Thursday, 14 June 2018

አማራ ብሄራዊ ንቅናቄ

ስለ አማራ ፖለቲካዊ ንቅናቄ ለኢትዮጵያ ህልውና ያለው አስፈላጊነት (http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2016/09/blog-post_23.html) ሁለት ዓመት በፊት ጽፌ ነበር። ያኔ አንዳንዶች  ከዚህ ንቅናቄ ተነስተው በአማራ ስም የተሰየመ የፖለቲካ ድርጅት ያቁቁማሉ ብዬ አልጠበቅሁም። ግን እንሆ «የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ» (አብን) ተወልዷል!

ዛሬ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሁኔታ በፍጥነት እየተቀያየረ ነው። በየቀኑ ያልተጠበቁ ለውጦች እየተካሄዱ ነው። የሀገር ግንባታ ወቅት ነው (http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/02/blog-post_20.html)። የጥያቄ፤ ውይይት፤ ምርምር፤ ድርድር እና ስምምነት ምመስረት ወቅት ነው። ይህን እድል ለማግኘታችን ተመስገን ማለት ያለብን ይመስለኛል፤ ማንናችንም ሁለት ዓመት በፊት ይህንን የተነበየ የለም። በዚህ የውይይት መንፈስ ነው ስለ «አማራ ብሄራዊ ንቅናቄ» ይህን  ጽሁፍ የማቀርበው።

የአማር ብሄራዊ ንቅናቄ አቋሙን፤ ፖሊሲዎቹን እና መመርያዎቹን አርቅቆ ባይጨርስም ሁለት ዋና ግቦቹን አሳውቋል። እነዚህ፤

1. የአማራ ህዝብን ከደረሰበት ያለው ግፍ እና ወንጀል ከነ መፈናቀል፤ መገደል፤ የተለያዩ ጥቃቶች፤ ታሪኩ እና ክብሩ በሃሰት መተቸቱ ወዘተ መከላከል እና ማዳን።

2. የጎሳ አስተዳደርን ማጥፋት። የህወሓትን ጎሰኛ ህገ መንግስትን ብዚህ መልኩ መቀየር፤ መሰረቱ «ብሄር ብሄረሰቦች ህዝቦች» ሳይሆን «ዜጋ» እንዲሆን፤ «ብሄር» ወይንም «ጎሳ» በህገ መንግስት ደረጃ እውቅና እንዳይኖረው (ቋንቋ ሊኖረው ይችላል)፤ ክልሎች የዜጎች እንዲሆኑ፤ ወዘተ።

ጥሩ ግቦች ናቸው። ብዙዎቻችን የምንስማማባቸው ይመስለኛል።

ግቦቹን እንደተቀበልን ወደ ዋናው ጥያቄ እንምጣ፤ እነዚህን ግቦች ለማሳካት በስመ «አማራ ብሄር» መደራጀት ነው የሚሻለው ወይንም በስመ «ኢትዮጵያ» በ«ህብረ ብሄራዊ» መልክ መደራጀት ነው የሚሻለው? እነዚህን ግቦች ለመምታት በህብረ ብሄራዊ መልክ መደራጀቱ ከበጀ ያ መንገድ ይሻላል ማለት ነው። አለበለዛ የ«አብን» መንገድ ነው የሚያስፈልገው ማለት ነው።

በ«አማራነት» ወይንም በ«ኢትዮጵያዊነት» የመደራጀት ጥቅም እና ጉዳት

በስመ «አማራ» መደራጀት ዋና ጥቅሙ የብሄራዊ ወይንም ጎሳዊ ስሜትን ሃይል እና አቅም ለመገንባት መጠቀም ነው። በስመ አማራ ከተደራጀን በ«ኢትዮጵያዊነት» ከምንደራጅ ይልቅ ህዝቡ በአማራነት ስሜት ይበልጥ ይሳተፋል ነው።  በታሪካችን ዛሬም ያሉት ሌሎቹ የጎሳ ድርጅቶች ይህ አንዱ ለመፈጠራቸው የሚሰጡት ምክንያት ነው። ሰውዉን በ«ኢትዮጵያዊነት» ይልቅ በ«ጎሳዊነት» መቀስቀስ ይቀላል ነው።

