የአዲስ አበባ ህዝብ እንደ ማንኛውም የኢትዮጵያ ህዝብ ለረዥም ዓመታት በማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ጭቆና ተጎድቷል። ከቤቱ ከመረቱ ከሰፈሩ ተፈናቅልዋል፤ መሬቱ ለባለ ሃብቶች አለ አግባብ ተሰጥቷል፤ ከከተማ ውጭ ባዶ መሬት ላይ ተጥሏል (ከገበሬ የተነጠቀ መሬት)፤ ውሃ መብራት ወዘተ ቢከፍልበትም አብዛኛው ጊዜ ይቋረጥበታል፤ ደካማ የመንግስት አገልግሎት ነው ያሚሰጠው፤ ጉቦ አምጣ ተብሎ ይገደዳል ወዘተ። ይህ ሁሉ እየደረሰበት ከሞላ ጎደል ዝም ብሏል።
ከአዲስ አበባ ውጭ ቄሮ፤ ፋኖ ወዘተ ላለፉት ሶስት ዓመት የፖለቲካ ለውጥ እንዲመጣ ኢህአዴግ ላይ ታላቅ ህዝባዊ ጫና አድርገዋል። የኦሮሚያ እና የአማራ ክልል ገዦች የሆኑት ኦህዴድ እና ብአዴን ደግሞ ኢህአዴግን ከውስጥ ተቆጣጥረው ይህ ለውጥ እንዲከናወን በመሪነት ደረጃ ሰርተዋል። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን የአዲስ አበባ ህዝብ ከሞላ ጎደል ብዙ አላደረገም ምናልባትም ተመልካች ነበር ማለት ይቻላል።
በርግጥ የአዲስ አበባ ህዝብ በፖለቲካ በተለይም በተቃውሞ ሰልፍ አይነት እንቅስቃሴዎች አለመሳተፉ ጥሩ ምክንያቶች አሉት። ትልቅ ከተማ ስለሆነ ህዝቡ ከተለያዩ ቦታዎች የሰፈረ ስለሆነ መተማመን፤ አብሮነት እና መደራጀት ከባድ ነው። የቅንጅት ጊዜ አመጽ እና ተከትሎ የመጣውን የመንግስት ጭቆናን በደምብ ያስታውሳል። በተወሰነ ደረጃም በደርግ ዘመን የነበረውን ቀይ ሽብርን ህዝቡ አልረሳም። አልፎ ተርፎ አዲስ አበባ ጥቅጥቅ ያለ ከተማ በመሆኑ ችግር ከመጣ እልቂቱ ብዙ እንደሚሆን ህዝቡ ያውቃል። በዚህ ምክንያቶች የአዲስ አበባ ህዝብ በፖለቲካው አንጀቱ እያረረ ቢሆንም ዝም ብሏል።
አሁን ግን የፍርሃት ዘመን አልፏል የነፃነት ዘመን ነው ተብሎ የአዲስ አበባ ህዝብ ለጠ/ሚ አብይ ድጋፍ ተብሎ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ አካሄደ። ይህ ጥሩ እርምጃ ነበር ግን ከመቶ እርምጃዎች ገና የመጀመርያው ነው። የሚቀጥለውን እርምጃ መውሰድ አለበት፤ የአዲስ አበባ ህዝብ ለራሱ የፖለቲካ ህልውና ሃላፊነት መውሰድ መቻል አለበት። ክፍለ ሀገር በሚደረገው ወይንም ፖለቲከኞች በሚወስኑለት ዝም ብሎ መነዳት ማቆም አለበት። የራሱን ውሳኔዎች ወስዶ ማስረገጥ አለበት። ይህን ማድረግ ያለበት ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለመላው ለሀገሪቷ ጤንነት ነው። አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ቁንጮ በመሆኗ ለመላው ሀገሪቷ አቋሟን የማሳየት እና የማስረገጥ ሃላፊነት አለበት። አለበለዛ አዲስ አበባ የሙስና፤ የሃላፊነት አልባ፤ የማጭበርበር፤ የተገዥ ወዘተ ስፍራ ይሆንና ለመላው ኢትዮጵያ ፖለቲካ እንደ ቻንሰር ትሆናለች።
