Showing posts with label ብአዴን. Show all posts
Showing posts with label ብአዴን. Show all posts

Friday, 13 July 2018

ገዱ አንዳርጋቸው እና «ነባር ብአዴኖች»

ገዱ አንዳርጋቸው ብአዴንም ኢህአዴግም ላደረጉት ጥፋቶች በሙሉ ይቅርታ ጠይቋል። ካሁን ወድያ ለህዝብ ተጠሪ እንሆናለን ህግ አክባሪም እንሆናለን አናሸብርም ብሏል። የ«ለማ ቡድንን» እና አብይ አህመድ ደግፎ ኢህአዴግንም መንግስትም እንዲቆጣጠሩት አድርጓል። የነ አቢይ አህመድ ደጋፊ ሆኖም እየሰራ ነው። ይህ ሁሉ ግልጽ ነው ሁላችንም ያየነው ነው።

ይህ ሁሉ ሆኖ ገዱ ትላንት ተነስቶ የብአዴንን ነባር አመራር አሞገሰ ተብሎ ጩሄት አይገባኝም። ምን ነው ለመፍረድ የምንቸኩለው? ሰውን ይሆን እንዲህ ያለው ብለን እራሳችችን አንጠይቅም? እኛም እንደዚህ በችኮላ እንዲፈረድብን እንወዳለን?

ጠ/ሚ አብይ አህመድ ከመቀለ ያሉትን እናስታውስ። «ዎርቅ»! «ወልቃይት የዲአስፖራ ጉዳይ አለበት»! አንዳንዶቻችን ወረድንባቸው። ለምን? የሚሉትን ያውቁ ነበር። የነበርውን ህዝብ ለማስደሰት ህወሓቶችን የፖሮፓጋንዳ አቅም ማሳጣት ነበር። የፖለቲካ ስልት ነበር። እና በውቅቱ ሰርቷል። እንኳን መከለ ሄድው የትግራይን ህዝብ አሞገሱ!

እሺ ያኔ ብዙዎቻችን አብይ አህመድን የለማ ቡድንንም በደምብ አናውቋቸውም ነበር። አሁን ግን ለብዙ ዓመት ከኢህአዴግ ውስጥ ታግለው ድርጅቱን እንደተቆጣጠሩት እናውቃለን። ዋዛ አይደሉም ከኛ ድርብ እጥፍ የሚሰሩትን ያውቃሉ እኛ ያማናውቀውን በርካታ መረጃዎች አላቸው። ስለዚህ ቶሎ ከመፍረድ እራሳችንን መቆጠብ አለብን። አላማትች አንድ ስለሆነ መደገፍ አለብን እንጂ ትናንሽ የማንስማማበት ነገሮችን ካደረጉ ማኩረፍ የለብንም። አለበለዛ አብሮ መስራት አይቻልም።

የገዱም እንደዚሁ። እነ በረከትን ያሞሳቸው። እስኪ በቃቸው ቂቤ ይቀባቸው ምን ቸገረን። ለጊዜው ለፖለቲካ ከተመቸው እሰየው። ነው አሁንም እነ በረከትን እንፈራለን ገዱ ከሃዲ ነው ብለን እንፈራለን!! እንደዚህ ከሆነ ችግራችን ካሰብነው በላይ ነው። በስመ ጥርጣሬ ክፍፍል እና አለመረጋጋት አምጥተን እንደልማዳችን ተከፋፍለን ልንገዛ ነው ማለት ነው። እስቲ ትንሽም የፖለቲካ ስልታችንን እናዳብር።

በመጨረሻ ለፖለቲካችን ገዱ ላይ መጮሁ ጥሩ ነው። የድሮዎቹን ምን ያህል እንደሚጠሉ እና ምን ያህል ቦታ እንደሌላቸው ጡረታ ብቻ እንደሚጠብቃቸው ያስረግጥላቸዋል። ግን እኔ የምፈራው ይህ ገዱ ላይ የተሰነዘረው ጩሀት እንደዚህ አይነት ስልታማ ሳይሆን የእውነት ቅሬታ እና ንዴት ነው። ባይሆን ይሻላል። ከነ ገዱ ጋር አብረን መስራት አለብን ስራቸው ጥሩ እስከሆነ ብአዴንንም ገብተን መቆጣጠር አለብን። አማራ አንድ መሆን አለበት። የ50 ዓመት እርስ በርስ መጋጨት መከፋፈል የፖለቲካ ስልት እና ትብብር አለማወቅ ማብቃት አለበት።

በረከት ስምዖን ይዙር!

በረከት ስምዖን አማራ ክልልን እየዞረ ገንዘብ እያደለም ድጋፍ እየሰበሰበ ነው ይባላል? ታድያ ምን አለ ይህን ቢአደርግ። ምንድነው የምንፈራ። ሰዎቻችንን ይገዛል ብለን ነው? ያሳምናል ብለን ነው?

በረከት በገንዘብ እና ሀሳብ የራሳችንን ሰዎች ከገዛ ካሳመነ ይህ ስለኛ ምን ይነግረናል። ምን አይነት ህዝብ ነን ማለት ነው? በገንዘብ እና ውሸት የምንገዛ ህዝብ ነን? እንዲህ ከሆነ ደግሞ መሰረታዊ እና መታረም ያለው ችግር የበረከት መዞር ነው ወይንም የኛ በገንዘብ እና በ ውሸት መገዛት ነው? 

