Wednesday, 11 July 2018

ንቀት

እኛ ኢትዮጵያዊዎች እንደ መንናቅ የምንጠላው ነገር የለም። ከአንዳንድ ቦታዎች ንቀት እና የተደጋገመ ዝልፍያ እስከ መገዳደል ያደርሳል! መንናቅ እየጠላን ግን መናቅን እንወዳለን  አያስችለንም። ይህ ነውረኛ የንቀት ባህላችን ለበርካታ ሀገራዊ፤ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮቻችን  አስተዋጾ አድርጓል። በቀላሉ ለመከፋፈል አጋልጦናል። እርስ በርስ መናናቅን ብናቆም እነዚህ ችግሮችን ለመፍታት ይረዳናል።

«ንቅት» ስል ሰውን ወይንም ማህበረሰብን ወደ ታች አድርጎ ማየት ማለቴ ነው። «ምቀኝነት» ሌላውን በመጉዳት ራስን መጥቀም የሚቻል እንደሚመስለው ንቀትም ሌላውን ወደታች በማየት ራስን ከፍ ማድረግ ይቻላል የሚል የውሸት አስተሳሰብ አለው።

ማንን ነው የምንንቀው? ከኛ «ዝቅተኛ» ስራ የሚሰሩትን፤ (ለምሳሌ) የቤት ሰራተኞቻችንን፤ ከኛ ድሃ የሆኑትን፤ ያነሰ ትምሕርት ያላቸውን፤ አማርኛ በደምብ የማይችሉትን፤ እንግሊዘኛ በደምብ የማይችሉትን!፤ ገጠሬዎትን፤ ቀጥቃጭ፤ ቆዳ ፋቂዎች ወዘተ የሆኑትን፤ የሌላ ቋንቋ ተናጋሪዎችን ወዘተ። ዝርዝሩ ረዥም ነው!

ተናቅን የሚል ስሜት ያላቸው ከሚንቋቸው ጋር አንድነት ሳይሆን ልዩነት ይሰማቸዋል። ልዩነት ብቻ ሳይሆን ቂም እና ጥላቻ አከማችተዋል የናቋቸውን ቢበቀሉ ደስ ይላቸዋል። ይህ ማለት ህብረተሰባችን ተከፋፍሏል ነው። እርስ በርስ ጥላቻ አለው ማለት ነው። ታድያ ለረዥም ዓመታት በከፋፍሎ መገዛት ፖለቲካ ብንመራ ለምን ይገርማል። በ«ብሶት ፖለቲካ» መቆየታችን ለምን ይገርመናል? ፖለቲካችን በመጣላት የተመረዘ መሆኑን ምን ይገርማል? የፖለቲካ ውይይቶቻችን በጥይትነና በጡንቻ መካሄዳቸውን ምን ይገርማል?

እስቲ አንዳንድ ተጨባጭ የንቀት ምሳሌዎች ልስጣችሁ፤ በኃይለ ሥላሴ ዘመን ሁላችንም እንደምናውቀው ከመሳፍንቱ እና ባላባቱ መካከል ብዙዎቻችን ገበሬውን፤ ጪሰኞውን፤ ሰራተኞቻችንን ወዘተ እንንቅ ነበር እንደ በታቾቻችን እናያቸው ነበር። አዲሱ «የተማረው» መደብም ራሱ የሚንቀው ቡድን ነበር ይህም ያልተማረውን፤ ሃይማኖታዊውን ወዘተ። ይህ ንቀት ህዝባችንን ከፋፈለ የአንድነት ስሜታችንን ቀነሰ። ሀገራችንን ለኮምዩኒዝም የሚያስተምረው «ጨቋኝ ተጨቋኝ» የክፍፍል ፖለቲካ አጋለጠ። መናናቃችን ለደርግ አብዮት ታላቅ አስተዋጾ አደረገ። አብዮተኞቹ የህዝቡን የመንናቅ ብሶትን እንደ ቤንዚን ተጠቅመው ነው አብዮቱን ያራመዱት። ወዛደሮችን፤ አርሶአደሮችን፤ ሴቶችን፤ «ጭቁን ዘሮችን» ወዘተ እረደሃለሁ እበቀልሃለሁ ብለው ነው ኮምዩኒስቶቻችን የተነሱት። ተናቅን የሚሉትን በሙሉ አቅፍያለሁ እያለ ነው ደርግ የሰበከው። ግን ንቀቱ ባይኖር ብሶቱም አይኖርም ነበር አብዮቱም አይነሳም ነበር።

