አንድ ጓደኛዬ «የቤት ሰራተኛዬን እንደ ቤተሰብ ነው የምቆጥራት። ካስፈለገ እንጀራ መጋገርም ቤት ማጽዳትም እረዳታለሁ። ግዴታ ትምሕርትቤት እንድትማር አደርጋታለሁ…» ብሎ ነገረኝ። ምን ነው ይህ ያልተለመደ እንክብካቤ ብዬ ስጠይቀው እንዴት ለልጆቼ እንጀራ ጋግራ የምታበላውን አልንከባከባትም አለኝ! እውነት ነው፤ ሌሎቻችን እንዲሁ ቢገባን።
አንድ ሰሞን የቤት ሰራተኛ ፍለጋ አዲስ አበባን ከደላላ ወደ ደላላ ዚርን! ደላሎቹ ምን እንርዳችሁ ብለው በጉጉት ይጠይቁናል። የቤት ሰራተኛ ስንላቸው ፈገግራቸው የጠፋል። ሹፌር ወይንም የቀን ሰራተኛ ወዛደር ብንላቸው ይሻላቸው ነበር ብዙ አላቸው። ግን የቤት ሰራተኛ የላቸውም፤ ለነሱም ብርቅ ሆነዋል።
ብዙ የማቃቸው ቤተሰቦች አዲስ አበባም ከገጠር ከተሞችም የቤት ሰራተኞቻቸው በየ ሁለት ሶስት ወር ይለቃሉ አዲስ መቅጠር ይሆንባቸዋል። ወይንም ለመቅተር የገንዘብ አቅም የላቸውም። ወይንም ከመቀቃየር ተስፋ ቆርጠው አለ ሰራተኛ ይኖራሉ።
ዛሬ በአዲስ አበባም በመላው ኢትዮጵያ የቤት ሰራተኛ ጠፍቷል። ወይንም በትክክለኛ አገላለጽ (እጅግ) ተወዷል። ለምን ይሆን? የ ኤኮኖሜ ምክንያቶች አሉ። የሰው ኃይል በጠቅላላው ተወዷል። ዛሬ የቀን የግንባታ ሰራተኛ በወር ወደ 3000 ብር ሊሰራ ይችላል። እንዲሁም የቤት ሰራተኛ ደሞዝ ጨምሯል። ሁለተኛ ምክንያት ዛሬ ሴት ልጆች ከድሮ ይልቅ በትምሕርታቸው ይገፋሉ። የገጠር ወይንም የድሃ ቤተሰብ ልጆቻችው እንዲማሩ ይፈልጋሉ እንጂ በልጅነታቸው ሰራተኛ እንዲሆኑ አይሰጧቸውም። ሶስተኛ ምክንያት ወደ አረብ ሀገር ሄዶ መስራት ነው። የአራብ ሀገር ክፍያ ይበልጣል ወደ «ውጭ» ሀገር መሄድም ምንም ችግር እንደሆነ መረጃ ቢኖርም ያጓጓል ይመስለኛል። በነዚህ ምክንያቶች የቤት ሰራተኞች ተወደዋልም አይገኙምም።
ከኤኮኖሚ ምክንያቶች በተጨማሪ ለቤት ሰራተኛ መጥፋት ማህበረሰባዊ ምክንያር አለ እና እዚህ ላይ ነው ማተኮር የምፈልገው። ዛሬ አንድ ሴት በህንጻ ጽዳት ስራ 2000 ብር በ ወር ታገኛለች። ከዚህ ብር የቤት ኪራይ፤ መጓጓዣ (ትራንስፖርት) እና የምግብ ወጪዎቿን ትከፍላለች። 1000 ከተረፋት ትልቅ ነገር ነው። ነይ በ2000 ብር የቤት ሰራተኛ ሁኚ የቤት ኪራይ፤ የመጓጓዣ እና የምግብ ወጪ አይኖርሽም ብንላት እምቢ ትላለች። ለምን ይሆን? ስራው ከባድ ስለሆነ አይደለም እትፍ ከባድ አይደለም። ነፃነቱ ይሆን እሱም 1000 ብር የሚያዋጣት አይመስለኝም። ምንም አይነት የሚመች የስራ ሁኔታዎች ብትዋዋልም የቤት ሰራተኛ መሆን አትፈልግም። ታድያ ምንድነው ምክንያቱ?
