ታማኝ በየነ በቅርቡ ባቀረበው «የቁልቁለት ዘመን» የሚባለው ትረካ የተለያዩ የብአዴንና ሌሎች ህወሓት ያልሆኑ የኢህአዴግ መሪዎች ለህወሓትና ለትግራይ ህዝብ ልክ የሌለሽ ሙገሳ ስያደርጉ አየን። ከሙገሳው ይሁን ግን አልፎ ተርፎ እነዚህ ሰዎች ሌላውን በተለይ የአማራ ህብረተሰብን ሲተቹ ሲሰድቡ ይታያል። እንደዚህ አይነት አመለካከት ለ27 ዓመታት ያየነው የሰማነው የኖርነው ቢሆንም እንዲዝህ አይነቱን ክስተት ደግሞ አይቶ መመርመሩ አስፈላጊ ይመስለኛል። ከነዚህ ሰዎች ባሕሪና አስተያየት የምንማረው ነገሮች ለፍትሕ እና ነፃነት ትግላችን ይጠቅማናልና።
ከትረካው ላይ እነ ካሳ ተክለብርሃን፤ አዲሱ ለገሰ፤ ዓለምነህ መኮነን፤ በረከት ስመዖን፤ ተፈራ ዋልዋ፤ ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ ታምራት ላይኔ፤ ወዘተ በዚህ አይነት አስተያየት ሲናገሩ ይታያል። ንግግራቸውም አነጋገራቸውም ስሜታዊ ነው። ለህወሓት ድርጅት እና ፍልስፍና ያላቸው ስሜት እና ተገዥነት በደምብ ይታይባቸዋል። እነዚህ አይነት ሰዎች ቁጥራቸው ትንሽ መሆኑ ቢታወቅም ህብረተሰባችንን ለመጉዳት ትልቅ ሚና ተጫውተዋል ይጫወታሉም። እንደዚህ አይነት ሰዎች ወይም እንደዚህ አይነት አስተሳሰብ እንዴት ሊመጣ ይችላል የሚለውን ጥያቄ ካሰላሰልን እና መመለስ ከቻልን ላሁንም ለወደፊቱም እንደዚህ አይነት ሰዎች እንዳይፈጠሩ ለማድረግ ይረዳናል። ብዚህ መንገድ ትግላችን ይረዳናል።
ዛሬ የነዚህ አይነት ሰዎች እና አስተሳሰብ አመጣትን በዚህ መንገድ እንየው… ለማቅለል ያህል
የንጉሳዊ መንግስቶቻችን የአገዛዝ መርህ በመደብ የተወሰነ ነው እንበል። እርግጥ እንደ አውሮፓ «ፍዩዳሊዝም» አልነበርም ከአንድ መደብ ወደ ሌላ ምሻገገር ይቻላል ግን ዞሮ ዞሮ ንጉሱ መሳፍንቱ ያሉበት የገዥ መደብ አለ ሌሎቹ ደግሞ ተገዥ መደም ውስጥ ናቸው። በዚህ ሥርዓት ሁሉም የራሱ ተልዕኮ አለው ውድድርና ግጭቶች በቀጥታ ከስልጣን እና መሬት ወይም ንብረት የተያያዙ ናቸው።
«ዘመናዊ» መንግስቶቻችን ደርግና ኢህአዴግ ግን በጨቋኝ እና ተጨቋኝ ርዕዮተ ዓለም የተመሰረተ መርህ ነው የሚመሩት። ሁልጊዜ ጨቋኝ ተጨቋኝ፤ በዳይ ተበዳይ፤ ተራማጅ አድሃሪ ወይን ኋላ ቀር፤ አብዮተኛ ትምክተኛ፤ ሰፊ ጠባብ፤ ወዘተ መኖር አለበት። በአንድ በኩል በጥላቻ የተመሰረተ ርዕዮተ ዓለምና ፍልስፍና ነው ማለት ይቻላል።
በዚህ አይነቱ ርዕዮተ ዓለም የሚመራ መንግስት ሁለት አይነት ሰዎችን ይገኛሉ። አንዱ አይነት «ቢሮክራት» ብለን እንሰይመው። እነዚህ ሰዎች በተለያየ ምክንያቶች ለርዕዮተ ዓለሙን «እውነት አማኞች» ሆነዋል። እውነት ነው ብለው አምነውበታል። ምሳሌ ልስጣችሁ። በ1966 አንድ አዲስ አበባ የተወለደ ባለ መጀመርያ ዲግሪ ወጣት ለስራ ወደ ክፍለ ሀገር ይላካል። የሚያየው ድህነት እና ረሃብ እጅግ አሳዝኖት ለ«እኩልነት» መታገል ይጀምራል። ደርግ ስልጣን ሲይዝ ዳኛ ሆኖ ይሾማል «አድሃሪዎችን» ያስቀጣል ንብረታቸውን ያስወስዳል። ለአድሃሪዎቹ ጥላቻ የለውም ብዙም አይተቻቸውም አይሰድባቸውም። ግን ርዕዮተ ዓለሙን በደምን ስላመነበት ጥያቄ ሳይጠይቅ እራሱን ሳይመረምር የፖለቲካ ተልዕኮውን ይፈጽማል። ይህ አይነቱን «ቢሮክራት» እንበለው።