ግልጽ ነው፤ ችግሩ እኛ ነን መፍትሄው እራሳችንን ማስተካከል ነው። አለበለዛ የኛ ህዝብ በገንዘብ እና ውሸት ሀሳብ ስለሚገዛ በረከትን እናባረው ከሆነ መሰረታዊ ችግራችንን አንፈታም። በርከት ቢጠፋ ሌላ ደግሞ ይመጣል። ሌላ ተቃዋሚ፤ ሌላ የ«አማራ ጠላት»፤ ሌላ ሽብርተኛ ወዘተ። የራሳችንን ችግር ካልፈታን ለአደጋ እና ክህደት ሁልጊዜ የተጋለጥን እንሆናለው። ልድገመው፤ የራሳችንን ችግር ካልፈታን ለአደጋ እና ክህደት ሁልጊዜ የተጋለጥን እንሆናለው።

ለኔ ስለ በረከት ዙረት መቸገር እጅግ እጅግ አሳፋሪ ነው። አንድ ህዝብ የማይወደው አማራ ነኝ ኤርትራዊ እየዞራ ሊበጠብጣችን ይችላል ማለት እኛ እጅግ ደካማ እና ቀሽም ነን ማለት ነው። ባሁኑ ጊዜ ያውም ሰፃነት የሰፈነበት በረከት ምንም ጡንቻ የሌለበት እንዴት ነው የምንፈራው? ያስንቃል። 

ወንድሞች እህቶች እንደዚህ አይነት አስተሳሰብ ያስንቃል። ያስንቃል። እንደዚህ ነው እነ ህወሓትን ያሞላቀቅናቸው። ትንሽ ሆነው በቀላሉ ሊገዙን እንደሚችሉ ያመኑት ገና አንዳቸውን ስናይ ሊበጠብጠን ነው ብለን ስንሸማቀቅ ሲያዩ ነው። ይህን ውሸት ማድረግ አለብን። በረከት ስምዖን እየዞረ ሰውን እያሳመነ ከሆነ እኛ ያን ሰው አንዳያምን ማድረግ አለብን። የክህደት መንፈስ፤ የመታለል መንፈስ፤ የመገዛት መንፈስ ከኛ እንዲጠፋ ማድረግ አለብን።

ድሮ ኩሩ ህዝቦች ነበርን። አንድ ሽፍታ ያጠፋናል ብለን አንፈራም ነበር። በራሳችን በራሳችን ህዝብ እንኮራ እንተማመን ነበር። አንድ ወቅት ግን እርስ በርስ መፈጃጀት ስንጀምር በራሳችን መተማመኑን ያቆምን ይመስለኛል። ከዛ ወዲህ በአንድ ክፍል ውስጥ 100 ሆነን ተግኝነት አንድ «ጠላት» ከመጣ ያንን አንድ ጠላት እንደ 100 ሃይል መፍራት ጀመርን። ይህን አስተሳሰብ ካልቀየርን ኢትዮጵያም አማራም አዲዮስ። በተዘዋዋሪ ለዚህ ነው እነ ሻ'ዕብያ እና ወያኔ አንዳችን የ10 አማራ ዋጋ አለው የሚሉት። ትንሽ ሆነን እናሸማቅቃቸዋለን የሚሉት።

ስለዚህ በረከት ስምዖን ይዙር። ከተማ ለከተማ ይዙር ጉቦ ይስጥ ወሬውን ያውራ። መብቱ ነው። እኛ ለህልውናችን ግዴታ የሆነውን ራሳችንን እናስተካክል እናስተምር አንድነት እናምጣ። ልድገመው፤ አንድነት እናምጣ። አንድ ከሆንን እንደ ብረከት አይነቱ 10,000 ሆነውም እየዞሩ ጉቦዋቸውን ቢያድሉ ዋጋ አይኖረውም። ይህ አይነት አንድነት ከሌለን ለዘላለም በቀላሉ የምንሸነፍ ሰዎች ነው የምንሆነው።

Friday, 20 April 2018

ህወሓትን የሚያመልኩ «አማሮች»

ታማኝ በየነ በቅርቡ ባቀረበው «የቁልቁለት ዘመን» የሚባለው ትረካ የተለያዩ የብአዴንና ሌሎች ህወሓት ያልሆኑ የኢህአዴግ መሪዎች ለህወሓትና ለትግራይ ህዝብ ልክ የሌለሽ ሙገሳ ስያደርጉ አየን። ከሙገሳው ይሁን ግን አልፎ ተርፎ እነዚህ ሰዎች ሌላውን በተለይ የአማራ ህብረተሰብን ሲተቹ ሲሰድቡ ይታያል። እንደዚህ አይነት አመለካከት ለ27 ዓመታት ያየነው የሰማነው የኖርነው ቢሆንም እንዲዝህ አይነቱን ክስተት ደግሞ አይቶ መመርመሩ አስፈላጊ ይመስለኛል። ከነዚህ ሰዎች ባሕሪና አስተያየት የምንማረው ነገሮች ለፍትሕ እና ነፃነት ትግላችን ይጠቅማናልና።