በስመ አማራነት መደራጀት ሁለተኛ ጥቅም የአማራ ህዝብ «አጄንዳ» ላይ ማተኮር ነው። ህብረ ብሄራዊ ድርጅት የሁሉንም ጉዳዮች ማስተናገድ አለበት። በዚህ መካከል የአማራው ጉዳይ አንዱ ይሆናል። ለምሳሌ በአማራ መፈናቀል ስራ መስራት ከተፈለገ የሁሉንም ትብብር ይጠይቃል። በአማራ ላይ የተለጠፈውን ሃሰተኛ ታሪክ ማስተካከል ከሆነም የሁሉን ትብብር ይጠይቃል። ወዘተ። ግን የአማራ ብቻ ድርጅት እነዚህን ስራዎች አትኩሮ መስራት ይችላል።

የህብረ ብሄር አደረጀት ዋና ጥቅም ኃይል እና አቅም (capacity) ነው። በማንኛውም ጉዳይ ላይ የአማራ ብቻ ሳይሆን የሌሎችም አቅም ማሳተፍ ይችላል። ለምሳሌ አማራ ከቤኒሻንጉል ሲፈናቀሉ አማራዎች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም የዚህ ህብረ ብሄር ድርጅት አባሎች አቅማቸውን ሰምስበው ጉዳዩ ላይ ይሰራሉ። ባጭሩ ትልቅ ድርጅት በመሆኑ ትልቅ አቅም ይኖረዋል።

ሌላው ጥቅሙ በአንድ ብሄር የተወሰነ ባለመሆኑ በርካታ አቋማቸው ያልሰከነ ሰዎችን የመሰብሰብ አቅም ነው። እንደሚታወቀው ከጎሳኝነት እና አንድነት ፖለቲካ የሚዋዥቁ በርካታ ኢትዮጵያዊያን አሉ። እነዚህ ጸንፈኛ ጎሰኛ ያልሆኑት በውይይት እና መግባባት ወደ አንድነት አቋም ሊመጡ ይችላሉ እና የህብረ ብሄር ፓርቲ አባል ሊሆኑ ይችላሉ። የህብረ ብሄር ድርጅት ይህንን ማድረግ ይችላል ግን መቼም የአማራ ድርጅት አይችልም።

ሶስተኛው ልጠቅስ የምወደው በህብረ ብሄራዊ መልክ መደራጀቱ ጥቅም ይህ ነው፤ በመአላው ኢትዮጵያ በተለይም በአማራ ህዝብ መካከል በኢትዮጵያዊነት መደራጀት የተለመደ ነው። በኢትዮጵያዊነት መደራጀት ረዥም እና የሰከነ ታሪክ አለው። ይህ አይነት አደረጃጀት ክርክር የለውም ተቃውሞ የለውም (ከጎሰኞች በቀር)። በታሪካችን የተለመደ ነው። ትክክል ቢሆንም ባይሆንም በስመ አማራ መደራጀት ግን ሁልጊዜ አከራካሪ ነው ግጭት እና ጥል ያመጣል። አቅምን ይጎዳል ሰውን ይከፋፍላል። ይህን ታሪክ ከዚህ በፊት አይተነዋል ዛሬም እያየነው ነው።

