Wednesday, 19 September 2018

«የእሽሩሩ ፖለቲካ»

በርካታ ሰዎች የጎሳ ብሄርተኖችን «እሽሩሩ» (appease) ማድረግ የለበንም ይላሉ። ልክ ልካቸውን መንገር አለብን። የጎሳ ፌደራሊዝም የግጭት እና እልቂት ምንጭ በመሆኑ መጥፋት እንዳለበት መናገር አለብን። ገና ለገና እናስቀይማቸዋለን ብለን ትክክለኛ ሃሳቦቻችንንም እውናተንም ከመናገር መቆጠብ የለብንም። ይባላል።

በመጀመርያ «እሽሩሩ» ግልጽ ያልሆነ የጅምላ አባባል ነው። ጉዳዩን በትክክል ለመተንተን precise መሆን አለብን። «እሽሩሩ»፤ «ዲፕሎማሲ»፤ «የአገላለጥ ስልት»፤ «ብልህነት» ምን ማለት ናቸው? ተግባሩን ካልወደድነው ወይንም ትክክል ካልመሰለን «እሽሩሩ» እንለዋለን፤ ትክክል ከመሰለን «ዲፕሎማሲ» ወይንም «የአገላለጽ ስልት» እንለዋለን። ስለዚህ «እሹሩሩ» አይነቱን ቃል ከመለጠፍ በፊት ጉዳዩን በትክክል እንየው።

ዓለም ዙርያም በኢትዮጵያም እንደምናየው በተግባርም በጽንሰ ሃሳብ እንደሚታወቀው የጎሳ ብሄርተኖች ከለዘብተኛ እስከ ጸንፈኛ እና በነዚህ መከከል አሉ። ባጭሩ ጸንፈኛው የጎሳ ብሄርተኝነቱ ከማንነቱ ጋር እጅግ ስለተቆራኘ ሃሳቡን መለወት ከባድ ነው ለመሞከርም ብዙ አያዋጣም። ግን ከዛ ለዘብተኛ የሆኑት እስከ ጥቂት የጎሳ ብሄርተኝነት ያላቸው ሰዎች ወደ ሀገራዊ ብሄርተኝነት ማምጣት ይቻላል። ይቻላል ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግድ ደው። ኢትዮጵያዊነት የሚዘልቀው ለዘብተኞቹን ወደሱ በማምጣት ነው።

እንዴት ነው ትንሽ እና ለዘብተኛ የጎሳ ብሄርተኝነት ስሜት ያላቸውን ወደ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ማምጣት የሚቻለው? እንዴት ነው ይህ ህዝብን በዜጋ የተመሰረተ ህገ መንግስትን እንዲደግፍ ማድረግ የሚቻለው?

የሚቻለው በአውንታዊ መንገድ ነው። ኦሮሞነት በኢትዮጵያዊነት ይንጸባረቃል በማለት ነው። ቋንቋቸው የኢትዮጵያ ቋንቋ ነው በማለት ነው። ባህላቸው የኢትዮጵያ ባሕል ነው በማለት ነው። አልፎ ተርፎ ጥያቄዎቹን (demands) ሰምቶ ተገቢ የሆኑትን ማለትም በህብረ ባህላዊ እና ህብረቋንቋዊ (ህብረ ብሄራዊ ሳይሆን ማለት ነው) ሀገር መስተናገድ የሚችሉትን ማስተናገድ እና ማስፈጸም። እንዲህ ነው ትንሽ እስከ ለዘብተኛ የጎሳ ብሄርተኝነት ወደ «ኢትዮጵያዊነት» ማምጣት የሚቻለው እና በሀገራችን ያለው ጣቅላላ የጎሳ ብሄርተኝነት ስሜትን መቀነስ እና ቀስ ብሎ ማጥፋት የሚቻለው።

ግን መልእክቶአቻችን አሉታዊ ከሆኑ ለዘብተኞችን ወደ ጸንፈኖቹ እንገፋቸዋለን! ማስተወስ ያለብን የጸንፈኞቹ ትግል ከኛ ይቀላል። ሰውን በጎሳ ማንነቱ ማስተባበር ቀላል ነው በሰው ልጅ ተፈጥሮ ምክንያት። ጸንፈኛው ጎሰኛ «ማንነትህ እየተደፈረ ነው» በማለት ብቻ በስሜታዊ መንገድ ለዘብተኞቹን መሳብ ይችላል። ስለዚህ እኛ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ለዚህ አይነት ቅስቀሳ ጥይት እንዳናቀብል መጠንቀቅ አለብን። ጥይቱ ምን ይመስላል? በጅምላ ኦሮሞነት ዘረኝነት ነው ማለት። የጎሳ አስተዳደር አሁኑኑ ሙሉ በሙሉ ይጥፋ ማለት። በጎሳዎች ልዩነቶች የሉም አንድ ቋንቋ አንድ ባህል ነው ያለን ማለት። ወዘተ። እንደዚህ አይነት መልዕክቶች ለዘተኞቹን ወደ ጸንፈኖች ይገፈትርዋቸዋል።

