Thursday, 6 September 2018

አባቶቻችን የጣልያኖች ጸረ-አማራ ጦርነትን በ«ኢትዮጵያዊነት» ነው ያሸነፉት

ሁላችንም እንደምታውቁት ከ1929 እስከ 1933 ታልያኖች መላው ኢትዮጵያን ለመግዛት በሚሞክሩበት ጊዜ አንዱ መሳርያቸው «ከፋፍሎ መግዛት ነበር። እንደ ማንኛውም ወራሪ፤ እንደ ማንኛውም የአውሮፓ ቅኝ ገዥ፤ ጣልያን የሚወረውን ሀገር ድክመቶች ገምግሞ የኢትዮጵያን ህዝብ ከፋፍሎ መግዛት ይቻላል ብሎ ገመተ።

ጣልያኖች መከፋፈል የፈለጉት በአጭሩ «አማራውን» እና ሌላውን ነው። የምኒልክ ወረራ በቅርብ ጊዜ (ወደ 70 ዓመት) ነበር እና የተወረሩት ህዝቦች ከኛ ጋር ይሆናሉ ብለው ገበቱ። ግን ከምኒልክ ጋር የተለያዩ ጎሳ ሰዎች ስለነበሩ ክፍፍልን በደንብ ለማምጣት ታሪክን የ«ጎሳ ትርክት» ማልበስ አለብን አሉ። ይህ ትርክት አማራ ገዥ እና ወራሪ ሌሎቹ ተገዥ እና ጭቁን ሆነ። ጣልያኖች እንደ ጅማ አይነቱ ቦታዎች ሄደው ይሀው «ነፃ አውጥተናችኋል» አሉ። «አማራውን አጥፉ» አሏቸው። የጣልያን ትርክት ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ተቆጣጠርናት ሳይሆን ጭቁን የኢትዮጵያን ህዝብ ከአማራ ቅኝ ግዛት አወጣናት ነበር። በዚህ ምክንያት አማራ ላይ የተለየ ዘመቻ አወጁ።

ሁላችንም እንደምናውቀው ይህ ሁሉ ሲሆን ጣልያንን የሚዋጉት አማሮች መቼም በአማራ ስም አልተዋጉም በኢትዮጵያዊነት ነው የተዋጉት። ጣልያን አማራን ለይቶ ሲያጠቃ እና ሌሎች ኢትዮጵያዊያን አስካሪ ሆነው አማራን ሲያጠቁ አማራው በአማራነቴ ነው የምጠቃው እና በአማራነቴ ነው እራሴን መከላከል ያለብኝ አላለም።

ይህ ማለት፤ 1) አማራው ከሌሎች አማራ ያልሆኑ ኢትዮጵያዊዎች አብሮ በኢትዮጵያዊነት ታገሉ፤ 2) አማራው አማራነቱን አስቀድሞ ለአማሮች ብቻ አልታገለም፤ 3) አማራው ለአማሮች በተለየ መንገድ ወይንም ለአማሮች አድሎ አድርጎ አልተዋጋም፤ 4) አማራው ስለ ኢትዮጵያ ተዋጋ ማለትም ስለ ሁሉም ኢትዮጵያዊዎች ስለ መላው ኢትዮጵያ ተዋጋ አለ አድሎ ማንንም ሳያስቀድም ማንንም ወደ ኋላ ሳይተው 5) አማራው ከሌሎች ጎሳዎች የሆኑትን ባንዳዎች ምክንያት አድርጎ በጎሳቸው ሰይሟቸው አላጠቃቸውም እራሱንም አጠቁኝ ብሎ ወደ አማራነት አልሸሸም።

አማራ ይህን በኢትዮጵያዊነት ዘመቻ ያካሄደው በጣልያን የከፋ እና ግዙፍ ጠንካራ ወረራ እና ጭቆና ነው። ከባድ ነበር፤ ከህወሓት አገዛዝ ምንሙ አይገናኝም! ህወሓት በራሳችን ፈቃድ ነው የገዛን (http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2016/09/blog-post_15.html)። የራሳችን ጥፋት ነበር። የጣልያን ወረራን ግን ባለመጠንከራችን የራሳችን ጥፋት አለበት ብንልም የኃይል ልዩነቱ እጅግ ከባድ ነበር። ሆኖም ጣልያን በጣም ቢጨቁነውም አማራው በአማራነቴ ተጭቆንኩኝ ወንድሞቼ በጣልያን ከለላ ወጉኝ ብሎ እራሱን ወደ ጎሰኝነት አላወረደም ነበር።

ሁን ታሪክ የማስታውሰው ምክንያት ትንሽ ታሪካዊ context እንዲኖረን ነው ዛሬ ስለ አማራ ብሄርተኝነት ስንወያይ። የአማራ ብሄርተኝነት የተመሰረተው በህወሓት እና በሌሎች የጎሳ ብሄርተኞች አማራው ላይ ባደረሱት ጥቃት ምክንያት ነው። የአማራ ብሄርተኝነት መሰረት ባጭሩ «ብሶት» ነው ብል አካራካሪ አይመስለኝም። ግን ከዚህ ጽሁፍ የፈለግኩት ይህ የመጀመርያ ጊዜ አይደለም አማራ ተመርጦ ሲጨቆን። ጣልያን መቶ ጊዜ ይበልጥ ለይቶ ጭቁኖታል። ግን ያኔ የአማራው መልስ «ኢትዮጵያዊነት» ወይንም «አንድነት» ነበር። መልሱ ተሳክቷልም።

ስለዚህ ዛሬ እስቲ ያንን ታሪክ እንመልከት። ተጭቁነናል ስንል ከዚህ በፊት ይበልጥ ተጨቁነን እንደነበር እናስታውስ። አባቶቻችን ደግሞ ሲጨቆኑ መልሳቸው «አማራነት» ሳይሆን «ኢትዮጵያዊነት» እንደነበር እናስታውስ። ስለዚህ አማራ ብሄርተኝነት ለአባቶቻችን ወይን ለትውፊታችን ብአድ እንደሆነ እናምን። ዛሬ አስፈላጊ ነው አይደለም የሚለውን ጥያቄ ብንተወውም አዲስ እና ኢ-ትውፊታዊ መሆኑን አንካድ (http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/05/blog-post.html)።  ኢ-ትውፊታዊ አካሄድ ደግሞ አማራነት አይመስለኝም። አማራ መሆን ለኔ ከሁሉም በላይ ትውፊቱን አጠንቅቆ መያዝ ነው እና አዲስ ፍልስፍናን (እንዳ የብሄር ጎሰኝነት) በጥርጣሬ ማየት ነው።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!