ግቦቻችንን ለመምታት የትኛው መንገድ ይሻላል

የመጀመርያ የ«አብን» ግብ አማራን ባለበት ቦታ ማዳን እና ለመብቱ መከራከር እና መታገል ነው። እንደ ቅንጅት አይነቱ በስመ «ኢትዮጵያ» የተመሰረተ የህብረ ብሄራዊ ድርጅት ይበልጥ ያአማራ መብትን ማስከበር ይችላል ብዬ ገምታለሁ። በመጀመርያ ደረጃ ይህ ድርጅት ከአማራነት የሰፋ ስለሆን ከላይ እንደጠቀስኩት በርካታ አማራ ያልሆኑ የሌላ ብሄር ሰዎች፤ ቅኝት (ከአንድ በላይ ጎሳ) የሆኑ ሰዎች፤ ጎሰኝነትን የማይወዱ ግን አማራ ወይንም አማራ ብቻ ያልሆኑ ሰዎች ወዘተ ያሳትፋል። ይህ በርካታ አቅም በአማራ የሚደርሰውን ግፍ ላማስቆም ታላቅ ሚና ይጫወታል። ለምሳሌ ከኦሮሚያ ክልል አማሮች ከተፈናቀሉ አማሮች ብቻ ሳይሆኑ ኦሮሞዎችም በአንድ በህብረ ብሄራዊ ድርጅት ስም ይህን ወንጀል ይታገሉታል። ኦሮሞ ከሶማሌ ክልል ሲፈናቀል እንዲሁም። ይህ አካሄድ አንድነትን ይጎለብታል።

ግን እንደ «አብን» የሆነ የአማራ ድርጅት አማሮችን ብቻ በጉዳዩ ማሳተፍ ስለሚችል አቅሙ ውስን ይሆናል። በስመ አማራ እራሱን የገለለ (exclusive) ስለሆነ ወይንም ለሁሉም ክፍት ስላልሆነ  የሌሎች ትብብር ለማግኘት ይከብደዋል። እራሳችሁ ተወጡት ይባላል። እኛ እና እነሱ አይነት ስሜትን ያጎለብታል።

አይ የአማራ ድርጅት ከሊሎች ብሄራዊ ድርጅቶች ለምሳሌ ከኦሮሞ ብሄራዊ ድርጅቶች ጋር አብሮ መስራት ከሆነ ለምን መጀመርያዉኑ በሰፊ በጎሳ ሳይሆን በዜግነት የተመሰረተ ጥላ አይሰራም! ይህ አስተሳሰብ አንዱ የጎሳ አስተዳደር ርዕዮት ዓለም ምሶሶ ነው አይደለምን? ጎሰኞቹ የሚሉት የኢትዮጵያ ፖለቲካ በጠቅላላ ጥሩ ሁኔታ ላይ የሚደርሰው ሁሉም በጎሳ ከተደራጀ ነው። እና ግን እምንለው ሰፊው (ህብረ ብሄራዊ ድርጅት) ጥላ የጎሰኝነት ስሜትን ያበርዳል ትብብርን ያመቻል ግን ሁለት የብሄራዊ ድርጅቶች ሲደራደሩ የጎሳ ስሜት እና አደገኛ የግሳ ውድድር ስለሚቀድም አዋጪ እና ዘላቂ ትብብር ለመፍጠር ከባድ ይሆናል።

በዚህ ምክነያቶች የአማራ ህዝብን ከጥቃት ለማዳን ህብረ ብሄራዊው መንገዱ ይሻላል።

እስቲ የሁለተኛውን ግብ እንመልከት፤ ጎሳዊ አስተዳደርን አፍርሶ ዜጋዊ አስተዳደርን እንዲሰፍን ማድረግ። ይህ ጉዳይ ብዙ ተሳታፊዎች በሚገኙበት ፖለቲካዊ ድርድር ላይ ነው የሚፈታው።  እንደ «አብን» አይነቱ የአማራ ድርጅት ለዚህ ድርድር ምን ሚና ይጫወታል። የአማራ ህዝብን በበርካታ ደረጃ ወክሏል እንበል። አብን ከዚህ ድርድር ማለት የሚችለው የአማራ ህዝብን ወክዬ ህገ መንግስታችን ከጎሰኝነት ወደ ዜጋዊነት እንዲቀየር እጠይቃለሁ ነው። ሌሎች ደግሞ የኦሮሞ ህዝብን ወክዬ ወይንም የቲግራይን ህዝብ ወክዬ ወዘተ ይህንን አንፈልግም ይላሉ። ከዚህ ድርድር የሚሳተፈው የህብረ ብሄር ድርጅቶች ደግሞ እንደግፋለን ይላሉ። ስለዚህ አንዱ «ሴናሪዮ» የአማራው እና የህብረ ብሄር ድርጅቶች ባንድ ወገን ሆነው ህገ መንግስቱ ይቀየር ይላሉ ሌሎቹ የጎሳ ድርጅቶች አይቀየር ይላሉ።

