልጣኑ ለፖለቲካ ህልውናው ያሉት ምርህዎች የሚያካሄደው ስራዎች ለሰላምና ፍትሕ ታጋዮች ከፍተት ፈጥሯል ይፈጥራልም። እነዚህን ክፍተቶች እንዳሉ ተገንዝበን መጠቀም አለብን።

ሶስተኛ ትምሕርት፤ ሀገራችን እንደ ማንም ሀገር «ትሁን» አንበል። አንድ፤ ማንም ፍፁም የለም። ከአሜሪካ እስከ ጀርመን እስከ ኮሪያ ሁሉም የራሳቸው ታሪክ የራሳቸው ችግሮች አሏቸው። ከሌሎች ሀገሮች ጠቃሚ ሃሳቦች መጠቀም አለብን ግን እነዚህ ሃሳቦችን ከኛ መሰረታዊ ማንነት ስር አድርገን ነው መጠቀም ያለብን። አለበለዛ እንደ ከላይ የጠቀስኩት ኢትዮ-አሜሪካዊ የገንዛቤ ድክመቶች ይኖርብናል።

በመጨረሻ መማር የሚገባን በፖለቲካ አስተያየት ትህትናና ለሰው መቆርቆር (empathy) ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆኑ ነው። ከላይ የጠቀስኳቸው ምሳሌዎችን ለመጠቀም… እራሳችንን በሰዎቹ በኩል አድርገን ማሰብ አለብን። ኢትዮጵያ ያለው ነጋደ ሀገር ውስጥ በመሆኑ ምንድነው የሚያጋጥመው የሚያስበው የሚያደርገው። ማናልባት ዙርያውን ያለውን ህዝብ በተለያየ መንገድ እየጠቀመ ይሆናል። ኢትዮ-አሜሪካዊው ደግሞ እንደ ማንም አሜሪካዊ ስለ ሀገሩ ችግር በደምብ አይገነዘብም። የሰው ልጅ ተፈጥሮ ነው ልንፈርድበት አይገባም። ወዘተ። አይመስልም እንጂ ትህትና ዋና የፖለቲካ መሳርያ ነው ሁላችንም ተገንዝበነው ትሁት መሆን መሞከር ይገባናል።

ስለዚህ ፖለቲካ ውስብስብ ነው። በተራ ግንዛቤ ብቻ የምናይ ከሆነ አሜሪካ ገነት ኢትዮጵያ ሲኦል ኢህአዴግ ሴጣን ይመስለናል። ግን እውነቱ እንደዚህ ቀላል አይደለም። ትክክለኛ ሀሳብና ተግባር እንዲኖረን ይህን መገንዘብ አለብን።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!