ሌላው አይነቱን «ብሶተኛ» ብለን እንበለው። እንደገና በምሳሌ ልግለጸው። የልጁ አስተዳደግ ምቹ አልነበረም። ትንሽ ሆኖ መንገድ ላይምን ትምሕርትቤትም ከሌሎች ልጆች በላይ ጥቃትና ስድም ይደርስበታል። እያደገ ሲሄድ ቤተሰቡ ከሰፈሩ የተገለሉ መሆናቸውን መረዳት ይጀምራል። የተገለሉበትን ምክንያት በትትክል ማወቅ አልቻለም ግን የተለያዩ ፍንጮችን ሲያቀናብር ድሮ አባቱ ባደረጉት ድርጊት ምክንያት መሆኑን ይረዳል። ሆኖም ልጁ እንደተሰደበ እንደተገለለ ያድጋል። ኢህአፓ አባላት ሲመለምል ጓደኝነት እና ማህበርነት ፍለጋ ልጁ ይሳተፋል። ጫካ ገብቶ በህውሓቶች ይማረካል። ጥሩ ወገናቸውን ያሳዩታል ሃላፊነት እና የቤተሰባዊ ስሜት ያሳዩታል። ኖሮት የማያውቀው ጓደኞች እና ዘመዶች ይሆኑለታል በዚህ ምክንያት ይወዳቸዋል። አብሮ ታግሎ አዲስ አበባ ይገባል። የህወሓት ስኬታማነት ይበልጥ እንዲወዳቸው እንዲወድሳቸው ያደርጋል። ፍልስፍናቸውም እውነት መሆኑን ያረጋግጥለታል። ትግሬ ባይሆንም ቀንደኛ የህወሓት ተቀናቃኝ ይሆናል። ሀወሓትን የማይወዱትን እንደ ጠላት ያያቸዋል። በተለይም የተወለደበት እና ያደገበት ህብረተሰብ ላይ ያለው ጥላቻ ይብሳል። አሁን ካለው ወርቃማ ሁብረተሰብ ጋር ሲያወዳድራቸው …
ስለዚህ «ቢሮክራት» እና «ብሶተኛ»። እርግጠኛ ነኝ ሁላችንም እንደዚህ አይነት ሰዎች እናውቃለን። (እራሳችንም እንደዚህ እንሆን ይሆናል።) ግን ምናልባት ይህ ሰው ክፉ ነው ወይም የተሳሳተ ነው ብለን ላዩን ወይም ሰሙን ብቻ አይተን ትተነዋል። ምንድነው እንደዚህ ያደረገው ብለን ሳንመረምር አልፈነዋል። ግን ለፍርድ ባንቸኩል እና ሰውየውን ተቆርቁረን ብንመለከተው ህይወቱ ለመን ወደዚህ እንዳመራ ለማየት እንችላለን።
ምን ዋጋ አለው እንደዚህ አይነቶችን ሰዎች ማስወገድ ነው ትሉኝ ይሆናል። ግን እንደዚህ ቀላል ቢሆን ኖሮ ድሮ አስወግደናቸው ሰላም አግኝተን ነበር! ያልቻልንበት ምክንያት ህብረተሰባችን እንዲዝህ አይነት ሰዎችን በርካታ አድርጎ ስለሚወልድ ነው። «ቢሮክራቱ» የሚፈጠረው 1) በህብረተሰባችን የእኩልነት፤ ስብዕና፤ ፍትሕ እጦት ስላለ 2) ትምሕርታችን ባህል እና ትውፊትን ንቆ የ«ዘመናዊ» ትምሕርት ላይ ስለሚያተኩር ተማሪዎቻችን መሰረታቸውን ማንነታቸውን ትተው ወደ የማያቁት ጸንፈኛ እና በአድ የሆነ ፍልስፍና ይገባሉ። ስለዚህ ህብረተሰባችን ያልፈታውን ችግር አይተን ችግሩን በራሳችን ትውፊት ከመፍታት በማይሆነው ጸንፈኛ እና በአዳዊ መንገድ መፍታት እንሞክራለን።