እዚህ ላይ የማን ድምጽ ያሸንፋል (ማስተዋል ያለብን እንደዚህ አይነት የሀገር ግንበታ ድርድር ላይ 50%+1 አይነት ሳይሆን ቢያንስ 70% በላይ ያስፈልጋል ለዘላቂ ስምምነት)። ህገ መንግስቱ አይቀየር የሚሉት ያሸንፋሉ። ለምን?

በአንድ ወገን ያሉት የአማራ እና የህብረ ብሄር ድርጅቶች ድምራቸው ደካማ ነው የሚሆነው። ለምን ብትሉ የአማራ ድርጅት በመፈጠሩ የተነሳው ክርክር እና ጥል የዚህ ወገንን አቅም (capacity) በታላቅ ደረጃ ይመነምናል። ይህንን በመላው አማራ እና መላው ኢትዮጵያ ክርክር ጊዜ አይተነዋል። አሁንም ለተወሰነ ዓመት በአማራ ብሄርተኝነት የሚያራምዱ እና በግንቦት 7 መካከል አይተነዋል። የታወቀ ነገር ነው ጉዳዩ ከፋፋይ ነው ቂም እና ቁስል ትቶ ነው የሚሄደው። ሁለቱ ድርጅቶች ሁለት ከሚሆኑ አንድ ቢሆኑ እጅግ ይበልጥ ተንካራ ይሆናሉ። ግን ለብቻ ሆነው አንድ አቋም ቢኖራቸውም ህገ መንግስቱን ለማስቀየር በቂ አቅም አይኖራቸውም። ህገ መንግስቱን ለመቀየር ግብ አይመታም ማለት ነው።

በተቃራኒው አማራው እንዳለ በህብረ ብሄር ድርጅቱ ስር ቢገባ ይህ ጎጂ ህዝብ ከፖለቲካእና ከመሳተፍ የሚያርቅ ክርክር ይቀራል። ለዚህ ውጤት ማስራጃ እንደ ናሙና ምርጫ 97ን መመልከት ይቻላል። እውነት ነው ረዝም ዓመት በፊት ነበር ሁኔታዎችም ተቀይረዋል ግን ያለን ናሙና ይህ ነው። ህብረ ብሄራዊ ቅንጅት ምርጫውን ጠረገው። ከአማራ ክልል ውጭ በርካታ ድጋፍ አግኝቶ አሸነፈ። ይህ የሚያሳየው አማራው በህብረ ብሄራዊ መልክ ሲጠቃለል የህብረ ብሄራዊ ድርጅቱ አቅም ግዙፍ እንደሚሆን ነው። በቀላል ቋንቋ የአማራ ድርጅት ሲደመር የህብረ ብሄራዊ ድርጅት አቅሙ "2" ነው ካልን አንድ ላይ በአንድ ህብረ ብሄራዊ ድርጅት ስር ቢሆኑ የዚህ ትልቅ ድርጅት አቅም "3" ነው የሚሆነው። እና ይህ ግዚፍ ድርጅት በህገ መንግስት ድርድር ላይ ታላቅ ሚና መጫወት ይችላል ግቡን በቁጥር ሃይል ሊአስፈጽም ይችላል።

በአጭሩ ለሁለቱም ከዚህ ጽሁፍ የገለጽኳቸው የ«አብን» ግቦች አንድ የሆነ የሌሎች ብሄር ሰዎች የሚያጠቃልል በህብረ ብሄር በኢትዮጵያዊነት የተመሰረተ ድርጅት ይበልት ይመረጣል። ይህ ድርጅት በግዙፍነቱ እና ሁሉን አቀፍ በመሆኑ ምክንያት የአማራ መብትን ለማስከበርም ህገ መንግስቱን ለመቀየርም አቅሙ ይኖረዋል።