ከትረካው ላይ እነ ካሳ ተክለብርሃን፤ አዲሱ ለገሰ፤ ዓለምነህ መኮነን፤ በረከት ስመዖን፤ ተፈራ ዋልዋ፤ ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ ታምራት ላይኔ፤ ወዘተ በዚህ አይነት አስተያየት ሲናገሩ ይታያል። ንግግራቸውም አነጋገራቸውም ስሜታዊ ነው። ለህወሓት ድርጅት እና ፍልስፍና ያላቸው ስሜት እና ተገዥነት በደምብ ይታይባቸዋል። እነዚህ አይነት ሰዎች ቁጥራቸው ትንሽ መሆኑ ቢታወቅም ህብረተሰባችንን ለመጉዳት ትልቅ ሚና ተጫውተዋል ይጫወታሉም። እንደዚህ አይነት ሰዎች ወይም እንደዚህ አይነት አስተሳሰብ እንዴት ሊመጣ ይችላል የሚለውን ጥያቄ ካሰላሰልን እና መመለስ ከቻልን  ላሁንም ለወደፊቱም እንደዚህ አይነት ሰዎች እንዳይፈጠሩ ለማድረግ ይረዳናል። ብዚህ መንገድ ትግላችን ይረዳናል።

ዛሬ የነዚህ አይነት ሰዎች እና አስተሳሰብ አመጣትን በዚህ መንገድ እንየው… ለማቅለል ያህል
የንጉሳዊ መንግስቶቻችን የአገዛዝ መርህ በመደብ የተወሰነ ነው እንበል። እርግጥ እንደ አውሮፓ «ፍዩዳሊዝም» አልነበርም ከአንድ መደብ ወደ ሌላ ምሻገገር ይቻላል ግን ዞሮ ዞሮ ንጉሱ መሳፍንቱ ያሉበት የገዥ መደብ አለ ሌሎቹ ደግሞ ተገዥ መደም ውስጥ ናቸው። በዚህ ሥርዓት ሁሉም የራሱ ተልዕኮ አለው ውድድርና ግጭቶች በቀጥታ ከስልጣን እና መሬት ወይም ንብረት የተያያዙ ናቸው።

«ዘመናዊ» መንግስቶቻችን ደርግና ኢህአዴግ ግን በጨቋኝ እና ተጨቋኝ ርዕዮተ ዓለም የተመሰረተ መርህ ነው የሚመሩት። ሁልጊዜ ጨቋኝ ተጨቋኝ፤ በዳይ ተበዳይ፤ ተራማጅ አድሃሪ ወይን ኋላ ቀር፤ አብዮተኛ ትምክተኛ፤ ሰፊ ጠባብ፤ ወዘተ መኖር አለበት። በአንድ በኩል በጥላቻ የተመሰረተ ርዕዮተ ዓለምና ፍልስፍና ነው ማለት ይቻላል።

በዚህ አይነቱ ርዕዮተ ዓለም የሚመራ መንግስት ሁለት አይነት ሰዎችን ይገኛሉ። አንዱ አይነት «ቢሮክራት» ብለን እንሰይመው። እነዚህ ሰዎች በተለያየ ምክንያቶች ለርዕዮተ ዓለሙን «እውነት አማኞች» ሆነዋል። እውነት ነው ብለው አምነውበታል። ምሳሌ ልስጣችሁ። በ1966 አንድ አዲስ አበባ የተወለደ ባለ መጀመርያ ዲግሪ ወጣት ለስራ ወደ ክፍለ ሀገር ይላካል። የሚያየው ድህነት እና ረሃብ እጅግ አሳዝኖት ለ«እኩልነት» መታገል ይጀምራል። ደርግ ስልጣን ሲይዝ ዳኛ ሆኖ ይሾማል «አድሃሪዎችን» ያስቀጣል ንብረታቸውን ያስወስዳል። ለአድሃሪዎቹ ጥላቻ የለውም ብዙም አይተቻቸውም አይሰድባቸውም። ግን ርዕዮተ ዓለሙን በደምን ስላመነበት ጥያቄ ሳይጠይቅ እራሱን ሳይመረምር የፖለቲካ ተልዕኮውን ይፈጽማል። ይህ አይነቱን «ቢሮክራት» እንበለው።

ሌላው አይነቱን «ብሶተኛ» ብለን እንበለው። እንደገና በምሳሌ ልግለጸው። የልጁ አስተዳደግ ምቹ አልነበረም። ትንሽ ሆኖ መንገድ ላይምን ትምሕርትቤትም ከሌሎች ልጆች በላይ ጥቃትና ስድም ይደርስበታል። እያደገ ሲሄድ ቤተሰቡ ከሰፈሩ የተገለሉ መሆናቸውን መረዳት ይጀምራል። የተገለሉበትን ምክንያት በትትክል ማወቅ አልቻለም ግን የተለያዩ ፍንጮችን ሲያቀናብር ድሮ አባቱ ባደረጉት ድርጊት ምክንያት መሆኑን ይረዳል። ሆኖም ልጁ እንደተሰደበ እንደተገለለ ያድጋል። ኢህአፓ አባላት ሲመለምል ጓደኝነት እና ማህበርነት ፍለጋ ልጁ ይሳተፋል። ጫካ ገብቶ በህውሓቶች ይማረካል። ጥሩ ወገናቸውን ያሳዩታል ሃላፊነት እና የቤተሰባዊ ስሜት ያሳዩታል። ኖሮት የማያውቀው ጓደኞች እና ዘመዶች ይሆኑለታል በዚህ ምክንያት ይወዳቸዋል። አብሮ ታግሎ አዲስ አበባ ይገባል። የህወሓት ስኬታማነት ይበልጥ እንዲወዳቸው እንዲወድሳቸው ያደርጋል። ፍልስፍናቸውም እውነት መሆኑን ያረጋግጥለታል። ትግሬ ባይሆንም ቀንደኛ የህወሓት ተቀናቃኝ ይሆናል። ሀወሓትን የማይወዱትን እንደ ጠላት ያያቸዋል። በተለይም የተወለደበት እና ያደገበት ህብረተሰብ ላይ ያለው ጥላቻ ይብሳል። አሁን ካለው ወርቃማ ሁብረተሰብ ጋር ሲያወዳድራቸው …