የአዲስ አበባ ህዝብ በፖለቲካ ህልውናው ሃላፊነት መውሰድ አለበት ማለት ምንድነው? ባጭሩ አቋሙን እና ፍላጎቱን ለማስረገጥ በፖለቲካ መልኩ መደራጀት አለበት። የአዲስ አበባ የፖለቲካ ድርጅትን ማቋቋም አለበት ወይንም በሌላ የፖለቲካ ድርጅት ስር ሆኖ አቋሙ በደምብ እንዲንጸባርቅ ማድረግ አለበት።
ዛሬ የአዲስ አበባ ህዝብ ብዙ አንገብጋቢ የህልውና ጉዳዮች አሉት። የነባሩን ደካማ አስተዳደር ከነሙስናው እና ሌብነቱ ማስቀየር አለበት ሃላፊነት እና ግልጽነት እንዲሰንፍ ማድረግ አለበት። ከከተማው ዙርያው ያለው ከኦሮሚያ ክልል ያለው ግንኙነትን ማስተካከል አለበት። ለሚመጡት ረዥም ዓመታት ሰው ከበየ ክፍለ ሀገሩ እንደ ጎርፍ ወደ አዲስ አበባ ስለሚገባ እንዴት ነው የከተማው መስፋፋት የሚስተናገደው? በምን መልኩ ይስፋፋ የሚለው ትልቅ ጥያቄ ነው። የከተማው ጠረፍ ይስፋ ወይንም እንድ ሆኖ ሁለት መንግስት ያለው «ሜትሮፖሊታን» ከተማ ይሁን? የኦሮሚያ «ልዩ ጥቅም» የሚባለው ጉዳይ ይስተናገድ አይስተናገድ በምን መልኩ የሚለው ትልቅ ጥያቄ ነው። ለተፈናቀሉት የኦሮሚያ ገበረዎች የአዲስ አበባ ህዝብ እዳ አለው ወይንም የስርአቱ እዳ ነው የከተማውም ህዝብ ምናልባትም ይበልጥ ዋጋ ከፍሎ ስለተፈናቀለ (ከውድ መሬት ማለት ነው)? ኦሮምኛ የአዲስ አበባ ሁለተኛ ቋንቋ ይሁን ውየንስ በቂ ተናጋሪ የለውም ወይንም መጀመርያ የፌደራል ቋንቋ ይሁን። መሬት መሸት መለወጥ ይፈቀድ እና የመንግስት ማፈናቀል እና በሊዝ መስጠት ያቁም የመሬት ገበያው ይጠራ ዘንድ?
እነዚህ እና በርካታ ሌሎች አንገብጋቢ ጉዳዮች ስላሉት የአዲስ አበባ ህዝብ እነዚህን ማስተናገድ የሚችለው በመደራጀት ብቻ ነው። ለምን በነፃ ምርጫ ህዝቡ ፍላጎቱን አይገልጽም ትሉ ይሆናል። በመጀመርያው ነፃ ምርጫ እንዲኖር የህዝቡ ግፊት ያስፈልጋል እንጂ እነ ጠ/ሚ አብይ ዝም ብለው ሊያደርጉት አይችሉም። ብዙ የፖለቲካ ጫናዎች አሉባቸው ድርጅታቸውም መንግስቱም ገና አልጠራምና የማጣራት ስራ ላይ ናቸው። ግን ህዝቡ ቢደራጅ እና ጉዳዩን ቢገፋበት ለነ ጠ/ሚ አብይ ታላቅ እርዳታ ነው ይሚሆነው። እንደዚህ አይነቱን እርዳታ ይፈልጉታል ይጠቅማቸዋል የሚያስቸግሯቸውን ኃይሎችን ለማስወገድ ይጠቅማቸዋል።
በመጨረሻ ይህንን የጻፍከው በአዲሱ ከንቲባ ሹመት ተነስተህ ነው ትሉኝ ይሆናል። እውነት ነው! በርካታ ሰዎች ይህን አሿሿም ሲቃወሙ ስምቼአለሁ። ግን የተለመደው የህፃን ለቅሶ መቃወም ነው የሰማሁት። እንደ ሚና እና ሃላፊነት የሌለው ዝም ብሎ ማልቀስ ትርጉም የለውም። ችግር ካለ እርምጃ መውሰድ ነው አለበለዛ እንደ ህፃን ታሳዥ ሆኖ መቀር ነው። ባህላችን መቀየር አለበት። አሁን ለመነጋገር እና ለመደራጀት ሜዳው ክፍት ነው። ስለዚህ የአዲስ አበባ ህዝብ መሪዎች፤ ባለ ሃብቶች፤ ሽማግሌዎች፤ ፖለቲከኞች ወዘተ ተሰብስበው ጉዳዩን ተነጋግረውበት ለህዝቡ ህልውና ግድ የሆነውን የአዲስ አበባ ህዝባዊ ድርጅት ያቋቁሙ። «ዴሞክራሲ» ይህ ማለት ነው!!
No comments:
Post a Comment
ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!