በተጨማሪ አንድ ነጥብ ላነሳ እወዳለሁ። ከላይ እንደጠቀስኩት አንዱ በአማራነት መደራጀት ጥቅሙ በጎሰኝነት ስሜት ምክነያት ተጨማሪ የአማራ ህዝብ ደጋፍ እና ተሳትፎ ለማግኘት ነው። በ«ኢትዮጵያዊነት» ከምንደራጀት በ«አማራነት» መደራጀት ከአማራ ህዝብ ይበልጥ ተሳትፎ እንደሚያመጣ እና የሚፈጠረውን ድርጅት ይበልጥ የሚያጠነክር ከሆነ የአማራ ህዝብ ለጎሳው ያለው ስሜት ለሀገሩ ካለው ስሜት ይበልጣል ማለት ነው! ወይንም በበቂ ቅስቀሳ እና ፕሮፓጋንዳ የአማራ ህዝብ ከኢትዮጵያዊነት ወደ ጎሰኝነት ስሜት እንዲያድል ማድረግ ይቻላል ማለት ነው። የአማራ ህዝብ እውነታ እንደዚህ ነው? አይመስለኝም። ምናልባት የተወሰነውን ይሳተፋል ሌላው በሚመጣው ጭቅጭቅ ምክነያት ወይንም በጎሳ አደረጃጀት ባለማመን ምክነያት ይቀራል አይሳተፍም።

ግን የህዝቡ ጎሰኝነት ስሜቱ አይሎ ጠንክሮ «አብን» ይጠነክራል እንበል። ይህ ድርጅት በስመ አማራ ተደራጅቶ በአማሮች ድጋፍ አግኝቶ ጠንክሮ እንዴት ነው ህገ መንግስቱ እንዲቀየር መታገል የሚችለው? የጎሳ አስተዳደር ጠፋ ማለት አብን ይጠፋል ነው። ድርጅት እራሱን አያጠፋም። ያቋቋሙት ሰዎች የህገ መንግስቱ መቀየርን ቢፈልጉም እንዴት አንድ ፓሪቲ ህልውናውን አውቆ ያጠፋል? ድርጅቱ አንዴ ከተቋቋመ እና መዋቅር ከሆነ በኋላ እራሱን ለማዘጋት ዝግጁ አይሆንም። በሌላ ቋንቋ አብን እንደዚህ ይላል፤ «የጎሳ ችግር የጎሳ አስተዳደር ነው እንድፈጠር ያደረገኝ፤ የጎሳ አስተዳደር ከጠፋ እኔም እጠፋለሁ፤ ስለዚህ ህገ መንግስቱ እንዳለ ይቀጥል!»

ለዚህ ነው እንደ አብን አይነቱ የጎሳ ወይንም የብሄር ድርጅት ማቋቋም እና የጎሳ አስተዳደር ይቅር ማለት ተቃራኒ ጉዳዮች የሚመስሉት። አብን የተቁቁመው ጎሰኝነት ስላለ ይህ ጎሰኝነት አማራን ስላጠቃ ነው። የአብን «ቤንዚን» ወይንም ኃይል ለጎሳው የተቆረቆረ አማራ ነው። አብን ከህብረ ብሄራዊ ድርጅት ይሻላል የተባለው ይህ የአማራ ተቆርቋሪ በህብረ ብሄራዊ መንገድ ከሚታገል በስመ አማራ ቢታገል ይሻለዋል ተሳትፎውን ይጨምራል ተባሎ ነው። ስለዚህ ጎሰኝነቱ በአማራውም አድሯል ማለት ነው። እንዴት አብን ይህ በንዚኑ ይቅር ይላል። አይለም። የጎሳ አስተዳደሩ ቢቀጥል ነው የሚጠቀመው። ይህ ነው «ፓራዶክሱ»።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!