ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ የእውንተኛ የይቅርታ ሰባኪ መሆናቸውን ሁላችንንም አይተናል። ለበደሉንን ሁሉ ይቅርታ በማድረግ በሰላም እና ፍቅር አብረን መኖር እንደምንችልም እንዳለብንም እያሳመኑን ነው። በዚህ ምክንያት ፖሊሱን፤ መርማሪውን፤ ፍርድ ቤቱን፤ ካድሬውን፤ ሰአላዩን፤ ጎረቤቴን፤ ወያኔን፤ ኦነግን፤ ሻዕብያን፤ ነፍጠኛውን፤ ጠባቡን ወዘተ በደሉን የምንለውን ሁሉ ይቅር ለማለት እራሳችንን እያሳመንን ነው። የበደሉን የመሰለንን ይቅር እንድንል በማሳመናቸው ጠ/ሚ አብይ ታላቅ ስራ ነው የሰሩት። ሆኖም ጠ/ሚ አብይ እኮ ማንንም ይቅር አላሉም። ይቅርታ ነው የጠየቁት! ንስሃ ነው የገቡት! እባካችሁን እንደ መንግስት ላደረግነው እንደ መንግስት አካል ላደረግኹት ይቅር በሉን በሉኝ ነው ያሉት። ከይቅር ማለት አልፎ ይህንን ንስሃ መግባት እና ይቅርታን መጠየቅን ነው በመጀመርያ ደረጃ ከአብይ አህመድ መማር ያለብን! ንስሃ መግባት እና ይቅርታ መጠየቅ ለሁላችንም የሰው ልጅ እጅግ ከባድ ነገር ነው። የማንፈልገው የምንሸሸው ነገር ነው። ጥፋታችንን ማመን ቁስላችንን በተለይም ህፈራትችንን በደምብ እንድንመለከት ስለሚያደርገን አንፈልገውም። ግን ለጤናማ እና እውነተኛ ኑሮ ግድ ነው። አንዳንዶቻችሁ እንደ አንድ ግለሰብ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዙርያ ምን ኃጢአት አለብኝ ትሉ ይሆናል። ጥሩ ጥያቄ ነው። ብዙ ጊዜ የኛ «ትናንሽ» ኃጢአቶች ታላቅ ጉዳት እንደሚፈጽሙ አይታየንም እንደናየውም አንፈልግም። ስለዚህም አንዳንዴ ንስሃ ለመግባት እና ይቅርታ ለመጠየቅ ትንሽ ግፊት ያስፈልጋል። እስቲ እኔ ልሞክር። የአብይ አህመድን ምሳሌ ተከትዬ እስቲ እንደ አንድ በአንድነት የሚያምን የኢትዮጵያ ብሄርተኛ ንሰሃ ልግባ ለነዚህ የፖለቲካ ኃጢአቶቼ ይቅርታ ልጠይቅ፤ 1. በጃንሆይ ዘመን ልጆቼን ወደ ውጭ ሀገር ትምሕርትቤት ልኬ እራሳቸውን እንዲንቁ የምዕራባዊ አስተሳሰብ ከነ ኮምዩኒዝም ይዘው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ እና እንዲበጠብጡ በማድርጌ ይቅር በሉኝ 2. ልጆቼን እትዮጵያዊ እንዲሆኑ ፈንታ ታሪካቸውን እንዳያውቁ ፈረንጅ እንዲያመልኩ የራሳቸውን ወግ እና ትውፊት እንዲጠሉ በማድረጌ ይቅርታ 3. አለአግባብ የወረስኩትን መሬት ለጪሰኞች መልሼ በሚቀረኝ (ሰፊ) መሬት ተደላድዬ ከመኖር በመስገበገቤ ይቅርታ 4. ሰራተኛዬን፤ ጎረቤቴን፤ እንደኔ ያህል ያልተማረውን፤ «ያልሰለጠነውን»፤ ገበሬውን ወዘተ ስለ ናቅኩኝ ይቅር በሉኝ 5. የፖለቲካ ለውጥ በጊዜው ባለማምጣቴ አቢዮትን እና የሁከት እና ግድያ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት ለተጫወትኩት ሚና ይቅርታ 6. አድሃሪ፤ ኢህአፓ፤ መኢሶን፤ ደርግ፤ ሻዕብያ፤ ወያኔ ወዘተ እያልኩኝ «ግደሏቸው» በማለቴ ይቅርታ 7. ከሰው ልጅ ይልቅ የፖለቲካ ጦርነት ይበልጣል እያልኩኝ በጦርነት የሚሞቱትን እንደ ምንም ባለመቁጠሬ ታላቅ ይቅርታ 8. ሻዕብያ፤ ወያኔ እና ኦነግ ስልጣን ሲይዙ ወደ ስልጣን የገቡበት ምክንያት በኔ ጥፋት ባዶ የፖለቲካ ሜዳ ስላገኙ ነው ብዬ ባለማመኔ ይቅርታ 9. ኢትዮጵያን በሽብር፤ በጦርነት እና መጥፎ አስተዳደር እጅግ የማይመች ሀገር እንድትሆን በማድረጌ የኤርትራ ህዝብን ወደ መገንጠል በመገፋፋቴ ይቅርታ አድርጉልኝ 10. ለትግራይ ህዝብ እንዲሁም ፖለቲካውን በአግባብ ማስተናገድ ባለመቻሌ ወደ ትውፊትና ሃይማኖታችሁን የሚጠላው ህወሓት እንድትሸገሸጉ በማድረጌ ይቅርታ 11. ለ27 ዓመት ለችግራችን ያለኝን አስተዋጾ በመካድ ለመፍትሄው ያለኝን ሃላፊነት በመካድ ቁም ነገር ሳላደርግ ለሁሉ ችግሬ እንደህጻን «ወያኔ ነው» ብዬ በማልቀሴ ይቅርታ ይህን የንስሃ መግባት እና ይቅርታን መጠየቅንም አንብባችሁ እኔ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዙርያ ምንም ይቅርታ የምልበት ነገር የለም የምትሉ ትኖራላችሁ። ከጎረ ቤቱ ጋር የተጣላ በተዟዋሪ የፖለቲካ ኃጢአት ፈጽሟል ማለት እንደሆነ አናውቅምን (http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2016/09/blog-post_14.html)? እስካሁን ያሉን የፖለቲካ ችግሮቻችን ከማህበረሰባዊ ክፍፍል የመነጩ ናቸው። ስለ ህወሓት የምንለው «ከፋፍሎ ገዛን» አይደለምን? ታድያ ከጎረቤታችን ጋር የተጣላን፤ ሰውን የናቅን፤ ሰው ላይ የፈረድን፤ ባለንጀራችንን ያልደገፍን ሁሉ ኃጢአተንኛ መሆናችንን ማመን ያለብን ይመስለኛል። «ህዝብ (አንዳንዴ) የሚገባውን መንግስት ያገኛል» ይባላል። አዎን ይቅርታን መጠየቅ ከባድ ነው። ሁላችንም ኃጢአተኞች እንደሆንን ልባችን ያውቃል። ግን ይህን ማመኑ የሚያገልጠውን ህፍረት እና ቁስል እንፈረዋለን። ስለዚህ ኃጢአቶቻችንን ለመሸፈን እንወዳለን። ይህንን በማወቅ ነው ቅዱስ ጳውሎስ ሲያስተምርን ዘንድ እራሱን «የኃጢአተኞች ዋና» ብሎ የሰየመው። ታድያ ሃዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ማለት ከቻለ እኛ እጅግ ኃጢአተኞች የሆንነው ምን እንበል? ንስሃ መግባት ነፃ ያወጣል ከአቅመ ቢስነት ወደ አቅም መጎልበት ያሻግራል። ሰው ላይ ጣትን መጠቆም ሽንፈት እና እራስን አቅመ ቢስ ማድረግ ማለት ነው። የኢትዮጵያ ችግሮች የራሴ ናቸው መፍትሄውም ከራሴ መጅመር አለበት ብዬ አምናለሁ። ይህንን ነው ጠቅላይ ሚኒስቴ አብይ ሊያስተምሩን የፈለጉት።
የሰላም ክፍሌ ይትባረክ ብሎግ፤ ስለ ሀገራችን ኢትዮጵያ ያለኝን ትናንሽ ሀሳቦች በትህትና አቀርባለሁ። ለስሕተቶቼም በቅድሚያ ይቅርታ እጠይቃለሁ
Monday, 9 July 2018
«ይቅር እንባባል»
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment
ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!