ዛሬ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሁኔታ ተገለባብጦ ቢሆንም አሁንም «የብሄር ብሄረሰብ ጥያቄ» ዋና ጉዳያችን ነው። በዚህ ዙርያ ያሉት ጥያቄዎች ናቸው ዋና የሀገራችን የክፍፍል እና የግጭት ምንጭ። ይህ አሳዛኝ ሁኔታ በዋናነት የተፈጠረው በጎሳ ብሄርተኞች ሚና ሳይሆን በሀገር ብሄርተኛ ጎራው ነው። እኛ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ብሄርተኞች ደጋግመን በሰራናቸው ስህተቶች እና ሀገራችንን በሚገባው ማስተዳደእር ስላልቻልን ነው የብሄር ጥያቄው እንደዚህ የሰፈነው። ለምሳሌ ያህል ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ በማያሻማ አገላለጽ አስቀምጠውታል፤ ኢህአዴግ ደርግን አላሸነፍም፤ ደርግ እራሱን አሸነፈ እንጂ። እኛ የሀገር ብሄርተኞች አድሃሪ፤ ተራማጅ፤ ኢህአፓ፤ ምኤሶን ወዘተ እየተባባልን አሳፋሪው ደርግን ፈጠርን ደርግ ሀገሪቷን አጥፍቶ ለኢህአዴግ፤ ኦነግ እና ሻዕብያ ስልጣን አስረከበ።
ለምንድነው ይህ ነጥብ ላይ የማተኩረው? ለምንድነው ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግሮች እንደ ኢህአዴግ አይነቱ የጎሳ ብሄርተኞችን ጥፋተኛ ከማድረግ የአንድነቱን ጎራ የሀገር ብሄርተኞችን ጥፋተኛ የማደርገው?
1. ሁለት አይነት ሰዎች አሉ። አንዱ ችግር ሲደርስበት ማንነው ይህን ያመጣብኝ ብሎ የሚአማርር
ሌላውን አድራጊ እራሱን ሰለባ በማድረግ እራሱን አቅሜ ቢስ ያደርጋል። ሌላው ሰው ምን አድርጌ ነው ይህ የደረሰብኝ ብሎ እራሱን በመገምገም እና ሃላፊነት በመውሰድ እራሱን አቅም እንዲኖረው ችግሩን መፍታት እንዲችል የሚያደርግ ነው። እኔ በአንድነት የማምን የሀገር ብሄርትኛ ነኝ እና ጥፋቴን ማምን ሃላፊነቴን መቀበል እፈልጋለሁ። ጣቴን በሌሎች ላይ በማተቆር የራሴን ጥፋቶች መካድ አልፈልግም። በተጨማሪ ሃላፊነት በመውሰዴ የችግሩ ምንጭ እኔ ነኝ በማለት የመፍትሄው ምንጭም እኔው ነኝ ማለት ነው። መፍትሄውን ከሌላ ሰው አልጠብቅም። ይህ ተመልካች ሳይሆን አስፈጻሚ ያደርገኛል። ይህ አቅሜን ከመመንመን ያጎለብተዋል።
2. እውነት ነው፤ እኛ የሀገር ብሄርተኞች ነን የኢትጵያ የፖለቲካዊ ችግሮች ያመጣነው። በጃንሆይ አገዛዝ ሀገሪቷን በተቆጣጠርን ጊዜ አስፈላጊ ለውጦች ባለማድረግ የመደብ እና የጎሳ ጥያቄዎችን አስነሳን። የሀገሩን ትውፊት የሚንቅ የተማሪ እንቅስቃሴን ወለድን። ደርግ የኃይለ ሥላሴን መንግስት አልገለበጠም የኃይለ ሥላሴ መንግስት ነው አስፈላጊ ለውጦች ባለማድረግ እራሱን ለአብዮት ያጋለተው። አብዮቱን የአንድነት