አንድ ጽሁፌ ላይ (http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/07/understanding-ethnic-soft-nationalism.html) ስለ ካናዳ ያለው የኬቤክ ጠቅላይ ግዛት የጎሳ ብሄርተኝነት። የጎሳ ብሄርተኛ ፖለቲከኞች አንድ ካናዳ ብሄርተኛ ጠንካራ ወይንም እንደ ስድብ ሊቆጠር የሚችል ንግግር እስኪያደርግ አድፍጠው ይጠብቃሉ። ልክ የሚፈልጉትን ስያገኙ ለሁለት ሶስት ቀን ሚዲያቸውን በሙሉ በዚህ ክስተት ያጥለቀልቃሉ። በፊት ለዘብተኛ የነበረው ወደ አክራሪነት ሲንሳፈፍ በድምጽ ቆጠራ (poll) እናያለን። ዓለም ዙርያ የታወቀ የተለመደ ስልት እና ክስተት ነው።

አንዱ የፖለቲካ ሙያ ስራ ለተላያዩ ሰዎች አቋምን በተለያዩ መንገዶች መግለጽ ነው። መዋሸት ሳይሆን የአገላለጽ ዘዴን በሚያስፈልገው መንገድ ማስተካከል ነው። ለኢትዮጵያ ፕሬዚደንት የሚወዳደር ሰው ግንደር ሲሄድ ስለ ጎንዳር ላይ የሚያቅደው ልማት ይናገራል። አፋር ሲሄድ ስለ አፋር ላይ የሚሰራው መስኖ ይናገራል። ይህ የታወቀ ነገር ነው። የጎሳ ብሄርተኝነትን manage ለማድረግ እንዲሁ ነው የሚደረገው። ምንም ልዩነት የለውም ምናልባት ይበልጥ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል እንጂ።

ባጭሩ በኢትዮጵያ የጎሳ ብሄርተኝነትን መቀነሻ እና የጎሳ ፌደራሊዝምን ማጥፍያ መንገድ ይህ ነው፤

1. ትንሽ እና ለዘብተኛ የጎሳ ብሄርተኝነት የሚሰማቸውን በስልት እና ተባር (እንደ ቋንቋ ፖሊሲን መቀየር) ወደ ኢትዮጵያዊነት ማምጣት እና ከጸንፈኞቹ መለየት።

2. ቋንቋ እና ባህል እንዲቀላቀል አስፈላጊ ፖሊሲዎችን ማስፈጸም። የ«ቅይጥ» ህዝቡን ቁጥር የሚጨምር ፖሊሲዎችን ማራመድ። በየ ክልሉ በርካታ ህዝብ ሶስት አራት ቋንቋ እንዲችል ማድረግ። (http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/07/towards-integrated-ethiopia.html)

3. አንዴ በህዝባችን መካከል የጎሳ ብሄርተኝነት ስሜት በቂ ከቀነሰ ብኋላ እና ህዝቡ ፖለቲካዊ ፈቃዱ ሲሆን ይህንን ጸንፈኛ ህገ መንግስታችንን ወደ ዜጋ ፖለቲካ መቀየር።

አዋጪ እቅዱ ባጭሩ ይህ ነው። ዝርዝሩ ልየያይ ይችላል። ምናላባት ህገ መንግስቱ ላይ አሁኑኑ ትናንሽ ለውጦች ማድረግ በቂ ፈቃደኝነት ሊኖር ይችላል። «ፕሬዚደንታዊ» አሰራር በህገ መንግስቱ በቅርብም ማካተት ይቻል ይሆናል። ግን ከሞላ ጎደል መንገዱ እላይ እንደዘረዘርኩት ነው።

ስለዚህ «እሽሩሩ» የሚለው እውነታን አይገልጽምም አሳሳችም ነው። ይህ ጉዳይ እንደማንም የፖለቲካ ጉዳይ ስልት እና ዘዴ ያስፈልገዋል። ዲፕሎማሲም ብልህነትም ያስፈልጉታል።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!