ምሳሌ ልስጣችሁ… በኃይለ ሥላሴ መንግስት የነበረው ዋና ቅራኔ የመሬት ጉዳይ ነው። ባላባቶች ሌሎችም በተለያየ አግባብ ያልሆነ መንገድ መሬት አግኝተው ወይም ወርሰው ጭሰኛውን ያሰቃያሉ። የተውፊታችን ምሶሶ የሆኑት ሃይማኖቶቻችን መስረቅ፤ መዝረፍ፤ መጭቆን፤ ወዘተ ልክ አይደለም ይላሉ። ሀብታም ድሃን መርዳት ግድ ነው ይላሉ። ይህን ተከትሎ የመሬት ሽግሽግ እንዲደረግ በርካታ ሰዎች እየሞከሩ ነበር። ቢያንስ ጪሰኞች የመሬቶቻቸው ባለቤት እንዲሆኑ ባላባቶች ሌላውን መሬቶቻቸውን ይዘው እንዲጠብቁ። ግን ይህን ትውፊታዊ አካሄድ ማድረግ ባለመቻላችን ጉዳዩን በማርክሲስት አብዮታዊ መንገድ እንፍታው ለሚሉት መንገድ ከፈትን። ከዚህ ጽሁፍ «ቢሮክራት» የምላቸው ከዚህ ጎራ ናቸው።
ይህ አይነቱ ክስተት እንዳይከሰት ህብረተሰብም ግለሰብም ማድረግ ያለብን በተቻለ ቁጥር ቢያንስ በግል ኑሮዋችን ሰላም እና ፍትሕ እንዲኖር የተጎዱትን ድኾችን መርዳት ነው። ከህብረተሰባችን መሰረታዊ ክፍፍሎችና ችግሮች እንዳይኖሩ ማድረግ ነው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ልጆቻችን ባህል እና ትውፊታቸውን ተምረው እንዲያድጉ በበአድ አስተሳሰብ እንዳይዋዥቁ ማድረግ ነው።
ወደ «ብሶተኛው» ስንመጣ ደግሞ… ከ«ቢሮክራቱ» ይብሳል ጉዳቱም ኃይለኛ ነው። ቢሮክራቱ በመረጃ ሀሳቡን ሊቀይር ይችላል ግን ብሶተኛው በጥላቻ ምክንያት እውነትን ማየት አይፈልግም ጭለማ ውስጥ ነው። ስለዚህ እንደ ማህበረሰብም እንደ ግለሰብም እንደዚህ አይነት ሰዎች እንዳይፈጠሩ ከተፈጠሩም ከማህበረሰቡ እንደ «ሽፍታ» ከሚፈነግሉ አቅርብን መያዝ ነው። «ንቀት» የሚባለውን ነገር በማጥፋት ነው።
ብሶተኛ እንዳይኖር ማህበረሰብ ውስጥ ክፍፍል እንዳይኖር ማድረግ አለብን። እስቲ የኃይለ ሥላሴ መንግስት ሲወርድ የሰማነውን «ሌባ፤ ሌባ» የሚለውን መፈክር እናስታውስ። ማን ነው በስሜት እና ንዴት እንደዚህ የጮኸው። ይንቁኛል ብሎ የሚያምን። በመደቤ በማንነቴ ወደ ታች አድርገው ያዩኛል ብሎ የሚያምን። ወዘተ።
የታማኝን ትረካ ሳይ ይሄ ነው በአዕምሮኤ የታየኝ። አንዳንድ «ቢሮክራቶች» ግን አብዛኛው «ብሶተኛ»። ያሳዝናሉ። የራስን ህዝብ የራሽን ማንነት መጥላት እና መናቅ ከባድ ነገር ነው። ለብሶተናውም ከባድ ነው ለማህበረሰቡም ከባድ ነው። እግዚአብሔር ብሶተኛ የማንወልድ ማህበረሰብ ያድርግን። ልጆቻችንን በአግባቡ በባህልና ተውፊታቸው እንድናሳድግ ይርዳን። ብሶት ያላቸውንም ብስታቸውን አይተን፤ ገብቶን፤ ሳንፈርድባቸው ከማህበረሰቡ ሳይሸፍቱ እንድንረዳቸው ይርዳን።
No comments:
Post a Comment
ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!