ስለዚህ «ቢሮክራት» እና «ብሶተኛ»። እርግጠኛ ነኝ ሁላችንም እንደዚህ አይነት ሰዎች እናውቃለን። (እራሳችንም እንደዚህ እንሆን ይሆናል።) ግን ምናልባት ይህ ሰው ክፉ ነው ወይም የተሳሳተ ነው ብለን ላዩን ወይም ሰሙን ብቻ አይተን ትተነዋል። ምንድነው እንደዚህ ያደረገው ብለን ሳንመረምር አልፈነዋል። ግን ለፍርድ ባንቸኩል እና ሰውየውን ተቆርቁረን ብንመለከተው ህይወቱ ለመን ወደዚህ እንዳመራ ለማየት እንችላለን።

ምን ዋጋ አለው እንደዚህ አይነቶችን ሰዎች ማስወገድ ነው ትሉኝ ይሆናል። ግን እንደዚህ ቀላል ቢሆን ኖሮ ድሮ አስወግደናቸው ሰላም አግኝተን ነበር! ያልቻልንበት ምክንያት ህብረተሰባችን እንዲዝህ አይነት ሰዎችን በርካታ አድርጎ ስለሚወልድ ነው። «ቢሮክራቱ» የሚፈጠረው 1) በህብረተሰባችን የእኩልነት፤ ስብዕና፤ ፍትሕ እጦት ስላለ 2) ትምሕርታችን ባህል እና ትውፊትን ንቆ የ«ዘመናዊ» ትምሕርት ላይ ስለሚያተኩር ተማሪዎቻችን መሰረታቸውን ማንነታቸውን ትተው ወደ የማያቁት ጸንፈኛ እና በአድ የሆነ ፍልስፍና ይገባሉ። ስለዚህ ህብረተሰባችን ያልፈታውን ችግር አይተን ችግሩን በራሳችን ትውፊት ከመፍታት በማይሆነው ጸንፈኛ እና በአዳዊ መንገድ መፍታት እንሞክራለን።

ምሳሌ ልስጣችሁ… በኃይለ ሥላሴ መንግስት የነበረው ዋና ቅራኔ የመሬት ጉዳይ ነው። ባላባቶች ሌሎችም በተለያየ አግባብ ያልሆነ መንገድ መሬት አግኝተው ወይም ወርሰው ጭሰኛውን ያሰቃያሉ። የተውፊታችን ምሶሶ የሆኑት ሃይማኖቶቻችን መስረቅ፤ መዝረፍ፤ መጭቆን፤ ወዘተ ልክ አይደለም ይላሉ። ሀብታም ድሃን መርዳት ግድ ነው ይላሉ። ይህን ተከትሎ የመሬት ሽግሽግ እንዲደረግ በርካታ ሰዎች እየሞከሩ ነበር። ቢያንስ ጪሰኞች የመሬቶቻቸው ባለቤት እንዲሆኑ ባላባቶች ሌላውን መሬቶቻቸውን ይዘው እንዲጠብቁ። ግን ይህን ትውፊታዊ አካሄድ ማድረግ ባለመቻላችን ጉዳዩን በማርክሲስት አብዮታዊ መንገድ እንፍታው ለሚሉት መንገድ ከፈትን። ከዚህ ጽሁፍ «ቢሮክራት» የምላቸው ከዚህ ጎራ ናቸው።

ይህ አይነቱ ክስተት እንዳይከሰት ህብረተሰብም ግለሰብም ማድረግ ያለብን በተቻለ ቁጥር ቢያንስ በግል ኑሮዋችን ሰላም እና ፍትሕ እንዲኖር የተጎዱትን ድኾችን መርዳት ነው። ከህብረተሰባችን መሰረታዊ ክፍፍሎችና ችግሮች እንዳይኖሩ ማድረግ ነው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ልጆቻችን ባህል እና ትውፊታቸውን ተምረው እንዲያድጉ በበአድ አስተሳሰብ እንዳይዋዥቁ ማድረግ ነው።

ወደ «ብሶተኛው» ስንመጣ ደግሞ… ከ«ቢሮክራቱ» ይብሳል ጉዳቱም ኃይለኛ ነው። ቢሮክራቱ በመረጃ ሀሳቡን ሊቀይር ይችላል ግን ብሶተኛው በጥላቻ ምክንያት እውነትን ማየት አይፈልግም ጭለማ ውስጥ ነው። ስለዚህ እንደ ማህበረሰብም እንደ ግለሰብም እንደዚህ አይነት ሰዎች እንዳይፈጠሩ ከተፈጠሩም ከማህበረሰቡ እንደ «ሽፍታ» ከሚፈነግሉ አቅርብን መያዝ ነው። «ንቀት» የሚባለውን ነገር በማጥፋት ነው።