ጎራውን ለሁለት ለ«አድሃሪ» እና «ተራማጅ» ከፋፈከው ተራማጁ አድሃሪውን አጠፋ። ከዛ ደግሞ ተራማጆቹ እርስ በርስ ተጨራረሱ። አልፎ ተርፎ ደርግ በ«ኢትዮጵያ ብሄርተኝነት» ስም «ነግዶ» ህዝብን ጭቆነ እና ለሀገር ብሄርተኝነት መጥፎ ስም ሰጠ። ይህ መጥፎ ስም የጎሳ ብሄርተኞችን እንቅስቃሴን አበረታታ። ደርግ ሲወድቅ የሀገር ብሄርተኝነት ጎራ እራሱን አጥፍቶ አልቋል። የጎሳ ብሄርተኞቹ ሙሉ በሙሉ ስልጣን ተቆጣጠሩ። በኃይለ ሥላሴ ምንም አቅም ያልነበርው የጎሳ ብሄርትኝነት አሁን ሀገራችንን ገዝቶ ኤርትራን አስገነጠለ። ይህ በአጭሩ እኛ የሀገር ብሄርተኞች ዛሬ ያለብንን የጎሰኝነት ችግር እንዴት እንዳመጣን ይገልጻል።
3. አሁንም ዋናው የሚያሳስበኝ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጎራ የሀገር ብሄርተኛው ነው። በህዝብ ደረጃ ይህ ጎራ ቢንገዳገድም ደህና ነው። እንደ አብይ አህመድ አይነቱን መሪዎች እየወለደ ነው። ገን በልሂቃን (elite) ደረጃ ችግር እንዳለ ነው። አንድ ሆነን ሀገራችንን ማዳን እንችላለን ወይንም እንዳለፉት 50 ዓመት እርስ በርስ ተከፋፍለን እንደገና የጎሳ ብሄርተኝነት እንዲሰፍን እናደርጋለን? ዋና ጥያቄ ነው። የቅርብ ታሪካችን ጥሩ አይደለም። ይሄው ለኢህአዴግ የ27 ዓመት አገዛዝ አንድ ጠንካራ የፖለቲካ ድርጅት ሀገር ውስጥም ውጭም ማቋቋም አልቻልንም። አሁንስ አንድ ሆነን ከ«ለማ ቡድን» ጋር እየሰራን ሀገራችንን ማዳን እንችላከን? ወይንስ እንደልማዳችን እንከፋፈላለን እና ሀገራችንን ለቀውስ እና ግጭት የሚፈጥረው ጎሰኝነት እንደገና አሳልፈን እንሰአለን? ቁም ነገር ከማድረግ አቅሙ አለን ትያቄ የለውም። ግን ፍላጎቱ አለን ወይ ነው ጥያቄው።
በነዚህ ምክንያቶች ነው በዚህ ወቅት ከሁሉም የፖለቲካ ጎራዎች የሀገር ብሄርተኛ ጎራው የሚያሳስበኝ። እንደ ህወሓት ምናልባትም ኦፌኮ አይነቱ የጎሳ ብሄርተኞች ምንም አያሳስቡኝም። የታወቁ ናቸው በልመና ልንቀይራቸው አንችልም። በስልት፤ በዘዴ እና በውይይት ከነሱ ጋር እንደራደራለን። ግን ለመደራደር እና ውጤታማ ለመሆን የአንድነት ጎራው አንድ እና ጠንካራ መሆን አለበት። ድርድር የሚሳካው እራስን መጀመርያ እራስን ጎልብቶ ነው አለበለዛ ደካማ ከሆንን አይሳካልንም። እርግጠኛ ነኝ የአንድነት ጎራው አንደና ተንካራ ከሆንን በነዚህ ድርድሮች እርግጥ ውጤታማ እንሆናለን የጎሳ ብሄርተኞችን በጥሩ መልክ እንይዛቸዋለን። ግን ከተከፋፈልን የበፊቱ 60 ዓመት ችግሮችን እንቀጥላለን።
No comments:
Post a Comment
ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!