እርግጥ ብዙ አይነት የአማራ ብሄርተኝነቶች አሉ፤ ለፖለቲካ ስልት ወይንም «ታክቲክ» ብቻ የሆነ አለ፤ በስመ አማራ ላለፉት 27/40 ዓመታት ለተበደሉት ፍትሕ መጠየቅያ የሆነ አለ፤ ዛሬ አማሮች ላይ የሚደርስባቸውን በደል ለመታገል የሆነ አለ፤ በሀገር ደረጃ በፖለቲካ ድርድር ለአማራ ህዝብ የሚቆም አለ፤ በሃሰት የታማው የአማራ ህዝብን ታሪክ እውነቱ እንዲታወቅ የሚንቀሳቀስ አለ፤ የአማራ ህዝብ ክብርና ማንነትን ለመመለስ የሚታገለው አለ፤ ወዘተ። ዛሬ እነዚህ ሁሉ አይነት እንቅስቃሴዎች በስመ አማራ ብሄርተኝነት ይጠራሉ።
ዞሮ ዞሮ ዋናው ነጥብ ይህ የፖለቲካና መሃበራዊ ንቅናቄ እራሱን የ«አማራ ብሄርተኝነት» ብሎ መሰየሙ ነው። አላማው ምንም ቢሆን በዚህ «አማራ ብሄርተኝነት» የሚለው ስም መጠራት ይፈልጋል። በዚህ ስም መጠራቱ ምን ይነግረናል? በተለይ በትውፊትና በተቃራኒው ምዕራባዊ ተራማጅነት ያለው ግንኙነቱ ምንድነው?
ደስ የሚለው ነገር የሁሉም አይነት የአማራ ብሄርተኝነት ምልክቶች ትውፊታዊ ናቸው። ለምሳሌ ዓፄ ቴዎድሮስ አንዱ ዋና የአማራ ብሄርተኝነት ንቅናቄ ምልክት ናቸው። የአማራ ታሪክን በትክክሉ ማስተዋወቅና መናገር ሌላው የአማራ ብሄርተኝነት አላማና ምልክት ነው። ግን ዓፄ ቴዎድሮስ እራሳቸውን ወይንም ሀገራቸውን ወይንም አገዛዛቸውን የአማራ ወይንም «አማራ ብሄርተኛ» ብለው ይሰይሙ ይሆን? የአማራ ታሪክ የምንለው በታሪክ ሰሪዎቹ እና በዘጋቢዎች ዘንድ የአማራ ታሪክ ይባል ነበር? የአማራ ብሄርተኝነትን ያንጸባርቅ ነበር?
ለነዚህ ሁለቱም ጥያቄዎች መልሱ «አይደለም» እንደሆነ ነው የማውቀው። ዓፄ ቴዎድሮስ እንደ ሁሉም ንጉሶቻችን በስመ ኢትዮጵያዊነት ነበር እራሳቸውን የሚመለከቱት። ታሪካችም እንዲሁ ኢትዮጵያዊነት ላይ ነው የሚያቶክረው አማራነትን አይደለም። ይህ ማለት «አማራ» የሚባል ህዝብ የለም አልነበረም ማለት አይደለም! መኖሩ በታሪክ በተለያየ ቦታ መመዝገቡ ይታወቃል። ግን እስከማውቀው ማንም በስመ አማራ አልተንቅሳቀስም። ትውፊታችንና ታሪካችን እንደዚህ ከሆነ እንዴት እራሱን «አማራ ብሄርተኝነት» ብሎ የሰየመ ንቅናቄ ትውፊታዊ ነው ማለት ይቻላል?