የኢህአዴግ ዘመንም እንዲሁ ምሳሌ ይሆነናል። ኢህአዴግ ስልጣን ስይዝ የሚናናቅ የተከፋፈለ እርስ በርስ ቂም የያዘ ህብረተሰብ ነው የጠበቀው! ይህን ህብረተሰብ ከፋፍሎ መግዛት እንደሚችል ቶሎ ተረዳ። ልክ እንደ ደርግ ግን በተሻለ ብልጠት ተንቀናል ሊሉ የሚችሉትን ቡድኖች ማፈላለግ እና ማቀፍ ጀመረ! እዚህ ላይ አንድ አስፈላጊ ነጥብ አለ። ኢህአዴግ የተጠቀመበት ክፍፍል አይነት የጎሳን ብቻ አይደለም። ሁሉንም ከላይ የጠቀስቋቸው ክፍፍሎችን፤ ሃብታም እና ድሃ፤ የተማረ ያልተማረ፤ ገበሬ ከተሜ፤ አሰሪ ሰራተኛ፤ ወንድ ሴት፤ ትልቅ ሰው ወጣት ወዘተ ተጥቅሞባቸዋል። እነዚህ ክፍፍሎች አልፈጠራቸውም ተተቀመባቸው እና አስፋፋቸው እንጂ። ስለዚህ ለኢህአዴግም አገዛዝ የንቀት ባህላችን ሙና እንደተጫዋወተ ግልጽ ነው።

ለማጠቃለል ያህል ያለፉት 60 ዓመት ፖለቲካችንን «የብሶት ፖለቲካ» ብለን መሰየም እንችላለን። ቂም እና መከፋፈል የሰፈነበት ፖለቲካ ነው። በ«ጨቋኝ ተጨቋኝ» አስተሳሰብ ተመርዟል። ስለዚህም ነው አብሮ አለመስራት፤ ውግያ፤ ጸብ፤ ቅራኔ አለመፍታት ወዘተ የሰፈነው። ንቀት እና ውጤቶቹ ብሶት እና ቂም ለዚህ ማህበረሰባዊ እና ፖለቲካዊ ችግር ትልቅ ሚና የተጫወቱ ይመስለኛል።

ከ ጠ/ሚ አብይ አህመድ ዋና መፈክሮች አንድነትን ወይንም አለመከፋፈል ነው። አንድ የሆነ ማህበረሰብ ጤነኛ ነው የተከፋፈለ ማህበረሰብ በሽተኛ ነው። የሚናናቅ ማህበረሰብ አንድ ሊሆን አይችልም ስለዚህም ይህ የ«ንቀት» ባህላችንን እንዋጋ እና እናሸንፍ!

አንድ የመጨረሳ ነጥብ ፍቀዱልኝ። ንቀት «አንተ የማትወደውን ለባለእንጀራህ አታድርግ» ስለሚሽር መጥፎ ስነ መግባር መሆኑ ሁላችንም ይገባናል። መንናቅ ስለማንፈልግ መናቅ የለብንም ነው። ግን ይህ ሙሉው ታሪክ አይደለም። ንቀት ኢተፈጥሮ ነው። የሰው ልጅ በእግዚአብሔር አምሳል ስለተፈጠረ ሰውን መናቅ ማለት የሚወደን ፈጣሪአችን እግዚአብሔርን መናቅ ነው። እንደዚህ ስንመለከተው ንቀት እጅግ ከባድ ማጣት ነው።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!