እኔ እንደሚመስለኝ ዋናው ምክንያት በባህላችን የቤት ሰራተኝነት እንደ ዝቅተኛ የሚናቅ ስራ ስለምንቆጥረው ነው። ይህን የዝቅተኝነት እና የመንናቅ ስሜት እጅግ ብዙ ብር ካልሆነ ብር አይተካውም። ተጎድቼ ውጭ ብሰራ ይሻለኛል ለብዙ ብር ከሰው ቤት ከምሰራ ነው ያለን አስተሳሰብ።
እስቲ ወደ ኋላ ሄደን የቤት ሰራተኞቻችንን እንዴት እንደምንይዝ እንደነበር እናስታውስ። 16 ሰዓት በቀን ይሰራሉ ለሌላው 8 ሰዓት ተጠሪ ናቸው። በወር አንድ ቀን እረፍት ቢኖራቸው ነው ይህም ላይከበር ይችላል። ኦርቶዶክስ ክርስትያን ነን የምንለው እንኳን እሁድ ቀን እረፍት መስጠት ቅዳሴም እንዲያስቀድሱ አንፈቅም (ከዚህ በላይ አሳዛኝ ነገር አላቅም)። እንደ ሰው ሳይሆን እንደ ባርያ እንጮህባቸዋለን እናጎሳቁላቸዋለን። እንደማንም ሰው አድገው ወደፊት ማግባት እና ቤተሰብ ማፍራት እንደሚፈልጉም አንገነዘብም ልንገነዘብም አንፈልግም። ከቤተሰቦቻቸው ርቀው በመኖራቸው እኛ እንደ ሁለተኛ ቤተሰባቸው መሆን እንዳለብን አናስብም። በጠቅላላ ለራሳችን የማንወደውን እናደርግባችዋለን ለራሳችን የምንወደውን አናደርግላቸውም።
ይህ ስር የሰደደ ባህል ሆኖ የቤት ሰራተኛ እጅግ ዝቅተኛ ስራ መሆኑ ሁላችንም አሰሪዎችም ሰራተኞችም እናውቃለን። በዚህ ምክንያት ይመስለኛል በርካታ ሴቶች ከቤት ሰራተኛ ስራ የሚርቁት። ብዙ ብር ቢከፈላቸውም ከገንዘብ አንጻር ቢያዋጣቸውም «ዝቅተኛነቱን» «ውርደቱን» አይፈልጉትም።
የቶሎ የስራ መቀያየር ጉዳይሳ? ለምንድነው ብዙ የዘመኑ የቤት ሰራተኛዎች ገና ወር ሁለት ወር ሳይቆዩ ለቀው ወደ ሌላ ቤት የሚሄዱት። አንዱ ምክንያት የኤኮኖሚው ነው። ብዙ ስራ ስላለ የደሞዝ ጭማሬ ቶሎቶሎ ያገኛሉ። ሌላው ምክንያት ግን እንደሚመስለኝ የቤት ሰራተኝነት የማይፈለግ ስራ በመሆኑ ብዙ ችግር እና የማመዛዘን ድክመት ያላቸውን ሴቶች ናቸው ወደዚህ ስራ የሚገቡት። ይህ ምክንያት የስራ መቀያየራቸውን ብቻ ሳይሆን ሌሊችን ችግሮች እንደ ሌብነት ወዘተ ያስረዳል።
ለረዥም ዘመን የቤት ሰራተኞቻችንን ጎድተናል። በተዟዟሪ ሙሉ መሃበረሰባችንን ጎድተናል። የጎጂ የአሰሪ እና የንቀት ባህላችን ከትውልድ ወደትውልድ አስተላልፈናል። የአሁኑ የሰራተኛ እጥረት እስኩመጣ ድረስ ጥፋቶቻችን አልታዩንም ይሆናል ግን አሁን ጎልተው ሊታየን ይገባል። ጥፋታችንን አይተን አምነን መጸጸት፤ ንስሃ መግባት እና ይቅርታ መጠየቅ የሚኖርብን ይመስለኛል ይህን ጎጂ ባህላችንን በቋሚነት ለማስወገድ። ይህ ለህላችንም ለጠቅላላ ህብረተሰባችን ሰላም እና ፍቅርም አስፈላጊ ይመስለኛል።
No comments:
Post a Comment
ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!