ብሶተኛ እንዳይኖር ማህበረሰብ ውስጥ ክፍፍል እንዳይኖር ማድረግ አለብን። እስቲ የኃይለ ሥላሴ መንግስት ሲወርድ የሰማነውን «ሌባ፤ ሌባ» የሚለውን መፈክር እናስታውስ። ማን ነው በስሜት እና ንዴት እንደዚህ የጮኸው። ይንቁኛል ብሎ የሚያምን። በመደቤ በማንነቴ ወደ ታች አድርገው ያዩኛል ብሎ የሚያምን። ወዘተ።

የታማኝን ትረካ ሳይ ይሄ ነው በአዕምሮኤ የታየኝ። አንዳንድ «ቢሮክራቶች» ግን አብዛኛው «ብሶተኛ»። ያሳዝናሉ። የራስን ህዝብ የራሽን ማንነት መጥላት እና መናቅ ከባድ ነገር ነው። ለብሶተናውም ከባድ ነው ለማህበረሰቡም ከባድ ነው። እግዚአብሔር ብሶተኛ የማንወልድ ማህበረሰብ ያድርግን። ልጆቻችንን በአግባቡ በባህልና ተውፊታቸው እንድናሳድግ ይርዳን። ብሶት ያላቸውንም ብስታቸውን አይተን፤ ገብቶን፤ ሳንፈርድባቸው ከማህበረሰቡ ሳይሸፍቱ እንድንረዳቸው ይርዳን።

Saturday, 25 November 2017

አቶ ለማና አቶ ገዱ

ይህ የአቶ ለማ መገርሳና የአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ንግግር ግዥ ፓርቲው ኢህአዴግ ውስጥ የአንድነት አስፈላጊነትና የኦሮምኛ ከአማርኛ እኩል የሀገር ቋንቋ መሆን ጥቅም (ይህንና ይህን አንብቡ) የሚረዱ ወገኖች እንዳሉ ብቻ ሳይሆን ይህን ጉዳይ ለረዥም ጊዜ ያሰላሰሉበት እንደሆነ ዪገልጻል። አቶ ለማና አቶ ገዱ ለንግግሮቻቸው ሊመሰገኑ ዪገባል።፡ ያንጸባረቁት አቋም ጥሩና ተስፋ ሰጭ ነው።

ሆኖም ወደ ተግባር ስንሄድ ይህን ልውጦች፤ አንድነት፤ መልካም አስተዳደር፤ ህብረተሰባዊ መሻሻሎች ብተለይ በወጣቶች ስነ መግባር ዙርያ፤ የወላጅና የሃይምናኦት መሪዎች በልጆቻችን ጤንነትና ደህንነት ሃላፊነታቸውን መዋጣት፤ ወዘተ አቶ ለማና አቶ ደጉ ሊፈጹሟቸው ይችሉ ይሆን?

አይችሁሉም ወይም እጅግ ይቸገራሉ አንዳንድ መሰረታዊ መዋቀራዊ ለውጦች ከሌሉ። እነዚህ ችግሮች ዛሬ ያሉት በግለሰብ ድክመቶች ብቻ ሳይሆኑ በመዋቅር ድክመት ነው። በተለይ የአውራ ፓርቲ ፖለቲካ ስርአት ለውቶችን እጅግ አፍኗል። ሌላው በዋንነት ሁለተኛው ችግር በኢህአዴግ ውስጥ የህወሃት የበላይነት መጠን ነው። እነዚህ ሁለቱ ነገሮች በመጠኑ መስተካከል አለባቸው።

የመጀመሪያውን ለማስተካከል ለባለስጣን («ህዝብ ተወካይ») ምርጫዎችን በመጠኑ ነጻ መደረግ አለበት። ሙሉ ነጻነት እንደማይሆን፤ ከአውራ ፓርቲ አገዛዝ ጋር እንደሚቃረን እረዳለሁ። ግን አውራ ፓርቲ 100% ማለት አይደለም።  100% ይባለስጣን ችለተኝነት ያመጣል። ቢሰርቅም ስልጣኑን ለማይሆን ነገሮች ቢጠቅምም ምንም አይደርስብኝም ብሎ። ግን ከስልጣን መውረድ የተወስንም ቢሆን እድል እንዳላቸው ሲረዱ ጥንቃቄ ይጨምራሉ። ስለዚህ ከ 100% ወደ 80 ወይም 70ም አስፈላጊ መሰለኝ።

ሁለተኛው ጉዳይ ይከብዳል። ከብአዴን ኦህዴድና ሌሎቹ ጅግንነትም ብልጠትም ይጠይቃል። ከህዝባቸው ጋር ያላቸውን ቅርበት ማጠናከር ግድ ነው። ይህ ነው ኢህአዴግ ውስጥ ስልጣናቸውን የሚጎለብተው። አሁንም ላለፉት ሶስት ዓመታት የዚህን ፍንጭ እያየን ነው ነገር ግን መጠንከር አለባቸው። መልካም አስተዳደር ለነሱ የህይወትና ሞት ጉዳይ ነው። መልካም አስተዳደር አቋማችንና ግባችን ነው ብለው ቢይዙትና በዚህ ጉዳይ ቆራጥ ቢሆኑ ከህዝቦቻቸው ጋር አንድነት ያመጣሉ። በዚህ ጉዳይ እጅግ ታላቅ ሳ መሰራት አለበት።

በተዘዋዋሪ ከላይ የጠቀስኩት በሙሉ ይሚቻል ነገር ነው። ደም አያፈስም ጦርነትም አያስነሳም። ትንሽ ብልጠት ብቻይ ነው የሚያስፈልገው። ማንንንም አይጎዳም ከሙስናና ጎጂ አስተዳደር መሪዎች በቀር። አይ፤ ማድረግ የሚቻል ነው።

እግዚአብሔር ይርዳቸው። እኛንም ከዳር ቆመን አንገታችንን ደፍተን የምንታዘበው ወይም የምናጨበችበው የምናዝነውም ከዳራችን ወደ መሃል ገትብተን የመፍትዬው አካል እንድንሆን ይርዳን!

Tuesday, 21 November 2017

ምርጥ ንግግር ከአቶ ለማ መገርሳ

ምርጥ ንግግር (https://www.youtube.com/watch?v=aim-D4EKMlI)።

1. በመጀመርያ በንግግሩ የጎሳ ብሄርተኝነትና የሱ መዘዞች አንዱ ዋና የኢትዮጵያ ችግር መሆኑን አምኗልም አስረድቷልም።

2. የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ወይም ርዕዮተ ዓለም ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ለህልውናው አስፈላጊ መሆኑን አሳየ።

3. ህብረተሳባዊ ችግሮች እንደ ስረዓትና ስነ መግባር ማጣት እያመለጠን (runaway) እያለ የሆነ ችግር መሆኑን ተረድቷል። በዚህ ረገድ የህብረተሰብ - ወላጅና የሃይማኖት መዋቅሮች - በዋናነት ሃላፊነት እንዳለበትም መገነዘቡ ትልቅ ነገር ነው። በርካታ ዪትዮጵያ ምሁራኖች በዘመናዊነት ርዕዮተ ዓለም ተለቅፈው መንግስት ሁሉን አዋቂ ሁሉን ማድረግ የሚችል ይመስለዋል።

4. መልካም አስተዳደርም አለመኖሩ (በሌላ አባባል የሙስና ከሙስና ጋር የተገ መብዛት) ሌላው ዋና ችግር መሆኑ የብአዴን ስብሰባ ላይ መቶ መናገሩ ትልቅ ነገር ነው። ባአዴን ከህዝቡ ጋር ያለው ዋናው ችግር በዚህ ዙርያ ነው። እርግጥ የወልቃይትና ሌሎች ከሌልች ክልሎች የሚያገናኗቸው ቢኖሩም ዋናው የብአዴን ችግር መልካም አስተዳደር ነው። ወንድ ሆነው ይህን እንቅፋት ቢያሸንፉና ጭቆናና ሙስናን ቢያጠፋ ከህዝቡ ጋር አንድ ይሆናል ሀገራዊ ሃይሉም እጅግ ያይል ነበር።

እግዚአብሔር አቶ ለማ መገርሳን በዚው መንገድ እንዲቀጥል ዪርዳው።

Monday, 29 August 2016

ፑቲኖቻችን የት አሉ?

2008/12/6 ዓ.ም. (2016/8/12)

የሶቪዬት ህብረት ከወደቀ ብኋላ ምእራቡ ዓለም በተለይ አሜሪካ ሩሲያኖችን እንረዳችኋለን፤ ኤኮኖሚአችሁ እንዲታደስና እንዲያድግ እንረዳችኋለን፤ ወደ ዓለም ኤኮኖሚ በቀላሉ እንድትቀላቀሉ እናደርጋለን፤ የቀዝቃዛ ጦርንነትን ለማፍረስ ስለተባበራችሁን ሩሲያ በጠቅላላ እንድትበለጽግ እናደርጋለን ብለው ቃላቸውን ሰጡ። ነገር ግን ቃላቸውን አጥፈው በሩሲያ ሀገር አፍራሽና ህዝብ ጎጂ የሆነ አመራርና መርህ በሀገሪቷ እንዲሰፍን ገፋፉ። በዚህ ምክንያት የሩሲያ ህዝብ የአስር ዓመት በላይ የስቃይ ዘመን አሳለፈ። ስቃይ ስል ህዝቡ ደህይቶ የሚበላውን ያጣበት፤ ወንጀልና ሽብርተኝነት የሰፈነበት፤ ህዝቡ ጤና አጥቶ የአማካኝ የህይወት እድሜ ከ70 ወደ60 የወረደበት፤ ሙስናና የማፊያ (ትብብር ወንጀል) ሥረዓት የሞላበት ሀገር ሆና ነበር ሩሲያ።

በዚህ የሩሲያ ስቃይ ዘመን የሀገሪቷ መሪ ፕሬዚደንት ቦሪስ ዬልትሲን ነበሩ። በ1991ዓ.ም. ከስልጣን በፈቃዳቸው ወረዱና ምክትላቸውን ቨላዲሚር ፑቲንን ፕሬዚደንት እንዲሆን ወከሉ። የዬልትሲን ደጋፊዎች የሆኑት በመንግስት አመራር ውስጥ የነበሩት ትላልቅ ባለ ሀብቶች የውጭ ሀገር «ንጂኦ» አንቀሳቃሾች የምዕራብ ሀገር መንግስታት ሁሉም ፑቲን በአስተሳብም በርዕዮት ዓለምም በእምነትም የዬልትሲን ተቃራኒ እንደሆነ ዓገር ወዳጅ እንደሆነ አልጠረጠሩም ነበር! በኢትዮጵያ ሁናቴ ለማምሳሰል ያህል መለስ ዜናዊ ይልቃል ጌትነትን ወይም ሌላ ተቃዋሚ ሾሙ እንደማለት ነው!

ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? እንዴት ዬልትሲንና ዙሪያቸው ያሉት መሪዎች ደጋፊዎች ባለሟሎችና የውጭ ሀገር መንግስታት የፑቲንን የእውነት ባህሪና አቋም አላወቁም? ምክንያቱ ቀላል ነው፤ ፑቲን እራሱን አላገለጠም። ማንነቱን በሚያስፈልገው መጠን ሰውሮ ነበር። ይልቁኑ በዬልትሲን መንግስት በተለያየ ቦታዎች ሲያገለግል ጎልማሳው ፑቲን በታታሪነትና በዓለቃን ማክበርና በተለይ ለዓለቃ ያለው ታማኝነት ነበር የሚታወቀው። ከአመራር ወስጥ ያሉትና ከየሀገሩ ገዥ የነበሩት ባለሃብቶች («የሩሲያ ቢሊዮኔሮች» የተባሉት) በደምብ ይግባባ ነበር። ከመጠን በላይ ብልጥም ፖሊቲካ የገባውም ነበር። በፍጹም አልተጠረጠረም!

ቨላዲሚር ፑቲን ፕሬዚደንትም ሲሆኑ የእውነት አቋሞቻቸውን ወድያው አላሳዩም። በመጀመርያ ስልጣናቸውን ቀስ በቀስ አጠናከሩ። ጓደኛ እንጂ ጠላት የማያፈራ መርህዎችን አራመዱ። አሸባሪዮችን አጠቁና የጦርሰራዊት የፖሊስና የጸጥታ ኃይሎችን ድጋፍ አረጋገጡ። ከምዕራብ ሀገሮች ጋር በጸረ ሽብርተኝነት ሩሲያ በደምብ እንድትተባር አደረጉና የምዕራብ መንግስታትንም ድጋፍ አገኙ። ከዚያ ቆይተው ፑቲን ስልጣናቸውን ካረጋገጡ በኋላ በዬልትሲን ዘመን በዝርፍያና በሙስና ያደጉት ባለሀብቶችን በማሳሰር በማሳመን ስልጣናቸውን ነጠቁ አጠፉ። እነዚህ እርምጃዎች የፑቲንን የህዝብ ድጋፍ መጠን በጣም እንዲልቅ አደረጉ (ስልጣን ከያዙ ጅምሮ ከ65 እስቀ 80 በመቶ ድጋር አላቸው)።

ከዬልትሲን ወደ ፑቲን የተካሄደው የሩሲያ ለውጥ ከሞላ ጎደል ሰላማዊ ነበር። እንዲሁም በኢትዮጵያ የሚፈለገው ሰላማዊ፤ ማንም የማይጠቃበት፤ ሀገር የማይረበሽበት፤ ጥላቻ የማይሰፍንበት፤ ቅራኔ የምያሳንስና መግባባት ለዘብተኝነት መቻቻል የምያጠቃልል ለውጥ ነው።

እንደዚህ አይነት ለውጥ የሚመጣው ከዓብዮት ሳይሆን ከውስጣዊ ቀስ በቀስ የሚመጣ ለውጥ ነው። ለንደዚህ አይነት ለውት የነባር መንግስት ውስጥ በርካታ የለውጥ አጋሮች ያስፈልጋሉ፦ ፑቲኖች ያስፈልጋሉ! ሥርዓቱ ሲናጋ ውግያና ሁከት ለማምጣት ወደኋላ የማይሉ አክራሪዮች ስልጣን እንድይዙ ውይም በውሳኔ ላይ እንዲያመዝኑ ያደርጋል። ይህ እንዳይከሰት እነዚህ የውስጥ ለውጥ የሚፈልጉ ለዘብተኛ የሆኑት አስፈላጊ ናቸው። አክራሪውም በለዘብተኛው እንደተከበበ ሲያይ ግድ ይመለሳል።

ነገር ግን እንደዚህ ሰርጎ ገብተው የሚያገለግሉ ሰዎች የራሳቸውን ህልውና ለመጠበቅና ይበልጥ ረጅም አላማቸው እንዳይከሽፍ ብለው እራሳቸውን መደበቅ አለባቸው። እዚህ ላይ ብልጠት ያስፈልጋል። መሪዎቻቸውን መምሰል አለባቸው። አለጊዘው ስልጣናቸውና የስልጣን ድራቸውን በቂ ሳያስፋፉ ሳያጠነክሩ ጠንካራ አቋም መውሰድ የለባቸውም። እንደ ፑቲን ስያስፈልግ አንገታቸውን ደፍተው መኖር አለእባቸው። «እንደ እባብ ብልዖች እንደ ርግብ የዋሃን ሁኑ» ውይም «ዛሬ ህይወትን ካጡ ወደፊት መታግል አይቻልም» እንደሚባለው።