በሁለተኛ (ወይንም አንደኛ!) ደረጃ ጠቅላላ የጎሳ ብሄርተኝነት የሚባለው ነገር የምዕራባዊ የፖለቲካ ፍልፍና እንደሆነ ይታወሳል። በትውፊታዊ ፖለቲካ «ሀገር» ነው ያለው፤ «ጎሳ» የለም። ይህ አባባሌ ብዙ ነገሮች ስለሚያከማች ሁሉንም በዚህ ጽሁፍ አልጠቅስም ግን በጠቅላላ የ«ጎሳ ብሄርተኝነት» የዘመናዊ የምዕራባዊ ጽንሰ ሐሳብ ነው።
የምፈራው ነገር ይህ አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት ልክ እንደ በፊቶቹ የኤርትራ፤ የትግራይ፤ የኦሮሞ፤ ወዘተ ብሄርተኝነቶች በብሶት እና በበአድ ምዕራባዊ ርዕዮተ ዓለም የተመሰረተ ኢተውፊታዊ ንቅናቄ ይሆናል ብሄ ነው። የኤርትራ እና የትግራይ ብሄርተኝነት በመሰረቱ ጸረ ትውፊት ናቸው። በቀላሉ ምሳሌ ለህዝባቸው መሰረት የሆነው ሃይማኖትና ባህልን የሚጠላ ርዕዮተ ዓለም ነው እነዚህ ብሄርተኝነቶች የተመሰረቱት። የኦሮሞ ብሄርተኝነት እንደዚህም ቢሆን ቢያንስ ወደ ኦሮሞ ትውፊት ለመመልከትና እንደ ገዳ አይነቱን ተውፊት ማክበር ሞክሯል። ሆኖም መሰረቱ የማርሲስት የጨቋኝ ተጨቋኝ የጎሳ ብሄርተኝነት አስተሳሰብ ነው። የአማራ ብሄርተኝነትም እንደዚህ እንዳይሆን መጠንቀቅ ይኖርበታል። ግን እራሱን «አማራ» ብሎ ከሰየመ እዚህ ወጥመድ ውስጥ ቀድሞ ገብቷል ማለት ይመስለኛል።
ጎበዝ፤ ጠንካራ፤ ሀገር ወዳድ ምሁራን በተለይ ወጣቶች የአማራ ብሄርተኝነት ያቀፉ አሉ። ምክንያቱ ለሁላችንም ሊገባን ይገባል፤ ለብሶት መልስ ነው። የአስራት ወልደየስ ፖለቲካ የብሶት ሳይሆን እራሳቸው እንዳሉት የግዴታ ነበር። የዛሬው ግን የ27/40 ዓመታት ያመጣው ብሶት ነው። ብሶቱ በህወሓት ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም፤ በድሮ ምሁራን፤ ልሂቃን፤ ተቃዋሚ፤ ወዘተ ነው። እኔ እንደሚመስለኝ የተማሪው ንቅናቄ ወደ እንደ ማርክሲዝም አይነቱ ምዕራባዊ ፍልስፍና እና ርዕዮተ ዓለም በብሶት ምክንያት እንደገባው የዛሬው ትውልድ በብሶቶች ምክንያት እንደ ቀድሞው ተማሪ ንቅናቄ ወደ ኢ-ትውፊታዊ (ምን አልባት ጸረ ኢትዮጵያዊ) የማይሆን አስተሳሰብ እየገባ ነው። ስለ ተውፊቱ ስላልተማረ በምዕራባዊ የቀለም ትምሕርት የሚሰግድ ህብረተሰብ ውስጥ ስላደገ ሳያውቀው ብዙ ኢ-ትውፊታዊ አስተሳሰቦች አድረውበታል።
ስለዚህ ጉዳዩን ወደ ኋላ ወደ መሰረታችን ተመልሰን አመለካከታችንን በሙሉ ከ«ሀ» ብንገመግም ጥሩ ይመስለኛል። ከዛ በኋላ ነው የአማራ ብሄርተኝነት ትውፊታዊ ነው ወይ የሚለውን ጥያቄ በትክክሉ ልንመልሰው የምንችል የሚመስለኝ።
No comments:
Post a Comment
ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!