በዚህ ጊዜ ብዙሐናም «ተቃዋሚዎች»ም ብልህ መሆን አለባቸው። ከውስጥ የስውር ጠቃዎሚዎች በይፋ እየተሟገቱ በስውር መተባበር አለባቸው። አንድ ነገር ማስታወስ አለብን፤ ዋናው የኢትዮጵያ ፖሊቲካ ችግር የተሳትፎ ጉዳይ ነው። ህዝቡ መሪውን ሲጠላ ከመንግስት ወስጥ ከመሳተፍ ይርቃል። «ፖለቲካና ኮሬንቲ» የሚባለው ስሜት ያመዝናል። ይህ ማለት በርካታ የኢትዮጵያ ህዝብ ወገኑን ውይም የሃሳብ አጋሩን ከመንግስት ወስጥ የለም። በታችኞቹ የመንግስት አካሎችም እንደ ቀበሌና ወረዳ ለመሳትፍ አይፈልግም ቤተሰቡም ዘመዱም እንዲሳተፍ አይፈልግም። መንግስትን «ለሌሎች» ትቶት በብአድ እየተገዛ ነው። ይህ አስተሳሰብ ተገቢ የሆነ የታሪክ ምክንያት ቢኖረውም ትክክል አይደለምም እጅግ ጎጂም ነው። አለመሳተፍ አክራሪነትንና ዓብዮትን የሚጋብዝ ለዘብትኘትና ትብብርን ቦታ የሚያሳጣ አስተሳሰብ ነው።

«እንዴት ኢህአዴግ ውስጥ መስራት ይቻላል፤ ሕሊናን መሸጥ ወይም ጥቃትን መቀበል ያስፈልጋል» ሊባል ይችላል። ታድያ በሰሞኑን የጎንደር ተቃውሞ ላይ የኃይል እርምጃ እንዳይወሰድ ያደረጉት ማን ናቸው? አልፎ ተርፎ በኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ወስጥ ያሉት በዝቅተኛ የስልጣን ደረጃ ያሉት ወታደሮች በአብዛኛው ማናቸው ከየት ናቸውም? በየቀበለውና ወረዳ የሚያስተዳደሩት (ከትግራይ ክልል በስተቀር) ማናቸው? የታወቀው ኢህአዴግን ለቆ የወጣው ኤርሚያስ ለገሰ ማን ነው? አምባሳደር ሆኖ በግዞት ወደ ቱርኪ የተላኩት አቶ አያሌው ጎበዜ ማን ናቸው? ለነገሩ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ማናቸው? እነዚህ በሙሉ የለውጥ አጋሮች ወይም ሁኔታዎች ሲፈቅዱ የለውጥ አጋሮች ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው!

መርሳት የለለብን የኢህአዴግ መንግስት የአናሳ መንግስት እንደሆነ ነው (በዚህ ካልተስማማን የህዝበ ድጋፍ አላቸው ብለን አመንን ማለት ነው!)። ኢህአዴግ መላ የኢትዮጵያን ህዝብን እንወክላለን ባይ ነው ግን ተቃዋሚዎችና በርካታ ህዝብ የትግራይ መንግስት ነው ብሎ ይከሰዋል። አናሳ ነው ብለን ከተቀበልን ማውቅ ያለብን አናሳ መንግስት ሀገርን መግዛት የሚችለው ሌላው ህዝብ ከፈቀደለትና በደምብ ከተባበረው ብቻ ነው! ኢህአዴግ እንደ ደርግ አለብልሃት በመጭፍለቅ ብቻ መግዛት አይችልም። ኢህአዴግ የሌላው አለመተባበር ውይም ከፖሊቲካ መራቅ ውይም በፈቃደኝነት መገዛት ያስፈልገዋል። ይህ ውነታን በግልፅ የሚያንጸባርቀው ኢህአዴግ ፓርቲውም ጦርሰራዊቱም በቁጥር ደረጃ በአብዛኛው የትግርኛ ተናጋሪ አለመሆኑ ነው።

ስለዚህ ኢህአዴግ ውስጥ ገብቶ ወዲያው ሳይሆን ከስ ብሎ ልውጥ ማምጣት ካልሆነም የለውጥ አጋር መሆን እንደሚቻል ግልፅ ነው። ህዝቡ ይግባ፤ ይሳተፍ፤ ሲያስፈልግ አንገቱን ደፍቶ እሺ ይበል፤ ቀስ ብሎ በስልጥ አብዛኛነትን ያረጋግጥና ጊዘው ሲደርስ ለውጥ ያመጣል።

ከፑቲን የምንማረው ትምህርት የህ ነው። ፑቲን ለዬልትሲን መንግስት ሲያገለግል ብቸኛ የውስጥ ተቃዋሚ አልነበሩም ሊሆኑም አይችሉም ነበር። ፕሪዚደንት ፑቲን ሲሾሙ እንድርሱ አንገታቸውን ደፍተው የመትፎ አገዛዙን ውስጥ ለውስጥ የሚሸረሽሩ ሀገር ወዳድ ይሆኑ ትናንሽ ፑቲኖች አብረው ተነሱና ፑቲንን ደግፈው አላማቸውን አራመዱ። ፑቲን ብቻቸውን ቢሆኑና የሳቸውን አላማ የሚደግፍ ከሥርዓቱ ውስጥ ባይኖሩ የትም አይደርስም ነበር።

በተዘዋዋሪ በሰሞኑ በአማራ ክልል በተካሄደው ተቃውሞ ሰልፎች ምክንያት አንዳንድ የህወሓት ተንታኒዎች ብአዴን በሰላይዎችና በከሃዲውች የተሞላ ነውና ጽዳት (በሌላ ቃል እስራና ግድያ) ያስፈልገዋል ብለው ይተቻሉ! ውነት ነው ህወሓት ለ26 ዓመት በመግዛቱ በፖሊቲካ ስልጥ ከሌላው ልቋልና እንደዚህ አይነት ነገር ቶሎ ነው የሚገባው። ሌላውም ሊገባው ይገባል።

መጀመርያ የታተመው ከዚህ